በአስራ ስድስተኝነት ሀገራችን በዩኔስኮ ያስመዘገበችው የሸዋል ኢድ

 በሚዳሰሱም ሆነ በማይዳሰሱ መስህቦች ልክ ውጤታማ እንዲሆን ወይም በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን እንዲማርክ፣ የማይረሳ ትውስታ በመተው የሀገርንም ሆነ የመስህቡ መዳረሻ የሆነው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እንዲያጎለብት ብዝሀነት ያላቸውን መስህቦች ማስተዋወቅ፣ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነትን ሥራ ላይ ማዋል፣ መስህቦችን የማስተዋወቅና የገበያ ሽያጭ ወይም የማርኬቲንግ ሥራን ማሳደግ፣ የመስህቦችን ቀጣይነት መጠበቅ፣ ሰላምንና ደህንነትን ማረጋገጥ፣ ተደራሽነትን ወዘተረፈ ማመቻቸት ግድ ይላል።

የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ መስህቦችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው። ከሰሞኑን የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር በማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቧል። ኢትዮጵያ ካሏት ደማቅ ማህበራዊ እሴቶች ውስጥ አንዱ የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ከማድረጉም ባለፈ የሀገር መልካም ገፅታ በመገንባት ረገድ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

የሸዋል ኢድ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ የክልሉን የቱሪዝም ማዕከልነት የሚያሳድገው ከመሆኑ በተጨማሪ የሕዝብን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንፃር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል። ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ሐረር ከተማን በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ የሀገራችን ከተማ አድርጓታል። ነገርን ነገር ያነሳዋልና እስከዛሬ በዩኔስኮ የተመዘገቡትን መስህቦች በወፍ በረር እንመልከት።

ኢትዮጵያ ውስጥ የመስቀል በዓል በሚከበርበት መስከረም 17 በየዓመቱ የዓለም የቱሪዝም ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል። በዚህ ዕለት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚንቀሳቀስበትን “ጭስ አልባ” ኢንዱስትሪ የሚባለውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማጎልበት ሀገራት ጥረት ያደርጋሉ። በተለያዩ ዝግጅቶችም ሁሉም እንደየ አቅሙ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሌሎችንም ጎብኚዎችን ሊስቡ የሚችሉ የቱሪዝም ሀብታቸውን በማስተዋወቅ ከዘርፉ ተጠቃሚነታቸውን ለማጉላት ጥረት ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በተለያዩ ዘርፎች የታደለች ከመሆኗ ባሻገር በርካታ የቱሪስት መስህቦችን በዓለም ደረጃ ለማስመዝገብ ችላለች። ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ ውስጥ የተካተቱ በርካታ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች አሏት። ቅርሶቹ ከአክሱም ሐውልቶች እስከ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ድረስ የተዘረጉ ናቸው። ከእነዚህም መካከል አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ እንዲሁም የሰው ዘር መገኛ ስፍራዎች ተካተውበታል። እነዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለቱሪስት መዳረሻነት ተመራጭ ከሚያደርጓት ነገሮች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ኢትዮጵያ ሰሞኑን የተመዘገበውን የሸዋል ኢድ ጨምሮ በዓለም ቅርስነት 16 ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ናት።

1. የላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተክርስቲያናት፦ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከአንድ ወጥ ድንጋይ በመፈልፈል የተሠሩ ሲሆን፣ እኤአ በ1978 በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል። በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ከአዲስ አበባ በ645 ኪ.ሜትር ላይ የሚገኙት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እንደተደቀኑበት በባለሙያዎች ሲነገር ቆይቷል።

2. የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፦ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እ.ኤ.አ በ1978 በዩኔስኮ የዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን፣ በ2009 ዓ.ም በዩኔስኮ የአደጋ ተጋላጭ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ተካቶ ነበር። በወቅቱ ፓርኩ በጥበቃ መጓደል፣ በደን መጨፍጨፍ እና በአካባቢው ሕዝብ እየታረሰ እንስሳትም እየተሰደዱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን የተመለከተው ዩኔስኮ፤ በአደጋ ላይ ነው በሚል መዝግቦት እንደነበረና ሁኔታዎች በአስቸኳይ ካልተስተካከሉ ሊሰርዘው እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር። ፓርኩ ከመጠን በላይ በግጦሽ በመጎዳቱ እንዲሁም ዋሊያ አይቤክስ፣ የሰሜን ቀይ ቀበሮ እና ሌሎች ግዙፍ አጥቢ እንስሳት ቁጥራቸው በመመናመኑ ነበር ለአደጋ የተጋለጡ የዓለም ቅርሶች መዝገብ ላይ ሰፍሮ የቆየው። ፓርኩ በ1960ዎቹ በሕዝብ ተከልሎ ሲጠበቅ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም በዩኔስኮ ተመዝግቦ የዓለም ቅርስ መሆኑ እና በተለይ በሀገሪቱ ውስጥ በሰሜን ተራሮች ላይ ብቻ የሚገኘው ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቀበሮ እና ጉሬዛ ይገኙበታል። በተጨማሪም ፓርኩ በርካታ አዕዋፋትን የያዘው እንደ ውጬ፣ ዝግባ፣ ወይራ እና ዋንዛ የመሳሰሉ ዛፎች እንዲሁም ሌሎች ቁጥራቸው የበዛ የተለያዩ እጽዋት የሚገኝበት ሲሆን፣138 ስኩዬር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው።

3. የፋሲል ግቢ እና የጎንደር ሐውልቶች፦ የፋሲል ግቢ እና ሌሎች ሥነ ሕንጻዎች እንዲሁም አብያተ መንግሥታት እኤአ በ1979 በዓለም ቅርስነት ተመዝግበዋል። ይህ በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ ከአዲስ አበባ በ748 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ታሪካዊ ቅርስ የሀገሪቱ ጥንታዊ ሥልጣኔ ሕይወት ያለው ምስክር ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። በጎንደር ከተማ የሚገኘው የንጉሥ ፋሲል ግቢ የንጉሣውያን ዋነኛ ማዕከል የነበረ ሲሆን፣ ዙሪያው 900 ሜትር ርዝመት ያለው ግንብ እና በ12 በሮች የተከበበውን መንገድ የሚዞር ድልድይ አለው። በ1632 ዓ.ም በንጉሥ ፋሲለደስ ዘመን ጎንደር የኢትዮጵያ የአስተዳደር ዋና ከተማ የነበረች ሲሆን፣ በ16ኛው እና በ12ኛው ክፍለ ዘመን የታጠረው የፋሲል ግቢ የንጉሥ ፋሲል እና የተከታዮቻቸው መኖሪያ ነበር።

4. አክሱም፦ አክሱም ሰው ሰራሽ አርኪዮሎጂ ስፍራ ሲሆን፣ እኤአ በ1980 በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ይህ በትግራይ ክልል ከአዲስ አበባ በ1080 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቅርስ ከፍተኛ የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት፣ እንዲሁም ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍን የሚወክል በመሆኑ መመዝገቡን የዩኔስኮ ሰነዶች ያሳያሉ። የኢትዮጵያ ጥንታዊ መዲና እና መንግሥት የነበረችው አክሱም፣ ተመራማሪዎች እንደሚገልጿት የኃያል መንግሥት ዋና ከተማ፣ ቀጥሎም የሃይማኖት ማዕከል ብሎም የጥንታዊ ሃይማኖታዊ መንግሥት በአፍሪካ ውስጥ የመሠረተች፣ አሁንም በርካታ ምዕመናን የምታስተናግድ ከተማ ነች።

5. የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፦ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ የተፈጥሮ (የፖሊዮ አንትሮፖሎጂ) ግኝቶች ስፍራ ነው። ሸለቆው የሰው ዘር እና የአትክልት ቅሪት በዙሪያው የተገኘበት ሲሆን፣ ተከታታይ የጥናት እና የምርምር ሥራ በቦታው ተሰርቷል። እኤአ በ1980 በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ይህ ስፍራ በአፋር ክልል ከአዲስ አበባ በ577 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል። ይህ ስፍራ ኢትዮጵያ ሰው ዘር መገኛ መሆኗን ያሳወቀ ስፍራ ነው። በዚህ ስፍራ በ1974 ዓ.ም 3.2 ሚሊዮን እድሜ ያስቆጠረችው ሉሲ ስትገኝ፣ 4.4 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረችው አርዲም የተገኘችው በዚሁ ስፍራ ነው። 3.6 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረችው የሦስት ዓመቷ ሕፃኗ ‘ሰላም’ ቅሪትም በዚሁ ቦታ ተገኝታለች።

6. የጢያ ትክል ድንጋዮች፦ ጢያ ትክል ድንጋዮች ባህላዊ (የአርኪዮሎጂ) ግኝት ስፍራ ነው። እኤአ በ1980 በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው እና ከአዲስ አበባ በ86 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በደቡብ ክልል ይገኛል። የእነዚህ ትክል ድንጋዮች ብዛት ወደ 36 የሚጠጋ ሲሆን የተለያየ ስፋት፣ ርዝመት (ከ1 እስከ 5 ሜትር) እና ውፍረት አላቸው። 32ቱ ትክል ድንጋዮች ላይ የተለያዩ ምስሎች (የጎራዴ፣ የጦር፣ የጨረቃ፣ ፀሐይ መሰል፣ የእጅ እና ምንነቱን መለየት ያልተቻለ ቅርጽ) ተቀርጾባቸዋል።

7. የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፦ ይህ የፖሊዮ አንትሮፖሎጂ ግኝቶች ስፍራ የሆነው የታችኛው ኦሞ ሸለቆ እኤአ በ1980 በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። በደቡብ ክልል ከአዲስ አበባ በ1000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

በዓለም አቀፍ ቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም የተመዘገበው ይህ ስፍራ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከኛንጋቶም እስከ ዳሰነች አካባቢ የሚገኘውን ክፍል ይሸፍናል። የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ስለሰው ልጅ አመጣጥ እና ቅድመ ታሪክ ጥናት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው። ከ2.4 ሚሊዮን ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ጥንታዊ ቁሳቁሶች እና የሰው ዘር ቅሪተ አካላት የተገኙበት ይህ አካባቢ በርካታ የተለያዩ ጥንታዊ ባህላቸውን እና አኗኗሯቸውን የሚከተሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ይኖሩበታል።

8. የሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ፦ የሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ በጥንታዊ በሮች እና ታሪካዊ ሥነ ሕንጻዎች ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ ተመዝግቧል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም እኤአ በ2006 የተመዘገበው ይህ ቅርስ፣ በሐረሪ ክልል ውስጥ ከአዲስ አበባ በ525 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል።

ጥንታዊ የኢትዮጵያ ከተማ የሆነችው ሐረር በ7ኛው ክፍለ ዘመን መቆርቆሯ ይነገራል። በጀጎል ግንብ የተከበበችው ሐረር ከተማ አምስት በሮች አሏት።

ሐረር ለዘመናት ከፍተኛ የንግድ ማዕከል ሆና ከመሃል ሀገር፣ ከአፍሪካ ቀንድ እና ከአረብ ሀገራት ጋር በንግድ ስትገናኝ ከቀሪው ዓለም ጋር ደግሞ በቀይ ባሕር ወደቦች አማካኝነት ትገናኝ ነበር።

9. ኮንሶ፦ የኮንሶ መልክዓ ምድር በእርከን የታጠሩ መንደሮች ባህላዊ ቅርስ ሆኖ እኤአ በ2011 በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ይህ በደቡብ ክልል የሚገኘው እና ከአዲስ አበባ 595 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ቅርስ በውስጡ በርካታ ባህላዊ ሀብቶችን ይዟል። በኢትዮጵያ የ400 ዓመት እድሜ እንዳለው የሚነገረው የኮንሶ ሕዝብ ባህላዊ መኖሪያ በውስጡ በካብ የታጠሩ መንደሮች፣ ባህላዊ ጎጆዎች፣ ጥብቅ ደኖች፣ ሐውልቶች እና ኩሬዎችን የያዘ ነው።

10. መስቀል፦ የኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርት እና ባህል ተቋም መዝገብ ውስጥ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ካስመዘገበቻቸው ታዳሽ ዓለም አቀፍ ቅርሶች በተጨማሪ የመስቀል ባህላዊ ክብረ በዓል አስረኛው የመጀመሪያው የማይዳሰስና የማይጨበጥ (ህሊናዊ) ባህላዊ ቅርስ በመሆን ነበር የተመዘገበው።

11. ፍቼ ጫምባላላ፦ የሲዳማ ብሔር አዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ የሆነው ፍቼ ጫምባላላ በዓል በሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ዝርዝር ውስጥ የተመዘገበው በኅዳር 2008 ዓ.ም ነበር።

ፍቼ ጫምባላላ በዓል በውስጡ በርካታ ባህላዊ ክንዋኔዎችን የያዘ ነው።

12. የገዳ ሥርዓት፦ የገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ተቋም ግዙፍነት በሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ወካይ መዝገብ (ሪፕረዘንታቲቭ ሊስት ኦፍ ዘ ኢንታንጀብል ካልቸር ኦፍ ሒውማኒቲ) መስፈሩ ይፋ የተደረገው ኅዳር 2009 ዓ.ም. ነበር። የኦሮሞ ሕዝብ በረጅም ዘመናት ውስጥ ካዳበራቸው የአኗኗር ዘይቤዎች እና ሥርዓቶች መካከል አንዱ የገዳ ሥርዓት ነው።

የገዳ ሥርዓት በዋናነት የአስተዳደር ሥርዓት ሲሆን የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመምራት የሚረዱ ዕሴቶችን አካትቷል። ይህ የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ እሴት ዋና ምሰሶ የሆነ ሥርዓት ሃይማኖታዊ እና የሕግ ሥርዓቶችን በውስጡ አካቶ ይዟል። በተጨማሪም የገዳ ሥርዓት ከውልደት እስከ ሽምግልና ድረስ በዕድሜ በመከፋፈል የተለያዩ የማኅበረሰብ ኃላፊነቶችን እና የሥልጣን ድርሻዎችን ይሰጣል። በገዳ ሥርዓት ውስጥ ዋቄፈና እና ኢሬቻ የተሰኙ የዕምነት እና ባሕላዊ ሥርዓቶች ይገኙበታል።

13. ጥምቀት፦ የጥምቀት በዓል የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ከመዘገባቸው የኢትዮጵያ ሀብቶች መካከል አንዱ ነው። ቦጎታ ኮሎምቢያ ውስጥ ድርጅቱ ስለ ቅርስ ጥበቃ በተነጋገረበት ስብሰባ ላይ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት በዓሉ በዩኔስኮ የተመዘገበ 4ተኛው የማይዳሰስ ቅርስ ሆኗል።

ጥምቀት በወርሃ ጥር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባዮች በድምቀት ተከብሮ የሚውል ሃይማኖታዊ በዓል ነው።

የጥምቀት በዓል ከዋዜማው ከተራ ጀምሮ ጥር 11 እንዲሁም በማግስቱ ጥር 12 በቃና ዘገሊላ በዓል በድምቀት ይከበራል። ጥምቀት በኢትዮጵያ ውስጥ በድምቀት ከሚከበርባቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አዲስ አበባ እና ጎንደር ተጠቃሾቹ ናቸው።

14. የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ ምድር፦ የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ ምድር፣ የመሬት አያያዝ፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ትክል ድንጋዮች፣ የዋሻ ላይ ጽሑፍ እና በባሕላዊ መንገድ ብቻ የሚተዳደሩ ደኖች ይገኙበታል። ከ6 ሺህ በላይ ትክል ድንጋዮች በዞኑ የተለያዩ ሦስት ስፍራዎች ይገኛሉ። እነዚህ የትክል ድንጋዮች የሚገኙባቸው ሦስት ስፍራዎች ጨልባ ቱቲቲ የአርኪኦሎጂካል መካነ ቅርስ፣ ቱቱፈላ እንዲሁም በርካታ ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ እና የድንጋይ ላይ ጽሑፎችን የያዘው ኦዶላ ገልማ ናቸው።

15. የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፦ በ1962 ዓ.ም የተመሠረተው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ በ400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። የመሬት ሽፋኑ 215 ሺህ ሄክታር የሆነው ብሔራዊ ፓርኩ በውስጡ በርካታ ብርቅዬ እንስሳትን ይዟል። 4377 ጫማ የሚረዝመው እና ከኢትዮጵያ በከፍታው ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የቱሉ ዲምቱ ተራራን ጨምሮ የአፍሮ አልፓይን ከፍተኛ ቦታዎች በዚህ ፓርክ ውስጥ ይገኛሉ።

የባሌ ተራሮች ከፍተኛ አካባቢ በተለያዩ መንገዶች የተፈጠሩ ሐይቆች፣ እርጥበት አዘል መሬቶች፣ የእሳተ ጎሞራ ቅሪቶችን አቅፎ ይዟል።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You