“ግድቤን በደጄ” የተሰኘው የውሃ ሽፋንን የማሳደግ የሙከራ ፕሮጀክት ውጤታማ ሆኗል

አዲስ አበባ፡- ከጣሪያ ላይ የዝናብ ውሃን በማሰባሰብ የውሃ ሽፋንን ለማሳደግ በሙከራ ደረጃ የተጀመረው “ግድቤን በደጄ” የተሰኘ ፕሮጀክት ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የውሃና ኢነርጂ እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የውሃ አማራጭን ለማስፋት የሚያስችል “ግድቤን በደጄ” የተሰኘ ፕሮጀክት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በወቅቱ እንደገለጹት፣ የ”ግድቤን በደጄ” ፕሮጀክት የጣሪያ ላይ የዝናብ ውሃን በማሰባሰብ ተጨማሪ የውሃ ሀብት አቅምን ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ የውሃ ጥምን የሚወጣው ተጨማሪ የውሃ አማራጮችንም በመጠቀም ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ውሃን በአማራጭ በማሰባሰብ ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ላይ እየተሠራ እንዳለ ጠቅሰው፤ በዚህ ላይ ትኩረት ያደረገው ፕሮጀክቱ በሙከራ ደረጃ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡ በተለይም ዝናብ አጠርና ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ፕሮጀክቱን በሰፊው ለመተግበርና ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

ከጣሪያ ላይ የዝናብ ውሃን የማሰባሰብ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት የውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ በሰፊው እንደሚሠራ ገልጸው፤ የውሃ እጥረት ባለባቸውና በተደጋጋሚ በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የፕሮጀክቱ ትግበራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ ለሥራው መሳካት የአጋር አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በውሃ ሀብት የታደለች አገር መሆኗንና ይህንን ፀጋዋን በቴክኖሎጂ አስደግፋ መጠቀም እንዳለባት ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ ግድቤን በደጄ ፕሮጀክት አንዱ ማሳያ እንደሆነና የንጹሕ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በማሳደግ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር የተካሄደው የድርጊት ስምምነት ዘርፉን ከሥራ ዕድል ጋር ለማስተሳሰር አጋዥ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በሙከራ ተጨባጭ ውጤት እንዳስገኘ በመጥቅስ፣ በቀጣይ በስፋት ወደ ሥራ ሲገባ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድልን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ ዜጐች የተፈጥሮ ፀጋን በአግባቡ በመጠቀም በራሳቸው የውሃ ባለቤት መሆን የሚችሉበትን እድል የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል። ግድቤን በደጄ ፕሮጀክት ተጨማሪ የሥራ እድል ለመፍጠር ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት በዘርፉ የሠለጠኑ ወጣቶችን በማሠማራት የሥራ ዕድል ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ እና በቀድሞ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባሉ 87 ትምህርት ቤቶች ላይ ሲተገበር መቆየቱ ተገልጿል፡፡

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2016

Recommended For You