የጓደኝነትን የፍቅር ገመድ የበጠሰች ቅፅበት

በልጅነት ፍቅር ተጫውተው ቦርቀው ነበር አብረው ያደጉት። ከጎሬቤታሞቹ ወላጆቻቸው ቅርበት የተነሳ እንደ ወንድማማች ነበር የሚተያዩት። አብረው አፈር ፈጭተው፤ ያደጉቱ ሕፃናት ከፍ ሲሉ ለእረኝነት ከብቶቻቸውን ይዘው የወጡትም አብረው ነበር።

ለእረኝነት ሜዳ ሲውሉ ልፍያቸው ጫወታቸው ሳቃቸው ሌሎችን ያስቀና ነበር። አንዱን ያለ አንዱ መመልከት እጅግ በጣም ይከብድ ነበር። የተቋጠረላቸውን ስንቅ ተካፍለው እየበሉ፤ ከብቶቻቸውን አሰማርተው በሜዳ በገደሉ ሲቦርቁ ነበር ያደጉት። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በአቅራቢያቸው ወዳለው የቀለም ትምህርት ቤት አብረው ገብተው እስከ አራተኛ ክፍል ተምረዋል። ልክ አካላቸው ጠንከር ሲል ነበር ከተማ ሄደው የመስራትን ሀሳብ ያመጡት።

ይህን ሀሰባቸውን ለማሳካት የሚችሉበት እቅድ ሲያወጡና ሲተውት የሰነበቱት ታዳጊዎቹ አንድ ከተማ ቆይቶ የመጣ አብሮ አደግ የጎረቤታቸውን ልጅ ያገኙታል። እነሱም እንደሱ ከተማ ሄደው መስራት እንደሚፈልጉ ነግረውት ተስማምተው ከወላጆቻቸው ጋር ተማክረው መልስ ለመስጠት ቀን ይቃጠራሉ። ሁለቱም በየግላቸው ወላጆቻቸውን ከተማ መሄድ እንደሚፈልጉና አብረው እየኖሩ መስራት እንደሚፈልጉ ሊያሳምኑ ታገሉ። እድሜያቸው አስራ አራት ዓመት ቢሆንም የሰውነታቸው መቀጨጭ ግን ከእድሜያቸው በታች ያስመሰላቸው ነበር።

ይህን የተመለከቱት ወላጆች ‹‹አንድ ሁለት ዓመት ቆይታቸሁ እድሜያችሁ ሲጠና ትሄዳላችሁ›› ቢሏቸውም ሀሳባቸውን መቀየር እንደማይፈልጉና አይሆንም ካሏቸው ጠፍተው ወደ አዲስ አበባ እንደሚሄዱ ለወላጆቻቸው ቁርጥ ባለ አንደበት ተናገሩ። ሀሳባቸውን ካልለወጡ ጠፍተው ከሚሄዱ ቀድሟቸው ከተማ ከገባው ከሰፈራቸው ልጅ ጋር አድርገው ያላቸውን ቋጥረው፤ ከመቀነታቸውም ላይ ያገኙትን አስጨብጠው ቸር ይመልሳችሁ ብለው መርቀው ወደ አዲስ አበባ ያሳፍሯቸዋል። ቀድሞ ቤት ተከራይቶ ከነበረው የጎረቤታቸው ልጅ ጋር ትንሽ እረፍት ካደረጉ በኋላ ልዩ ስሙ ካራ በሬ ተራ የሚባል አካባቢ የሸክም ስራ እየፈለጉ መስራት ጀመሩ።

ጋደኛሞቹን ያቃቃረቻቸው ገጠመኝ

በእርሱ ፍቃድ አሳዬ እና ሳሙኤል አድነው ተመስገን ከተወለዱባት ቀዬ ከወጡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋጩት። አንድም ቀን ክፉ ደግ ሳይነጋገሩ ያገኟትን ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው በመላክ በሰላም ይኖሩ ነበር። ስራ ሰርተው እህል ቢጤ አፋቸው ላይ የሚጥሉባት አንዲት ምግብ ቤት ነበረች። የምግብ ቤቷ ባለቤት ፍቅራቸውን እያዩ እንዳይለያዩ እየመከሩ የሰሩበትን ብርም እንዳያጠፉ የቀን እቁብ ይጥሉላቸው ነበር። ልጆቹም ከሞቀ ቤታቸው ከወጡ በኋላ እንደ እናት የሚንከባከባቸው ሰው በማግኘታቸው የዘውዴ ቁርስ ቤት ቋሚ ደንበኛ ሆኑ።

እንዲህ እንዲህ እያሉ ከቆዩ በኋላ ከእለታት አንድ ቀን የምግብ ቤቷ ባለቤት እማማ ዘውዴ የምትረዳቸው ሰራተኛ ያመጣሉ። ልጅቷ ከመጣች በኋላ የጓደኛሞቹ ውሎ አዳር እዛው ቤት ውስጥ ሆነ። ልጆቹ አዲሷን ልጅ ወደዋታል። ሁለቱም የራሳቸው ለማድረግ እንቅልፍ አጥተው ያስባሉ። ማልደው ወደ ምግብ ቤቱ እየሄዱ ይመለከቷታል። ልባቸው ልጅቷን ቢወዳትም ቃል አውጥተው አልተነጋገሩም ነበር። ሁለቱም ለመነጋገር ተፋፍረው ወራትን አሳለፉ። አንድ ቀን ግን ሳሙኤል በድፍረት ልጅቷን እንደወደዳትና የእሱ ሊያደርጋት እንደሚፈልግ ለአብሮ አደጉ በእርሱ ፈቃድ ይነግረዋል።

በእርሱ ፈቃድ ደግሞ እኔ እንደወደድኳት ስላወክ ነው፤ ልትመቀኝ ፈልገህ ነው በማለት አንድ አንድ ሲባባሉ ቆይተው ለምሳ ወደ ምግብ ቤቷ ይሄዳሉ። ከተዋወቁ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጣሉት ጓደኛሞች ተኮራርፈዋል። ምግብ ቤቷ እንደደረሱ እማማ ዘውዴ ባለመኖራቸው ሁለቱም ልጅቷን ለማነጋገር ቆረጡ። ምሳ አዘው እየበሉ እያለ ነበር ̋ በሱዬ ብላ ̋ የሚል ቃል ከልጅቷ አፍ የወጣው። ይህን ግዜ ሳሙኤል ቀድሞኝ ነግሯት ይሆናል በሚል በቅናት ጨሰ። እየበላ የነበረውን ምግብ አቋርጦ ወደ ደጅ ወጣ።

ስሙ በቁልምጫ መጠራቱ የልብ ልብ የሰጠው በእርሱ ፈቃድ ግን ቁጭ ብሎ ምሳውን ከጨረሰ በኋላ በኩራት ቆመው የሚያሰራቸው ሰው የሚጠብቁበት ቦታ ሄደ። የበእርሱ ፈቃድን መምጣት የተመለከተው ሳሙኤል ንዴቱን መቆጣጠር አቅቶት የጓደኛውን አንገት አንቆ ይደበድበው ጀመር። ድብድባቸውን የተመለከቱ ሰዎች መሀል ገብተው ከገላገሏቸው በኋላ የተለያዩት ጓደኛሞች የሚሸከሙት ነገር አግኝተው በየፊናቸው በረሩ።

የእማማ ዘውዴ አዲሷ ረዳት

ባዩሽ ትባላለች። ከወሎ አማራ ሳይንት አካባቢ ነው የመጣችው። አጠር ጎረድረድ ያለች ቆንጆ ልጅ ናት። አማማ ዘውዴ ለቅሶ ለመድረስ ወደ ትውልድ ሀገራቸው በሄዱበት ወቅት ነበር የተመለከቷት። ባዩሽ ለቀስተኛውን ልታስተናግድ ተፍ ተፍ ስትል አይናቸው የገባችው እማማ ዘውዴ ̋ ይችን ልጅ ወስጄ ላስተምራት ̋ በማለ ት ወላጆቻን ያስፈቅዳሉ። ልጅቷ ገና ከማደጓ አይን የምትገባ ልጅ በመሆና የተነሳ ስጋት የገባቸው ወላጆች ልጅቷ ከሰፈሩ ጎረምሶች አይን ተርፋ ትምህርቷን መማር ከቻለች በሚል ያለ ምንም ቅሬታ ነበር የፈቀዱት። ወላጆቿ አዲስ አበባ እንድትሄድ የፈቀዱላት ወጣት ስታልመው የኖረችውን የከተማ ኑሮ ልታገኘው እንደሆነ በማሰብ በደስታ ስትፈነጥዝ ሰንብታ ከእማማ ዘውዴ ጋር ወደ አዲስ አበባ መጣች።

ለቀጣይ ዓመት ትምህርት ቤት እንደምትገባ የተነገራት ባዩሽ እማማ ዘውዴን በሙሉ ልቧ ለማገልገል ቆርጣ ተነስታለች። ማልዳ ተነስታ የቁርስ ቤቷን አጸዳድታ የሚሰራውን በፍጥነት ትሰራለች። ተስተናጋጆች ሲመጡም በፈገግታ ተፍ ተፍ የምትለው ወጣት የተመጋቢውን አይን ይዛለች። ምግብ ለመመገብ ከሚመጣው ተስተናጋጅ በተጨማሪ ልጅቷን ለመመልከት የሚመጡት ደንበኞች የእማማ ዘውዴን ቤት ሞቅ ሞቅ አድርገውታል። ይቺ የቤታቸው ድምቀት የሆነችውን የዘመዳቸውን ልጅ እንዳትበላሽባቸው በመስጋት በአይናቸው ቢከታተሏትም በእሷ ምክንያት ገበያው መድራቱን ወደውታል።

ባዩሽም ተጠቃሚው እየተንጋጋ ቤቱን ቢሞላም ከስራዋ ባሻገር ምንም አይነት የተለየ እንቅስቃሴ አታደርግም። ከደንበኞቻቸው ሁሉ ግን በተለየ አይን ሁለት የማይለያዩ ጓደኛሞችን ትቀርባቸው ነበር። ሁለቱ ጓደኛሞች ወንድሞቿ ስለሚመስሏት ሲመጡ ልቧ በደስታ ጮቤ ይረግጥ ነበር። በዛች በተረገመች ቀንም የበእርሱ ፈቃድ ስም አፏ ገብቶ ጠራችው እንጂ ለሁለቱም አንድ አይነት ስሜት ነበር የሚሰማት።

የሳሙኤል አኩርፎ መሄድ ቢከነክናትም ከቅርበታቸው የተነሳ የከፋ ፀብ ላይ ይደርሳሉ ብላ አላሰበችም። በእለቱ እንዲያ እየተሳሳቁ የሚመገቡት ጓደኛሞች መኮራረፋቸው ቢያስጨንቃቸው ልታባብላቸው ፊታቸው መመላለሷ በእርሱ ፈቃድን መጥራቷ ነበር እንግዲህ የጠባቸው መነሻ።

ልብ ሰባሪው ጥቃት

በሱ ፈቃድ እንዴት ይመታኛል እያለ ቢያጉረመርምም የትናንት ጓደኝነታቸውን እያሰበ ይቅርታ ሊያደርግለት እየዳዳ ነበር የተሸከመውን እቃ አድርሶ ሲመለስ እያሰላሰለ የቆየው። ሳሙኤል ግን ከሸክሙ ሲመለስ ወደ ሚያድሩበት ቤት በመሄድ ደብቆ አስቀምጦት የቆየውን ጩቤ ይዞ መጣ። የጓደኛውን መምጣት የተመለከተው በእርሱ ፈቃድ ይቅርታ እንዲጠይቀው በማሰብ ፊቱን ዞር ያደርጋል። ወትሮም ለጥቃት ተዘጋጅቶ የመጣው ሳሙኤል ጀርባ የሰጠውን ጓደኛውን ከጀርባ በኩል በያዘው ጩቤ ይወጋዋል። ያላሰበው ጥቃት የደረሰበት በእርሱ ፈቃድ ፊቱን ወደ ጓደኛው አዙሮ ሲወድቅ ከፊት ደረቱ አካባቢ ይደግመዋል።

ያኔ ወዲያው መተንፈስ ያቃተው በእርሱ ፈቃድ ለመሞት ያጣጥር ጀመረ። ይህን የተለመለከተው ጓደኛው በድንጋጤ የሚያደርገው ጠፍቶት እግሩ ወደ መራው አቅጣጫ መሮጥ ጀመረ። ቦታው ላይ የደረሱት ሰዎችም ለእርዳታ ቢረባረቡም የወጣቱን ሕይወት ግን ማትረፍ አልቻሉም ነበር። ተወልደው ካደጉባት ቀዬ አብረው የተሰደዱት ጓደኛሞች በማይረባ ነገር እስከ ነፍስ መጠፋፋት ደረሱ። አብረው የማደግ ሕልማቸው በዛች ቅፅበት ጠፋ። አንዱ ከዚች ዓለም በሞት ሲለይ አንደኛው ደግሞ ማረፊያው ወህኒ ሆነ።

የፖሊስ ምርመራ

የሰውን መሰባሰብ የተመለከተው የሕግ አካል በአካቢው በፍጥነት በመገኘት ሲመለከት የሆነውን ያያል። ወንጀሉን የፈፀመው ማን እንደሆነ አጣርቶ ሲፈልግ በድንጋጤ ሮጦ መግቢያ ያጣው ሳሙኤል ወንጀሉ ከተፈፀመበት ቦታ ብዙም ሳይርቅ በሚገኘው የመድሀኒዓለም ቤተክርስትያን ተቀምጦ ሲያለቅስ ያገኘዋል። አብሮ አደጉን ለአንዲት ልጅ ሲል እንዳጠፋው ሲያስብ ፀፀት እንደ እግር እሳት እያንገበገበው የሚያነባው ወጣት በፖሊሶች ቁጥጥር ስር ሲውል እራሱን ስቶ ነበር።

በግልፍተኝነት ያደረሰው ጥቃት ሁለቱን የሚከባበሩ ጎረቤታሞች ወላጆቻቸውን ደም የሚያቃባ መሆኑን ሲያስበው ሁሉ ነገር ከአቅሙ በላይ ሆኖበት በሀዘን ተቆራም ዷል። ፖሊስ ገዳዩን ሳሙኤልን ይዞ ሟቹን በእርሱ ፈቃድን ለአስክሬን ምርመራ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆሰፒታል ሚሊንየም የሕክምና ኮሌጅ የፎረንሲክ ሕክምናና ምርመራ ክፍል በመላክ አስክሬኑ እንዲመረመር ያደርጋል። ፖሊስም የአይን እማኞችን ቃል፤ የገዳይን የእምነት ክህደት ቃል፤ የአስክሬን ምርመራውን ውጤት አንድ ላይ በማጠናቀር ክስ እንዲመሰርት ለአቃቤ ሕግ ይልካል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ

ከሳሽ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሲሆን ተከሳሽ ሳሙኤል አድነው ተመስገን እድሜ 16 አድራሻ የካ ከፍለ ከተማ ወረዳ 13 የቤት ቁጥር ተከራይ መሆኑን በክስ አቀራረቡ ላይ ተመልክቷል። ወንጀሉ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 540 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ ሲሆን ወንጀሉም እንደሚከተለው በዝርዝር ቀርቧል።

የወንጀሉ ዝርዝር ተከሳሹ ሰውን ለመግደል አስቦ በቀን 1/5/13 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ክልል ልዩ ቦታው ካራ በሬ ተራ አካባቢ። ሟች በሱፍቃድ አሳዬ ጋር ተጣልቶ ከተገላገሉ በኋላ ወደ ቤቱ ሄዶ ጩቤ በማምጣት በግራ በኩል ጀርባውን እንድ ጊዜ ወግቶ ጥሎታል። በመቀጠልም ደረቱ ላይ በስለት ይወጋዋል። የስለት ውጊያ ጉዳት በማድረሱ ምክንያት ሳንባው ላይ የመበሳት ጉዳት ደርሶ ደም በመፍሰሱ ምክንያት በእለቱ ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጎታል። ያደረገው ድርጊትም ሆን ብሎ የተፈፀመ ሲሆን አቃቤ ሕግም በፈፀመው ተራ ሰው የመግደል ወንጀል ከሶታል።

 ውሳኔ

 ተከሳሽ ሳሙኤል አድነው ተመስገን በተከሰሰበት ተራ ሰው የመግደል ወንጀል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በ 1/2/2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስና ማስረጃውን አገናዝቦ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቶታል። ተከሳሹ ሆን ብሎ በፈፀመው ተራ ሰው የመግደል ወንጀል በአስር ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።

 አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ህዳር 1/2016

Recommended For You