በኢትዮጵያ ከ168 ሺህበላይ ለሚሆኑ ስደተኞች የትምህርት እድል ተሰጥቷል

 አዲስ አበባ፦ ከ168 ሺህ በላይ ስደተኞች በኢትዮጵያ የትምህርት እድል እንዲያገኙ መደረጉን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በትምህርት ሚኒስቴር የስደተኛ ትምህርት መርሃ-ግብር ከፍተኛ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ እንግሊዝ ከተማ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ትምህርት ሚኒስቴር ከግብረ-ሰናይና ልማታዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር 168 ሺህ 269 የሚሆኑ ስደተኞች የትምህርት እድል እንዲያገኙ አድርጓል።

ተማሪዎቹ በ65 ቅድመ አንደኛ ደረጃ፣ በ53 አንደኛ ደረጃ እና በ11 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት እድል እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን በአቅራቢያቸው በሚገኙት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከአካባቢው ማህበረሰብ ልጆች ጋር ተቀላቅለው እየተማሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በተመሳሳይ የማህበረሰቡ ልጆችም ለስደተኞች ተብሎ የተሠሩት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከስደተኞች ጋር ተቀላቅለው እንዲማሩ እድሉ የተመቻቸበት ሁኔታ አለ ያሉት ዶክተር እንግሊዝ፤ ይህም ቋንቋ፣ ባህል እና አብሮነትን እንዲለማመዱ እድል ፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

12ኛ ክፍልን አጠናቀው መግቢያ ነጥብ ያገኙ ተማሪዎች እንደማንኛውም ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ የሚሰጣቸው ሲሆን በርካቶች አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲ ገብተው እየተማሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር እንግሊዝ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ ከአፍሪካ ከዩጋንዳና ከሱዳን በመቀጠል በሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን በቁጥር 927 ሺህ 300 ለሚሆኑ ስደተኞች መጠለያ ሆና እያገለገለች ያለች ሀገር ስትሆን በብዛት ስደተኞቹ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራና ጥቂት የሚባሉት ደግሞ ከሌሎች ሀገሮች የመጡ ናቸው።

በዋናነት ስደተኞቹ በጋምቤላ፣ በሱማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የተጠለሉ ናቸው። ኢትዮጵያ ካስጠለለቻቸው ስደተኞች ግማሽ የሚሆኑት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ቢሆኑም ቀላል ቁጥር የማይባሉ በራሳቸውና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ትምህርት ቤት ሊመጡ አልቻሉም ብለዋል።

የስደተኞች ትምህርት መርሃ-ግብር ዓላማ አንደኛው የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚያገኙትን አገልግሎቶች ለስደተኞች ተማሪዎች ማዳረስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማካተት የሚባል ነው። ይህም ሁለተኛ ደረጃ የስደተኞች ትምህርት ቤቶችን በመንግሥት አስተዳደር ስር ማስገባት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለስደኞች ትኩረት በመስጠት ከሰብዓዊ አገልግሎት በተጨማሪ ከዜጎቿ ያልተናነሰ የትምህርት እድል በመፍጠሯ ከስደተኞቹና ከሌሎች ሀገሮች ጋር መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲኖራት አድርጓል ያሉት ባለሙያው፤ “ሀገራችን የስደተኞች ትምህርት ላይ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ብታከናውንም ብዙ ተግዳሮቶች ተስተውለዋል” ብለዋል።

አንደኛው የበጀት ማነስ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የመብራት እጥረት፣ የመማሪያ ክፍል ማነስ፣ የተወሰኑ መምህራን የትምህርት ዝግጅት ከደረጃ በታች መሆን እና ሁሉንም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱትን ህፃናት ወደ ትምህርት ገበታ ያለመምጣት በዋናነት የተለዩ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እነዚህን ችግሮች ከማቅለል አንፃር የትምህርት ሚኒስቴር በራሱ መፍታት የሚችላቸውን መፍትሄ እየሰጠ ይገኛል። ሆኖም የስደተኞችን የትምህርት መርሀ-ግብር በታቀደው መልኩ እንዲካሄድና ተማሪዎቹ ጊዜውን ያገናዘበ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ መተባበር ያስፈልጋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

 አዲስ ዘመን ኅዳር 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You