
በ2018 ዓመተ ምሕረት ማብቂያ ከ90 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ እንዲኖራቸው እንደሚደረግ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት አስታውቋል። ለመሆኑ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ ተግባራዊ መደረጉ ምን ፋይዳ አለው?
በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ከፍተኛ የፖሊሲና የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ በላይሁን ይርጋ ጉዳዩን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ማብራሪያ ብሔራዊ መታወቂያ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ ዓመታዊ የኢትዮጵያ ጂዲፒ በሰባት በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል ይላሉ። ይህም ማለት አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ እንዲካተት የሚያደርግ መሆኑን ያነሳሉ።
አሁን ላይ ግን 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከፋይናንስ ሥርዓቱ ውጭ ነው የሚሉት አቶ በላይሁን፤ ይህም የሀገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ሲሉ ይገልፃሉ።
እንደ አቶ በላይሁን ገለፃ፤ በኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መዘርጋት ነዋሪዎች የመታወቂያ መብታቸው እንዲረጋገጥ ይረዳል፡፡ ዜጎች ሌሎች መብቶችን የመጠቀም እድላቸው ይሰፋል፤ አገልግሎት ሰጪና ተቀባይ መካከል በሚኖር ግንኙነት ላይ እምነት እንዲዳብር ያደርጋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃም የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የተሳለጠ አሠራር ሥርዓትን ለመዘርጋት ያስችላል ይላሉ።
ብሔራዊ መታወቂያ ሁሉም ዲጂታል አገልግሎቶች እና ግብይቶች በታመነ ማዕቀፍ ውስጥ ሊከናወኑ የሚችሉበት መሠረት ነው የሚሉት አቶ በላይሁን፤ የብሔራዊ መታወቂያ በአሁኑ ጊዜ የሚመራው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስር መሆኑን አንስተዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት የተሻሻሉ የፋይናንስ፣ የማኅበራዊ፣ የሕዝብ እና ሌሎች አገልግሎቶችን ተግባራዊ ሳይሆን መሠረታዊ ግለሰባዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ሰውን የሚለዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት በማቀድ ለሁሉም ነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያ እንዲመዘገብ እና እንዲሰጥ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት በ2018 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ90 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት ታቅዷል ያሉት አቶ በላይሁን፤ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በአሁኑ ወቅት የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባን በተለያዩ ቦታዎች በመተግበር ላይ ይገኛል ብለዋል።
እንደ አቶ በላይሁን ገለፃ፤ የፋይዳ ቁጥር የዲጂታል መታወቂያ ሲሆን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዋሪዎችን የተመጠነ የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃ በመሰብሰብ “አንድ ሰው አንድ ነው” በሚል መርሕ አንድን ሰው ልዩ በሆነ ሁኔታ መለየት የሚያስችል ሥርዓት ነው።
የፋይዳ ቁጥር በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ለሚያሟሉ ነዋሪዎች የሚሰጥ ባለ 12 አኃዝ ልዩ መለያ ቁጥር ነው ያሉት አቶ በላይሁን፤ የፋይዳ ቁጥር (ዲጂታል መታወቂያ) የያዙ ነዋሪዎች በሀገሪቱ ውስጥ ማንነትን በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት ያስችላል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የባንክ ሒሳብ ለመክፈት፣ ሥራ ለማመልከት እና የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት እንዲሁም ለተለያዩ ዓላማዎች ለመጠቀም የማንነት መሠረታዊ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል። የሚቀርበውም መረጃ ትክክለኛ መሆኑን በማረጋገጥ ከመጭበርበር እና ተመሳሳይ ድርጊቶች ለመከላከል ይረዳል ብለዋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፤ መርሐ ግብሩ በ2014 ዓመተ ምሕረት ምዝገባ መጀመሩን ጠቁመው፤ እስካሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ከ125 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መሰጠት ተችሏል ብለዋል።
በ2015 ዓ.ም ማብቂያ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጥምረት በተሠሩ ሥራዎች ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ዮዳሄ ገለፃ፤ የዲጂታል መታወቂያን ኅብረተሰቡ በተለያዩ አካባቢዎች እንዲያገኝ የማመቻቸት ሥራ እየተሠራ ነው። በ2018 ዓ.ም ማብቂያ ከ90 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ እንዲኖራቸው ይደረጋል። በዘንድሮ ዓመትም ለ25 ሚሊዮን ዜጎች ዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት ተማሪዎችንና የባንክ ደንበኞች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል።
ለዚህም ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከፋይናንስ ዘርፉ፣ ከገቢዎች ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር እንሠራለን ያሉት አቶ ዮዳሄ፤ ትግበራው የአሠራር ሥርዓትን ለማዘመን ያለመ ነው ብለዋል። የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያው ኅብረተሰቡ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ጉልህ እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
እንደ ባንክ፣ ጤና፣ ኢንሹራንስ እና የመሳሰሉ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለኅብረተሰቡ የተፋጠነ እና ዘመናዊ ሥራ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አቶ ዮዳሄ ገልጸዋል።
አቶ በላይሁን በበኩላቸው፤ ብሔራዊ መታወቂያ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ ዓመታዊ የኢትዮጵያ ጂዲፒ እስከ ሰባት በመቶ እንደሚያድግ ገልጸዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም