ከሰው ልጅ የመግባቢያ መሳሪያዎች ውስጥ አንዱ የንግግር ቋንቋ ነው። የንግግር ቋንቋ መቼና የት እንደተጀመረ በእርግጠኝነት የሚያስረዳ መረጃ ባይኖርም ከሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ሂደት ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ይነገራል። በአሁኑ ወቅት ቋንቋ ከሉዓላዊነት ጋር ተያይዞ የሰው ልጅ አብሮ የመኖር እና የመገናኘት እድልን እያሰፋ መጥቷል። በዚህም አንዱ የሌላውን ቋንቋ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በራሱ ቋንቋ ውስጥ እየቀየጠ የመናገር ባህል አዳብሯል። ሰዎች ታዲያ ቋንቋን ቀላቅለው ወይም ጉራማይሌ የሚናገሩት በተለያዩ ምክንያቶች እንደሆነ የቋንቋ ምሁራን ይገልፃሉ። ይህ ልምድ የራሱ ተጽእኖ እንዳለውም ይጠቅሳሉ።
መስፍን ፈቃደ(ዶ/ር) በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጹሑፍና የባህል መምህር ናቸው። የሀዲስ ዓለማሁ የባህል ጥናት ተቋም ዳይሬክተርም ሆነው ይሰራሉ። እርሳቸው እንደሚገልፁት ቋንቋን ቀላቅሎ /ጉራማይሌ/ መናገር ከመደበኛው የቋንቋው መድብለ ቃላት ጋር አብሮ ስለማይሄድ የሌላውን ቋንቋ በንግግር ውስጥ ማስገባት የሚፈለገው መልእክት እንዳይደርስ ያደርጋል። ጉራማይሌ የቋንቋ ለአብነት የአማርኛ ቋንቋ ንግግር ውስጥ በተደጋጋሚ የእንግሊዘኛ ቋንቋን ወይም ሌላ ቋንቋን አስገብቶ መናገር ነው። ይህም በተናጋሪውና መልእክት ተቀባዩ መካከል የተሟላ ተግባቦት እንዳይኖር ከማገዱም በላይ ቋንቋው እንዳያድግ እንቅፋት ይሆናል።
የጉራማይሌ ቋንቋ ንግግር አዋቂነትን ለመግለጽ ተብሎ የመጠቀም ሁኔታ እንዳለ ጥናቶች ያመለክታሉ። ይሁንና አንዳንዴ ለመግለጽ የተፈለገውን ቃል በመደበኛው ቋንቋ የማይገለጽበት ሁኔታ ሲፈጠር ቃሉን አስገብቶ የመጠቀም ሂደት አለ። እንዲያም ሆኖ ግን ቋንቋን ቀላቅሎ መናገር ተገቢ አይደለም። አንዳንዴ ግን በሚዲያ፣ በመደበኛ ማስተማር ስርዓት እና በንግግር ወቅት ለመግለጽ የተፈለገውን ቃል መደበኛው ቋንቋ የማይገልጽ ከሆነ ቀላቅሎ መናገር የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ ቋንቋ ቀላቅሎ መናገር አድማጭ መልዕክቱን በትክክል እንዳይረዳ፡- ቋንቋው እንዳያድግ ብሎም የቋንቋው ሥርዓትና ቅንብር እንዲፈርስ ያደርጋል። ለምሳሌ አንድ የህግ ባለሙያ ስለህግ ትንታኔ በሚሰጥበት ወቅት ሀሳቡን የሚገልጽ የተሟላ ቃል እያለ የሌላን ቋንቋን የሚጠቀም ከሆን የተማረውም ሆነ ያልተማረው መልእክቱን በሚገባ እንዳይረዳ ያደርጋል።
በኢትዮጵያም ከታችኛው እስከላይኛው ትምህርት እርከን ይህ ቋንቋን ደባልቆ ወይም ጉራማይሌ የመናገር ዝንባሌ በስፋት ይታያል። ከዚህ አንፃር ይህ ሁኔታ ለመቀልበስ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት ወቅት የሚማሩት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ከሆነ ያልተቀላቀለ እንግሊዘኛ መጠቀም፡- ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ መደበኛ መዝገበ-ቃላትን ማስቀመጥ እና ቀላቅሎ መናገርን እንደስልጣኔ ለሚመለከቱ ሰዎች ድርጊቱ ተገቢ አለመሆኑን መናገርና ግንዛቤ መስጠት ይገባል።
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህር ሰጠኝ ማየው(ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚናገሩት፣ ቋንቋን ቀላቅሎ መናገር ሁለት ቋንቋዎች በሚነገሩባቸውት አካባቢዎች የማይቀር ቢሆንም፡- እንግሊዘኛ ቋንቋ የሚገኘው በብዛት በትምህርት ቤቶች በመሆኑ ያልተማረው ህብረተሰብ የሚነገረውን መልእክት በትክክል መረዳት ይቸግረዋል።
ቋንቋን ቀላቅሎ መናገር በስፋት በሁለት ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል። የመጀመሪያው ተናጋሪው ቋንቋውን አጠቃሎ የማይችል ሲሆን፡- ሌላኛው ቋንቋው እራሱ ክፍተት የሚታይበት ሲሆን በተለይ አዳዲስ የመጡ የቴክኖሎጂ ቃላት የሚገልጽ ቃል ሲያጥር የመቀላቀል ሁኔታ ይፈጠራል። ይህም አድማጩ ላይ ብዥታ መፍጠር፣ አድማጩ ለእኔ ሊነገር ያልተፈለገ መልእከት አለ ብሎ እንዲያስብ ከማድረጉም ሌላ የሌላን ቋንቋ የማበረታታት ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል። በተጨማሪም አዋቂነትን ለመግለጽ፡- ከሌላኛው ቋንቋ ተናጋሪ ተቀባይነት ለማግኘት ፡- በልማድ እና ሚስጥር ለመደበቅ ቋንቋን ቀላቅሎ የማውራት ሁኔታም ይኖራል፡፡
እንደ ዶክተር ሰጠኝ ገለፃ፣ በሶስት ዓይነት መልኩ ቋንቋ ቀላቅሎ የመናገር ሁኔታ አለ። የመጀመሪያው በመደበኛው ቋንቋ ሃሳብን ጨርሶ ከተናገሩ በኋላ ቀጣዩን በሌላ ቋንቋ መናገር፡- ሁለተኛው በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ሌላ ቋንቋ አስገብቶ መናገርና ሶስተኛው አጫጭር ቃላትን በንግግር መሀል ማስገባት ናቸው፡፡
አዳዲስ የቴክኖሎጂ ቃላት ሲመጡ አቻ ትርጉም ሊሰጡ የሚችሉ ቃላትን በመፍጠር ረገድ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ሆነ በሚመለከታቸው አካላት ሰፊ ሥራ ሊሰራበት ይገባል። በተጨማሪም በቋንቋ ዙሪያ ተገቢውን ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡
አለመወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 13/2016