ኅዳር 29 -ከብሔራዊ ቀንነት በዘለለ

ኅዳር 29 የብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ነው። ይህ ቀን ጥቂቶች ከብዙኃን፤ ብዙኃንም ከጥቂቶች ጋር እኩል እይታ እና ምልከታ እንዲሰጣቸው የሆነበት፤ የዜጎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሻታቸው ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና አግኝቶ መተግበር የጀመረበት ቀን ነው።

ይህ ቀን በዘመናት ውስጥ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት መሠረት የተጣለበት ታሪካዊ ዕለትና ክስተትም ጭምር ነው። ቀኑ በዋነኛነት የሚከበረው በሕገ-መንግሥት የተደነገጉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድንጋጌዎች በአግባቡ መተግበራቸውን በመገምገም፣ የተፈጠሩ ክፍተቶችን እያረሙ በሕገ- መንግሥቱ የተገኙ ድሎችን እያጠናከሩ እንዲሄዱ ለማስቻል ነው።

በሕገ-መንግሥቱ የመግቢያ ምዕራፍ ላይም፤ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነፃ ፍላጐታችን፣ በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል›› ሲል ያብራራል። ዓላማውን ከግብ ለማድረስም፣ የግለሰብ፣ የብሔር እና ብሔረሰብ መሠረታዊ መብቶች መከበራቸው፣ የፆታ እኩልነት መከበሩ፤ ባሕሎችና ሃይማኖቶች ካለአንዳች ልዩነት እንዲራመዱ የማድረጉ አስፈላጊነት ጽኑ እምነታችን ስለመኖሩና በዚህ ላይም የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብሎ እንደሚያምንም በማስቀመጥ ቀጣይ ዕድልንም በጋራ ለመወሰን ሕገ-መንግሥቱ ኅዳር 29 ቀን 1987 መፅደቁን ያብራራል።

የዚህ የዜጎች የጋራ ሰነድ /ሕገ-መንግሥት መፅደቅ ለበዓሉ መከበር ዋነኛ ምክንያት ሲሆን፣ የበዓሉ መከበርም ሆነ ኃይለ ቃሉም የሚመዘዘው፤ ተግባሩ የሚመነዘረው ከላይ ከተጠቀሰው ሕገ-መንግሥታዊ ሃሳብ ነው። በዓሉ በዚህ ዓመትም ለ18ኛ ጊዜ ‹‹ብዙኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት›› በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ተከብሯል።

በርግጥ ቀኑ ላለፉት 17 ዓመታት ተክብሯል፤ ተዘክሯል። አሁን ላይ መነሳት ያለበት መሠረታዊ እውነታ ግን ባለፉት ዓመታት በተከበሩ በዓላት የተገኙ ለውጦችና ትሩፋቶች ምንድን ናቸው? የሚለው ሊሆን እንደሚገባ ይሰማኛል። በተለይም በኢትዮጵያ የአብሮነት ታሪክ ውስጥ ያስቀመጠው መልካም ተሞክሮ ምንድን ነው? የሚለውን ማየትና በቀጣይ ደግሞ ይህ በምን መልኩ የበለጠ ሊፈካ እና ሊዳብር ይችላል ብሎ ማሰላሰል ተገቢ ነው።

የሀገሪቱ ምሁራን በተለይም በታሪክ እና በፌዴራሊዝም ላይ ትኩረት ያደረጉ ምሁራን እስካሁን የመጣንበት መንገድ (የፌዴራሊዝም) ምን ይመስላል? የሚለውን በማየት በቀጣይ ለምንፈልገው አሰባሳቢ ትርክት የሚሆን ግብዓት ማሰባሰብ ይኖርባቸዋል።

ከሕገ-መንግሥቱ በፊትና በኋላ ያለችው ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች? ኅዳር 29 ቀን መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሕገ-መንግሥቱ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተገኙ ለውጦች ምንድን ናቸው? ለሚሉና መሰል ጥያቄዎች ሙያዊ / ሳይንሳዊ ትንታኔ መቅረብ የሚችሉበትን የቤት ሥራ ወስደው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ሕገ-መንግሥቱ እውን ከተደረገ ወዲህ ያሉ ዓመታት እንደ ሀገር የመጣንበት መንገድ ምን ይመስል ነበር ? ጠንካራ ጎኖቹስ ምን ነበሩ? ብሎ ማየት፣ በቀጣይ ለመገንባት ለምንፈልጋት የጋራ ሀገር የሚኖረው አሉታዊና አዎንታዊ ገጽታ ምን ይመስላል? የሚለውን በመለየት ችግሮችን ማስተካከል፣ መልካም የሆኑ ነገሮችን እያጠናከሩ መቀጠል ያስፈልጋል።

እንደ ሀገር ከትናንቱ ወቃሽ ተወቃሽ ትርክት ወጥተን የአንድነትና የምሉዕነት ትርክት መፍጠርና ማበረታታት ወደሚያስችል የታሪክ ምዕራፍ ለመሻገር፤ ነገሮችን በቀና ልብ እየተመለከትን ለመጭዎቹ ትውልዶች የተሻለች ሀገር ለማስረከብ የቀኑ መከበር ከበዓል በአለፈ አቅም የሚሆንበትን እድል መፍጠር ይኖርብናል።

ኅዳር 29 ቀን የብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ከሚለው እሳቤ በዘለለ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጠናክረን የምንቀጥልበት፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ፈጥረን የምንቀሳቀስበት መሆን አለበት።

ገና ያላለቁ፣ በጅምር ያሉ በርካታ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን የተመለከቱ የባህል፣ እሴትና የወግ ልማት የቤት ሥራዎች አሉብን። ጅምር ሥራዎች ወደ ፍጻሜ ለማድረስ ሰፊ ጥረቶች ይጠይቃሉ።

የኢትዮጵያ መፃዒ ጊዜ በፅኑ መሠረት ላይ የተጣለ እንዲሆን፤ ሀገራዊ አንድነትና ፍቅር ብሎም ሕገ- መንግሥታዊ መሠረቱ በጠነከረ አለት ላይ እንደተገነባ ሕንፃ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት። የጋራ ታሪክ፣ ድል ብሎም ዕድል ያለን ሕዝቦች መሆናችንም የቆየ ታሪካችንን የሚሳይን ሲሆን፤ በቀጣይም ይህ የበለጠ ውበት ባለው ሁኔታ እንዲጓዝ መሥራት ይኖርብናል።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህልና እሴት ብዙኃነትን የያዘች ሀገር ናት። በመሆኑም በዚህ ሂደት ውስጥ ጠንካራ የሆነ ፌዴራል ሥርዓት መገንባትና የብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት የሚከበርባት ብሎም የዴሞክራሲ መሠረት ያላት ሀገር ማድረግም የሁላችንም ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።

የብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ከማክበር በዘለለም የፌዴራል ሥርዓቱን የበለጠ የሚያዘምን፣ መተማመን፣ መከባበርና መቻቻልን የሚያጎናጽፍ ብሎም ለሀገር አንድነት ድርና ማግ የሆነ እሳቤ እንዲፈጠር አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የውክልና ማዕከል የሆነው ፌዴሬሽን ምክር ቤትም ይህ ቀን የበለጠ ሳይንሳዊ እና ሀገራዊ ፋይዳው በጎላ መንገድ እንዲከበር የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ በመሆኑ በቀጣይ እስካሁን ከመጣንበት አካሄድ የበለጠ ሊሠራበትና የፌዴራል ሥርዓቱ በሚጠናከርበት ላይ ሚናውን ሊወጣ ይገባል የሚል እምነት አለኝ።

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You