ዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን ነጥብ በመጋራት ጀምረዋል

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ለ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከትላንት በስትያ ምሽት የሴራሊዮን አቻውን ገጥሞ በአቻ ውጤት ተለያይተል። በጨዋታው ጫና ፈጥሮ ለመጫወት ዝግጅት አድርገው የነበሩት ዋልያዎቹ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ቢሆኑም ያገኙትን እድል ወደ ጎል መቀየር አልቻሉም። በዚህም ኳስና መረብ ማገናኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ተጫዋቾች እርስ በርስ መተያየት እስኪቸገሩ በጉም ተሸፍኖ በሞሮኮ ኤል አብዲ ስታዲየም በተካሄደው የመጀመሪያው 45 ደቂቃ የጨዋታ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ከእረፍት መልስም ስቴድየሙ ሙሉ በሙሉ በጉም በመሸፈኑ ሁለተኛውን 45 ለማስቀጠል ከሰላሳ ደቂቃ በላይ መጠበቅ አስፈልጓል።

ዋልያዎቹ በኢሱ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እየተመሩ ይህን ወሳኝ ጨዋታ ለማሸነፍ ቢዘጋጁም በጨዋታው የነበረው የአየር ሁኔታ እንዲሁም የወሳኝ ተጫዋቾች አለመኖር ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ይህን አስመልክቶ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታውን ለፊፋ ያሳወቀ ሲሆን በዚህ የአየር ሁኔታ ጨዋታ ሊቀጥል መደረጉ አግባብ አለመሆኑን እና ለቀጣይ ጊዜ መተላለፍ ቢኖርበትም አለመደረጉ ፍትሃዊ እንዳልሆነ በደብዳቤ ቅሬታውን ገልጿል። በተያያዘ መረጃ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቀጣይ ኢትዮጵያ ከቡርኪና ፋሶ የምታደርገው ጨዋታ ሰዓት ላይ ለውጥ እንዲደረግ ለፊፋ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ጉዳዩን እየተመለከተ እንደሆነ እና በፍጥነት ምላሽ እንደሚሰጥ ፊፋ አሳውቋል።

ቡድኑ የዓለም ዋንጫ ዝግጅቱን ያደረገው በመጪው ሳምንት እዚያው ሞሮኮ ላይ ከቡርኪና ፋሶ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ጭምር ሲሆን በተለየ አቀራረብ በተቃራኒ ሜዳ ላይ ጫና ፈጥሮ ለመጫወት ሞክሯል። የመፈራራት እና የመቀዝቀዝ ሁኔታን ያስመለከተው የመጀመሪያ አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከፍተኛ በሆነ ጭጋግ ታጅቦ ተመልካች የሚናፍቀውን ጨዋታ ሳያስመለክት ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመራ ግድ ብሏል። በዚህ ጨዋታ ክፍለ ጊዜ በስፍራው በነበረው ከፍተኛ የሆነ ጭጋግ ምክንያት ተጨዋቾቹን እንኳን ሜዳ ላይ ለማየት አዳጋች አድርጎት የሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ከግማሽ ሰዓት በላይ እንዲዘገይ አስገድዶታል። ይህ ሁኔታ በጨዋታው መቆራረጥን በመፍጠርም ውጤቱ ላይ ተጽእኖ እንዳሳደረም ታይቷል። በዚህም ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ወጥተዋል።

በዚህም ዋልያዎቹ ይህን ጨዋታ ጨምሮ ባለፉት ስድስት የነጥብ ጨዋታዎች አንድም ሳያሸንፍ ቀርቷል። ዋልያዎቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በቻን ዋንጫ በሊቢያ ሦስት ለአንድ ከተሸነፉ ወዲህ አንድም የነጥብ ጨዋታ ማሸነፍ አልቻሉም። በሊቢያ ከተረቱ በኋላ በ2023 አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በጊኒ ሁለት ለዜሮ እንዲሁም ሦስት ለሁለት በሆነ ውጤት በሁለት ጨዋታ ሽንፈት አስተናግደዋል። በተመሳሳይ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከማላዊ ጋር ካለምንም ግብ ከተለያዩ በኋላም በግብፅ ካይሮ ላይ አንድ ለዜሮ ተረተዋል።

ዋልያዎቹ በአዲሱ አሰልጣኝ ገብረመድህን በተቃራኒው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያለመሸነፍ ጉዛቸውን የቀጠሉበት ሆኗል። አሰልጣኙ እኤአ 2016 ላይ የዋልያዎቹ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆነው በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ አሁን የገጠማትን ሴራሊዮንና ሲሼልስን ማሸነፋቸው ይታወሳል። ከዓመታት በኋላ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ተመልሰው በቅርቡ ሲሾሙም ከሴራሊዮን ጋር በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ነጥብ በመጋራት የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ደምድመዋል።

ጫናን ፈጥሮና ተጭኖ ለመጫወት የተጫዋቾች በአእምሮ ዝግጁ አለመሆን የሚጠቀስ ችግር ቢሆንም በመታተርና ተሯሩጦ ለመጫወት የሚያስችል ዝግጅትን በማድረግ ወደ ስፍራው ያቀኑት፣ የዋልያዎቹ ተጫዋቾች የተስተዋሉትን ችግሮች በመቅረፍ ከቡርኪናፋሶ ይፋለማሉ። ሁለተኛውን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዋን በመጪው ማክሰኞ በተመሳሳይ ቦታና ሰዓት ይደረጋል። ዋልያዎቹ በዚህ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሴራሊዮን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጅቡቲ፣ግብፅና ጊኒ ቢሳው ጋር መደልደላቸው ይታወቃል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን   ኅዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You