ልዩነታችን ውበታችን.. ውበታችን አንድነታችን … አንድነታችን ኃይላችን ነው

በአንድ ሀገር ላይ ልዩነት እና ውበት ሀገራዊ መልክ እንዲኖራቸው ህብረብሄራዊ አስተሳሰብ ወሳኝ ነው። በዚህ መልኩ ከሚገለጹ የዓለም ሀገራት መካከል ሀገራችን ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ሀገራችን ከሰማንያ በላይ የተለያዩ አስተሳሰቦች ከቋንቋና ባህላቸው ጋር ያደመቋት የብዙሀነት አብራክ ናት።

ብዙሀነት ውበትና ድምቀት ሆኖ እንዲቀጥል እንደመጀመሪያ ምዕራፍ የሚነሳው የመቻቻል ጽንሰ ሃሳብ ነው። የሀገራችንን የብሄር ስብጥር በትክክል ይገልጻሉ ተብለው ከሚታመኑ አንደበቶች የመጀመሪያው መከባበር የሚለው አንደበት ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነን ደግሞ ላለፉ ብዙ ዓመታት በልዩነቶቻችን አምረን በአንድነትና በብዙሀነት የቆምንባቸው ጊዜአቶች ናቸው።

በብዙ ልዩነት ውስጥ ተከባብረንና ተቻችለን ብዙ የአብሮነት ታሪኮችን ጽፈናል። ልዩነቶቻችንን የኃይል ምንጭ አድርገን ስለአንዲት ሀገራችን የፍቅርን ቤት ሠርተናል። ዛሬም በዛ ቤት ውስጥ በጋራ ያቀነቀነውን የአንድነት ዜማችንን እያሰማን ስለብዙሀነታችን ቀናችንን በማክበር ላይ እንገኛለን።

18ኛው የብሄር ብሄረሰብ ቀን ‹ብዙሀነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት› በሚል መሪና አብሳሪ መልዕክት እንዳለፈው ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ በጅግጅጋ ምድር እየተከበረ ይገኛል። በልዩነት ውስጥ የአንድነታችን ካባ ኢትዮጵያን ለብሰን በጋራ ድምጽ ከፍታችንን በማወጅ ላይ እንገኛለን።

በዓሉን አስመልክተው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሸጋ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ሰፊውን ማህበረሰብ ‹እንኳን ለኢትዮጵያዊነት በዓል አደረሳችሁ› በማለት የጀመሩ ሲሆን ‹በዓሉ ከምንም በላይ ይዘነው የመጣነውን የመከባበርና የመቻቻል መንፈስ የምናስቀጥልበት፣ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ እንደመሪ ሃሳቡ ብዝኃነትን ከእኩልነት ጋር የቀየጠ ሀገራዊ ህብረት የሚፈጥር ነው› ብለዋል።

መሪ ቃሉ እንደሚያመለክተው ፤ይህ በዓል የኢትዮጵያዊነት በዓል ነው። ኢትዮጵያዊነት ማለት ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማዕከል ያደረገ ሀገራዊ ማንነት ማለት ነው። ኢትዮጵያዊነት የብሔር ብሔረሰቦችን ብዝኃነት የሚቀበል፤ ይሄንን ብዝኃነት አስተሳስሮ የያዘና ለዘመናት የተሻገረ ጠንካራ አንድነት የያዘ ነው።

ብሄራዊ ትርክት ብሄራዊ ተሀድሶ ነው። አንድ በሚያደርገንና ዘላቂ ተግባቦትን በሚፈጥሩ አስታራቂ ትርክቶች ስር መቆማችን ከዛሬ አልፎ ወደነገ የሚሻገር አስተማማኝ ጉርብትናን የሚፈጥር ነው። በጋራ ታሪክ እና ትርክት ውስጥ ከማንና የማን እንደሆነ የማይታወቅ ነጣጣይ ትርክት እየፈጠርን ተከባብረን ሳይሆን ተፈራርተን መቆማችን እርግጥ ነው።

ከዚህ አይነቱ የአብሮነታችንን ካስማ ምሶሳችንን ከነቀነቀ መነሻ አልባ ትርክት ለመውጣት ከብሄር ብሄረሰቦች መሀል ተምጦ የተወለደ ከሁላችን ለሁላችን የሆነ ትርክት ያስፈልገናል። ይሄ እንዲሆን ደግሞ ወቅት እየጠበቁ የሚመጡ እንደብሄር ብሄረሰብ ቀን ያሉ ኢትዮጵያዊ በዓላት መነሻችን መሆን ይችላሉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው ፤ ‹የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ብሔራዊ ሀገርን ለመከፋፈልና ለማዳከም ከተገነባው ነጠላ ትርክት የምንወጣበት መንገድ ነው። ከፖለቲካዊ ታሪካችን ይልቅ ማኅበራዊ ታሪካችንን በማጉላት፣ ከትናንትና ይልቅ በዛሬና በነገ ዕድሎቻችንና ሥራዎቻችን ላይ በመመሥረት፣ በሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ላይ የቆመ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመመሥረት የሚያስችል ገዥ ትርክት ነው› ሲሉ ተደምጠዋል።

‹የብሔራዊነት ትርክት መነሻዎችም ባለቤቶችም ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው። ሃሳቡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መከራና ፈተና ሳይነጣጥላቸው፣ ለጋራ ዕጣ ፈንታቸው ሲሉ በአንድነት የከፈሉትን መሥዋዕትነት ከማፅናት የሚነሣ ነው። ኢትዮጵያን ያልገነባ፣ ለኢትዮጵያ ዋጋ ያልከፈለ፣ ማንም ሕዝብ የለም› ብለዋል።

‹ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በገነቧትና ዋጋ በከፈሉባት ኢትዮጵያ በፍትሐዊነት፣ በእኩልነትና በነጻነት የመኖር መብትም አላቸው። ኢትዮጵያን ከልመና የማላቀቅና የብልጽግናን መሠረት የመጣል ግዴታም አለባቸው። ብሔራዊነት ትርክት ይሄን ብዝኃነትና አንድነት ማዕከል ያደረገ አሰባሳቢ ትርክት ነው። ዘመን ተሻጋሪና ሁሉን አሰባሳቢ ኢትዮጵያዊነት መገንባት የምንችለውም በብሔራዊነት ትርክት አማካኝነት ነው። በዓሉን ስናከብር በዚህ መንፈስ እንደምናከብረው አምናለሁ› ሲሉ ገንቢ የህብረ ብሄራዊነት ትርክትን መሠረት ያደረገ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ብሄራዊ ትርክት ምን ያክል ዋጋ እንዳለው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት መረዳት እንችላለን። ያጣነው ግለሰባዊ ወይም ቡድናዊ ትርክት አይደለም። እየከፋፈሉንና እያፈራሩን ያሉት ከአንድ ወገን ስለአንድ ወገን ተብለው የተፈጠሩ ትርክቶች ናቸው። ኢትዮጵያ ሁሉም የደከሙባት የብሄርብሄረሰብ ቤት ናት ካልን ለእርቅና ለተግባቦት የሚያስፈልገን ብሄር ብሄረሰባዊ ትርክ ነው ማለት ነው።

ሰፊና ብዙ በሆነች ሀገር ውስጥ ገንቢ ትርክቶች ፋይዳቸው ላቅ ያለ ነው። ሀገር ከመገንባትና ተያይዞ የመጣውን የአብሮነት ገመድ ከማጥበቅ አኳያ የማይናቅ ሚና አላቸው። ልዩነታችን ውበታችን፣ ውበታችን አንድነታችን ብለን ስንነሳ ማዕከል ያደረግንው ሰፊውን ሕዝብና ሰፊዋን ሀገር ነው። ከየትም ያመጣነው ሳይሆን ካለን፣ ከነበረን ልዩነትና አንድነት፣ አስተሳሰብና ሥርዓት የቀዳነው ነው።

ብሄራዊ ትርክት ጎጂና ተጎጂ የሌለበት ሀገር የሚያጸና፣ ሕዝብ የሚያፋቅር አለፍ ሲልም በልዩነት ውስጥ ያለውን ጸጋና በረከታችንን መለስ ብለን እንድናይ እድል የሚሰጥ አጋጣሚ ነው። ከብዙሀነት ውስጥ ባልወጡ ግለኛ ትርክቶች ብዙ ነገሮቻችንን አጥተናል። ከክብር ያወረዱን አብዛኞቹ ድጦቻችን ማን እንዳቦካው በማናውቀው የጭቃ ውስጥ እሾህ ነው።

የብሄር ብሄረሰብ በዓል የመላው ኢትዮጵያውያን በዓል ነው። የእኔ የአንተ የሌለበት የሁላችን የጋራ ትርክት። በአንድ ቦታ ስለአንዲት ሀገር በፍቅር የተሰባሰብንበት የህብረት መዐድ ነው። መልካም በዓል።

በማርያም

አዲስ ዘመን   ኅዳር 29  ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You