ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ትምህርት እና ጥናት እንዴት ነው? ልጆች የእረፍት ጊዜያችሁን እንዴት ነው የምታሳልፉት? ምን መጫወት ያስደስታችኋል? መቼም ለእናንተ ብዙ ጨዋታዎች እንዳሉ ታውቃላችሁ አይደል?፣ ለምሳሌ መሀረቤን አያችሁ ወይ? አኩኩሉ፣ አባሮሽ፣ ድብብቆሽ ሱዚ፣ ሰኞ ማክሰኞ፣ ጢባጢቤ፣ ብይ፣ ሸርተቴ እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ኅዳር 22 ቀን 2014ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በተከናወነው የ‹‹ኑ ጭቃ እናቡካ አንድ ቀለም ፌስቲቫል›› እነዚህን ጨዋታዎች ልጆች ከቤተሶቦቻቸው ጋር እንዴት እንዳሳለፉት እናቀርብላችኋለን።
ልጆችዬ በፌስቲቫሉ ላይ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በመሆን ጭቃ በማቡካት እንዲሁም በጭቃ ጀበና ሲኒ፣ እንስራ፣ ድስት፣ ሳህን፣ የተለያዩ ፊደላት እና የተለያዩ ቅርፃ ቅርፆችን ሠርተዋል። በተጨማሪም አባሮሽ፣ ጥምጣም፣ ሱዚ፣ ሰኞ ማክሰኞ እና ሌሎች ጨዋታዎችን ከመጫወት በተጨማሪ በግመል እና በፈረስ ላይ በመንሸራሸር ደስ ብሏቸው አሳልፈዋል።
ናኦድ ኃይለ ማያርም ይባላል። ሰባት ዓመቱ ነው። የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ በፌስቲቫሉ ላይ ከአባቱ ጋር ጥምጣም ሲጫወት ነበር ያገኘነው። ብዙ ነገር እንደተመለከተ እና ብዙ ጨዋታዎችን እንደተጫወተ የሚናገረው ናኦድ፤ ጥምጣም እና ሌሎች ጨዋታዎችን በመጫወት ቀኑን በደስታ ማሳለፉን ይናገራል።
በፌስቲቫሉ ሙዚቃ፣ ውዝዋዜ እና የተለያዩ ትዕይንቶች የነበሩ ሲሆን፤ ልጆች እና ወላጆች ደስ የሚል ጊዜን በጋራ አሳልፈዋል። ልጆችዬ ነጠላ፣ ጋቢ እና ሌሎች አልባሳት በጥጥ እንደሚሠሩ ታውቃላችሁ አይደለም?፤ ድሮ ድሮ እንደ አሁኑ ሽመና ሳይስፋፋ በፊት እናቶቻችን ጥጥ በመፍተል ለጋቢ እና ሌሎች አልባሳት ያዘጋጁ ነበር። በዚህ ፌስቲቫል ጥጥ እንዴት እንደሚፈተል ልጆች ሲማሩ ተመልክተናል።
የ11 ዓመት ታዳጊ የሆነችው ቢታንያ ዓለሙ በግመል ላይ ስትንሸራሸር አግኝተናት ነበር። በዕለቱ ሰኞ ማክሰኞ በመጫወት፣ ጥጥ እንዴት እንሚፈተል በመማር እና በጭቃ ሰሃን በመሥራት ከቤተሰቦቿ ጋር በደስታ ማሳለፏን ትናገራለች።
እሺ ልጆች ‹‹ወፍጮ ከመነጁ›› ሲባልስ ሰምታችኋል? እንደ አሁኑ የኤሌክትሪክ ወፍጮ ሳይስፋፋ በፊት እናቶቻችን የተለያዩ እህሎችን በመፍጨት ምግብና መጠጥ ለማዘጋጃነት ይጠቀሙበታል። ልጆችዬ የድሮ ሰዎች ጎበዞች ናቸው አይደል?፣ በርግጥ ይህ የወፍጮ ዓይነት አሁንም ቢሆን በገጠራማው የሀገራችን ክፍል ይጠቀሙበታል።
ሌላዋ የዚህ ፌዚቲቫል ታዳሚ ቤተልሔም ዓለሙ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ልክ እንደሌሎቹ ልጆቹ ሁሉ አስደሳች የሚባል ጊዜ አሳልፋለች። የተለያዩ ነገሮችን በፊስቲቫሉ ተመልክታለች። ጭቃ በማቡካት ለቤተሰቦቿ ፍቅሯን ገልፃለች። ብዙ ጊዜ ባይሆንም ከዚህ በፊት በቤቷ ጭቃ እያቦካች ተጫውታለች።
ሱዚ የተሰኘውንና ከዚህ በፊት ተጫውታ የማታውቀውን ጨዋታ በዚህ ፌስቲቫል ላይ ተገኝታ ተጫውታለች፤ አጨዋወቱንም ተምራለች። በተጨማሪም ጥጥ በመፍተል እና እህል እንዴት እንደሚፈጭ አውቃለች። በዚሁ አጋጣሚ ቤተልሔም ልጆች እንደዚህ ዓይነት ጨዋታዎችን ሲጫወቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው መክራለች።
ወይዘሮ ሀና ገብረ ክርስቶስ ከልጇ ጋር ሱዚ ስትጫወት ነበር ያገኘናት። ከዚህ ቀደም ልጅ ሆና ትጫወታቸው የነበሩትን ጨዋታዎች ከልጇ ጋር በመጫወቷ ደስተኛ ናት። ጨዋታዎቹም የልጅነት ሕይወቷን ተመልሳ እንድታስታውስ መለስ ብላ እንድታስታውስ አድርጓታል። በጭቃ ጀበና እና ስኒ በመሥራት ጥሩ ጊዜ አሳልፋለች።
በዚሁ «ኑ ጭቃ እናቡካ አንድ ቀለም ፌስቲቫል» በልዩ ቤተሰባዊ ፍቅር ከነገ ተስፋዎች ከሆኑት ሕፃናት ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል ይላሉ የፕሮግራሙ አዘጋጆች። ከልጆቻችን ጋር በውሃ እየተንቦራጨቅን፣ ጭቃ እያቦካን እና በውሃ እየተራጨን በደስታ አብረን እየፈነደቅን አይረሴ ጊዜ አሳልፈናል። ጢባጥቤ፣ ሱዚ፣ ቴዘር፣ ብይ፣ ሴንተር፣ ሰኞ ማክሰኞ እና ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያዊ የልጅነት ጨዋታዎችን ሀገራዊ እሴቶቻችንን ሲሞክሩ እና ሲጫወቱ አይተናል። «የነገ ተስፋዎቻችን፤ እድግ በሉልን! አብቡልን ሲሉም» ምርቃታቸውን ሰጥተዋል።
በ«ኑ ጭቃ እናቡካ አንድ ቀለም ፌስቲቫል» ላይ በተለያየ ምክንያት መሳተፍ ላልቻሉ እንዲሁም ከልጆቻቸው እና ከወዳጆቻቸው ጋር መጫወት የሚፈልጉ ቤተሰቦች እንዲህ ያለውን ቀን ለማሳለፍ አንድ ዓመት መጠበቅ አይጠበቅባቸውም የሚሉት አዘጋጆቹ፤ 22 ከድንበሯ ሆስፒታል ጀርባ በሚገኘው ማዕከል ዘወትር ከሰኞ እስከ እሁድ በመምጣት መታደም እንደሚቻል ይጠቁማሉ።
ልጆች እና ወላጆች መጥተው ጭቃ እያቦኩ፣ ጥጥ እየፈተሉ፣ እህል እየፈጩ፣ እየወቀጡ እና በሌሎች የልጅነት ጨዋታዎች ሲደሰቱ እንዲውሉም ይጋብዛሉ። ልጆችዬ በፌስቲቫሉ ላይ ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጥሩ ጊዜ እንደነበራቸው ለማወቅ ችለናል። ታዲያ ልጆችዬ ለሁሉም ነገር ጊዜ እና ወቅት እንዳለው በመረዳት ማጥናት ባላባችሁ ሰዓት ማጥናት፤ መዝናናት ባለባችሁ ሰዓት ደግሞ መዝናናት እንዳለባችሁ መዘንጋት የለባችሁም። ታዲያ ሁልጊዜ እንደምንላችሁ ጥንቃቄ አይለያችሁ!
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም