ታሪክ ካለፈው ለዛሬው ይተላለፋል፤ ከወላጅ ወደ ልጅ እንደመሻገር ማለት ነው። ንፉግነትም ሆነ የበዛ ለጋስነትን ታሪክ አይፈልግም፤ መስታወት ሆኖ ያለውን ያሳያል እንጂ አያጎላም ወይም አያኮስስም። ጊዜን ተሻግሮ የተከተበ ከሆነ ደግሞ ሚዛናዊ ይሆን ዘንድ ይጠበቃል። በርካታ የታሪክ መጻህፍቶችንም በመስታወትነት የተዘጋጁ፤ ትላንትንና የትላንት መንገድን አሳይተው ለዛሬ ቀናውን እንድንቀይስ የሚያግዙ ናቸው ብለንም እናምናለን።
ባሳለፍነው ሳምንት ነበር «ለወገንና ለአገር ክብር – ሜጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ እና ኢትዮጵያ» የተሰኘ መጽሐፍ በሳፋየር አዲስ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተመርቆ ለንባብ የበቃው። ይሄ መጽሐፍ በጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ሕይወት ዙሪያ የተጻፈ ሲሆን መጽሐፉን ያዘጋጁት ደግሞ የጄኔራሉ ልጆች በጋራ በመሆን ነው። በመጽሐፍ ምርቃት መርሐ ግብሩም ላይ እያንዳንዳቸው ከመጽሐፉ የተወሰኑ ክፍሎችን አቅርበዋል፤ ሃሳባቸውንም አጋርተዋል።
ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ማን ናቸው? አንዳንድ ጊዜ ብዙ ታሪክ የሚነገርበትና የተረሱ የሚታወስበት ሆኖ ይገኛልና ይህም ያለንበት ጊዜ ቸል የተባለ የመሰለውን የግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት አስታውሷል። ቀድሞ ጥቂት መገናኛ ብዙሃን በታሪክ ትውስታ የሚያነሱትን፤ አሁን ላይ ብዙዎች በትኩረት ተመልክተው አስታውሰውታል። ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ ማለት የግንቦት 8ቱ መፈንቅለ መንግሥት መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ጄኔራል መርዕድ በመጽሐፉ ላይ በልጆቻቸው ከቀረቡት በላይ የሚያውቋቸው ጓደኞቻቸውና በሠራዊቱ አብረዋቸው ለመሥራት እድል ያገኙ የሠራዊት አባላት በብዙ መስክረውላቸዋል።
በመጽሐፉ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ በግልጽ ያልታወቀውና ውስጠ ምስጢሩ ያልተገለጸው፤ እንደምን ከሸፈ? ምን ተባብለው ነበር? ምን ተወራ? ወዘተ የሚለው የመፈንቅለ መንግሥቱ ነገር በስፋት የለም። ምንአልባት አንዳንዶች ስለ መፈንቅል መንግሥቱ ወይም ስለአስራ ሁለቱ ጄኔራሎች በብዛት የሚያትት ምስጢር አገኝበታለሁ፤ ያልተነገረ እሰማለሁ ብሎ አይጠብቅ። ነገር ግን ስለ ጄኔራል መርዕድ ያልተሰሙ የግል ታሪኮችና ስብእናቸውን ለማወቅ ያግዝ ይሆናል።
ይህን ጉዳይ ቤተሰቦቻቸውም ተናግረውታል። በተለይም በቤት ውስጥ ስለሥራቸው ብዙ የማያወሩና የማይናገሩ መሆናቸውንና ልጆቻቸው ሳይቀሩ የአባታቸውን ጉዳይና አንዳንድ ነገሮችን ከውጭ የሚሰሙ መሆናቸውን ገልፀዋል። ነገር ግን መጽሐፉን በጥልቀት መዳሰስ እና ከሌሎች ሰነዶች ጋር በጥልቀት ማመሳከር ከቻልን የአንዳንዶቻችንን የጎደለ የታሪክ ቋት ሙሉ ሊያደርግልን ይችላል፡፡
በአንድ አገር ውስጥ በሚከሰት ጉልህ ታሪክ ላይ ሁሌም ቢሆን ሁለት ፅንፎች መኖራቸው የማይቀር ነው፡፡ በተለይ የሀሳብ ልዩነት ባላቸው እና ክስተቱን ራሳቸው በቆሙበት መሬት ልክ ብቻ ተገንዝበው የሚያራግቡ ቡድኖች ሲፈጠሩ ከውጭ ቆሞ እውነትን ለሚፈልገው ወገን ግራ የሚያጋቡ ሁኔታዎች መፈጠራቸው የማይቀር ነው፡፡
እንደዚህ ላለው ጫፍ እና ጫፍ ይዞ ለሚወጥር ጉዳይ ዋናው መፍትሄ ከሁሉም ወገን ያለውን እውነታ እና ማስረጃ አግኝቶ በራስ ህሊና የግል ግምትን መውሰድ መቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይ ዛሬ ላነሳነው ጉዳያችን የጎደለውን የሚሞላ እና አዲስ እይታ የሚጨምር ዳጎስ ያለ የታሪክ ሰነድ ከጄኔራል መርድ ንጉሤ ቤተሰቦች ማግኘት ተችሏል፡፡ በተለይ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን በወሳኝ ምዕራፍ ላይ አስቀምጧት የነበረን መፈንቅለ መንግሥት የመክሸፍ ሚስጢር በጥቂቱም ቢሆን ለመገንዘብ ከዚህ የተሻለ መፍትሄና አጋጣሚ ይገኛል ብሎ ማሰብ ከመታበይ አይተናነስም፡፡
ለዚህም ነው በዛሬው የአዲስ ዘመን የኪነ ጥበብ የመጽሐፍ ዳሰሳ አምድ ላይ የጄኔራሉን የግል የህይወት ታሪክ በስፋት የያዘውን ዳጎስ ያለ ሰነድ በትንሹም ቢሆን ቀነጫጭቦ በመዳሰስና አንባቢያንን መኮርኮር አስፈላጊ ሆኖ ያገኘነው፡፡
ልጆቻቸው ስለ አባታቸው
በወቅቱ በጦር ሜዳ አብረዋቸው ከጠላት ጋር የተፋለሙ፣ በስኬትም ሆነ በአስስቸጋሪ ጊዜያቶች ከጎናቸው የነበሩ ወዳጅ ዘመዶች፣ የሥራ ባልደረቦች እንዲሁም የታሪክ አዋቂዎች በተገኙበት በደማቅ ስነ ሥርዓት መጽሐፉ በተመረቀበት ወቅት ልጆቻቸው ጄኔራል መርድ ንጉሤ ስለነበሯቸው ልዩ ባህሪያት ከመጽሐፉ ላይ ቀንጭበው በማቅረብ ታዳሚውን ‹‹ለካ እንዲህም ነበሩ›› በሚል ማስደመም ችለዋል፡፡
በተለይ በግል ታሪካቸው ላይ ከተጠቀሰው ቀልብ የሚስብ ማንነታቸው ውስጥ ለአገር እና ለወገን ያላቸው ፍቅር በተግባር እንዴት እንደሚያሳዩ የሚተርከው ክፍል ነው፡፡ ከ1944 ዓ.ም ከክቡር ዘበኛ እጩ መኮንን ህይወታቸው እስካለፈበት 1981 የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ከፍተኛ ስልጣን እርከን ያደረሳቸው ፅናት የአገር ፍቅር እና የወገን ክብር ነበር፡፡ ለዚህም በጦር ሜዳ ግንባር ታላላቅ ገድሎችን ከመፈፀም አልፈው ሰውነታቸው በጥይት እስከመበሳሳት እና ለከፋ ቁስለኝነት እስከመዳረግ መድረሱን የግል ህይወታቸውን የሚያወሳው መጽሐፍ ይነግረናል፡፡
ከዚህ ባሻገር ልጆቻቸው ስለ አባታቸው የፃፉትን ታሪካዊ መጽሐፍ ለአንባቢው በህሊናው እንዲፈርድ እንዳቀረቡት ሲናገሩ ‹‹ልባቸው በጥላቻ የተደፈነ ሰዎች አመለካከት ይቀየራል የሚል የዋህ አመለካከት የለንም›› በማለት በማስረጃ የተደገፈ እና ከተራ አሉባልታ የፀዳ ታሪክ ለሚሹ ወገኖቻቸው በርካታ መረጃዎች አጣቅሰው መጽሐፉን ለንባብ ማብቃታቸውን ‹‹ለወገን እና ለአገር ክብር›› የሚል መሪ ርዕስ በሰጡት መጽሐፍ ላይ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር መጽሐፉን ሲከትቡ በዋናነት ዋቢ አድርገው የጠቀሱት አባታቸው ጄኔራል መርድ ንጉሤ በተለያየ ጊዜ ያሠፈሯቸውን ማስታወሻዎች እንደ ቀዳሚ መረጃ በመጠቀም መሆኑን በመግቢያው ላይ ባሠፈሩት መሪ ገፅ ይጠቅሳሉ፡፡ ጄኔራል መርድ መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉን ተከትሎ እራሳቸውን ካጠፉ በኋላ የደርግ የፀጥታ መሥሪያ ቤት ባልደረቦች በርካታ ማስታወሻዎችን መኖሪያ ቤታቸውን በመበርበር መውሰዳቸውን አንዳንዶቹም በጥንቃቄ ጉድለት በጊዜ ሂደት መጥፋታቸውን ያነሳሉ፡፡ እነዚህ የተወሰዱና የጠፉ ማስታወሻዎች ብዙ ቁምነገሮችን ይዘው እንደነበር ምንም ጥርጣሬ እንደሌለው በማመን የፈጠሩትን የታሪክ ሽንቁር በማሰብ ቁጭታቸውን በመጽሐፉ ላይ አስፍረዋል፡፡
ግንቦት ስምንት
በዚህ መጽሐፍ ላይ ቀልብን ይዘው ከሚነጉዱ ገፆች መካከል የጄኔራል መርድን የመጨረሻ ቀን የሚተርከው የግንቦት 8/ 1981 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥቱ ተሞክሮ የከሸፈበት ክፍል ነው፡፡ ጓድ መንግሥቱ ሃይለማሪያምን ወደ ምስራቅ ጀርመን ለሥራ ጉብኝት ከመሸኘት የጀመረው እንቅስቃሴ የመከላከያ ሚኒስቴር ግቢን ለመክበብ ትንቅንቅ እስከማድረግ ደርሷል፡፡
ጭርሱኑ በኤርትራ ክፍለ አገር አሥመራ የደርግ ሥርዓት መገርሰሱን በሬዲዮ እስከ መለፈፍ ተደርሷል፡፡ መጽሐፉ በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ ሚስጥር የሆኑ እና ግራ የሚያጋቡ እንቅስቃሴዎች በዕለቱ መደረጋቸውን ልብ በሚያንጠለጥሉ ቃላቶች ይተርክልናል፡፡
ለመሆኑ መፈንቅለ መንግሥቱ ለምን ከሸፈ? ይህ መጽሐፍ የራሱን መረጃዎች እና በወቅቱ የተከሰተውን ሁኔታ የታሪክ መዛግብትና በቦታው የነበሩ የዓይን ምስክሮች በማጣቀስ ምላሽ ለመስጠት ይሞክራል፡፡
ከሁሉም ከሁሉም ግን የዚህ ኦፕሬሽን ፊት መሪ የሆኑት ጄኔራል መርድ ንጉሤ በዕለቱ በፍፁም እርጋታ ይታይባቸው ነበር፡፡ ጓድ መንግሥቱ ሃይለማሪያም ወደ ምስራቅ ጀርመን ካቀኑ በኋላ የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የዕለት ሥራቸውን በቢሯቸው አጠናቀው ለሚቀጥለው ታላቅ ግዳጅ ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ማቅናታቸውን የሚያወሳን ክፍል አንዳች ቁምነገር ይነግረናል፡፡
ታዲያ ጄኔራሉን እንዲህ ያረጋጋቸው እና በራስ መተማመናቸውን አጉልቶ የሚያሳየው ዙፋን ግልበጣ በምን ተአምር ከሸፈ? ልጆቻቸው ዓመታትን በፈጀው ጥረታቸው የከተቡት የታሪክ ድርሳን ምላሽ አለው፡፡ እኛ ስለመጽሐፉ ጥቂት መንደርደሪያን አልን ቀሪውን አንባብያን አንብበው የጎደለ ታሪክ ሊያሟሉበት ያላወቁትን ሊያውቁበት የሚያውቁትንም ሊያስታውሱበት ይችላሉና እንዲያነቡት በመጋበዝ ተሰነባበተን ። ሠላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2011
ሊድያ ተስፋዬ