የእናትነት ሚዛን

«የምፈልገው እናቴን መሆን ነው …» ትላለች የዛሬ የሴቶች አምድ እንግዳችን፤ ወይዘሮ ናርዶስ ተስፋሁን። ልጅ እያለች የእናቷን ጥንካሬ፤ እየተመለከተች በማደጓ ምንም ዓይነት የሕይወት ፈተና ቢመጣ ከእርሷ አቅም በላይ ሊሆን እንደማይችል ታምናለች።

ወይዘሮ ናርዶስ እናትነትን ለመግለፅ አንድ ቃል መምረጥ ቢኖርብኝ «ሁለንተና» የሚለውን ቃል እመርጣለሁ ትላለች። እናት እያንዳንዱ ቀኗ ቢታይ ብዙ ሥራዎችን ትሠራለች። ዘወትር የምታደርገው ቢታይ ነገሮችን የመለወጥ ሂደት ውስጥ እንደሆነች ማረጋገጥ ይቻላል። በየዕለቱ የቆሸሹትን ልጆቿን አጥባ ማፅዳት፣ ሲርባቸው መመገብ፣ ሲደክማቸው ማስተኛት፣የተዘበራረቀውን ማስተካከል፣ የቆሸሹትን ልብሶች ማጠብ፣ የከፋቸውን ልጆች ማጫወትና ባዶ የሆነውን መሶብ መሙላት፣ የመጀመሪያዋ የልጆች አስተማሪ የሕይወት መምህርት ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል።

እነዚህ ትንንሽ የለውጥ ሂደቶች ተደምረው ትልቅ ለውጦችን ይፈጥራሉ። የሚጠባ ሕፃን አድጎ መራመድ ይጀምራል፤ ሊነሳ ሲል ይጋጭ የነበረ ሕፃን አድጎ ድክ ድክ ይላል፤ አለፍ ብሎም ወንድምና እህት ለመሆን ይበቃል፤ እንግዲህ እናት ያሳደገችው ልጅ ከወንድም እና እህትነት አልፎ እርሱም ለወላጅነት ይታጫል።

እናት ነፍሰጡር ሆና ሳይቀር ሆዷ ውስጥ ያለው ልጅ ስለሚደርሰው የምግብ ንጥረ ነገር ሳይቀር ትጨነቃለች። ነፍሰ ጡር እናት ምሳ ስትበላ፣ የበላችው ለተረገዘው ልጅ ምግብ ሆኖ ይቀይረዋል። ታዲያ የምትመገበው ለሕፃኑ መሆኑን ስትረዳ የተሻለውን ለመምረጥ ትጥራለች። ለሕፃኑ ቀጥታ ቢሰጥ ከባድ የሚሆንበት ነገር ለልጁ በመጠኑ ቀይሮ የሚያስፈልገውን ምግብ በእናትየው ሰውነት በኩል ይሰጠዋል። ይሄ ደግሞ ልጆች እራሳቸውን ለመመገብ ብቁ እንዲሆኑ የሚያስችል የተፈጥሮ ጅማሮ የሚያስደንቃት መሆኑን ትናገራለች።

እርግዝና እና ሕፃናትን መንከባከብ ልጆችን የማሳደግ ትንሹ የእናትነት ክፍል ነው። እያንዳንዱ ህመም እና ሁሉም እንቅስቃሴ ከእናት ነፍስ ላይ እየተቀነሰ መሆኑ ሲታሰብ እናትነት ሁለንተናዊነት ነው ለማለት ያሰኛል ትላለች።

የወይዘሮ ናርዶስ አባት በሥራ ምክንያት ከቤተሰባቸው ተለይተው ክፍለ ሀገር ይኖሩ ነበር። ያኔ ሦስት ልጆቻቸውን የመንከባከብ ኃላፊነት የተጣለባቸው እናት፤ ባላቸው ከሚቆርጡላቸው ተቆራጭ በተጨማሪ በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው ልጆቻቸው ምንም ሳይጎድልባቸው ማሳደጋቸውን ስትመለከት ያደገችው ወይዘሮ ናርዶስ እናቷን በብዙ መልኩ የሕይወት መመሪያዋ አድርጋ ይዛቸዋለች።

« ሴት ያሳደገው እንዳንባል እየቀጣች፤ የእናት ፍቅር እንዳይጎድልብን እያቀፈች፤ ምንም ቢቸግራት ምሬት የሚባል ነገር ከአፏ የማይወጣ፤ እናቴን እሷን ስመሰል ውለታዋን መክፈል የምችል ይመስለኛል » የምትለው ወይዘሮ ናርዶስ፤ ለሰው ሁሉ የሚገባው የእናቷ ጥንካሬ ሦስት ልጆቻቸው ትምህርታቸውን በሥርዓት ተምረው ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ትናገራለች። የእናቴን ጥንካሬ ወርሼ ለልጆቼ እንደ ራሴ እናት ዓይነት እናት ለመሆን እተጋለሁ ትላለች።

የእናትነት መለኪያ የሆኑትን እናት ሆና ለመገኘት የምትታትረው ወይዘሮ ናርዶስ ተስፋሁን ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን በጥሩ ውጤት ያለፈችው ወጣት፤ አድማስ ዩኒቨርሲቲ ገብታ የመጀመሪያ ዲግሪ በአካውንቲንግ አግኝታለች። በተማረችበት የትምህርት መስክ ተቀጥራ እየሠራች ትገኛለች።

የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከያዘች በኋላ ባንክ ትሠራ እንደነበር ትናገራች። በሥራ ዓለም ብዙም ሳትቆይ ወደ ትዳር ከገባች በኋላ የመጀመሪያ ልጇን ወልዳለች። ከመኖሪያ ቤቷ ራቅ ያለ ቦታ ሥራ መመደቧ የተነገራት ከአራስነት ወደ ሥራ በተመለሰች በወራት ጊዜ ውስጥ ነበር። በዚህ የተነሳ ሥራውን ለቃ የግል ሥራ በማፈላለግ ከቤቷ አቅራቢያ ሥራ ፈልጋ ገብታ ልጇን በቅርበት እያየች ኑሯቸውን መግፋት ጀመሩ።

በዚህ ሁኔታ ልጇም ሳይጎዳ ሥራዋም ሳይበደል የቆየችው እናት፤ ከሁለት አመት በኋላ ሁለተኛ ልጇን ተገላገለች። የልጆች ቁጥር ሲጨምር ካለው የኑሮ ወድነት ጋር የኑሮ ጫናውን ከፍ ስላደረገው ሌላ ኑሮዋን ልትደግፍበት የምትችለውን አማራጭ መፈለግ ጀመረች።

ምን ብሠራ ይሻላል በማለት ስታወጣና ስታወርድ ዘመኑ በቸረው የቴክኖሎጂ ውጤት በዩ ትዩብ የተለያዩ እጅ ሥራዎች ከእነ አሠራራቸው ሲለቀቁ ተመለከተች። ዕለት ዕለት እየደጋገመች መመልከት የጀመረችው ናርዶስ ወትሮም ትወደው ወደ ነበረው የእጅ ሥራ ቀልቧ ተሳበ። ከዚያም ካላት የተጨማሪ ሥራ ፍላጎት ጋር ተደማምሮ ሥራዎቹን መሞከር ጀመረች። የእጅ ሥራዎችን ለመሥራት ስትነሳ የእውነት ተሳክቶ እንጀራዋ ይሆናል የሚል ግምት እንዳልነበራት የምትናገረው ወይዘሮ ናርዶሰ ሥራዎቹን በትክክልና በጥራት መሥራት መቻሏ ገበያው ውስጥ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት እንድታገኝ አድርጓታል።

መጀመሪያ ገበያ ለማግኘትና የተጠቃሚዎችን ፍላጎቶች ለመረዳት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ፎቶግራፍ በማስቀመጥ ሰዎች የሚያዟቸውን ሥራዎች መሠራት ጀመረች። ከቋሚ ሥራ ጎን ለጎን የተለያዩ ውበት ያላቸውን ሥራዎች በመሥራት የኑሮን ጫና ቀለል ማድረግ ቻለች።

የምትሠራቸውን እጅ ሥራዎች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እያስተዋወቀች ትዕዛዞችን እየተቀበለች በስፋት መሥራት ጀመረች። ሥራዎቿ ተወዳጅነት አግኝተው በርካታ ትዕዛዞችን መቀበል ጫና ቢፈጥርም እሷ ስታድግ ያላገኘችውን ለልጆቿ በማድረግ ለማሳደግ የግድ ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅባት በማመን በጥንካሬ ትሠራለች።

«ሕፃናት ልጆች ባሉበት ቤት ቋሚ ሥራ ኖሮ ትርፍ ሥራ ማሰብ የማይመስለ ነገር ቢሆንም መሰናክሎችን በማለፍ ለልጆች የተሻለ ነገር ለመስጠት እታትራለሁ» የምትለው ወይዘሮ ናርዶስ ለልጆቿ እናት፤ ለባለቤቷ ሚስት፤ ለመሥሪያ ቤቷ ትጉህ ሠራተኛ፤ ለደንበኞቿ ታማኝ አገልጋይ በመሆን የምትሠራ ሴት ናት።

«ባለቤቴ ዕቃዎችን በመግዛት፤ የተሠሩ ሥራዎችን ወደ ደንበኞች በማድረስ፤ እኔም ሥራ ላይ ስሆን ልጆቹን በመንከባከብ አጋርነቱን ያሳየኛል» ትላለች። ናርዶስ እንደምትለው በእጅ ሥራ የምትሠራቸው ሥራዎች በደንበኞች ትዕዛዝ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም በብዛት፤ በመስታወት የሚዋቡ የግድግዳ ጌጦች፤ በቃጫ የሚሠሩ ወንበሮችና ሳጥኖች፤ የተለያዩ በጨርቅ የሚሠሩ አበቦችን ትሠራለች።

ጊዜን ጠብቀው የሚፈለጉ ምርቶች ያሉ ሲሆን፤ በፍቅረኞች ቀን አካባቢ የስጦታ ሳጥኖች፤ በጨርቅ የተሠሩ የስጦታ ሳጥኖች ውስጥ የተሞሉ አበቦች ይፈለጋሉ። ለበዓላት ደግሞ እንደየ በዓላቱ የተለያዩ ጌጣጌጦች ትዕዛዝ እንደሚኖራት ታስረዳለች።

ገቢው ጥሩ የሚባል ዓይነት መሆኑን የምትናገረው ናርዶስ፤ ለምሳሌ አንድ የመስታወት ጌጥ ለመሥራት ከአንድ ሺ ብር አንስቶ እስከ አምስት ሺ ብር ድረስ ይጠየቅበታል ትላለች። በዓላትን አስታከው የሚሠሩ የበዓል ጌጣጌጦችም በመጠናቸውና በዓይነታቸው ዋጋ ወጥቶላቸው በብዛት እንደሚሸጡ ትናገራለች፡፡

በሥራው ላይ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉ የምትናገረው ወይዘሮ ናርዶስ፤ ገበያው ላይ አስፈላጊ ግብዓቶችን ማጣት፤ የመሥሪያ ቦታ ከመኖሪያ ቤት ጋር አብሮ መሆኑ፤ ሰዎች የእጅ ሞያ ውበት እንዳለው ሁሉ በቀላሉ የሚሠራ የሚመስለቸው መሆኑ፤ የተሠሩት ሥራዎች ደንበኞች ጋር ሳይደርሱ መሰበርና ሌሎች ጉዳዮች ሥራውን እንደሚያከበዱት ታብራራለች።

« እኔ የኑሮን ሸከም ለማቅለል በቀላሉ የጀመረኩት ሥራ በስፋት የሚሠራ በደንብ ቢያዝ ራሱን የቻለ ገቢ ሊያስገኘ የሚችል መሆኑን ተረድቻለሁ» የምትለው ወይዘሮ ናርዶስ ሥራ የለንም ብለው እጃቸውን አጣጥፈው በየቤታቸው የተቀመጡት ሴቶችም መሥራት የሚችሉትን ነገር በማሰብ ራሳቸውን በገንዘብ አቅም መደገፍ የሚገባቸው መሆኑን ታስረዳለች።

«በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሴቶች ጫና የሚበዛባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በመሆናቸው በትምህርትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች በመደገፍ ማበረታታት ያስፈልጋል።» የምትለው ወይዘሮ ናርዶስ፤ ሌሎች ዕድሉን እስኪሰጡ ድረስ መጠበቅ ግን የማይደገፍ ሃሳብ መሆኑን ታብራራለች።

አንዲት ሴት እራሷን ከተለያዩ ጫናዎች ለማላቀቅ በገንዘብ አቅም እራሷን ማሳደግ ተቀዳሚ ተገባሯ ሊሆን እንደሚገባ ትናገራለች። በገንዘብ አቅም ራስን ለማሳደግ ደግሞ መሥራት የምትችለውን ነገር በማሰብ በቀላሉ ለመነሳት መጣጣር አስፈላጊ መሆኑን ትናገራለች።

ለወደፊት ሥራዋን በስፋት የመሥራት ዕቅድ እንዳላት የምትናገረው ወይዘሮ ናርዶስ፤ በሥራዋ ሌሎችን ቀጥራ በማሠራት የራሷንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት ለማሻሻል እንደምትሠራ ገልፃለች። «አሁን ከምሠራቸው ጌጣጌጦች በተጨማሪ ችግር ፈቺ ፈጠራዎች ላይ ትኩረቴን በማድረግ ለመሥራት እቅድ አለኝ። ይህንን ህልሜን እውን ለማድረግ ደግሞ ዛሬ ላይ የቆምኩበትን መደላድል አጠንክሬ እሠራለሁ» ብላለች።

ከዚህም በተጨማሪ በቀጣይ ሌሎች ምንም ነገር ሳይኖራቸው እጃቸውን አጣጥፈው ለተቀመጡ ሴቶች እሷ የምትሠራውን ሥራ ላይ ሥልጠና በመስጠት ራሳቸውን የሚችሉበት መንገድ ማሳየት እንደምትፈልግ ተናግራለች።

«አብዛኞቹ ሴቶች ከመሥራት ይልቅ እጃቸውን ለመፅዋት ሲዘረጉ እመለከታለሁ፤ ይህ ደግሞ በተለይ መሥራት ለሚችል ሰው ፀያፍ ተግባር ነው» የምትለው ወይዘሮ ናርዶስ፤ እርዳታን ከመጠበቅ ይልቅ የተለያዩ የሥልጠና ዕድሎችን በመጠቀም ሕይወታቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጡ ለማድረግ የምትሠራ መሆኑን ገልፃለች።

የተዋቡ ጌጣ ጌጦችን ፈጣሪ፤ ካፊቴሪያዎችና የባህል ቤቶች በቃጫ የተሠሩ ወንበሮች አቅራቢ፤ የሁለት ልጆች እናት የሆነችውን የጥንካሬ ተምሳሌት የሃያ ዘጠኝ አመቷን ወጣት ናርዶስ ተስፋሁንን ያሰብሽው ይሰካልሽ በማለት የዛሬ ቆይታችንን አብቅተናል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን   ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You