ሳቤላ ከድር ትባላለች። የተወለደችው ኤርትራ አስመራ ከተማ ውስጥ ሲሆን በሁለት አመቷ ወደ አዲስ አበባ ለህክምና መጣች። ሳቤላ የተወለደችውም ሆነ ያደገችው ከአካል ጉዳት ጋር ነው። የአካል ጉዳቷ የተከሰተው እናቷ የዘጠኝ ወር ድረስ እርጉዝ እያለች አስመራ ውስጥ ድንገት ከጀርባዋ የሆነ ሰው ነክቷት ሰትዞር መለመሉን ከቆመ የአእምሮ ህመምተኛ ጋር ተፋጠጠች። ልታመልጥ ስትሞክር ከፊት የነበረው ትልቅ ትቦ ላይ በፊቷ ወደቀች። በሰአቱ ሰው ተረባርቦ እናቷን ወደ ሆስፒታል ቢወስዷትም በጣም ብዙ ደም ፈሷት ስለነበር በሆዷ ያለችው ሳቤላ ከአካል ጉዳት ጋር እንድትወለድ ሆነ ።
በመካከል ዶክተሮቹ ፅንሱም የሳቤላ እናትም በጣም ክፉኛ እንደ ተጎዱ ለአባቷ እና ለቀሩት ቤተሰቦቻቸው የተናገሩ ቢሆንም ፅንሱ ምንም ቢሆን መትረፍ እንዳለበት ነገሯቸው ሳቤላ በኦፕራሲዬን ተወለደች። ስትወለድም በከባደ ሁኔታ የተጎዳች ህፃን ሆነች።
ከህፃንነት ጊዜዋ ጀምሮ ለበርካታ ጊዜ ትልልቅ ቀዶ ህክምናዎች ማድረጓን የምትናገረው ሳቤላ ስትወለድ አይኗ እጇና እግሯ ብቻ ጉዳት የነበረበት ሲሆን እስከ አስራ አንድ አመቷ ድረስ መንቀሳቀስ ምግብ መብላትና ሌሎችን ነገሮች በቤተሰብ እርዳታ ነበር የምታደረርገው።
ከ11 አመቷ በኋላ በቀዶ ህክምናና በሌሎች የህክምና እርዳታዎች መንቀሳቀስ ጀመረች። ቀስ በቀስም መራመድ ጀመረች። ከአካል ጉዳቱ በላይ የአእምሮ ጉዳት ይኑርባት አይኖርባት ያልተረዱት ወላጆቿ አእምሮዋ ደና መሆኑን የሚያረጋግጠ ምርመራ ካደረጉ በኋላ በእዝልም ቢሆን ትምህርት ቤት እየወሰድን እናስተምራታለን በማለት የትምህርት አለምን አስተዋወቋት።
ቤተሰቦቿ ለእሷ ብለው ብዙ መሰዋእትነት ከፍለዋል ትምህርት ቤት ከጓደኞቿ የተለየች አካል ጉዳተኛ መሆኗ ለብዙዎች እንደ ትንግርት መታየት ከዛም አለፍ ሲል ህብረተሰቡ ለአካል ጉዳት ባለው ዝቅተኛ ግንዛቤ ከእርግማን ጋር በማያያዝ ቤተሰቦቿም የተለዩና የተገለሉ ሆነው እንደ ነበር ታስታውሳለች።
በአስራ አንድ አመቷ ትምህርት ቤት የገባችው ሳቤላ ሶስት አመታትን በተከታታይ ደብል በመምታት በፍጥነት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ለማጠናቀቅ ቻለች። ልጇን ለማስተማር በየቀኑ እያዘለች ትምህርት ቤት የምታደርሰው እናት ልጇ ላይ የሚደርሰውን ጫና እንዳትሰማ ሳቤላ ዝም ማለት ጀመረች።
በትምህርቷ በጣም ጎበዝ መሆኗ እሷም ተማሪዎችን ለማቅረብ በመጣር ብዙ ጓደኞችን ለማፍራት ቻለች፤ ይህም በአካል ጉዳት ምክንያት የሚደደርስባትን አድሎና መገለል ለመቀነሰ አስችሎኛል ትላለች። ይህች ወጣት አካል ጉዳተኞች ስለጉዳታቸው እያሰቡ ከሰው ከመሸሽ ይልቅ ወደ ሰዎች ቀርበው አቅማቸውን ማሳየት እንደሚገባቸውም ታስረዳለች።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም ከመጀመሪያው በተሻለ ሁኔታ ከተማሪዎች ጋር በመቀራረብ አስራ አንደኛ ክፍለ ስትደርስ እናትና አባቷ ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው በእግር መንቀሳቀስ ከበዳት። በእግር በመሄዷ ምክንያት እግሯ ቆስሎ ለአመት ትምህርት አቋርጣ ህክምናዋን መከታተል ጀመረች። ከዛ በኋላ ጫማ ማድረግ ጀመረች። ̋እግሬ የተገለበጠ መሆኑ ጫማ ማድረግ ይከብደኛል ኢትዮጵያ ውስጥ አካል ጉዳተኞችን አስበው ቢሰሩ መልካም ነው ̋ ትላለች።
̋…ሰዎች ድንገት ሲመለከቱኝ ይደነግጣሉ መደንገጣቸው ቢያስከፋኝም መቀየር በማልችለው ነገር ከመጨነቅ ወደተሻለው መትጋት መርጫለሁ ̋ የምትለው ሳቤላ ̋ አሁን ያለኝ አካል ጉዳት የእግር የእጅ የአይንና የህብለሰረሰር (ስፓይናል ኮርድ) ጉዳት መሆኑ ህይወቴን ከባድ አድርጎብኛል ̋ ትላለች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ከጉዳቷ ጋር እየታገለች አጠናቃ ውጤት ብታመጣም ዝንባሌዋ ወደ ጥበብ (አርት)ላይ ነበርና ̋ ሚራክል ̋ የተባለ የፊልም ትምህርት ቤት በትወናና በፊልም ኤዲቲንግ በእስክሪፕት አጻጻፍ ትምህርት ጀመረች ። ትምህርት ቤቱ ፎቅ ላይ ስለነበር አሳንሰር ( ሊፍት ) አለመስራት፤ አስክሪብት አንብቦ መስራት፤ በተገቢው መልኩ ትወናውን መስራት በጉዳቷ ምክንያት ይከብዳት እንደነበር ታስታውሳለች።
̋ከስድስት አመታት በላይ ፊልም ለመስራት በጣም ለፍቻለሁ። ማህበረሰቡ ላይ የአካል ጉዳትን የሚመለከት መልእክት በተገቢው መንገድ ለማስተላለፍ የተለያዩ ጥናቶች በማድረግ ለመስራት ሞክሬያለሁ። አካል ጉዳተኞች ማርገዝ መውለድ አይችሉም በማለት “የሚታሰበውን ነገር ለማስቀየር እስክሪብት ብጨርስም ወጪውን የሚሸፍንልኝ ማግኘት አልቻልኩም” የምትለው ሳቤላ ̋የተለያዩ ፊልሞችን ፅፌ ከፕሮዲሰሮች ጋር በስልክ አዳምጠውኝ ግን ልፈራረም ስሄድ የአካል ጉዳቴን አይተው ያባርሩኛል። ልለምን ሳልል ልስራ በማለት አጠገባቸው ብመጣም ማንም ሰው ሊረዳኝ ባለመቻሉ ፊልም የመስራት ህልሜን አቁሜ ቆም ብዬ አሰብኩና ሌላ ስራ ለመሞከር ተነሳሁ ̋ ትላለች።
በዚህም በፋሽኑ ዘርፍ ለመሰማራት በማቀድ በ 2009 ዓ.ም የራሷን የፋሽን ዝግጅት በማድረግ ህልሟ ላይ የሚያደርሳትን ጉዞ አንድ ብላ ጀመረች ። የፋሽን መድረኩን ለማዘጋጀት ያሰበችው ሰዎች እየተዝናኑ ስለ አካል ጉዳተኝነት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ነበር። ̋ቢሮ፣ገንዘብ ሳየኖረኝ ነው ሥራውን የሠራሁት። አንዳንድ ተቋማት ምግብና አዳራሽ እንዲሁም የገንዝብ ድጋፍ አደረጉልኝ በዘርፉ ላይ የሚንቀሳቀሱ የፋሽንና የስነ ጥበብ ትምህርት ቤቶችም ስራቸውን በማቅረብ እንዲሁም ሞዴሎችን በመስጠት ስራው የተሳካ እንዲሆን አደረጉልኝ እኔም የመጀመሪያውን ፋሽነ ሾው ስራዬን ለእይታ አበቃሁ ̋ትላለች።
ከፋሽን ሾው ትዕይንት በኋላም አዲስ ዘመን ጋዜጣን ጨምሮ ሌሎች የግልና የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ስራውን አይተው በማድነቅ ለህዝቡ እንዲደሰርስ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ገልጻ፤ የአሜሪካ ኤምባሲ አካል ጉዳተኞች ፋሽን ሾ ሊያዘጋጅ ሲያስብ የሚያቋት ሰዎች ስለእርሷ ተናግረው ሸራተን አዲስ ላይ 28 አካል ጉዳተኞች በርካታ ጉዳት አልባዎች በአስር ፋሽን ዲዛይነሮች የተካተቱበት ስራ መሰራቱን ትናገራለች።
11 ፋሽን ሾዎች ላይ ስራዎቿን ይዛ ለማቅረብ የቻለችው ሳቤላ በራስ የመንቀሳቀስ አቅም ኖሯት ፋሽን ላይ የሰራች የመጀመሪያዋ አካል ጉዳተኛ መሆኗን ተናግራለች። ምንም ነገር ለማድረግ የሚወስነው የራስ ጥንካሬ ነው የሚትለው ሳቤላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ “ያልታበሱ እንባዎች” በሚል ፊልም ከተሳተፈች በኋላ ለአካል ጉዳተኛ በፊልም ሥራ መሳተፍ ብዙ ፈተና እንዳለውና በመጀመሪያ የሠሩት ፊልም ላይ ልምምድ ሲያደርጉ፣ በታዳሚዎች ፊት ወድቀው በደም የተለወሱበትን ቀን የማትዘነጋው መሆኑን ትናገራለች።
ሳቤላ እንደሌሎች አካል ጉዳተኞች በደረሰባት የአካል ጉዳት ተማርካ መክሊቷን መቅበር አትፈልግም። ይልቁንም “የተመቻቸ መንገድ መፍጠር የሚቻለው ያልተመቸ መንገድ ላይ ሆኖ ነው” ትላለች ። “እሾህን በእሾህ” እንዲሉ፣ በሳቤላ ግንዛቤ መፍትሔ የሚፈጠረው ችግር ሲገጥም ነው። በመሆኑም አንዴ የተከሰተን ጉዳት እያሰቡ አንገት ከማቀርቀር፣ ችግሩ ከምንም ሥራ እንደማያግድ ለራስ መንገር የስኬት ቁንጮ ነው ትላለች።
“መስራት የሚቻለው በታጣው ነገር ሳይሆን ባለው ነገር ነው። በታጣ ነገር ላይ ሙጭጭ ማለት ያለውንም ማጣት ነው” ሳቤላ ሁሌም ለውስጧ የምትነግረው ሀሳብ ነው። “አካል ጉዳተኛ ነኝ” ብሎ መደበቅ፣ መውጣት የሚችለውን ችሎታ በመደበቅ ሌላም ጉዳት መጨመር ነው በማለትም ትመክራለች። ‹‹ጉዳቴን እኔ ፈልጌ አላመጣሁት፤ ደግሞስ ያልተሰጠኝን ብቻ ለምን እመለከታለሁ! ካልተሰጠኝ ይልቅ የተሰጠኝ ይበዛል እኮ…›› በማለት ራሷን እንደምታበረታ ነው የምትናገረው።
ሳቤላ ሁሌም የፈለገችውን መሥራት እንደምትችል ታምናለች። ይህ በራስ መተማመኗ ከአካል ጉዳተኞች ለየት ያለች እንደሚያደርጋት ታምናለች። “እንደ ሌሎች የኔ ዓይነት ሰዎች ጎደሎ ነኝ የሚለው ሐሳብ ቢያሸንፈኝ፣ የደረሰብኝ የአካል ጉዳት ለልመና በቂ ነበር” የምትለው ሳቤላ፣ ይህን ችግር በማለፍ በፊልም ሥራ ላይ ለመሳተፍ በቅታለች።
̋አሁን ላይ ሳቤላ ከወንድምና ከእህቷ ጋር ትኖራለች። አላገባችም አልወለደችም አምላክ ከፈቀደ ማግባትንም መውለደንም ታስባለች። ሳቤላ ” ሰዎች አካል ጉዳተኞች ቢጢያቸውን ብቻ የሚያገቡ ይመስላቸዋል ሲወልዱም አካል ጉዳተኛ የሚወልዱ ነበር የሚያደርጉት ፤ አሁን ላይ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ተቀይሯል፤ እኔም እዚህ በመድረሴ ደስተኛ ነኝ ̋ ትላለች።
̋በተለይ እኛ አካል ጉዳተኞች ሴትም እንሁን ወንድ ሁሉም ነገር የሚመጣው ጊዜውንና ሰአቱን ጠብቆ እንደሆነ ማመንና ይኖርብናል፤ ምክንያቱም እኛ መወሰን አንችልም፤ ልክ እንደማንኛውም ጉዳት አልባ ሰው ትዳር ላይ የፍቅር ግንኙነት ላይ አለመግባባት ሊያጋጥመን ይችላል ያ ማለት ግን ጉዳተኛ ስለሆንኩኝ ነው ብሎ ራሰን ከመውቀሰ አጋራችንን በእውቀትና በተሻለ አእምሮ በልጠን ያለንን ግንኙነት ማጥበቅ ያስፈልጋል። ለጓደኝነትም ይሁን ለትዳር ያሰበንና የጠየቀን እኛ በመረጠን ሰው ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ግምትና ቦታ እንዲሁም ትልቅ የክብር በር ስለተከፈተልን ነው ። ̋ ትላለች።
̋የኔ ጉዳት ከሌሎቹ ጉደተኞች ጓደኞቼ ጋር ሳወዳድረው እጅግ በጣም ከባድ ነው። ግን አንድም ቀን ጌታ ሆይ ትዳር እንዳታሳጣኝ ብዬ አዝኜም ጠይቄም አላውቅም። ምክንያቱም ፈጣሪ ለእኔ ያዘጋጀልኝን እንደሚሰጠኝ አምናለሁ ። የጉዳቴ መጠን በሰዎች አይን ሲታይ እጅግ ከባድ ቢመስልም እኔ ግን ጉዳቴን አምኜ ተቀብዬው ወድጄው እና ቀለል አድርጌ ነው የምኖረው፤ እኔ የተመረጥኩኝ ነኝ እንጂ ምራጭ አይደለሁም ብዬ ሁሌም ለራሴ እነግረዋለሁ ።የተመረጥሸ ስትሆኚ ትኩረትሸ ለውጥና ስራ ላይ ይሆናል። ምራጭ ስትሆኚ ደግሞ ተገፊና ሰው ጠባቂ ጥገኛ ትሆኛለሸ ። ስለዚህ ህይወት እጃችን ላይ ናት ምድር ሁሉንም ተቀብላ ታኖራለች የሰው ልጅ ደግሞ መርጦ ይቀበላል መርጦ ይተዋል ። ስለዚህ ቀና እና መልካሙን እያሰብንና እየሰራን እንለፍ የመጣነው የተሰጠንን አላማ እንድንፈፅም ነው ̋ በማለት መልእክቷን አስተላልፋለች።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2016