የአባቷ ጌጥ – ሲቲያና

ጋሽ ቴኒ ቦንገር፤ የቤታቸው የበኩር ልጅ ሆና የመጣችውን ድንቡሽቡሽ ሕጻን ልጅ ተመልክተው፤ ጌጥ እንደምትሆናቸው በመተማመን ስሟን ሲቲያና ሲሉ ሰየሙት። በጉራጊኛ የኔ ጌጥ እንደማለት ነው።ዳሩ ምን ያደርጋል ጌጤ ነሽ ሲሉ ያወጡላትን ሥም ትርጉሙ ሳይገባት ቀረና ‘አመለ’ ስትል ለራሷ ባወጣችው ሥም ለወጠችው።ለረዥም ጊዜያት መጠሪያዋ ይሄው ሥም ሆኖ ቆይቷል።ለዚህም ነው፤ አመለ በሚለው ሥሟ ይበልጥ የሚያውቋት የቅርቦቿ ሁሉ ‘ኤሚ’ በሚል የቁልምጫ ስም የሚጠሯት።

ነገር ግን፤ ከልጅነት ወደ እውቀት ስትሸጋገር በማንነት ፍለጋ ውስጥ አባቷ ያወጡላትን ሲቲያናን መልሳ ያገኘችው ይህቺው ድምጻዊት፤ የዛሬው የዝነኞች ገጽ ምርጫችን ሆናለች። ድምጻዊቷ፤ በረዥም ጉዞ ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፋ በቅርቡ “ማንነቴን” የተሰኘ የአልበም ሥራ ለአድማጭ ጆሮ ለማድረስ በቅታለች።

ድምጻዊት ሲቲያና ቴኒ ቦንገር ውልደትና ግማሽ የልጅነት ዘመን እድገቷ ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ነበር። ሰላማዊ የልጅነት ሕይወትን በዚያው አሳልፋለች። ገና በጊዜ ሙዚቃ መስማትና መሞከርም ትወድ ነበር። በአቅራቢያዋ ያሉ ሁሉ ድምጿ እንደሚያምር አስተያየት ሲሰጧትና ከሌሎች ልጆች በተለየ እንድትዘፍን ሲጋብዟት፤ እሷም የተለየ ነገር እንዳላት ብትረዳም ብዙም ቁብ አልሰጠችውም ነበር።እያደር በሙዚቃ ፍቅር ይበልጥ እየተለከፈች ሄደች።

ስለሙዚቃ ምኑም ሳይገባት ያንንም ይሄንንም ትሰማለች፤ የሰማችውንም ታንጎራጉረዋለች። የነገ ሕይወቷ በትምህርት እንደሚለወጥ የሚያምኑት ቤተሰቦቿ አንዳችም ሳይሰስቱ ለትምህርቷ አስፈላጊውን ሁሉ ያሟሉላት ነበር። እሷም ብትሆን ጎበዝ ተማሪ ነበረች።ታዲያ ይህ የዘለቀው ሙዚቃ እስኪያሸፍታት ድረስ ብቻ ነበር።

ልቧ በሙዚቃው በተረታ ጊዜ ሀሳቧ ሁሉ ማን አልበም አወጣ…ከየትኛው ሙዚቃ በኋላ የትኛው ተከተለ…የሚለውን መያዝ እንዲሁም ግጥምና ዜማ መሸምደድ በመሆኑ የትምህርት ጥናት ጊዜዋን ተሻማው።በዚህም ከቤተሰቦቿ ጎሽ!…ከሚል ድጋፍ ይልቅ “ምነው ትምህርትሽን እንዲህ በሸመደድሽ!” የሚል ተደጋጋሚ ተግሳጽ አስተናግዳለች።እናት፤ ልጇ ሙዚቀኛ እንድትሆን ምንም ሀሳቡም ፍላጎቱም የላትም።አባቷ ግን፤ እሷ ባትሰማውም ቢያንስ ተምረሽ ያሬድ ጊቢና የተማረ ሙዚቀኛ ሁኚ የሚል ሀሳብ ነበረው።

ሲቲያና የ14 ዓመት ታዳጊ ሳለች ከቤተሰቦቿ ጋር መኖሪያቸውን ከቢሾፍቱ ወደ ወልቂጤ ከተማ ቀየሩ። ኑሮዋን በወልቂጤ ካደረገች በኋላ፤ በአንድ ወቅት የዞኑ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ወጣቶችን እንደየፍላጎታቸው ለማሰልጠን ማስታወቂያ ያወጣል።ሥልጠናው በውዝዋዜ፣ በድምጽ፣ በትወና እንዲሁም የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነት ሲሆን፤ በመረጡት ዘርፍም መሰልጠን የሚቻል ነበር። እሷም እንደ ጊዜ ማሳለፊያ በአቋራጭ ከምትወደው ሙዚቃ ጋር መገናኛ ይሆናት ዘንድ፤ ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመጡ ምሩቃን የሚሰጠውን የድምጽ ሥልጠና መከታተል ጀመረች።

ለሦስት ወራት ያህል ተብሎ የተጀመረው ሥልጠና አስር ወራትን አስቆጠረ።ያኔ ከአሰልጣኞቿ የምታገኘው ማበረታቻ ይበልጥ ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኗን አመለከታት።በትምህርት ቤት ውስጥ በሚኒ ሚዲያና መሰል ክበባት ያገኘችው የሙዚቃ እውቀት ይበልጥ እንዲዳብር መንገድ ተመቻቸላት።በሕይወቷ ውስጥም የበርካታ ድምጻውያንን ሙዚቃ እያደመጠችና ሥራቸውን እየሞከረች ቆይታለች።

ከሁሉም በላይ በሙዚቃ የይቻላል መንፈስን ያጎናጸፋት ድምጻዊ ግን፤ ፋሲል ሽመልስ ነው።ድምጻዊው የመጀመሪያ አልበሙን ሲያወጣ እድሜው 12 ነበር።ህጻኑ ሙዚቀኛ እየተባለ በሁሉም ዘንድ መነጋገሪያ በሆነበት ወቅት እሷ ደግሞ 14 ዓመቷ ነበርና የ12 ዓመት ልጅ አልበም ካወጣ እኔም ማድረግ እችላለሁ የሚል ስሜት በውስጧ ዳበረ።ያኔ ታዲያ እናቷ ምን ሲደረግ! አሉ፤ አባቷ ግን ተምረሽ በወጉ ያሬድ ገብተሽ ሙዚቃን ትማሪያለሽ አሏት። እሷም “ሌላው በ12 ዓመቱ አልበም ይሠራል እኔ ምን ሲደረግ ገና እስከ አስረኛ ክፍል እማራለሁ” አለች።

የ14 ዓመት ታዳጊ በነበረችበት በዚሁ ጊዜ ክለብ ውስጥ ሙዚቃን ትጫወት ነበር።ቤተሰቦቿ አይሆንም ሲሉ ለሙዚቃው ከነበራት ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ከቤት እስከመጥፋት ደርሳለች። እድሜዋ ከፍ ሲል ግን ቤተሰቡ፤ ከመቀበል ውጭ እሷና ሙዚቃን መነጠል የማይታሰብ መሆኑ ገባው።በዚህ ሁኔታ እሷና ሙዚቃ በነጻነት መቀራረብ ሲጀምሩ መላው ቤተሰብ ከሀገር ወጣ።መኖሪያዋ ከሀገር ውጭ በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ከተማ ሆነ።በስደት ሕይወቷ ያገኘችውን ሥራ ትሰራለች፤ የተሻለ ገቢም ታገኛለች።ነገር ግን ውስጧ ሰላም፤ ደስታ ይሉት ነገር ጠፋ።ያኔ የምወደውን ሙዚቃ ብሰራ ልቤ ይረጋል ስትል አሰበች።

እናም በ2001 ዓ.ም “ዝም አትበል” የተሰኘ የመጀመሪያ ነጠላ ዜማዋን በኦዲዮ ብቻ አወጣች።በሥራው ምንም እንኳን ገቢ ባታገኝበትም ከሰላሟ ጋር ተገናኘች።ሙዚቃ ይሄን ያህል ደስታ ከሰጠኝ በሚል በሙዚቃ ሥራዋ ገፋችበት።“የኔ ጀግና” የተሰኘ ሁለተኛ ነጠላ ዜማዋን ደገመች። የቪዲዮ ክሊፑ እንደነገሩ በደቡብ አፍሪካ ስለተሰራ ያን ያህል ሕዝቡ ጋር አልደረሰም ትላለች። ሙዚቃ የውስጧ ሠላም ሰጪ ነውና፤ በመሃል ለእረፍት ወደ ሀገሯ ስትመጣ ለአልበም ይሆኑኛል ብላ ያሰበቻቸውን ግጥምና ዜማዎችን ሰብስባ ሄደች። እዛው እያለች ከሌላው ሕይወቷ ጎን ለጎን ግጥምና ዜማ ስታጠና ቆየች።

የወሰደችውን ግጥምና ዜማ ተለማምዳ ጨረስኩ ብላ ስታስብ በድምጽ ለመቀዳት ወደ ሀገሯ ለመምጣት ማቀድ ያዘች።በሷ ሀሳብ የቀራት ስቱዲዮ ገብቶ ማቀናበር ብቻ ነበር።የሚያውቁ ሰዎች ለዚህ ስድስት ወር ብቻ እንደሚበቃት ነገሯት።እሷም ከደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ የስድስት ወራት ቆይታ አድርጋ አልበሟን ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ በሻንጣዋ ሸክፋ ወደ ሀገሯ ኢትዮጵያ መጣች።

የአልበም ሥራዋን ለማጠናቀቅ የስድስት ወራት ቆይታ ብቻ በቂ እንደሆነ አስባ ብትመጣም፤ ነገሩ እንኳንስ ለአልበምና ለነጠላ ዜማ እንኳን የሚሆናት አልነበረም። አልበም ጨርሼ እመለሳለሁ ያለችባቸው ስድስት ወራት በስቱዲዮ ወረፋ ብቻ እንደቀልድ ወደመጠናቀቅ ተቃረቡ። በዚህ መሃል እሷም ተስፋ ወደመቁረጡና ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመመለስ ሻንጣዋን ወደማዘጋጀቱ ተሸጋገረች።የስድስት ወር ቆይታዋ ያለስኬት ተጠናቆ መኖሪያዋ ወደሆነው ደቡብ አፍሪካ ልትመለስ መሆኑን የተረዳው የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች ጓደኛዋ፤ ኤልያስ መልካ ጋር ልውሰድሽና እዛ ሞክሪ ሲል ከኤልያስ ጋር አገናኛት።በስቱዲዮው ውስጥ ያገኘችው ኤልያስ መልካ የሰበሰበቻቸውን ሳምፕሎች ሰምቶ ሲያበቃ “ይሄ ለሆነ ሰው የተዘጋጀ ግጥምና ዜማ ነው፤ መጀመሪያ አንቺን እንፈልግሽና ለአንቺ የሚሆን ግጥምና ዜማ እናዘጋጅ” ሲል በአዳዲስ ግጥምና ዜማዎች ሥራው ሀ ተብሎ ተጀመረ።

ለአልበም ሥራዋ የሚሆኑ ሙዚቃዎችን እዚያው ተመርጦ መዘጋጀቱ ይበልጥ ምቾት ሰጣት።ሆኖም ግን ኤልያስ ፈላጊው ብዙ ነውና በዚህ የተነሳም ስቱዲዮ ለመግባት ወረፋው ከባድ ሆነባት። አንድ ዙር ስቱዲዮ ለመግባት ረዥም ጊዜ መጠበቅ የግድ ነበር። በዚህ መሃል ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄድ መለስ እያለች፤ ለአልበም የሚሆኑ ሙዚቃዎቿ ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት መጠናቸው እየጨመረ ሄደ። ኤልያስ ጋር በቅንብሩ ሰበብ ሲገናኙ በመሀል ተግባቡ። ሲያወሩ የምታነሳቸውን ሀሳቦች ግጥም አድርጎ ያቀርብላታል።በዚህ መልኩ ከቅንብር በዘለለ አዲስ ግጥምና ዜማ እየተፈጠረ ለሰባት ዓመታት ያህል ቆይተዋል። የአልበሟ መጠሪያ የሆነው “ማንነቴን” በዚህ አይነት ሂደት የተፈጠረ ነበር።

ሲቲያና ለረዥም ጊዜያት በደቡብ አፍሪካ የቆየች ስለሆነ፤ በኢትዮጵያ ቆይታዋ እየተመለከተች የነበረውን የሴት ልጅ አያያዝ እንግዳ እየሆነባት ግራ ተጋብታም ነበር። ኤልያስም፤ አብዛኛውን ጊዜውን ለሙዚቃ ሥራው የሰጠና በስቱዲዮ የተወሰነ ስለነበረ ስለከተማው እንቅስቃሴ ብዙም መረጃው አነበረውም። እሷ ወጣ ብላ ባየችው ነገር አንዳንዴ እየተገረመች አንዳንዴም እንዴት ይሆናል? እያለች በንዴት ስሜቷን ታካፍለዋለች።እርሱም፤ ከዚህ ጨዋታቸው መሃል ከሲቲያና ያገኘውን ሀሳብ “ማንነቴን” ሲል በግጥም ከተበው።

ዘፈኑ ሴት ልጅ ሴትነቷን እና ቁንጅናዋን ለሌላ ነገር መተላለፊያ እንዳታደርገው ታስቦ የተሰራ ነው።የአልበም ሥራውን ከመጀመሯ በፊት በሠራቻቸው ሁለት ነጠላ ዜማዎች ላይ፤ ከአልበም ሥራው ጎን ለጎን ሌላ ሦስት ሙዚቃዎችን በማከል፤ ከአልበሟ ውጭ አምስት ነጠላ ዜማዎችን ለመሥራት ችላለች። “አጉላባይ” የተሰኘው ነጠላ ዜማዋ አልበሙ ወደማለቁ እየተቃረበ ነው ተብሎ ስለታሰበ ለአልበሙ ማስታወቂያነትም እንዲያገለግል ታስቦ የተለቀቀና አልበሙ ውስጥ ሊካተት የታሰበ ሥራ ነበር።በወቅቱ ሲቲያና ነብሰጡር ስለነበረች እንዲሁም ኤልያስም ሕመሙ እየተባባሰበት በመሄዱ አልበሙ ይወጣል ተብሎ በታሰበው ጊዜ ሳይወጣ ቀረ።

“ወለባ” በቪድዮ ክሊፕ የተሠራላት ሌላው ነጠላ ዜማዋ ነው።ወለባ በግጥምና ዜማ ብስራት ሱራፌል በቅንብሩ ደግሞ ታምሩ ማሞ ተሳትፈውበታል።“መልሰው” የተሰኘው ነጠላ ዜማ ማንነቴ የተሰኘው አልበሟ ከመውጣቱ በፊት የወጣ የመጨረሻ ነጠላ ዜማዋ ነው።አራቱ ነጠላ ዜማዎቿ በድምጽና ምስል፤ በክሊፕ መልክ የተሠሩ ናቸው። ስድስት ወራት ብቻ በቂ ናቸው ብላ የጀመረችው የአልበም ሥራ እንደቀልድ አስር ዓመታትን ፈጅቷል። የቅንብር ሥራው በኤሊያስ ተጀምሮ እንዲያልቅ ቢታሰብም፤ ነገር ግን ኤሊያስ ከቅንብሩ ባሻገር በአውታር መተግበሪያና ተዛማጅ የቅጂ መብቶችንም በማስጠበቅ ዋነኛ ተንቀሳቃሽ እንደመሆኑ፤ ጊዜ በማጣትና ጤናው ከዕለት ወደ ዕለት እየታወከ በመሄዱ በሥራው ሌሎች አቀናባሪዎችንም ለማካተት የግድ ሆነ።

“ማንነቴን” በተሰኘው አልበሟ ውስጥ 14 ዜማዎች የተካተቱ ሲሆን፤ ኤልያስ መልካ በግጥምና ዜማ እንዲሁም በቅንብር በስድስቱ ተሳትፎባቸዋል።የሌሎቹን ስድስት ሥራዎች ቅንብር በአቤል ጳውሎስ የተሠሩ ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለት ሙዚቃዎች ደግሞ በካሙዙ ካሳ ተቀናብረዋል።በዜማ ደረጃ ኤልያስ መልካን ጨምሮ አብነት አጎናፍር፣ ጃሉድ አወል፣ ብስራት ሱራፌል አበበ፣ አንተነህ ወራሽና ካሳሁን እሸቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።በግጥም ሥራው አሁንም ኤልያስ መልካ፣ አብነት አጎናፍር፣ መሰለ ጌታሁን፣ ወንደሰን ይሁብ፣ ካሳሁን እሸቱ አሻራቸውን አኑረዋል።በሥራው ላይ እያሉ የአልበሙ የጀርባ አጥንት የነበረው የኤሊያስ መልካ ድንገተኛ ሞት ነገሮችን ይበልጥ አክብዷቸው ነበር።እሷም ለጊዜው ልረፍ ስትል ሥራዎቿን ሰብስባ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመልሳ መሄዷ አልቀረም።

በስድስት ወር አጠናቅቀዋለሁ ብላ የገባችበት የአልበም ሥራ አስር ዓመት ቢፈጅባትም አልበሙ ተጠናቀቀ ስትል፤ ሌላው ያላሰበችው አድማጭ ጋር ማድረሱ ራሱን የቻለ አድካሚና አሰልቺ ሂደት የነበረው መሆኑን ነው።ከብዙ አሰልቺ ጉዞ በኋላ ለእያንዳንዱ ሥራ ክፍያ መፈጸምና እንዲሁም ማስተዋወቁ የእርሷ ድርሻ መሆኑን ስትረዳ ሥራዋን ይዛ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመለሰች።በሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ባለው ሂደት ተስፋ ቆርጣ ወደ መተው በተሸጋገረችበት ወቅት ነበር ሰዋሰው መልቲሚዲያ ወደ ሥራ የገባው።

የሷን ሙዚቃ ካቀናበሩት አንዱ የሆነው አቤል ጳውሎስ ለሰዋሰው አጭቶ ሥራዋን አስደመጣቸው፤ የሠራችውን ሥራ ስለወደዱት አልበሟን ገዙት።ይሄን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለችበት የሙዚቃ አልበሟ በሰዋሰው መተግበሪያ በኩል ለአድማጮች ቀርቧል።መተግበሪያው አዲስ ከመሆኑና እሷም ለአድማጮች አዲስ ከመሆኗ አንጻር ጥሩ አቀባበል እንዳገኘች ታምናለች።መተግበሪያው እየታወቀና እየተለመደ ሲመጣ አልበሟ ከዚህ በላይ እንደሚደመጥ ተስፋ ታደርጋለች።

በአልበሟ ሥብጥር ውስጥ ታስቦበትና ምን ቢተላለፍ ይሻላል ተብሎ የተካተቱ ሥራዎች እንዳሉ ሁሉ “ብርድ ብርድ አለኝ” የሚለው ሥራዋ በአጋጣሚ የተካተተ ነበር።ሲቲያና፤ ወደ ካሙዙ ስቱዲዮ ለሥራ መጥታለች።ሆኖም ካሙዙ ስቱዲዮ ውስጥ ከሌላ ድምጻዊ ጋር ሥራ ላይ ነበሩ።በሰዓቱ ዝናብ ነበር፤ የሚጥለውን ዝናብ ተከትሎ ብርዱ ኃይለኛ ነው።ድምጻዊ ጃሉድ፣ ድምጻዊ ብስራት እና ሲቲያና እሷ ልትሄድ ቆመው እያወሩ ነው።ውጪው ብርድ ስለነበረ፤ ጃሉድ ዝናቡን እያየ “ብርድ ብርድ አለኝ ባክሽ” እያለ እዛው ግጥም ደርሶ ያቀነቅናል።

በሰማችው የተመሰጠችው ሲቲያና ስልኳን አውጥታ ቀዳችው።ሙዚቃውን ሰምታ ስትጨርስ ለጃሉድ እኔ ልሄድ ነው፤ ግን ይሄንን ቆንጆ ሙዚቃ አድርጌው ትሰማዋለህ ብላው ሄደች።እንዳለችውም ብርሀኑ ሞገስ የሚባል ሰው፤ ከዛው ሀሳብ ሳይርቅ ግጥም ጨመረበት። ካሙዙ ቅንብሩን ሠራላትና በአልበሟ ላይ የተካተተ ቆንጆ ሥራ ሆነ።የአልበሟ መጠሪያ ለሆነው “ማንነቴን” እና “ዘራፍ ስል” ለተሰኙት ለስለስ ያሉ ሁለት ሙዚቃዎቿ የቪዲዮ ክሊፕ ተሠርቶላቸዋል።የአልበሟ መጠናቀቅን ተከትሎ መኖሪያዋን፤ የትዳር አጋሯ ወደሚገኝበት አሜሪካን ሀገር ቀይራለች።መኖሪያዋ ከሆነው አሜሪካ ተመልሳ፤ የአልበሟን ምርቃት እንዲሁም ኮንሰርት በሀገሯ ስታቀርብ ለመመልከት በመመኘት አበቃን።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ህዳር 16/2016

Recommended For You