በልዩነት የደመቀ ህብረ- ብሄራዊ ኢትዮጵያዊነት

ብዙ መልክ ከአንድ ነጠላ እውነት ተፈልቅቆ ሲወጣ ሀገር ስያሜዋ የብዙሃን እናት ይሆናል። በአንድ አይነት የመንፈስ ልዕልና ከዘመን ዘመን መወሳት ምስጢሩ መቻቻል ቢሆንም የሕዝቦች የባህልና የታሪክ ውርርስም በዚህ ብኩርና ውስጥ ቀዳሚ ሆኖ የሚጠቀስ ጉዳይ ነው።

ዘመን ላስቆጠረ የአብሮነታችን ዳና ሌላም የብርታት ክንድ መጥቀስ እንችላለን። እርሱም በጋራ ታስበው በጋራ የተበጁ የሥርዓትና የባህል ውርሶቻችን ናቸው። እምነትና ፍቅር ከይቅርታና ከእርቅ ጋር ጥንተ ወዛችን ሆነው ስለወንድማማችነታችን ከፊት የሚመጡ ፋና ወጊያችን ናቸው።

በአብሮነት ውስጥ ለሚፈጠሩ እክልና ቅራኔዎች መልካም እሴቶቻችን አስታራቂና አዋሃጅ ሆነው ሶስት ሺ ዘመናትን አልፈናል። ከራሳችን አልፈን ጥበብና እውቀት ለራቃቸው ጎረቤቶቻችን የመኖር ዋስትና ሆነን ከሰላማችን ስናካፍል፣ ከፍቅራችን ገምሰን ስንሰጥ ታሪክ መዝግቦናል።

ከሰማንያ የላቅን፣ የአንድነት መንፈስ ያበረታን የጦቢያ ልጆች ተብለን በድል አድራጊነት ከፊት ቆመናል። ግን እንዴት በረታን? እንዲህ አይነት በብዙሃነት ውስጥ አንድነት የተንጸባረቀበት የብርታት መንፈስ መገኛው ሕዝባዊነት ነው። ከራስ ወዳድነት የጸዳ፣ ሀገርን ያስቀደመ፣ ትውልድን አርቆ ያየ አእምሮና ልብ የፈጠሩት ብርታት ነው።

ህብረት ያገነነው፣ ፍቅር የማገረው የታሪክ ወገብ፣ አንድነት ያጸናው፣ እኛነት ያበረታው የማንነት ራስ ኢትዮጵያዊነት ይሄን ነው። ሥርዓት ያቆመው፣ ጨዋነት ያነጸው የሰላም ዓርማ ሀበሻነት ይሄን ነው። እየሠጠንና እየተቀበልን፣ እየመከርንና እየተግባባን ሀገር የሠራን ባለሀገሮች ነን።

ዘመናዊነት ስም ሳያገኝ በፊት በእጆቻችን ተባርኮ፣ በከንፈራችን ተስሞ ሂድ ወደዓለም ብለን አቅጣጫ የሰጠን በትረ ሙሴዎች፣ ምክረ ዮቶሮች እኛ ማለት ይሄን ነን። እምነትን ከእውነት ቀይጠን ፍትህንና ሚዛናዊነትን ያሰማራን፣ በአንደበታችን ሀቅ፣ በምላሳችን ፍርድ ሂዱ ወደሀበሻ የተባለልን ከሁሉም ደማቆች ሕዝቦች ነን።

ከዚህ ውስጥ ወጥተን ነው እኔንና እናንተን የሆነው። የትኛውም ትርክት ይነገረን ኢትዮጵያዊነት መነሻው ይሄ ነው። የትኛውም ፖለቲካ፣ የትኛውም ወዳጅ ይንገረን ቀለማችን ይሄን ነው። አሁን ላይ የምንሰማቸው የታሪክ ሽርፈቶች ኢትዮጵያዊነትን የማይገልጹ የጥቂት ግለሰቦች የእብለት ከንፈር ነው።

ከሁሉም የሚልቀው እውነት እኔና እናተ በተያያዙ..በተፋቀሩ..በተመካከሩ አባቶቻችን ተያይዘን የተፈጠርን ነን ። እንዲህ ያለውን ካልሆነ ስለሀገራችን ከማንም ምንም ለመስማት የተዘጋጀ ማንነት ሊኖረን አይገባም። መርጦ መስማት እና መርጦ መናገር አሁን ላይ ለሀገራችን እጅግ ጠቃሚ ነገር ሆኖ ከፊት የሚመጣ ጉዳይ ነው።

ሳንመርጥ የሰማነውና ሳንመርጥ የተናገርናቸው አሉባልታዎች ከትናንት አምልጠው ዛሬ ላይ የብዙሃነት ቤታችንን ሊያፈርሱብን እየተገዳደሩን ነው። ትናንት የሆነ ወደ ዛሬ እንደመጣ ሁሉ ዛሬ የሆነ ሁሉ ወደነገ የሚሄድ ነው። የክብሮቻችን ጫፎች በከንፈራችን ድባብ ላይ ናቸው። ከቻልን ስለአንድነትና ስለኢትዮጵያዊነት በጎ እንናገር ካልቻልን ዝም እንበል። ዝምታ ከመልካም ቃል እኩል እንደውለታ የሚቆጠርበት ጊዜ አለ።

ከሌላው ተለይተን እኛ ማለት ብለን በኩራት የምንናገረው ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን። የታሪኮቻችን ውበት ደግሞ ተያይዘን መምጣታችን ነው። አብረን የበላንባቸውን እና ባንድ የተቀመጥናቸው ሸንጎና ደቦ፣ ሳንሳ እና ጎሜ ትናንትን ዘካሪ ምስክሮቻችን ናቸው። ብዙሃነት አብቦና ፈክቶ በብዙ ልዩነት ውስጥ አንድነትን የሰጠን በእንዲህ ባለው የታሪክ ውርርስ በኩል ነው።

ድርና ማግ ሸማ እንደሚሠሩ ሁሉ ብዙሃነትም ኢትዮጵያን ሠርተዋታል። ህብረብሄራዊነት ኢትዮጵያዊነትን አድምቀውታል። ተዋርሰንና ተደባልቀን ሀገርና ሰው የሆንን ሕዝቦች ነን። በጋራ ታሪክ እና ሥርዓት ውስጥ ተደባልቀን የተበጀን ውህድ ወንድማማቾች ነን።

ህዳርን ለብሄር ብሄረሰብ ሰጥተን ደምቀንና ተውበን የምንታየው በምክንያት ነው። ህዳር 29 በልዩነት ውስጥ የደመቀ አንድነታችንን ተሰባስበን በልዩ ልዩ ባህሎቻችን የምናከብረው የብዙሃነት ቀናችን ነው። ዘንድሮም እንዳለፈው ጊዜ ልዩነታችን ውበታችን ውበታችን አንድነታችን እንደሆነ በጋራ ድምጽ ለጋራ ታሪክ የምናስተጋባበት ነው።

ኢትዮጵያና ህብረብሄራዊነት ሁሌም የሚወሱ የታሪክ አልቦዎች ቢሆንም በአንዳንድ ትርክት ፈጣሪ አፎች የሚገባቸውን ክብር እያገኙ ግን አይደለም። ተያይዞና ተደጋግፎ ከዘመን ዘመን የተሻገረ ታሪክና እሴት ግላዊ ፍላጎት ባላቸው ጥቂት ሰዎች ውበቱን እንዳያጣ አክራሪ ብሄር ተኮር እሳቤዎችን የሚንድ የአንድነት መድረኮች ያስፈልጉናል።

ሀገር የቀደመችበት የታሪክ ምንጣፍ ማንንም አደናቅፎ አይጥልም። ግለሰብና ቡድን የቀደሙበት የታሪክ ምንጣፍ ግን ሀገር ይጥላል። ሕዝብ፣ ትውልድ ያደናቅፋል። አሁናዊ መደነቃቀፎቻችን ከሀገር ቀድመን ለመቆም የምናደርገው የብኩርና ግፊያ የፈጠረው ስለመሆኑ ሁለት ጊዜ ማሰብ አይጠይቅም።

ሀገር ከሠሩ የታሪክ አንጓዎች ውስጥ ቀዳሚው ብዙሃነት ነው። ብዙሃነት የሃሳብና የባህል፣ የሥርዓትና የአብሮነት ትስስር ነው። የፍቅርና የመቻቻል፣ የታሪክና የመተሳሰብ መነሻ ነው። እንዲህ ብለን ከማመንና ከመረዳት ባለፈ እንዴትም ብንጠይቅ ሌላ ስያሜ አናገኝለትም።

አንዳንድ ክፉ ልብ ያላቸው ሰዎች ይሄን የሚታይና የሚዳሰስ እውነታ ከልለው ልዩነትን ለማጉላት ይቃጣቸዋል ሆኖም ተሳክቶላቸው አያውቅም። አይሳካላቸውም ብሎ መቀመጥ ሁልጊዜም ልክ አይመጣም። እንዳይሳካላቸው እውነትን መንገርና የጋራ ትርክትን መፍጠር ወደረኞቻችንን እንድንረታ ይረዳናል።

ባለፈውና ባለው የታሪክ ዳና ላይ ኢትዮጵያዊነት ከሚገለጽባቸው ደማቅ እውነታዎች ውስጥ አንዱ ብዙሃነት ነው። ይሄ እውነት ወደፊትም የሚቀጥል የመቶሃያ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ፍላጎትና ምኞት ነው። ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ ገዝፈንና ተልቀን የተጠራንባቸው የታሪክ ገድሎቻችን በዚህ ስም በኩል ገናናነትን ያገኙ ናቸው። ተነጣጥለን ታሪክ ጽፈን አናውቅም። ተለያይተን ደምቀን አናውቅም። የመጣንባቸው የመከባበርና የመተሳሰብ ዘዬዎቻችን ሀገር እንደሠሩልን መረዳት ቀላል ነው።

በመጣንበት መሄድ ሳንንገዳገድ ለመድረስ አማራጭ የሌለው ግዴታችን ነው። እንደሀገር አሁን ያሉብንን ተግዳሮቶች ለመሻገር ከአሁን ይልቅ ትናትን ማሰቡ የተሻለ ነው። ከዚም ከዛም የሚሰሙ አብሮነትን የሚንዱ ትርክቶች አይቶ ከማለፍና ሰምቶ ከመቻል ባለፈ ሁላችንንም የሚያግባባ የጋራ ትርክት ልንፈጥር ይገባል።

ብዙሃነትን ለመሻር አንዳንዶች ውሸት ሲፈጥሩ እኛ እውነት የማንናገረው ለምን ይሆን? አስመሳዮች ኢትዮጵያዊነትን ሊያደበዝዙ የአንድ ወገን ትርክት ሲናገሩ እኛ አንድነትን ለማስቀጠል የብዙሃን ትርክት መፍጠር ለምን ተሳነን? እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሻሉ።

ጥያቄ የሚጠየቀው በምክንያት ነው ምክንያታዊ መልስ መስጠቱ ደግሞ ሀገር የሚያሽር፣ ትውልድ የሚያሻግር መሆኑ አመራማሪ አይሆንም። መንግሥት የጋራ ትርክቶች የሚፈጠሩባቸውን መድረኮች በማዘጋጅት ሚናውን መወጣት ይችላል። ሕዝብ ዋጋ ያላቸውን ድምጾች እየመረጠ በመስማት አጋርነቱን ማስመስከር ይጠበቅበታል።

ብዙሃነት ጠብቀን የተገመድንበት፣ ተገምደን የጠነከርንበት የታሪካችን መሀሉን ነው። ይሄ መሀል በአጉል ትርክት ላልቶ እንዳይበጠስ እንደነበር የሚያስቀጥል የሥርዓትና የጨዋነት አፍ ያስፈልገናል። መለያየትን የሚሰብኩ፣ አንድነትን የሚያላሉ አንደበቶች ሊዘጉ፤ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን በአግባቡ ሊታይ ፤ ሊቃኝ ይገባል።

አብሮነትን ከማስቀጠል አኳያ ፤ በጋራ ሃሳብ የጋራ ማንነትን እንደሠራን ሁሉ የችግሮቻችን መፍትሄም በጋራ መጠይቅ መፍታት ይጠበቅብናል። በጀግንነትም ሆነ በልማት፣ በሥልጣንም ሆነ በሉዓላዊነት ከፊት ቀድመው የሚታዩ ታሪኮቻችን ብዙሃነትን የለበሱ ሆነው እናገኛቸዋለን። አሁን ላሉብን አሉባልታና የእርስ በርስ ፉክክር ለመውጣት እንደቀዳሚ መፍትሄ ሆኖ የሚነሳው ጉዳይ ከብቻ ትርክት ወጥተን የጋራ ትርክትን የመፍጠር ጉዳይ ነው።

ብዙሃነት እና ኢትዮጵያዊነት የአንድ እጅ መዳፍና አይበሉባ ናቸው። በአንድ ዛፍ ላይ የበቀሉ አበባና ፍሬ፣ ቅርንጫፍና ግንድ። እንዴትም ብናስብ ከዚህ እውነታ መራቅ አንችልም። ኢትዮጵያ ሥሯ የጠነከረ ዋርካችን ናት። እኛ ደግሞ በዋርካው ላይ ያለን አበባና ፍሬ፣ ቅርንጫፍና ግንድ ነን። የተነሳነው በአብሮነት ነው የምንሄደውም በአብሮነት ነው። ለመለያየት ብንሞክር እንለያይ ይሆናል በአንድ አቅፋ ለያዘችን ኢትዮጵያ ግን አንበጃትም።

ሀገር የህልማችን መጀመሪያ፣ የምኞታችን መጨረሻ ናት። ሥልጣኔን ለተረዳ ማህበረሰብ ልዩነት ጌጥ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ከሰማንያ በላይ ብሄር፣ ከሰማንያ በላይ ቋንቋ፣ ከሰማንያ በላይ ባህልና ወግ፣ ልማድና ሥርዓት አለን። እኚህ ሁሉ የአንድነት፣ የመከባበር ጌጦቻችን ናቸው። እኚህ ሁሉ የብዙሃነት ውበታችን ናቸው። እንደ ሀገር ብዙ ጌጦች አሉን። በጌጦቻችን የምንደምቀው ግን አንድነት ሲኖረን ነው። ፍቅር ሲኖረን ነው። መቻቻልና መግባባት ሲኖረን ነው። በታላቁ ስም በኢትዮጵያዊነት መጠራት ስንችል ነው።

ፍቅርና አንድነት፣ መቻቻልና ወንድማማችነት በሌለበት ሁኔታ ጌጦቻችን አያደምቁንም። ተነጋግረን የማንግባባ፣ ተግባብተን አብረን የማንኖር ከሆነ ጌጦቻችን አያደምቁንም። ጌጦቻችን እንዲያደምቁን ልዩነትን የተቀበለ አእምሮና ልብ ያስፈልገናል። የገዘፈ እኔነት ጌጦቻችን አያደምቀውም። ብዙሃነታችንን ለልማትና ለብልጽግና የማንጠቀመው ከሆነ አንደምቅም። ሀገሬ..የብዙሃን እናት..ሰላምሽ ይብዛ።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከሰማንያ በላይ ብሄር፣ ከሰማንያ በላይ ቋንቋ፣ ከሰማንያ በላይ ባህልና ወግ፣ ልማድና ሥርዓት አለን። እኚህ ሁሉ የአንድነት፣ የመከባበር ጌጦቻችን ናቸው። እኚህ ሁሉ የብዙሃነት ውበታችን ናቸው። እንደ ሀገር ብዙ ጌጦች አሉን። በጌጦቻችን የምንደምቀው ግን አንድነት ሲኖረን ነው። ፍቅር ሲኖረን ነው። መቻቻልና መግባባት ሲኖረን ነው። በታላቁ ስም በኢትዮጵያዊነት መጠራት ስንችል ነው

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ኅዳር 29  ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You