ዓመታትን በፍቅርና በመተሳሳብ ያሳለፉት ጎረቤታሞች ዛሬም እንደትላንቱ ናቸው።ግርግዳ ለግርግዳ በሚጋሯቸው ቤቶች ህይወትን መምራት ቀጥለዋል።በዚህ የቀበሌ ግቢ ልጆቻቸው በአንድ ገበታ በልተው በእኩል ተጫውተው አድገዋል።በአንድ ትምህርት ቤት ውለው፣ በአንድ ሰፈር ቦርቀዋል።የአብዛኞቹ ህይወት መመሳሰል ደግሞ በኑሯቸው ላይ የሰፋ ልዩነት እንዳይኖር አድርጓል።
የዚህ ግቢ ነዋሪዎች ራሳቸውን አሸንፈው ቤተሰባቸውን ለማሳደር እንደ አቅማቸው ይሮጣሉ።እንጀራ ጋግረው የሚሸጡ፣ጠላ ጠምቀው የሚኮምሩ ፣ጉልት ውለው የሚገቡ ወላጆች ስለነገው የልጆቻቸው ተስፋ አብዝተው የሚጨነቁ ናቸው።ይህ ስሜት ደግሞ በእያንዳንዱ ወላጅ ልቦና ውስጥ ለዓመታት ታትሞ ዘልቋል።
ብዘዎች ክፉ ደጉን ባለፉበት በዚህ ግቢ ሀዘንና ደስታው የጋራቸው ነው።አንዱ ከሌላው ተበድሮ፣ያለው ለሌለው አካፍሎ መኖሩ ተለምዷል።ይህ እውነት ደግሞ የግቢው መገለጫ ነው።ይህ ታሪክ የሰፈሩ መለያ የመተሳሰብና መረዳዳት ማሳያ ነው።
ሰናይት ግደይ ተወልዳ ባደገችበት የልደታ ሰፈር ከወላጅ እናቷ ጋር ትኖራለች። ከልጅነት የአፈር መፍጨት እስከወጣትነት ዕድሜዋ ባለፈችበት ግቢም ከትንሽ ትልቁ ጋር ተግባብታ ታድራለች።ህይወትን ለማሸነፍ እሷና እናቷ እየጋገሩ በሚሸጡት ደረቅ እንጀራ ኑሯቸውን ይደጉማሉ።ይህ ይሆን ዘንድም የግቢው ነዋሪዎች መልካምነት ሲያግዛቸው ቆይቷል።
ለእናትና ልጁ የገበያ ስኬት ሁሉም ጎረቤቶቻቸው ከጎናቸው ናቸው።እነሱ በሌሉ ቀን ቤታቸው ተዘግቶ አይውልም።ጓዳቸውን ዘልቀው ሞሰባቸውን ከፍተው እንጀራውን ይሸጡላቸዋል። ተመልሰው ሲመጡም ገንዘቡን አንድ ሁለት ብለው ያስረክቧቸዋል።ይህ እውነት ደግሞ ለግቢው የዓመታት አብሮነት አዲስ ሆኖ አያውቅም። በዚህ መልኩ መረዳዳቱ ለጊዜያት ዘልቋል።
ሰናይትን በቅርቡ የሚያውቋት ብዘዎች ራሷን ጠብቃ በመኖሯ ያደንቋታል።እንደ እኩዮቿ የፍቅር ጓደኛ ለመያዝ አለመቸኮሏ ለበርካቶች ምሳሌ ነው። እናቷን እየረዳች ኑሯቸውን ለማገዝ የምታደርገው ጥረትም የሚያስመሰግናት ሆኗል። ሰናይት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ካናዳ ለመጓዝ በሂደት ላይ መሆኗ ተሰምቷል።በወጣትነት ዕድሜዋ ወደውጭ መሄዷ ለቤተሰቦቿ እገዛ መሆኑን ዘመዶቿ ያስባሉ። የነገውን መልካም ህይወት እያለሙ በጎውን ሁሉ ይመኛሉ።
ተሻለ ሲሳይ በዚህ ግቢ ተወልደው ካደጉ ወጣቶች መሀል አንዱ ነው።ወላጆቹ እሱንና ወንድሞቹን አስተምረው ከቁምነገር ለማድረስ የአቅማቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። እሱም ቢሆን እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ትምህርቱን ሳያቋርጥ ዘልቋል።ጥቂት ቆይቶ ግን በጅምሩ መግፋት አልፈለገም። የነበረበት ዕድሜና የሚያዘወትራቸው ቦታዎች ለበርካታ ሱሶች አጋለጡት።
ይሄኔ ደብተር ይዞ ወደ ትምህርት ቤት መመላለሱ አስጠላው። ማጨስ፣ መቃምና መጠጣትን ምርጫው አደረገ።የዛኔ ለሱስ ፍላጎቱ ገንዘብ ያስፈልገው ነበር።ተማሪ ሆኖ ግን የሃሳቡን ማድረስ አልቻለም።እናም አማራጮችን ፍለጋ በሃሳብ ዋለለ።በወቅቱ የነበረው ዕድል በጉልበቱ ሠርቶ ማደር ብቻ ነበር።ውሎ አድሮ ተሻለ ከአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በኤሌክትሪክ ሠራተኝነት ተቀጠረ።
የሥራው መገኘት ለኪሱ ገንዘብ ማግኛና ለፍላጎቱ እርካታ ሆነለት።ደመወዙ ለጫትና ሲጋራ፣ለመጠጥና ለመዝናኛ በቂ ነበር። ባገኘው ሥራ ግን እምብዛም መዝለቅ አልቻለም።የድርጀቱን ሠራተኞች ለአመጽ አነሳስተሀል በሚል ከሥራ ተባሮ ቤቱ መዋል ጀመረ።ይሄኔ ብዙ የለመደው ወጣት ይጨንቀው፣ይጠበው ያዘ።በአንድ አጋጣሚ ግን የሰማው ማስታወቂያ ከጭንቀቱ ሊገላግለው ምክንያት ሆነ።
ወቅቱ ለፖሊስ ወታደራዊ ስልጠና ምልመላ የሚካሄድበት ጊዜ ነበር።ተሻለም ማስታወቂያውን አንብቦ በዕድሉ ለመጠቀም ፈጥኖ ተመዘገበ።አጋጣሚው አግዞትም የተቀመጡትን መስፈርቶች አልፎ ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተጓዘ።በማሰልጠኛ ተቋሙ ግን ከሁለት ወራት በላይ መዝለቅ አልቻለም።በአጋጠመው ድንገተኛ ህመም ቆይታውን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።
ተሻለ ከህመሙ ማገገም በኋላ ቤቱ ተቀምጦ መዋል ሰለቸው።አስቀድሞ የጀመረው የሱስ አመል ከእጁ ማጠር ጋር ተዳምሮ ሰላም ይነሳው ያዘ።ሁሌም በግቢያቸው ከሚሸጠው ጠላ ቤት ጎራ እያለ በሚጎነጨው አምሮቱ ብቻ መቀጠል አላሻውም። ኪሱን አርጥቦ ከቢራና ከአልኮሉ ለሚልበት ፍላጎቱ በቂ ገንዘብ ያስፈልገዋል።አንዳንዴ በተባራሪ የሚያገኘው ሥራ ለፍላጎቱ በቂ ባልሆነ ጊዜ በትካዜ ሲቆዝም ይውላል። እንዲህ ሲሆን ደግሞ በግቢው ጠላ ጉሮሮውን ማራስ ልማዱ ነው።
ሰናይትና ተሻለ እርስ በርስ ተደጋግፈው በቆሙት የቀበሌ ቤቶች ከተገኙት ወጣቶች መሀል ናቸው። ሁለቱም በቤተሰቦቻቸው ጥላ ስር ይኖራሉ።ወላጆቻቸው ዓመታትን በመተሳሰብ በገፉበት ግቢ እነሱም የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል።አሁን የሚገኙበት ዕድሜ አፍላ መሆኑ ደግሞ በተለየ ስሜት እያቀራረባቸው ነው።የሰናይት ጭምት ባህርይ የሁለቱን ግንኙነት ይፋ ማድረግ አላስቻለም። ያላትን መልካምነት ማጉደፍ ያለመፈለጓም ዕርምጃዋን በጥንቃቄ አድርጎታል።
ሰናይት እናቷም ሆኑ ሌሎች የሁለቱን ቅርበት እንዲያውቁት አትፈልግም።እሱ ግን ለማንም ግድ ሰጥቶት አያውቅም። የእሷን ፍላጎት ለመጠበቅ ሲል ግን ያለቸውን ሁሉ ለማድረግ ፈቅዷል።የሁለቱ ወጣቶች የፍቅር ግንኙነት ለብዘዎች ምስጢር ነው።በተለይ ሰናይትን ሁሉም ስለሚያምኗት ተደረገ ቢባል እንኳን የሚያምን አይኖርም።እነሱ ግን የሦስት ዓመታት የድብቅ ፍቅራቸውን ቀጥለዋል።
የተሻለ የስካር ልማድ ሰናይትን ሁሌም ያበሳጫታል። በቆዩባቸው ዓመታት ለውጥ ያለማሳየቱን ስታስብም ተስፋ ትቆርጣለች። ከቅርብ ጉዜ ወዲህ የሚያሳያት የተለየ ባህርይ ደግሞ እያሳሰባት ነው።ከሌላ ሴት ጋር ፍቅር መጀመሩን እየጠረጠረች በንዴትና በኩርፊያ ትብከነከናለች።ይህን ጉዳይ ለተሻለ ደጋግማ ልታስረዳው ብትሞክርም በምትለው ነገር አልተስማም።እንዲህ መሆኑም በሁለቱ መሀል ቅሬታ እንደፈጠረ ቀናት ተቆጥረዋል።
ግንቦት 22 ቀን 2002 ዓ.ም
በዚህ ቀን ተሻለ በግቢው ውስጥ ከሚገኘው ጠላ ቤት በረንዳ ላይ ሲጋራውን እያጤሰ ጠላውን ሲጠጣ ውሏል። ሰናይት ቀኑን ሙሉ በዚህ ሁኔታ እሱን በማየቷ ተበሳጭታለች። አጋጣሚውን ባገኘች ጊዜም ድርጊቱ ተገቢ ያለመሆኑን እያነሳች ልትመክረው ሞከረች። በጨዋታቸው መሀል መግባባት ጠፋ።ይህ ስሜት ደግሞ ሌላ ምክንያት እየጫረ ያወዛግባቸው ጀመር።
ሰናይት አጋጣሚውን ተጠቅማ ከሌላ ሴት ጋር ፍቅር ስለመጀመሩ አነሳችበት። ተሻለ ፈጽሞ ሊያምንላት አልቻለም። እንደውም ከእሷና ካነሳችው ጉዳይ ለመራቅ ከግቢው ወጥቶ ሌላ ቦታ ለመጠጣት ሄደ። ከነበረበት ሲነሳ በፕላስቲክ መያዣ ጠላውን አስሞልቶ ነበርና ይህን ስታይ ይበልጡኑ ተናደደች። በሆነው ሁሉም ስትበግንና ስትበሳጭ ቆየች።ያየችውን ለሰው ተንፍሳ እንዳይወጣላት ፍቅራቸው ድብቅ ነበር። በውስጧ ከማመቅ በቀር ምርጫው አልነበራትም።
ተሻለ ግቢውን ትቶ ከወጣ በኋላ ሰናይት የጣለችውን አብሲት ለማየት ወደቤቷ ገባች። ሰሞኑን እናቷ ወደ ሌላ አገር በመሄዳቸው ብቻዋን ከርማለች። ለደንበኞቿ የሚሆነውን ደረቅ እንጀራ በወቅቱ የማቅረብ ኃላፊነት አለባትና በጊዜ ገብታ መጋገር ይኖርባታል። ሰናይት ጋገራውን እያጋመሰች ሳለ የተሻለ እናት የሚሞቅ እንጀራ ሰላለ ስትጨርስ እንድታሞቅላቸው ነገሯት። ቃላቸውን አክብራ ያሉትን አደረገች። የእሳቸውን እንጀራ አሙቃ
እንዳስረከበች ተሻለ ከቆየበት እየተንገዳገደ ወደ ቤቷ ደረሰ። ከቀድሞው የበለጠ በመስከሩ በሁኔታው ተናደደች። በረንዳ ላይ ወንበር አወጣችለትና ሲጫወቱ አመሹ።
ጥቂት ቆይቶ ግን ተሻለ ወደ ቤት ገብቶ አብሯት ተቀመጠ። ይህ በሆነ አፍታ ጊዜ ውስጥም ሰናይት ለብሳው የቆየችውን ልብስ አውልቃ ፒጃማዋን ቀየረች። ጥቂት ቆይታም በገመድ የታሰረውን ፍራሽ ፈታ ከወለሉ ላይ አነጠፈች። የቀኑ የኩርፊያ ስሜት አሁንም አለቀቃትም። የተከራየችው የቪዲዮ ፊልም መጫወቱን ቀጥሏል።
ፊልሙ ምክንያት ሆኗቸው ለመነጋገር ቢሞክሩም ጨዋታቸው ሰላማዊ አልሆነም። ተሻለ ቀን ባነሳችው የጥርጣሬ ጉዳይ ላይ መወያየት ፈልጓል። እሷም ብትሆን ከእሱ ይበልጥ አምርራ ውሳኔዋን ልታሳውቀው ፈልጋለች። ተሻለ አሁንም የጥርጣሬዋን ምክንያት ደጋግሞ ጠየቃት። የሰማችውን ሁሉ ዋቢ አድርጋ መለሰችለት። አስከትላም ከዚህ በኋላ እሱን እንደማትፈልገውና ወደቀድሞው ጓደኛዋ ለመመለስ መወሰኗን በመሀላ አረጋ ገጠችለት።
ተሻለ ይህን ሲሰማ ንዴቱ ይበልጥ ጦፈ። «የአንተ ጉዳይ በቅቶኛል» ስትል መማረሯ አበገነው። በቅርቡ ወደውጭ ለመሄድ በሂደት ላይ መሆኗን ከተናገረችው ጋር አገናኘው። እንደዋዛ በአጭር ንግግርና ውሳኔ ልትርቀው መሆኑ ሲገባው ከነበረበት ተነስቶ አንገቷን አነቃት። ሰናይት እጆቹን በእጆቿ ለማላቀቅ የአቅሟን ሁለ ሞከረች። አልቻለችም። እሱ ግን ቀጠለ። ከትከሻዋ ጣል ያደረገችውን ሻርፕ በአንገቷ ላይ ደጋግሞ እያሰረ አጠበቀው።
ፍራሹ ታስሮበት የነበረውን ገመድ አንስቶም ትንፋሿ እስኪቋረጥ እያጠበቀ፣ እያላላ አነቃት። ይህ ብቻ አልበቃውም። ድምጿ እንዳይሰማ በአጠገቧ ያገኘውን ትራስ በአፏ ላይ ጭኖ አፈናት። በአፍንጫዋ መፍሰስ የጀመረው ትኩስ ደም የህይወቷን ህቅታ ሲያሳየው በዓይኖቹ ፊት ለፊት ወደሚታየው የልብስ ቁምሳጥን አማተረ። በሳጥኑ ውስጥ የሚጠቅሙትን ነገሮች እንደሚያገኝ ተማምኗል።
የቁምሳጥኑን ቁልፍ ለመክፈት አልዘገየም። እጆቹን ሰደድ ሲያደርግ የብር ማስቀመጫውን ተመለከተው። ከዚህ በፊትም በዚህ ስፍራ ገንዘብ እንደሚቀመጥ ጠንቅቆ ያውቃል። ጊዜ አልፈጀም። ሳጥን መሰሉን ማስቀመጫ በቢላዋ ለመፈልቀቅ ታገለው። አልተሳካላትም። የቢላዋው እጀታ ተቀንጥሶ ወደቀ። በንዴት ቢላዋውን ወርውሮ የቁምሳጥኑን መሳቢያዎች በረበረ። በአንደኛው ውስጥ አምስት ሺህ ብር እንደታሰረ አገኘ።
ብሩን ከኋላ ኪሱ አስቀምጦ የወደቀውን ሞባይል አነሳና ወደ በሩ አመራ። ዞር ሲል ሰናይትን በገመድና ሻርፕ እንደታነቀች ተመለከታት። በአፍና በአፍንጫዋ የፈሰሰው ደም መላ ፊቷን ሸፍኖታል። አላሳዘነችውም። በለበሰችው ፒጃማ ላይ ብርድ ልብሱን ደርብሎላት እየተጣደፈ ወጣ። የውስጠኛውን በር ሳይዘጋ የደጁን መዝጊያ ብቻ መለስ አድርጎም ወደቤቱ ገባ። ቤቱ ደርሶ ነጠላ ጫማውን ከቀየረ በኋላ ጓደኛው ቤት እንደሚያድር ተናግሮ ከአካባቢው ራቀ።
ግንቦት 23 ቀን 2002 ዓ.ም ማለዳ
መንጋቱን ለማብሰር ወፎች መንጫጫት ጀምረዋል። የግቢው ነዋሪዎች ወደ ጉዳያቸው ለማምራት መጣደፍ ይዘዋል። የሁሉም በሮች መከፈት የጀመሩት ገና በማለዳው ቢሆንም እስከአሁን የሰናይት ድምፅ አልተሰማም። የእንጀራ ደንበኞቿ በሩን ማንኳካት ቢጀምሩም የሰማቸው አልነበረም። ይህን ያስተዋለችው አንዷ ጎረቤት ደንበኞች ከደጅ እንዲመለሱ አልፈለገችም። እንደተለመደው የደጁን በር ከፍታ የተጠየቀችውን እንጀራ እየሸጠች ነው። የሰናይትን አለመኖር ከዛሬው የእናቷ መምጣት ጋር አያይዛ እሳቸውን ለመቀበል እንደወጣች ጠርጥራለች።
ሰዓቱ ረፈድ ብሎ ፀሐይ መውጣት ስትጀመር የሰናይት እናት ለቀናት ከቆዩበት አገር ተመልሰው ግቢያቸው ደረሱ። እንደወትሮው በራቸው ክፍት
ባለመሆኑ ቅር ያላቸው ይመስላል። ለጎረቤቶቻቸው ሰላምታ ካደረሱ በኋላ ስለሰናይት ጠየቁ። ጎረቤታቸው ከነጋ እንዳላየቻትና እንጀራውን ግን ስትሸጥ እንደቆየች ነገረቻቸው። እናት በሁኔታው ተገርመው ወደቤት ዘለቁ።
ልጃቸው ሰናይት ከወለሉ ከተነጠፈው ፍራሽ እንደተኛች አገኟት። ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በስሟ ተጣሩ። መልስ የለም። ብርድ ልብሱን ገልጠው ሊቀሰቅሷት ሞከሩ። ቢጃማዋን እንደለበሰች ነው። ከአንገቷ ላይ የተተበተበውን ሻርፕ ገመድና የፊቷን ላይ ደም ሲመለከቱ ሰፈሩን በአስደንጋጭ ጨኸት አደባለቁት።
ተሻለ ከቤቱ እንደወጣ በአካባቢው ከሚገኝ አንድ ግሮሰሪ አመራ። ሲጠጣ አምሽቶም አልጋ ይዞ አደረ። ሲነጋ ወደ ለገሀር በማምራት ወደ ሞጆ የሚያደርሰውን ሚኒባስ ተሳፈረ። ከከተማው እንደደረሰ ከአንድ ሆቴል አልጋ ይዞ ራሱን ሲያዝናና አደረ። እየጠጣ እያጨሰና እየቃመም ራሱን ለመርሳት ሞከረ።በኪሱ ያለው ገንዘብ እስኪያልቅ ያሻውን ለማድረግ ፈልጓል።
በእጁ የያዘውን ሞባይል መሸጥ እንዳለበት ያውቃል። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ሲም ካርዱን አውጥቶ በወራጅ ወንዝ ላይ ወረወረው። ወዲያውም በዚያው አካባቢ ከሚገኝ የኤሌክትሮኒክስ መሸጫ ሱቅ ሞባይሉን በሦስት መቶ ብር ሸጦ ገንዘቡን ያዘ። ቀጣዩን መዝናኛም አለመ። አሁን ወደ መቂ መሄድ እንዳለበት ወስኗል። በስፍራው ከበርካታ ሴቶች ጋር የመዝናናት ዕቅድ አለው። እንዳለው መቂ ደርሶ ለሁለት ቀናት ያሻውን ሲፈጽም ቆየ።
በሚቀጥለው ቀን ወላይታ ወደሚገኘው ታላቅ ወንድሙ ዘንድ ለመሄድ አስቦ መኪና ተሳፈረ። ወላይታ ካለበት ስፍራ ሲደርስ ወንድሙ መምጣቱን አይቶ ደነገጠ። ለምን እንደመጣ ተጠራጥሮ ሲጠይቀውም ለሥራ ጉዳይ መሆኑን ገለጸለት።
የፖሊስ ምርመራ
የግድያ ወንጀሉን መፈጸም ከስፍራ ደርሶ ያረጋገጠው ፖሊስ ከቴክኒከዊ ምርመራዎች በኋላ መረጃዎችን አሰባሰበ። ያገኛቸው መረጃዎች በሙሉ ወደ ተሻለ የሚያመላክቱ ነበሩ። የተሻለን መገኛ ለማወቅ ፖሊስ ከቤተሰቦቹ በቂ መረጃዎችን ሰበሰበ። የልጃቸውን መድረሻ የት ሊሆን እንደሚችል አልደበቁትም። ወላይታ ታላቅ ወንድሙ ዘንድ ሊሆን እንደሚችል የጠረጠረው ፖሊስ አስፈላጊውን ሁሉ አድርጎ ከዞኑ ፖሊስ ጋር በቅንጅት ተንቀሳቃሰ።
የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ አውጥቶ ወደስፍራው ያቀናው ቡድን በረዳት ሳጂን ግርማ ሞገስ እየተመራ በስፍራው ደረሰ።አስቀድሞ ያገኛቸው መረጃዎች ተጠርጣሪውን ወጣት በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችለው ነበር። ተሻለ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ ወንጀሉን ለመፈጸሙ አልካደም። ድርጊቱን መርቶ ለማሳየትም ፈቃደኛ ሆነ።
አሁን ፖሊስ በበቂ ማስረጃዎችና መረጃዎች ያጠናከረውን የወንጀል ሂደት ለክስ አዘጋጅቷል። በፖሊስ የመዝገብ ቁጥር 590/2002 የተመዘገቡት ፍሬ ሃሳቦች ተከሳሹን ለዐቃቤ ህግ ክስ አሳልፎ የሚሰጥ በመሆኑ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አምርቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለቀጠሮ ደርሷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
መልካምሥራ አ ፈወርቅ