የኑሮን ውድነት በመፍትሄ ርምጃ…

በየጊዜው እየናረ የሄደው የሸቀጦችና የመሠረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ ከተጠቃሚው ህብረተሰብ አቅም ጋር የተመጣጠነ አለመሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡ የግብዓት ምርቶች ማነስና የንግድ ሥርዓቱ ወጥ አለመሆን ከአንዳንድ የስግብግብ ነጋዴዎች ፍላጎት፣ ጋር ተዳምሮ በሀገሪቱ የኑሮ ውድነትን ካስከተለ ሰነባብቷል፡፡

ጠዋት ማታ በየሰዉ ልቦና ይመላለስ የያዘው የኑሮ ውድነት ዛሬም መፍትሄ ያገኘ አይመስልም። የየዕለቱ የሚዲያ ዘገባዎች፣ ይህንኑ መሠረታዊ ችግር እያነሱ ይወያዩበታል፡፡ ለኑሮ ውድነቱ ዋንኛ ሰለባ የሆነው ሰፊው የህብረተሰብ ክፍል ቤት ጓዳውን እያሰበ ስለኑሮው ያስባል፣ ይጨነቃል፡፡

ተደጋግሞ እንደሚነገረው የዋጋ ጭማሪ አጋጠመ ማለት የዋጋ ንረት ተፈጥሯል ማለት አይደለም። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉትም በአንድ ሀገር ላይ የሚስተዋል የዋጋ ጭማሪ የአንድ ጤናማ ኢኮኖሚ አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡

እንዲህ አይነቱን እውነታ ባደጉ ሀገራት የሚገኙ ታላላቅ ባንኮች ዋንኛ የፖሊሲያቸው ግብ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ይህ በልኬታ የተቀመጠ መስፈርት በአግባቡ የሚካሄድ እስከሆነ ድረስ ኢኮኖሚው ስብራት አይገጥመውም፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ያለአግባብ የሚጓዝ የዋጋ ጭማሪ ግን የሀገርን ኢኮኖሚ ለመጉዳትና የህብረተሰቡን የመኖር አቅም ለመፈተን መንገዱ ፈጣን ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በሀገራችን ለኑሮ ውድነት እንደምክንያት ከሚጠቀሱት መሀል በአቅርቦትና ፍላጎት መሀል የሚያጋጥም ኢኮኖሚያዊ አለመጣጣም አንዱ ነው፡፡

ከምርት በኋላ የሚኖር ስርጭትና የገበያ ሥርዓት መዛባትም የኑሮ ውድነቱን ችግር ለማፋጠን ዋነኛ ሰበብ ይሆናል፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ አሁንም ድረስ ኢኮኖሚውን የፈተነ ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡

በአንድ ሀገር የተትረፈረፈ የምርት አቅርቦት አለ ቢባልም ስርጭቱ በወጉ ካልሆነ ኪሳራው የበዛ ነው፡፡ ይህ አይነቱ አሠራር በተለመደ ቁጥር የኑሮ ውድነቱን ሸክም የሚያከብዱ አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡

ለኑሮ ውድነቱ ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶች ጋር ተያይዞ የሚስተዋል የዋጋ መናር ነው፡፡ ሀገራችን በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ ካለመሆኗ ጋር ተያይዞ የዓለም ገበያ ዋጋን ከመቀበል ውጭ ምርጫ የላትም፡፡ ይህ አይነቱ ገበያን የመወሰን አቅም ማጣትም የዓለምን ገበያ ዋጋ ከነጫናው ተቀብላ እንድትጓዝ ምክንያት ይሆናል፡፡

ይህ እውነታ አንደኛው ሰበብ ሆኖ ይጠቀስ እንጂ በሀገራችን የውጭ ሀገራትን ምርቶች የሚጠቀመው ሃይል ጥቂት የሚባለው ክፍል መሆኑ ይታወቃል። ይህ እንዳለ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ ወቅትን ጠብቀው የሚገቡ የሀገር ውስጥ ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ ጭምር ምክንያቱን አሳማኝ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡

ከገንዘብና የመንግሥት በጀት ፖሊሲ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር የዋጋ ጭማሪም የኑሮ ውድነቱን ከሚያጎሉ ምክንያቶች መሀል አንዱ ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡ የተጠቀሱ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ በአንድ ሀገር ለኢኮኖሚው መሳሳት ምክንያት ናቸው የሚባሉ ጉዳዮች ተደራርበው በሚከሰቱ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ ይበልጥ ያይላል፡፡

እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ትንታኔ፤ የኢትዮጵያ የምግብ ንግድ ሁኔታ ምርት ሲኖር ዝቅ የሚል፣ ምርት ባነሰ ጊዜም ከፍ የሚል ሆኖ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ ግን ይህ እውነታ ተቀይሮ ፍሰቱ በተቃራኒው እየተጓዘ ይገኛል ፡፡ ይህ እውነታም የኑሮ ውድነቱን የማያረግብ ከመሆኑ አኳያ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

ባላደጉ ሀገራት የኑሮ ውድነቱን ለማባባስ በርካታ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ ፡፡ ለወቅታዊው የሀገራችን ችግር ዋነኛው መንስዔ ግን ያለፍንበትና አሁንም የምንገኝበት የሰላም ማጣት ችግር ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ሰላም ከሌለ ገበሬው ከእርሻው ፣ ምርት ከገበያው አይውልም፡፡ የተለመደው የንግድ ሥርዓት በአግባቡ አይጓዝም፡፡ ለከርሞ የታሰበው ለዘንድሮው ሳይበቃ፣ አውድማው ይራባል፣ ጎተራው ይራቆታል፡፡

በርካቶች እንደሚስማሙት ለኑሮ ውድነቱ ሌላው አይነተኛ ምክንያት የዋጋ ግሽበት አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ግሽበቱን አስመልክቶ አንዳንዶች እንደሚሰጡት አስተያየትም ገንዘብን ያለእንቅስቃሴ ማስቀመጥ አንዱ ምክንያት ይሆናል፡፡ ያልተንቀሳቀሰ ገንዘብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያይላልና ኦኮኖሚውን አስሮ ለመያዝ ሰበብ ነው፡፡

ለኑሮ ውድነቱ መባባስ መንግሥት በየጊዜው የሚወስዳቸው የመፍትሄ ርምጃዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እንዲህ መሆኑ ብቻ ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አቅም ሊሆን አይችልም። በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚከሰተውን ሰው ሰራሽ ክፍተት ለመሙላት አማራጮችን ማስፋት የግድ ይላል።

በየጊዜው ለሚያጋጥሙ የኢኮኖሚ ስብራቶች የግብርናውንና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ቅብብሎሽ ማቀላጠፍ አስፈላጊ ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉትም ከግብርናው ምርት የሚገኘውን ውጤት ለኢንዱስትሪው ግብዓት በመመገብ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ማድረግን በአማራጭነት መያዝ ያስፈልጋል፡፡

በመንግሥት አሠራር ላይ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮች የዋጋ ንረቱን በማባባስ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። ባላደጉ ሀገራት ውስጥ አብዝቶ የሚስተዋለው የሙሰኝነት ችግርም ኢኮኖሚውን እያቀጨጨ ተጠቃሚውን በግልጽ እየጎዳው ይገኛል፡ ፡

በተገቢው ጊዜ ተመርቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ መቅረብ የሚኖርበት ምርት በአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች፣ በተላላኪ ደላሎችና በጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናት ፈጻሚነት በታሰበው ልክ የማይጓዝበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡

እነዚህ አካላት የምርት እጥረት በማይኖርባቸው ጊዜያት ሁሉ አቅርቦቱን በማሰናከል የገበያ ሂደቱን የሚያደናቅፉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የግል ባለሀብቱን በሚያበረታታ የንግድ ሂደት ያለው መንገድ ከአምራች እስከ ገበያ የሚደርስ ሰንሰለታዊ ጉዞን የተከተለ ነው። ከችርቻሮ ፣ እስከ ጅምላና ሀገራዊ የንግድ ትስስር የሚኖረው ሂደትም ጤናማ መሆኑ እስካልተፈተሸ ለኑሮ ውድነቱ መነሻ የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ይህ አይነቱ ስር የሰደደ ችግር ባለበት የህብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላትና የታመመውን ኢኮኖሚ ማዳን አዳጋችና ፈታኝ ይሆናል፡፡ መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት እስከዛሬ የወሰዳቸው አማራጮች በጎ የሚባሉ ናቸው፡፡ ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖም በተሻሉ አማራጮች ተጨማሪ መፍትሄዎችን መፍጠር ያስፈልጋል ፡፡

ሁሌም ቢሆን ምርቶችን በነፃነት በማንቀሳቀስ የገበያ ዝውውሩን ማስፋት ጠቀሜታው የጎላ ነው። በታላላቅ ከተሞች የሚስተዋለውን የኢኮኖሚ ድቀት ለማረጋጋትም አነስተኛ የንግድ ማዕከላትን በማስፋት ለተጠቃሚው መድረስ ተገቢ ይሆናል፡፡

ይህ አይነቱ ልማድ ዕውን መሆኑ ብቻውን ወደ መፍትሄው ላያደርስ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚሁ ጎን ለጎን ጥቃቅን የንግድ አማራጮችን በማስፋት ከታክስ ነጻ የሆነ አሠራርን መፍጠር ተገቢነቱ መልካም ነው፡፡ እንዲህ አይነቶቹን አዳዲስ አሠራሮች ማስተዋወቅ በተለይ መካከለኛ ኑሮ ላይ ለሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ጠቀሜታውን ያጎላዋል፡፡

በተማረው የሰው ሃይል ብርታት የግብርና ሂደቱን በማዘመን ኢኮኖሚውን ማከም ከተቻለ ችግሩን ለመቅረፍ አንድ ርምጃ መፍጠን ይሆናል፡፡ በከተማ ግብርናና ፣ በበጋ መስኖ ፕሮጀክት ምርቶችን በመደጋገም አርሶደሩን በዕውቀት የሚያግዝ ሃይል መፍጠርም አንዱ መፍትሄ ነው፡፡

ገበያ መር የሆነ ሥርዓትን በኢኮኖሚው መደገፍ ከተቻለ ፍላጎትና አቅርቦትን ማጣጣም የማይቻልበት አግባብ አይኖርም፡፡ ከአምራቹ፣ አስከ ሸማቹ ያለውን ትስስር ጤናማ በማድረግ ሀገራችን እየተፈተነችበት ያለውን ኢኮኖሚያዊ ህመም በወጉ ማከም ይቻላል፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግ ግን ቅን ልቦና፣ ሀገር የመውደድ ስሜትና የእኔነት መንፈስን መላበስ ግድ ይላል፡፡ የኑሮ ውድነት የሁሉንም ወገን በርና ጓዳ አንኳኩቷልና፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You