
አዲስ አበባ፦ በመዲናዋ መግቢያ በሮች የሦስት የገበያ ማዕከላት ግንባታ በመጠናቀቁ በመዲናዋ በቅርቡ ከፍተኛ የምርት አቅርቦት እንደሚኖር የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው የተያዘው በጀት ዓመት ሩብ ዓመት አፈፃጸምን በሚመለከት ከወረዳ እና ክፍለ ከተማ ከሚገኙ አመራሮች ጋር ትናንት ተወያይቷል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድና ግብይት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፤ በበጀት አመቱ የኑሮ ውድነትን ለማቅለልና የምርት አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። በዚህም አምራቾችና ሸማቹ በቀጥታ ግብይት የሚፈፅሙባቸው ከታክስ ነፃ የሆኑ የቅዳሜና እሁድ የገበያ ቦታዎችን የማስፋት ሥራ ተሠርቷል።
በገበያው የኢንዱስትሪ ምርቶች በቀጥታ ከአርሶ አደሩና ከአምራች ኢንዱስትሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለከተማዋ ነዋሪዎች እንዲቀርብ ተደርጓል ያሉት አቶ መስፍን፤ በመዲናዋ መግቢያ በሮች የሦስት የገበያ ማዕከላት ግንባታ በመጠናቀቁ በቅርቡ በመዲናዋ ከፍተኛ የምርት አቅርቦት ይኖራል ብለዋል።
እንደ አቶ መስፍን ገለፃ፤ በአሁኑ ጊዜ በመዲናችን እየተስተዋለ ላለው የኑሮ ውድነት ዋነኛ ምክንያቱ የምርት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ነው። ይህንን ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ ስትራቴጂካዊ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል። ለአብነትም በከፍተኛ በጀት በመዲናዋ መግቢያ በሮች ግዙፍ የገበያ ማዕከላትን ገንብቷል።
የሰብል ምርቶች ገበያ ማዕከላቱ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በለሚ ኩራ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች የተገነቡ ሲሆን፣ እነዚህም እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ነው ያሉት አቶ መስፍን።
በእነዚህ የገበያ ማዕከላት የሚቀርቡ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ውጪ ካለው የምርቶች መሸጫ ዋጋ ከ 10 እስከ 15 በመቶ ቅናሽ ይኖራቸዋል ያሉት አቶ መስፍን፤ የእሁድ ገበያዎችም የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል። በገበያው የሚቀርቡ ምርቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት በተለያየ መልኩ የሚያቀርባቸውን መሠረታዊ ሸቀጦች ለህብረተሰቡ ለማድረስ እየተስተዋሉ ያሉ ብልሹ አሠራሮችን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ አገልግሎት መሰጠት መጀመሩንም ያብራሩት አቶ መስፍን፣ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የተለያዩ ሕግ የማስከበር ሥራዎች እየተሠሩ በመሆኑ ኅብረተሰቡ አስፈላ ጊውን ትብብር እንዲያደርግ እና በ 8588 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
በእለቱ ቢሮው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ ሙስና ቀንን አክብሯል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ኅዳር 21ቀን 2016 ዓ.ም