የሀገራችን ትንሳኤ የእኛ ትንሳኤ ነው

ሀገራችን ኢትዮጵያ መልከ ብዙ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እናት ናት። ብዙ ልጆችን፣ ብዙ መልኮችን፣ ብዙ ወግና ልማዶችን፣ ብዙ ሥርዓትና ባሕሎችን ታቅፋ የያዘች ናት። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው ቁርጥ እሷን መሳይ እልፍ መልከኛ ልጆችን ታቅፋለች። ይሄ የእናት ጉያ..ይሄ የእምዬ እቅፍ ልዩነት የለውም። በተለያዩ ብሔሮች፣ በተለያዩ ቋንቋዎች፣ በተለያዩ ባሕሎችና ሥርዓቶች የቆነጀ የእናት ዓለም ክንድ ነው። በተለያዩ መልኮች፣ በተለያዩ ቀለሞች፣ በተለያዩ ዘዬዎች የበረታ የእናት ዓለም ጉያ ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ልጆቿን ለመታቀፍ፣ ልጆቿን ለመሰብሰብ ታክታ አታውቅም። ቢዘረጋ ከዚህ እስከዛ የሚደርስ የርህራሄና የደግነት፣ የታሪክና የሥልጣኔ ክንድ አላት። እኛ እንዋደድ፣ ልዩነታችንን ለውበት፤ ውበታችንን ለአንድነት እንጠቀመው እንጂ የኢትዮጵያ መዳፍ ሰፊ ነው። እኛ ፍቅርን እንወቅ፣ በምክክርና በንግግር ችግሮቻችንን እንፍታ እንጂ፤ ጉያዋ ለብዙዎች የሚበቃ ነው። እኛ በአንድ ሀሳብ፣ በአንድ ልብ እንቁም እንጂ ቤቷ..ሳሎኗ ሙሉ ነው።

ለየትኛውም ሀገርና ሕዝብ ብዙኃነት በረከት እንጂ መርገምት የለውም። አሁናዊ የልዩነት ትርክቶቻችን ብዙኃነት የፈጠራቸው ሳይሆኑ ጥቂቶች ለራሳቸው ፍላጎት የፈጠሩዋቸው ናቸው። ቁጭ ብሎ ለመነጋገር ፈቃደኛ ባልሆኑ አካላት ያመጣብን ጣጣ ነው። የትኛውም ቀዳዳ በምክክር የሚደፈን ነው። የትኛውም አባጣና ጎርባጣ በመተሳሰብ የሚቀና ነው።

ተስፋ የአንድነት ቀለም ነው። የኢትዮጵያ ተስፋ የእኛ አንድነት ነው። የሀገራችን ቀና ማለት የእኛ ወንድማማችነት ነው። ያለን ነገር ከኢትዮጵያዊነታችን አይበልጥም። ለልጆቻችን ልናወርሳቸው የምንችለው ትልቁ የሰውነት ውርስ በብዙኃነት ውስጥ አብሮነትን የማስቀጠል ጥበብን ነው። ፍቅርን አግነን፣ አብሮነትን አስበልጠን እንደ አብረሃምና ሎጥ እኛ ወንድማማቾች ነን ልንባባል ይገባል። በዚህ ሀሳብ እና እውነት ውስጥ ነው ዋጋና ክብር የሚኖረን።

ሰው በሀገር ሲጠራና ሀገር በሰው ስትጠራ አንድ አይነት አይደለም። ሰው በሀገር ሲጠራ እዛ ጋ ሙሉ መሆን ይጀምራል። ሰው ስሙን፣ እምነቱን፣ ክብሩን፣ ማንነቱን ሀገሩ ሲያደርግ ሥልጣኔና ዘመናዊነት ዋጅተውታል እንላለን። ሰው በሀገሩ ሲጠራ የዜግነት ግዴታውን እየተወጣ ነው። ሀገር በሰው ስትጠራ ግን ብዙ ጊዜ ልክ አይመጣም። ብሔራችንን ታከን፣ የብቻ ታሪካችንን ተንተርሰን ሀገራችንን በእኛ ስንጠራ እዛጋ ስህተት እየሠራን ነው። በመሠረቱ ሰው በሀገር እንጂ ሀገር በሰው ተጠርታ አታውቅም። እናም መጠሪያ ስማችንን ከእኔነት ወደእኛነት፣ ወደብዙኃነት በመቀየር የኅብረብሔራዊነት እድላችንን ወደ ድል መቀየር እንችላለን።

ብዙ መልክ አንድ ስም የኢትዮጵዊነት የታሪክ መነሻ ነው። ብዙ ነን..ሰማኒያ እና ከዛ በላይ። የተትረፈረፍን..ይሄ ሁሉ የሀሳብና የኑባሬ ውሕደት በሀገርና ሕዝብ ላይ የሚንጸባረቅ ነው። መልካም ሀሳብ መልካም ታሪክ መፍጠሪያ ነው። ለፍቅር እንጂ ለጠብ መቧደን አያምርብንም። በፍቅር ስም ለአንድነት በአንድነት ተቧድነን የጋራ ታሪክ ጽፈን ፊተኞች ተብለናል። ያን ደማቅ እድልና ድል ለመመለስ ለጥላቻ የተዘረጉ እጆቻችን፣ ለጠብ ያሞጠሞጡ አፎቻችን ፍቅርን መስበክ አለባቸው።

አንዳንዶቻችን በሀገራችን የምንጠራ ነን አንዳንዶቻችን ደግሞ ሀገራችንን በማንነታችን የምንጠራ ነን። የሚልቀው እውነት ሰው በሀገሩ ሲጠራ የሚለው እውነት ነው። ከሀገር የቀደመ ነገር ሁሉ የውድቀት ምንጭ ነው። ከሕዝብ የበረታ ነገር ሁሉ መድረሻው ምንምነት ነው። ሀገር የሚያቆመው፣ አንድነት የሚፈጥረው ከሀገር ያልቀደመው ነገር ነው። እርሱ የሥልጣኔ መጀመሪያ ነው። ከሀገር የቀደመ ነገር እንዳይኖረን እንጠንቀቅ ።

ሰው ራሱንም ሆነ ብሔሩን፣ ታሪኩንም ሆነ ማንነቱን ከሀገሩ ሲያስቀድም ያኔ ባለውለታነቱ ያበቃል። ኢትዮጵያ ሀገራችን እስከዛሬ ድረስ በሥልጣኔና በታሪክ፣ በባሕልና በወንድማማችነት ከፍ ብላ የታየችው ሀገራቸውን ባስቀደሙ ብሔር ብሔረሰቦች ነው። ዛሬም ካሉብን ወደፊትም ከሚኖሩብን ሀገራዊ ትርክቶችና ተረት ወለድ ጥላቻዎች እንላቀቅ ዘንድ ሀገሩን ያስቀደመ፣ ወገኑን ከፊት ያደረገ ፖለቲካና ፖለቲከኛ ያስፈልገናል።

ብዙ ነን..ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የምንተርፍ። ብዙ ነን ጥበብን፣ ታሪክን፣ ጀግንነትን አጣምረን የያዝን። ልዩነታችን ውስጥ ብዙ የአንድነት መንፈስ፣ ብዙ የኅብረብሔራዊነት ጌጦች አሉ። ልዩነታችን ውስጥ ሀገር የሚያሻግር፣ ትውልድ የሚቀርጽ የታሪክና የሥርዓት ጀብደኝነት አለ። ብዙኃነታችን ውስጥ እኛነትን የሚያወሳ፣ ግለኝነትን የሚኮንን የሥርዓትና የጨዋነት ልማድ አለ። እኛ ዝም ብለን ሀገርና ሕዝብ አልሆንም። ሌሎችን ባቀናና ባነቃ ባሕልና ሥርዓት እሴትና ልማድ ውስጥ ሀገርና ሕዝብ የሆንን ነን።

በልዩነታችን ብናጌጥ፣ በብዙኃነታችን ብንቆም ዓለምን የሚያስፈራ የኃይልና የለውጥ ባለቤቶች እንሆን ነበር። በወንድማማችነት ብንሰለፍ እንደጥንቱ ዘመን ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ብርሃን መሆን የምንችል ነበርን። ለመበርታት በፍቅርና በአብሮነት ለመቆም ያሉንን ግን ደግሞ መለስ ብለን ያላየናቸውንና ዋጋ ያልሰጠናቸውን ፀጋዎቻችንን መጠቀም አለብን። በእኔነት ያደበዘዝናቸውን የወንድማማችነት እሴቶቻችንን የመጪው ዘመን የትንሳኤ ማብሰሪያ እንዲሆኑን እንግለጣቸው።

ሀገር መቼም አንድ ዓይነት ሆና አታውቅም.. የዓለም ታሪክ በመለያየት ውስጥ፣ በመደባለቅ ውስጥ የቆመ ነው። አንድ ዓይነት ብሔር፣ አንድ ዓይነት ባሕል፣ አንድ ዓይነት ቋንቋ፣ አንድ ዓይነት ታሪክና ሥርዓት ያላት ሀገር የለችም። ሁሉም የዓለም ሀገራት በድብልቅልቅ ብሔርና ቋንቋ፣ በልዩ ልዩ ባሕልና ወግ የተሰባጠረ ነው። ውበት ማለት በልዩ ልዩ ባሕሎች መድመቅ ነው። ሥልጣኔ ማለት የብዙኃነትን ሀሳብና ፍላጎት በሠለጠነ መንገድ ማራመድ ነው። ዘመናዊነት ማለት በዚህ ልዩ ልዩ ባሕልና ወግ መድመቅና መዋብ ነው።

ልዩነት ጌጥ ነው። ብዙ ሀገራት አሁናዊ ሥልጣኔያቸውን፣ አሁናዊ ልዕለ ኃያልነታቸውን ያገኙት ኅብረብሔራዊነታቸውን ተጠቅመው ነው። መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሀገራት በኅብረ ብሔራዊነት ስብጥር ውስጥ የቆሙ ናቸው። ተፈጥሮ ብዙኃነትን ካደለቻቸው ጥቂት ሀገራት መካከል ደግሞ በዋናነት እኛ ኢትዮጵያውያን እንጠቀሳለን። ልዩነት ውበት ነው..በልዩ ልዩ ባሕልና ወግ፣ ሥርዓትና ታሪክ መከበብ መታደል ነው። ይሄን ተፈጥሮ ያደለንን የብዙኃነት ልዩነታችንን በአግባቡ በመጠቀም ሀገራችንን ማሻገር ይኖርብናል።

ለነውጥ ሳይሆን ለለውጥ፣ ለመገፋፋት ሳይሆን ለመተቃቀፍ ልንጠቀመው ግድ ይለናል። ለመለያየት ሳይሆን ለአንድነት፣ ለመራራቅ ሳይሆን ለመቀራረብ ልናውለው ይገባል። ልዩነት ከተጠቀምንበት ለውጥ ካልተጠቀምንበት ነውጥ ነው። ከተጠቀምንበት ወደሥልጣኔና ወደ ከፍታ ልንወጣጣበት እንችላለን። ካልተጠቀምንበት ደግሞ በልዩነታችን ቀዳዳ ውስጥ አፍራሽ አስተሳሰቦችን እያስገባን ልንበላላበት እንችላለን። መቼም የትም ልዩነት ጉድለት ሆኖ አያውቅም። ልዩነት ጌጥ ነው..ሀገር የምታምርበት፣ ትውልድ የሚቆነጅበት፣ ታሪክ የሚያብብበት ስፍራ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ሲበረበር አንድ ዓይነት ግን ደግሞ ልዩ ውበትና ደም ግባት ይገኝበታል። ውበታችን በልዩነታችን ውስጥ ያካበትነው ባሕል፣ ልማድ፣ ወግና ሥርዓታችን ነው። ውበታችን በልዩነታችን ውስጥ ያገኘነው ፍቅርና መከባበር፣ መዋደድና መቻቻላችን ነው። ውበታችን በልዩነታችን ውስጥ የተወራረስነው የአብሮነት መንፈስ ነው። ውበታችን በብዙኃነታችን ውስጥ ማግረን ያቆምነው፣ አቁመን ያጸናነው ኢትዮጵያ የሚለው የጋራ ስማችን ነው። አንድ ዓይነት ውበት የለውም። ውበት ያለው በልዩነት ውስጥ ነው።

ዛሬ ላይ በዚህ ልክ ባለታሪክ የሆንነው በልዩ ልዩ ትውፊታችን ነው። ኢትዮጵያ የተሠራችው ከእያንዳንዳችን ባሕልና ወግ፣ ሥርዓትና ታሪክ በተዋጣ ሀሳብ፣ በተዋጣ ጽናት፣ በተዋጣ እውቀት፣ በተዋጣ ገንዘብ ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን በዚህ ልክ የቆነጀችው በእያንዳንዳችን ብዙኃነት ተከባ ነው። መብዛታችን..የተለያየ መሆናችን የተለየችውን ሀገራችንን ፈጥሯታል። እናም ልዩነታችን ውበታችን ነው ።

ኢትዮጵያን ካስጌጡ ጌጦች ውስጥ ሌላም ሊጠቀስ የሚችል እውነት አለ እርሱም አንድነታችን ነው። ከብዙኃነታችን ውስጥ በተወለደ አንድነታችን ከትላንት እስከዛሬ ብዙ ድሎች በጋራ አጣጥመናል። በልዩነታችን ውስጥ በተዋጡ የአብሮነት መንፈሶች ብዙ ተግዳሮቶችን በጋራ አልፈናል። አሁንም በልዩነታችን ውስጥ ያለውን አንድነታችንን ለሀገር ክብር የምናውልበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ነን። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከፊቷ ብዙ ተስፋዎች አሏት። እነኚህ ተስፋዎቿ እውን እንዲሆኑ የእኛ በአንድነት መቆም ዋጋ አለው።

የሀገራችን ትንሳኤ እንዲመጣ፣ ጨለማዋ እንዲነጋ ሰላም ያለበት፣ ምክክር ያለበት፣ ፍቅር ያለበት፣ አንድነት ያለበት፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለበት አብሮነት ያስፈልገናል። ሀገር በዜጎቿ የምትሠራ ናት። እኛ ደግሞ ሀገር ለመሥራት የሚሆን ብዙ ጥበብ ብዙ ማስተዋል ያለን ሕዝቦች ነን። እጆቻችን ከእኛ ርቀው ለመላው ጥቁር ሕዝብ ባለውለታ ናቸው። በአንድነት ከቆምን፣ ልዩነቶቻችንን አቻችለን መጓዝ ከቻልን የተሻለች ኢትዮጵያ ለመሥራት በቂዎች ነን።

በብሔር የተለያየን ነን፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በባሕል የተለያየን ነን። ይሄ ሁሉ ልዩነታችን ግን ኢትዮጵያ በሚል የጋራ መጠሪያ ታስሯል። ያማርነው ስለተለያየን ነው..ኢትዮጵያ በሚል የጋራ ስም የታሰርነው ልዩዎች ስለሆንን ነው። በተፈጥሮ እውነት በብዙ ልዩነት ውስጥ አንድ ነን። በብዙ አንድነት ውስጥ ልዩ ነን።

በድብልቅ ውሕደት ኢትዮጵያዊ ተብለናል። ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ፍልጥ የታሰረባት ገመድ ናት። ልጡ በአንድ ላይ አስሮናል። ልጡ ቢፈታ ፍልጡ ይበታተናል። ልጡ ቢላላ ፍልጡ ይመሳቀላል። በኢትዮጵያዊነት ስምና ገመድ ነው እንዳንበታተን ሆነን የታሰርነው። ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ነው..በልዩነት ውስጥ ጸንቶ የቆመ፣ በልዩነት ውስጥ ጠብቆ የተገመደ..ማንም የማያላላው ሥጋና ደም። የታሰርንበት የአንድነት ልጥ፣ የታሰርንበት የወንድማማችነት ገመድ እንዳይፈታ ልዩነታችንን ማክበር መቻል ይኖርብናል። የታሰርንበት የኢትዮጵያዊነት ገመድ፣ የተያዝንበት የመቻቻል ልጥ እንዳይላላ ልዩነታችንን እንደውበት አምነን መቀበል ይኖርብናል።

ብዙኃነት ለሀገር ያለው ሁለንተናዊ ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በብዙ ነገር የተባረክን ሕዝቦች ነን። በእያንዳንዱ ብሔር ውስጥ ለሀገር የሚሆን ብዙ ነገር አለ። ያ ብዙ ነገር የሀገርን ቀዳዳ፣ የማኅበረሰቡን ችግር የመፍታት አቅም አለው። ችግሮቻችን እንዲበልጡን እድል ካልሰጠናቸው በስተቀር አይበልጡንም። በዚህም በዛም የምንሰማቸው ብሔር ተኮር እኩይ አስተሳሰቦች ሀገራዊ ችግር ከመፍጠር ባለፈ ጥቅም ስለሌላቸው ብዙኃነታችንን ለለውጥ መጠቀም ይኖርብናል። ችግር ፈቺ አስተሳሰብ ይዘን የለውጥና የመፍትሔ አካል መሆን እንጂ በልዩነታችን ውስጥ ሰርገን እየገባን በምንፈጥራቸው ጥቃቅን የልዩነት በሽታዎች ወደ ፊት መሄድ አንችልም።

ተስፋዎቻችን በመዳፋችን ውስጥ ነው ያሉት። ከፍታዎቻችን በእያንዳንዳችን ጫንቃ ላይ የተቀመጡ ናቸው። ሕዝቦቿ በጋራ ያልቆሙባት ሀገር ታሪክ አይኖራትም። ታሪክ የሚፈጠረው ከአንድነት አብራክ ውስጥ ነው። የዓድዋ ታሪክ የመላው ኢትዮጵያዊ ታሪክ ነው። የዓድዋ ታሪክ የብሔር ብሔረሰብ ታሪክ ነው። የህዳሴ ግድባችን ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት ያቆሙት የጋራ ታሪካቸው ነው።

ልዩነታችን እንድንደምቅበት የተሰጠን እንጂ እንድንደበዝዝ የተሰጠን እንዳይደለ በማመን ለአንድ ዓላማ በአንድ እንቁም። ባለን አቅም ሁሉ በአንድ አቅፋ ለያዘችን ለድሀዋ ሀገራችን የምንለፋበት፣ የምንደክምበት ጊዜ ላይ ነን። የሚጠቅመን ፍቅርና አብሮነት ብቻ ነው።

ሀገራችንን የጋራ መጠሪያችን አድርገን ለትንሳኤዋ ብርሃን መሆን ይጠበቅብናል። የሀገራችን ትንሳኤ የእኛ ትንሳኤ ነው..ትንሳኤዋ እውን የሚሆነው ደግሞ በእኛ አብሮነት ነው። አብሮነታችን ኃይላችን ነው። ኃይላችን ደግሞ ከድህነት መውጫችን ነው። በልዩነታችን ተውበን፣ በብዙኃነታችን ደምቀን የሀገራችንን ትንሳኤ እውን እናድርግ ።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You