ወጣት ናት። በ20ዎቹ እድሜ መጀመሪያ አካባቢ የምትገኝ። ወጣትነቷ ይሁን ሌላ ዓይነግቡ የምትባል ዓይነት ቆንጆ ልጅ ናት። ጸጉሯ የሀር ነዶ የሚባል ዓይነት ነው። በፍልቅልቅ ፊቷ ላይ ከእድሜዋ በላይ ብስል ያለች ጨዋታዋ የማይሰለች ዓይነት መሆኗ ደግሞ ይበልጥ ትኩረቴን ስቦታል። ሰላማዊት ተስፋዬ ትባላለች። ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው ውስጥ ኖሮ ከተወለዱ ልጆች መካከል አንዷ ናት።
በአጋጣሚ ከሰዎች ጋር ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ ሥርጭት መብዛት፤ ይበልጥ አፍላ ወጣቶችን እያጠቃ መሆኑንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በምንጨዋወትበት ወቅት ነበር የተዋወቅነው። ስሟን በሌላ እንድቀይርና ፎቶዋን እንዳልጠቀም ካስጠነቀቀችኝ በኋላ ነበር ለዛሬ የሴቶች ዓምድ እንግዳ ለመሆን የተስማማችው። ከሰላም ጋር የነበረንን አፍ አያስከድኔ ወግ በዚህ መልኩ ይዘንላችሁ ቀርበናል መልካም ንባብ።
እንደምታይኝ ወጣት ነኝ። ቆንጆም ነኝ። አይደለሁም እንዴ ? አለች በፈገግታ። እንደ ሌሎቹ ወጣቶች ግን እንደ ልቤ ለመሆን ያልታደልኩ ስወለድ ጀምሮ ኤች አይ ቪ በደሜ ውስጥ ይዤ የተወለድኩ ልጅ ነኝ። ኤች አይ ቪ ኤድስ በደሜ ውስጥ መኖሩ በየቀኑ መድኃኒት እንድወስድ ከማድረጉ ያለፈ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ አሳድሮብኛል ብዬ አላምንም። ያለፈኩትን በሙሉ አልፌ ዛሬን የሰጠኝን አምላክ እያመሰገንኩ ባለሁበት መትጋትን ሥራዬም ምርጫዬም አድርጌዋለሁ።
አባቴ ኮንትሮባንድ ንግድን የሚቆጣጠር መውጫ መግቢያ ኬላዎች ላይ የሚውልና የሚያድር የፖሊስ አባል እንደነበረ አሁን አብሬያት የምኖረው አክስቴ ነግራኛለች። አንድ ወርም ሁለት ወርም ቆይቶ ነው የሚመጣው። አባቴ ከእናቴ ጋር የነበራቸው ፍቅር እጅግ በጣም የሚያስቀና እንደነበረም ጎረቤቶቻችን ነግረውኛል። እና አሁን አብራን የምትኖረው አክስቴ እናቴ ብቻዋን እንዳትሆን አምጥታ ታስተምራት የነበረች እህቷ ናት።
እናትና አባቴ በጣም የሚተማመኑና የሚከባበሩ ባለትዳሮች ስለነበሩ በሽታው እስኪጎዳቸው ድረስ ወደ ሕክምና አልሄዱም ነበር። እናቴም ከሕክምና ክትትል በላይ ፀበልን የምታዘወትር ሴት ነበረች። እርጉዝ ሆና እንኳን ለክትትል ስትሄድ የኤች አይ ቪ ምርመራ አለማድረጓን ሰምቻለሁ።
እንደዛ በፍቅርና በመከባበር የሚኖሩት እናትና አባቴ አንዴ መንፈስ ነው፤ አንዴ የሰው እጅ ነው በማለት ፈለቀ የተባለ ፀበል በሙሉ አንድም አይቀራቸውም ነበር። ቀኑ እየረዘመ በሽታ የመከላከል አቅማቸው እየደከመ ሲሄድ እንደ ጉንፋን አድርጎ የጀመራቸው ሕመም በጣም ሲባባስ ሆስፒታል ቢሄዱም በቂ ሕክምና ሳይደረግ በሽታቸው ከመታወቁ በወራት እድሜ ውስጥ ተከታትለው አለፉ።
ያኔ እኔ ሶስት ዓመቴ ነበርና አብራን ትኖር ለነበረችው የእናቴ እህት ሐኪሞቹ እንድታስመረምረኝ ነግረዋት ወላጆቼም በኤች አይ ቪ መሞታቸውን እኔም በደሜ ውስጥ መኖሩን ያረዷታል። የኮሌጅ ተማሪ የነበረችው አክስቴ በሽታው እንዳለብኝ ስትሰማ ወዲያው የመሞት መስሏት በጣም አዝና እንደነበረ ነግራኛለች።
በወቅቱም የኤች አይ ቪ ቫይረስ እንዴት እንደሚተላለፍ እና ከኤች አይ ቪ ጋር መኖር ምን እንደሚመስል እጅግ በጣም ብዙ የተሳሳቱ አመለካከቶች፤ ጭፍን ጥላቻ እና መገለልን ስለነበር አክስቴ ስለህመሜ ሳትናገር ሐኪሞቹ የሚሏትን በማድረግ እስካለሁን ድረስ ልትንከባከበኝ ወሰነች።
በድብቅ ልትንከባከበኝ ብታስብም ስለበሽታው መተላለፊያ መንገዶች የምትሰማው ነገር እሷም በበሽታው እያዝ ይሆን የሚል ስጋት ውስጥ ከቷት እንደነበረ ታስታውሳለች። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ለረዥም ጊዜ በኤች አይ ቪ በሚኖሩ ሰዎች ላይ መድልዎ ሲያስከትል መመልከቷን አክስቴ የነገረችኝ ሲሆን በወቅቱ ብዙ ሰዎች ኤች አይ ቪ በቆዳ ንክኪ ወይም በምራቅ እንደሚተላለፍ ያምኑ ነበር ብላኛለች።።
በንክኪ፣ በእንባ፣ በላብ፣ በምራቅ ወይም በሽንት፤ ተመሳሳይ አየር መተንፈስ ማቀፍ፣ መሳም ወይም እጅ መጨባበጥ የመመገቢያ ዕቃዎችን መጋራት የውሃ ፍሳሽ መጋራት የግል ዕቃዎችን መጋራት የስፖርት ማዘውተሪያ መሳሪያዎችን በጋራ መጠቀም የመጸዳጃ ወንበርን፣ የበርን እጀታ ወይም እጀታውን መንካት ቫይረሱን የማያስተላልፍ መሆኑንና በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ኤች አይ ቪ የሚተላለፈው እንደ ደም፣ የዘር ፍሬ፣ የሴት ብልት ፈሳሽ እና የጡት ወተት በመሳሰሉ የፈሳሽ ልውውጥ መሆኑን ዶክተሮች አስረግጠው ከነገሯት በኋላ ነው እንግዲህ እኔን እንደ ብቸኛ ልጇ ማሳደግ የጀመረችው።
ቀን ቀንን እየወለደ የሕክምና ክትትልን በቋሚነት መውሰድ ስጀመር ደህና እየሆንኩ ሄድኩ። አክስቴም የራሷን ሕይወት ትታ እኔን እንደ ልጇ ማሳደግና መንከባከብ ጀመረች። ወላጆቼ የራሳቸው ቤት ስለ ነበራቸው በኪራይ በምናገኘው ገቢ ዘና ብለን መኖር ጀመርን።
እኔም ለትምህርት ስደርስ ጥሩ የሚባል ትምህርት ቤት ገብቼ መማር ጀመርኩ። ከጓደኞቼ ጋር በደስታ የምጫወት ቢሆንም ከልጅነቴ ጀምሮ መድኃኒት መወሰዴ ግን በጣም ያስጠላኝ ነበር። በተለያዩ ጊዜያት ለክትትል ሆስፒታል ስሄድም ሌሎቹ ልጆች ሐኪም ቤት ብለው ያለመቅረታቸው ውስጤን ይበላው ነበር።
አክስቴ ከሕክምናው ጎን ለጎን በመንፈሳዊ ሕይወት እንድጠነክር አድርጋ ስላሳደገችኝ ሁልጊዜ ተስፋ መቁረጥን አላውቅም ነበር። ሰባተኛ ክፍል ስደርስ ግን ጓደኞቼ መድኃኒት የማይወስዱ መሆኑና እኔ ለምን እንደምወስድ ስጠይቅ የሚመልስለኝ ባለመኖሩ መድኃኒቱን ለመተው ወስንኩ። ያን ጊዜ በጣም የተጨነቀችው አክስቴና ክትትል የሚያደርጉልኝ ሐኪሞች አብረው በመሆን ኤች አይ ቪ በደሜ ውስጥ እንዳለና የግድ መውሰድ እንደሚኖርብኝ አስረዱኝ።
ለመጀመሪያ ጊዜ በደሜ ውስጥ ኤች አይ ቪ እንዳለ ካወኩ እለት ጀምሮ በጣም ነበር ያዘንኩት። በኔ እውቀት ልክ ኤች አይ ቪ የሚይዛቸው ሰዎች ከወንድ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ለምን እኔን? እያልኩ በጣም ነበር ያዘንኩት።
የኤች አይ ቪ መተላለፊያ መንገዶች ጥንቃቄ በጎደለው ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፤ ኤች አይ ቪ ካለባት እናት ወደ ፅንስ ወይም ልጅ እና በደም አማካኝነት ማለትም በኤች አይ ቪ የተያዘ ሰው ደም በመጠቀም ኤች አይ ቪ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ መቻሉን እንኳን ያወኩት ከብዙ ጊዜ በኋላ ነበር።
እኔ ኤች አይ ቪ የያዘኝ ከእናት ወደ ፅንስ ወይም ልጅ የሚተላለፈው መንገድ ነው። ይህም ኤች አይ ቪ ካለባት እናቴ በእርግዝናዋ ወቅት፣ በወሊድ ጊዜ እና ጡት በምታጠባበት ጊዜ ኤች ከአይ ቪው ወደ ፅንሱ/ልጁ ስለተላለፈ እንደሆነ ዶክተሮቹ አስረዱኝ።
በጣም ራሴን ጠልቼ ተስፋ ቆርጬ የነበረ ቢሆንም የነበረኝ ጠንካራ መንፈሳዊ መሠረት በፈጣሪ ላይ ያለኝ እምነት ያንን እንድሻገረው አድርጎኛል።
ራሴን ተቀብዬ ራሴን መንከባከብ ስጀምር ፍፁም ጤነኛ የመሆን ስሜት ይሰማኛል። እንደ ጓደኞቼ ለብሼ አምሬ መውጣት ያስደስተኛል። እስካለሁ ድረስ ጎበዝ ተማሪ ሆኜ ማለፍ ነው የምፈልገው ብዬ በትጋት እማራለሁ። በማትሪክ ውጤት ጥሩ ባመጣም አክስቴ ክፍለ ሀገር ሄጄ እንድማር ስላልፈቀደች እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ የግል ኮሌጅ ቢዝነስ አድምንስትሬሽን እየተማርኩ እገኛለሁ። በቀጣይ ዓመትም እጨርሳለሁ።
አሁን ላይ በእኔ እድሜ ያሉ ወጣቶች ምንም ዓይነት ግንዛቤ እንደሌላቸው መመልከቴ እጅጉን ያሳስበኛል። ከማሳሰብ አልፎ ግን እኔ እንደዚህ ነኝ ብዬ መውጣት አልፈልግም። ምክንያቱም ከልጅነታችን ጀምሮ አብሪያቸው ያደኩት ጓደኞቼ ይሄንን እንዲያውቁ ጭርሶውንም አልፈልግም።
አንዳንዴ ግን ስለ ፆታዊ ግንኙነት ስናወራ ሁሉም ወጣቶች የሚያሳስባቸው እርግዝና መፈጠር እንጂ ኤች አይ ቪ አለመሆኑ አዲሱ ትውልድ በከፋ ደረጃ ሊጠቃ የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር አውቄያለሁ። ኤች አይ ቪ ላይ ያለው ግንዛቤ በአፈላ ወጣቶች ዘንድ እጅግ በጣም አናሳ ነው።
አሁንም ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ የምፈለገው ጉዳይ ወጣቶች ስለ ኤች አይ ቪ በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ራሳቸውን መጠበቅ እንዲችሉ ማድረግ ላይ ነው። ወጣቶች ኮንዶም ከመግዛት ይልቅ ፖስት ፒልን መግዛት ላይ ቅድሚያ ሰጥተዋል። በአፍላ እድሜ ግብረ ሥጋ ግንኙነትን መጀመረን እንደ ጀብዱ የሚያዩትም አይጠፉም። ስለዚህ ትኩረት አፍላ ወጣቶች ላይ ተደርጎ ቢሰራ መልካም ይሆናል እላለሁ። በማለት ሰላማዊት ሀሳቧን አካፍላናለች።
ዘንድሮው የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን ሲከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡ ዕለቱ በተከበረበት ወቅትም የጤና ሚንስትር (ዶ/ር) ሊያ ታደሰ ባደረጉት ንግግር፤ የኤች አይ ቪ ሥርጭትን በመከላከል ረገድ መንግሥትና ማህበረሰቡ ባደረጉት ጥረት ከነበረበት ከፍተኛ የሥርጭት መጠን አሁን ወዳለበት 0.91 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
የዓለም ሀገራት በ2030 ኤች አይ ቪ ኤድስ ለማኅበረሰብ ሥጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት ሚንስትሯ፤ በኢትዮጵያ በ2025 ኤች አይ ቪ በደማቸው ከሚገኙ ሰዎች 95 በመቶ የሚሆኑት ተመርምረው እራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ፣ ኤች አይ ቪ በደማቸው ከሚገኘው ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት ሕክምና እንዲያገኙ እና ሕክምና ከጀመሩት 95 በመቶ የሚሆኑትን የቫይረሱ መጠን ዝቅ እንዲል የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ጄ ማሲንጋ በበኩላቸው የአሜሪካ ሕዝብ እና መንግሥት ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል እስከ አሁን ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ባደረጉት ድጋፍ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በቀጣይም የሚደረጉ ድጋፎች እና ህብረተሰቡ የሚያደርገው የመከላከል ሥራ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
በሌላ መረጃ ደግሞ ዌልስ ውስጥ በሙከራ ላይ የነበረውና በሰውነት ውስጥ የኤች ኤይ ቪ ቫይረስ ሥርጭትን የሚገታው መድኃኒት ውጤታማ መሆኑ በጥናት መረጋገጡም ሰሞንኛው አስደሳች ዜና ነው።
የመድኃኒቱ ውጤታማነት የተረጋገጠው በመላው እንግሊዝ ከተውጣጡ እና በጥናቱ በተካተቱ ከ24 ሺህ በላይ የመድኃኒቱ ተጠቃሚዎች ላይ ምርመራ ከተካሄደ በኋላ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ይፋ ሲያደርጉ እንደ ሰላማዊት ላሉ ብዙ ተስፋ ላላቸው ወጣቶች ሊደርስ መቻሉ አስደስቶኛል።
ለሁሉም ግን ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ ነውና ወጣቶቻችን ላይ የግንዛቤ ሥራዎችን የመሥራት ኃላፊነታችንን እንወጣ እላለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ኅዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም