እንመካከር

የምክክርን ምንነት የእንመካከርን ትርጉም የአለቃ ደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት መጽሐፍ ጠቅሼ አልበይንም። ምስጢሩ ለማንም ግልጽ ነውና! ምክክር ሃሳብ ማዋጣት ነው። እንመካከር! ይህን ይቅር እንባባል፣ ይህን እንተወው፣ ይህ ጥፋት ነው፣ ይህ ደግሞ እስካሁንም ያቆየን መልካም ጎናችን ነው። እየተባባልን የሚቀጥለውን አጽንተን የሚያስቸግረውን በይቅርታ አጥፍተን የምንሻገርበት ያለ የነበረ ብሂል ነው።

ምክክር ስህተት ሲታረምበት፣ ባለጌ ሲቀጣበት ደግነት እና መልካም ሥራ ሲወደስበት የኖረ ብሂል መሆኑን ምሳሌያዊ ንግግሮቻችን ያስረዱናል። ምክክርን በተመለከተ በምሳሌያዊ ንግግሮቻችን ምን ተባለ አሁን ካለንበትስ ወቅት ጋር እንዴት ተሳሰሩ የሚለውን እንደሚከተለው በወፍ በረር እንቃኘው።

ለሹመት ካልመከሩለት ለጥርስ ካልከደኑለት! (ለሹመት ካልመከሩለት ለጥርስ ካልነከሩለት!)

ሥልጣንህ እንዲጠና ወንበርህ እንዳይነቃነቅ ምክክር መልካም መሆኑን ያስረዳናል። ወደታች ባለሙያዎችንን እና ወጣቶችን ወደ ላይ እድሜ ጠገብ አዛውንቶችን እና የሃይማኖት አባቶችን ማማከር ይገባል። በትይዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማኅበራትን በሌሎች መንገዶች የተቧደኑ ማኅበረሰቦችን እንዲሁም ግለሰቦችን ወደ ጎን አማካሪዎችን እና የየዘርፉ ባለሙያዎችን ማማከር ወንበርን ያረጋል።

ሥልጣንን በጉልበት ሳይሆን በፍቅር ያስቀጥላል። ለዚህም ነው ያልተመካከሩበት ሹመት ካልከደኑለት ወይም ካልነከሩለት ጥርስ እኩል የሆነው። ያልተነከረ ባቄላ ብትጎረድምበት ጥርስህ በታምር ከመነቀል ቢተርፍ መነቃነቁ እና አስቸጋሪ ሕመም ማስከተሉ አይቀርም። በዚህኛው ብናየውም ጥርስን በከንፈር ካልከለሉት በአቧራው፣ በነፋሱ ከመጎዳቱም በላይ ልቅሶ ቤት ላይ አሊያም አልሆነ ቦታ ላይ ፈገግ ብሎ ዱላ ያስመዝዝብሃል።

ገላጋይ ከተገኘ ተነቃንቆ ይተርፋል። ገላጋይም ከሌለ ጥርስህን በእጅህ ይዘህ መመለስ የመጨረሻ አማራጭህ ነው። ተመካክረንስ ቢሆን ሹመትም ደህና ጥርስም መልካም ይሆኑ ነበር። እንደ ሀገር አብሮ ፈገግ በሚባልበት አብረን ስቀን በምናዝንበት አብረን ተክዘን የጋራችን ደስታ የጋራችን ሕመም የሆነች ሀገርን መመሥረት ያስችላል።

ባለጌ የመከሩት ዕለት ቁንጫ የጠረጉት ዕለት ይብሰዋል!

ይህን ምሳሌያዊ ንግግር በማወቁ መሰለኝ በሀገራችን የተቋቋመው እና በሥራ ላይ ያለው የምክክር ኮሚሽን የምክክር ተሳታፊዎች በጥንቃቄ የመምረጡን ነገር ረጅም ሰዓት ሠጥቶ እየሠራው ያለ! ባለጌማ ባለጌ ነው! ለራሱ ካለመስማቱም በላይ ሲሳተፍ ነገርን ያለውሉ በማዞር ልክ ዝንብ እንደገባበት እርጎ አድርጎት ነገሩን እንዳይበላ እንዳይዘራ አድርጎት ይቀመጣል። ሁሉንም ማማከር ቦታም ጊዜም በመፈለጉ የተወሰኑ በእውነት እና በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ያላቸው አፋቸው ላይ ጨው የማይሟሟ ሐቀኛ ወኪሎችን ለምክክር ማግኘት ተገቢ ነው። ይህ ካልሆነማ ”ባለጌ ያለበት ሸንጎ ዝንብ የገባበት እርጎ!የሚባለውም ይሆንብናል።

በተደጋጋሚ ስለውይይት ስለ ምክክር ሲነሳ እኔም ምሳሌያዊ ንግግሮችን ጠቅሼ ሳወራ ”ምክር እና ቡጢ ለሰጭው ቀላል ነው! ተውን እባካችሁ ብለው ሊሞግቱን ያስባሉ። ምክክር ግን ሰጪ እና ተቀባይ የለውም። የአንተም፣ የእኔም፣ የአንቺም፣ የእሱም፣ የእሷም… ሃሳብ ይፈልጋል። ሃሳብ የሚጣለው ወይም ተቀባይነት የማይኖረው የእኔ ስለሆነ ያንቺ ወይም ያንተ ስለሆነ አይደለም።

ሃሳቡ ከሌሎች ሃሳቦች የተሻለ ሳይሆን ሲቀር ብቻ ነው። በምክክር ላይ ሃሳብ እንጂ ተናጋሪ አይወዳደርም። በምክክር ላይ ሰጪ ብቻ ወይም ተቀባይ ብቻ አይኖርም። ሰጪም ተቀባይም እንጂ የምንቀበል የጎደለንን ነው። የምንሰጥ ደግሞ ያለንን ይህ ደግሞ ምልዑነትን ያመጣል።

 ምከረው ምከረው እምቢ ካለው መከራ ይምከረው!

ሀገራችን ይህንን ምሳሌያዊ ንግግር በሥነቃሎቿ ውስጥ አስገብታ መጠቀም ከጀመረች ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን ከምክሩ በፊት መከራው ቀድሞናል። መከራው ሳይጠነክር አሁንም መሥራት ይጠበቅብናል። ተመካክረን ልናስቀራቸው የሚገቡ ችግሮች ጤና ነስተውናል። ድሃ አድርገውናል። ሕይወት አስገብረውናል። ምክርን እምቢ ባንልም ባለመጀመራችን መከራው አበሳችንን አሳይቶናል።

አሁንም ከእዚህ ሳይከፋ ከመከራው ሳይሆን ከክፉ መከራችን ሳንማር(መከራውንማ ጀምረነዋል) ወደ ሸንጎው ጥላ እንሰባሰብ። እንመካከር መከራውን በጥቂቱ አየነው። ጠንከር ብሎ ቢመጣ ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ መረዳቱ ቀላል ነው። ይህን ከመረዳት በላይ ደግሞ መመካከር ቀላል ነው። ከመከራው ወደ ምክክሩ የምናደርገው ጉዞ ደግሞ ያየነው የተበደልንበት ስለሆነ ውጤቱ ጥሩ እንደሚሆን አያጠራጥርም።

በመሆኑም በፍጥነት ወደ ምክክር መሄድ ለወደፊቱ ቀና እና ዋናው መንገድ ነው። አባባሉም በምክክር ያልታረመ ከችግር ከሰቆቃው እንደሚማር ይነግረናል። መቸም መከራን የሚመርጥ አይኖርም።

ለብልህ አይመክሩ ለአንበሳ አይመትሩም!

የአንድ ሰው አዋቂነት በአንድ ጉዳይ ብቻ ነው። ቢበዛ በሁለት፣ በሦስት ጉዳይ ተሰጥዖም እውቀትም ሊኖረው ይችላል። ሀገር ደግሞ የሁለት ሦስት ጉዳይ ብቻ ውሕድ አይደለችም። ምክክራችን ለሀገራችን ሉዓላዊነት ለሀገራችን ሥልጣኔ እስከሆነ ድረስ መምከር መመካከር ብልሁን ባይጠቅመው ምን ሊጎዳው!? የሕክምና ባለሙያዎች ስለመድኃኒት አጠቃቀም ሲያስረዱ “ተጓዳኝ ችግር የሌለው መድኃኒት የለም። ካለም ውሃ ብቻ ነው ይላሉ። ”

ቢዘነጉት እንጂ ምክርም ምንም ተጓዳኝ ችግር የለውም። እንዲያውም ምክክር አንዱ የሥነልቦና ሕክምና ዓይነት አይደል። ምክክር ለጤናም አስፈላጊው መድኃኒት መሆኑ ነው። ስለዚህ የፖለቲካ ጤናችን፣ የማኅበራዊ ሕይወት ጤናችን እና የኢኮኖሚ ጤናችን ለመመለስ አሊያም ለማሻሻል ምክክር ዓይነተኛው መድኃኒት ነው።

አዎ! ብዙ ብልሆች ብዙ አዋቂዎች ምክርም ዝክርም የማይፈልጉ ይኖራሉ። እንምከራችሁ ብቻ አይደለም ሃሳባችን እንመካከር ነው። ስለዚህ ምክራችንን ባትፈልጉ ምክራችሁ ያስፈልገናል። በአንድ ጥላ እንረፍ፣ ሃሳብ እናዋጣ፣ በሃሳብ ከተቀራረብን በጉልበት የሚያግዘን ብዙ ነው። እውነትም የወጣቶች ሀገር ሆና ኃይል እና ችኩልነት ያጠቃናል። ስንቸኩል ወደ ኋላ እንዳንመለስ እንጠንቀቅ። ለጥንቃቄው መነጋገር ሃሳብ ማንሸራሸር ተገቢ ነው።

በምክክር ጊዜ ጥሩ አለመሆኑንም መግለጽ ያስፈልጋል። እንደዚህ አይሠራም። አሠራሩን ግን አላውቅም ማለትም ጥሩ ነው። መቸም የሚጣፍጠንን እና የማይጣፍጠንን ምግብ ለመለየት የምግብ ባለሙያ መሆን አይጠበቅብንም። ስለዚህ አለመጣፈጡን ከተናገርን ትክክል ነን ብለው እንዳይቀጥሉ እና ሌላ ትክክለኛ ባለሙያ እንዲያየው ያደርጋሉ። ስለዚህ የሚፈለገው የምክክር ሃሳብ አሠራሩን ማሳየት ብቻ አይደለም። እንደዚያ አለመሠራቱንም መንገር ያስፈልጋል። ሌላውንም ሌላኛው ተመካካሪ ያመጣዋል።

ችግሮቻችን በጥበብ ከያዝናቸው በብርሃን ፍጥነት የሚያልፉ ናቸው። አብረውን እንዲዘልቁ ቂም እንዲያስቋጥሩ የምናደርጋቸው በእኛው የአያያዝ ችግር ነው። ሲጀመሩ ምልክት ሲያሳዩ ብንወያይባቸው ቋሚ ቁርሾ ሳይወልዱ ባለፉ ነበር። ለእዚህም ነው። ”ተማክረው የፈሱት ፈስ አይሸትም! የሚሉት አበው! ችግሩ በተወሰነ ደቂቃ ነፋስ የሚጠፋ ነው። እሰከዚያው የተወሰነ ዞር ማለትም ይቻላል። ይህም ባይሆን ግን ምክክር ሲኖር የፈስን ግማት ባያስቀርም አፍንጫችንን እስክንይዝ ጊዜ እና መረጃ ስለሚሰጠን ችግሩን ያስቀርልናል። እንመካከር

እንዳለው ሙሉዓለም

አዲስ ዘመን   ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You