ቅናትና መዘዙ

ይወዳታል ከልቡ። በሁለቱ መካከል ያለው የእድሜ ልዩነት ግን ፍቅሩን በአግባቡ እንዳያጣጥም አድርጎታል። አይደለም ወጣ ገባ ብላ ቤት ውስጥም ብትሆን አምሮባት ሲመለከት በቅናት እርር ድብን ይላል። ቅናት በተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር የሚችል ቢሆንም ለእርሱ ግን የሚወደውን ሰው ከማጣት ጋር የተያያዘ የስጋት እና ሽብር ስሜት ፈጥሮበታል፡፡

ይሄ የሽብር ስሜት በተለያዩ ምክንያቶች ቢፈጠርበትም የፍቅሩ መብዛት እያሰበ በቀላሉ ሊያልፈው ሲታገል ሰነባብቷል። አቶ ፍቃዱ ሽፈራው በፍቅሯ የወደቀላትን ሐረገወይንን አሰፋን እጁ ካስገባም በኋላ ምንም ልቡ ሊያረፍለት አልቻለም።

ወዳና ፈቅዳ የትዳር አጋሩም ብትሆን ቅሉ የእርሱ ልብ ግን ትታኝ ትሄዳለች በሚል ስጋት ተወጥሮ ትኩሱን ፍቅሩን እንዳያጣጥም እግር ከወርች አስሮታል። ይህ የቅናት ስሜት በሚፈጠርበት ወቅት ስሜቱን ለመግለፅ ቃላትን ሳይሆን ጉልበትን መጠቀም እንዲጀምር አድርጎታል። በግልፅ ስለጉዳዩ ከመወያየት ይልቅ ባለቤቱ ላይ ለዱላ ሲጋበዝ መታየት የተለመደ ሆነ፡፡

ቤት ውስጥ ተቀምጣ የምትውለው የትዳር አጋሩ ‹‹ምን እያደረገች ይሆን?›› በማለት ቀኑን ሙሉ እየተብሰለሰለ መዋል አልፎ ተርፎም ቀኑን ብቻ ሳይሆን ሌሊትም ኮርኒስ እየቆጠረ ነገር መብላት ሥራው ሆነ።

የሱ የቅናት ስሜት ከፍቅር የመነጨ ሳይሆን እምነት ከማጣት የመጣ እንደሆነ መረዳት ተስኖታል፤ እሷም ለትዳር አጋሯ ውሎዋን ለመናገር ወይም አንተ በሌለህበት ሰዓት የተፈጠሩ ነገሮችን እነዚህ ናቸው ማለት ከብዷታል።

በዚህ በመዘዘኛ ቅናት ምክንያት ባለቤቷ ለምግብ ያለው ፍላጎት ቀንሷል። እሷም በእርሱ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ ከገባች ሰነባብታለች። ባለቤቷ ወደቤት ሲገባ እንደ መደሰት ፈንታ በጭንቀት የልብ ምቷ የሚጨምርበት ሁኔታ ተፈጠረ።

እሱን ስታይ በጭንቀት ከልክ በላይ ያልባት ገባ። ጭንቀቱ ነው መስል ቶሎ ቶሎ መድከምም መገለጫዋ ሆነ። በመጨረሻም ቅናት ከትዳር አጋሯ ጋር ያላት ግንኙነት ላይ ክፍተት እየፈጠረ መጣ፡፡

አባወራው ይሄ ቅናት የዕለት ተዕለት ኑሮቸው ጋር እየተጋጨ መሆኑን ቢረዳም የምወደውን ሰው እያሳዘነ እና እየጎዳ እንደሆነ ቢገነዘብም ቅናቱ እርሱ ራሱን ከሚቆጣጠረው በላይ እሱ ተቆጣጥሮት ነበር።

የባልየው ቅናት ባለቤቴ በሥራ ብዙ ሰዓቷን የምታሳልፍ ወይንም ብዙ ጊዜዋን በማንበብ የምታሳልፈው ሆን ብላ ከእኔ ለመራቅ ብላ ነው በማለት በቅናት እርር ድብን ሲል ይታያል፡፡ ቅናቱም የፍቅር ግንኙነቱን እየሻከረ መምጣት ጀመረ።

ሰውየው ‹‹እርር ድብን ማለት አንገሽግሾኛል፤ ጨጓራዬን ልተፋው ነው፤ አንድ በሉኝ›› በማለት ወዳጅ ዘመዱን ቢያማክርም ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም። ውስጥ ውስጡን እየበላ ከቁጥጥር ውጭ ያደረገው ቅናትን ፈፅሞ ሊቆጣጠረው አለመቻሉ ከብዶታል። ይህ ቅናቱ ግን እጁን በእጁ ያስቀጥፈኛል ብሎ አስቦ አያውቅም ነበር።

የፍቅር መጀመሪያ ሰሞን

ወጣቷ ሐረገወይን አሰፋ በአንዲት አነስተኛ ካፍቴሪያ ውስጥ በመስተንግዶ ሥራ ትሰራ ነበር። የአርባ ስድስት ዓመቱ ጎልማሳ ፍቃዱ ሽፈራው ደግሞ ከሥራ መልስ በካፍቴሪያዋ ተቀምጦ ሻይ ቡና ማለት ልማዱ ነበር። ሐረግ ቆንጆ የምትባል ሴት አይደለችም። ይህ ነው የሚባል መልክ ባይኖራትም ዓይነ ግቡ ነበረች። ከልጅነቷ ጋር ተደምሮ ከፊቷ የማይጠፋው ፈገግታ ብዙ ተመልካች እንዲኖራት አድርጓታል።

ብቸኛ ሆና ኑሮዋን ለመርታት የምትታትረው ወጣት በእርጋታ ተቀምጦ ለረጅም ሰዓታት የሚመለከታት ትልቅ ሰውዬ ነገር ልቧን ከንክኖታል። በስህተት ሲቀር ዓይኗ ደጅ ደጁን ማማተር ከጀመረ ሰነባብቷል። ሲመጣም እሷ እንድትታዘዘው የመፈለጉ ነገር ማርኳታል።

እርጋታው ከልክ በላይ የሰውን ስሜት ይገዛል። ከእለታት አንድ ቀን ብዙም ተስተናጋጅ በማይኖርበት ሰዓት ወደ ካፍቴሪያው ጎራ ያለው ጎልማሳ ይችን የደም ገንቦ በነፃነት ለማናገር እድሉን አግኝቷል።

አጠገቡ እንድትቀመጥ ጋብዞ ጨዋታ የጀመረው ሰው ጨዋታ አዋቂ ጥርስ አያሰከድኔ የሚባል ዓይነት ሰው መሆኑ ደግሞ የሐረገን ልብ ይበልጥ አሸፈተው። ስለኑሮዋ በደንብ ከተረዳ በኋላ እሱ ጋር ሆና መማር እንደምትችል አባብሎ በእጅ በእግሯ ገብቶ ቤት ይወስዳታል።

ቤቱ ባስገባት በወራት ጊዜ ውስጥ ትምህርት ቤት ቢያስገባትም መውጣት መግባቷ ግን ጭንቅ ሆኖበታል። እሱ ከልቡ ስለሚወዳት ሁሉም ሰው በእርሱ ዓይን የሚያይበት እየመሰለው ሲጨነቅ ሲጠበበ ነበር የሚውለው።

ለባብሳ ትምህርት ቤት ስትሄድማ ከቁጥጥር ውጭ ይሆንና ስትገባ ስትወጣ በነገር መተክተኩን አላቆም ብሏል። እንደዛ በፍቅሩ ተረታ ቤቱ የገባቸው ወጣት ከዛሬ ነገ ያጠፋኝ ይሆን ወደሚለው ስጋት ውስጥ ለመግባት ሁለት አመታት አልተቆጠሩም ነበር። ትምህርቷን አቋርጣ ቤት ብትቀመጥም ልቡ ሊያረፍለት ያልቻለው አባ ወራ በድብቅ ይሰልላት ጀመር።

የስለላው መረብ ያጠመደው አሳ

በፊት የምትሰራበት ካፍቴሪያ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ተሰብስበው የሚጥሏት አነስተኛ እቁብ ለሐረገወይን ይደርሰታል። ለሁለት ዓመታት ያልተቋረጠው እቁብ ለሐረግ ስለደረሰ አንድ የሥራ ባልደረባዋ ገንዘቡን ሊሰጣት መኖሪያ ቤቷን አጠያይቆ ይመጣል።

በጥርጣሬ የእለት ከእለት ሥራው ሚስቱን መከታተል የሆነበት አባ ወራ የደጃፋቸውን መዝጊያ የሚቆረቁረው ወጣት ማን እንደሆነ ለመመልከት ጠጋ ከማለቱ ባለቤቱ በር ከፍታ እንግዳውን ሰው በፈገግታ ስትቀበለው ይመለከታል።

ልጁም በር ላይ ቆሞ ከባለቤቱ ጋር ሲያወራ ቆይቶ በፖስታ የያዘውን ነገር ሰጥቷት ሲመለስ ይመለከታል። የቅናት ዛር የጋለበው አባ ወራ በሩጫ ወደ ቤቱ ይገባና መጥቶ የነበረው ሰው ማን እንደሆነ ጠይቆ እንድታስረዳው እንኳን ፋታ ሳይሰጣት ይቀጠቅጣት ጀመር።

በእጁ ደብድቧት አልረካ ያለው አባ ወራ ወደ ምግብ ማብሰያው ክፍል በመግባት የአጥንት መከትከቻ መጥረቢያ በማምጣት የሚወዳት ሚስቱ ላይ የጭካኔ እጁን ያሳረፍባት ጀመረ።

የማለዳው የጭካኔ ምሳር

ወይዘሮ ሐረገወይን የምወደውን ሰው አገባሁ ብላ በሰላም ከምትኖርበት ቤቷ ውስጥ ፍቅር ይሁን እብደት በቅጡ ያለየ መንፈስ የነበረው ባለቤቷ በአሰቃቂ ሁኔታ በመጥረቢያ እየደጋገመ ይመታታል። ወደ ሥራ መሄዴ ነው ብሎ በጠዋት የወጣው ባለቤቷ በግምት ሶስት ሰዓት ከሰላሳ አካባቢ ተመልሶ እንደ እብድ ሲጮህ የምትይዘው የምትጨብጠው ነበር የጠፋት።

ለማምለጥም ይሆን ስለጉዳዩ አስረድታ ነገሩን ለማለሳለስ እድል ሳይኖራት በያዘው የሥጋ መከትከቻ አንገቷን፤ ትከሻዋን፤ ዓይኗ ስር፤ ክንዶቿን፤ ጭንቅላቷን በመምታት ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል።

ነገን ተስፋ አድርጋ ረጅም የትዳር ሕይወት ይኖረኛል ብላ ያለመችው ህልም ሳይፈታ በአጭሩ ተቀጨ። ልጅ ወልዳ ከብዳ ለወግ ማዕረግ እበቃበታለሁ ያለችው ቤት ውስጥ ሕይወቷን ከፈለች።

የሚስትየው የጣር ድምፅና የባልየው የጭካኔ በትር ጆሯቸውን የሳበው በበር የሚያልፉ መንገደኞች ጉዳዩ ፖሊስ ጆሮ እንዲደርስ ያደርጋሉ። ፖሊስም በፍጥነት በአካባቢው ሲደርስ ገዳይ የገደለበትን መሳሪያ እንደያዘ እጅ ከፍንጅ ይይዙታል።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ በ29/02/2015 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት ሶስት ሰዓት ከሰላሳ አካባቢ ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ አርሴማ አደባባይ ከሚባለው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤት ውስጥ ጩኸት እንደሚሰማ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ወደ ቦታው ይሄዳል።

ቦታው ደርሶ የአጥር በር ሲያንኳኳ የሚከፈትለት በማጣቱ በአጥር ዘሎ በመግባት የሆነውን አሰቃቂ ድርጊት ይመለከታል። ይህን ከባድ ሰው የመግደል ወንጀል የፈፀመውን ግለስብ ሰው ለመግደል ከተጠቀመበት መሳሪያ ጋር እጅ ከፍንጅ በመያዝ ወደ ማረፊያ ቤት ይወስደዋል።

የወንጀል አድራጊውን የእምነት ክህደት ቃል፤ የዓይን ምስክርነትንና ፤ የሕክምና ምርመራውን በማስረጃነት በማቅረብ አቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሰርት ይልካል።

የፌደራል አቃቤ ሕግ

ከሳሽ የፌደራል አቃቤ ሕግ ሲሆን ተከሳሽ ፍቃዱ ሽፈራው አያኖ እድሜ 48 የትምህርት ደረጃ አስራ ሁለተኛ ክፍል የሆነውን ግለሰብ ወንጀሉ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 539(1) (ሀ) ስር የተመለከተውን መተላለፍ ክስ መስርቶበታል።

አድራሻ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የቤት ቁጥር አዲስ ነዋሪ የሆነው ይህ ግለሰብ የትዳር አጋሩ የሆነችው ሟች ሐረገወይን አሰፋ የተባለችውን ከሌላ ወንድ ጋር ማግጠሽብኛል በሚል ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል።

የወንጀል ዝርዝር

ተከሳሽ ሰው ለመግደል የተጠቀመበት መሳሪያና ዘዴ እና አገዳደሉ ሁኔታ ሲታይ በተለየ ጭካኔና አደገኝነትን በሚያሳይ ሁኔታ 29/02/2015 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት ሶስት ሰዓት ከሰላሳ አካባቢ ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ አርሴማ አደባባይ ከሚባለው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የትዳር አጋሩ የሆነችው ሟች ሐረገወይን አሰፋ የተባለችውን ከሌላ ወንድ ጋር ማግጠሽብኛል በሚል ምክንያት ያለመግባበት መፈጠሩንና ያለመግባበቱ ሲካረር ምግብ ማብሰያ ክፍል ውስጥ ተቀምጦ የነበረውን የአጥንት መከትከቻ መጥረቢያ በማምጣት አንገቷን፤ ትከሻዋን፤ ዓይኗ ስር፤ ክንዶቿን፤ ጭንቅላቷን በመምታት ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል።

 ውሳኔ

 ከሳሽ የፌዴራል አቃቤ ሕግ ተከሳሽ ፈቃዱ ሽፈራው አያኖ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የነበረው ክርክር በ28/9/2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እንዲሁም ከሕዝባዊ መብቶቹ ለዘወትር እንዲሻር እንዲሁም በኤግዚቢትነት የተያዘው መጥረቢያ በሚመለከተው አካል እንዲወገድ ውሳኔ ተሰጥቷል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን   ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You