የ15 ዓመት ጥያቄ ለ25 ዓመታት በረከት

በርካታ ዓመታትን በጎዳና ላይ አሳልፏል፤ ብርድና ሀሩሩ፤ ተባይና ነፍሳቱ ሲያሰቃዩትም ከርሟል። በሽታው ደግሞ ከዚህም ይለያል። ለወራት ያህል የአልጋ ቁራኛም ሆኖ ሰንብቷል። አንዳንዱ ስቃዩ አሳዝኗቸው ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ተጸይፈውት ነጋ ጠባ ሰዎች ሞቱን ሲሹለትም ነበር። በዚህ ስቃይ ውስጥ የነበረው ይህ ብርቱ ሰውም አንድ ቀን አምላኩን አንድ ነገር ለመነ። ይህቺም ዕለት ደግሞ በጠና የታመመባት ነበረች።

‹‹አምላኬ ሆይ ሙሉ አካል ኖሮኝ ፤ ሙሉ ጤና ሰጥተኸኝ የተቸገሩትን አይቼ አላልፍም። ስለዚህም እኔ ስቸገር ሰዎች ሊደርሱልኝ አልቻሉም። እናም ደራሼ አንተ ብቻ ነህና ጤናዬን መልስልኝ። የ15 ዓመት እድሜን ብቻ ጨምርልኝ። በዚህች የእድሜ ጭማሬ ላይም ወገኔን ላገልግል›› ሲልም ነበር የወደቁትን አንሱ የነደያን መርጃ ማህበር መስራች አቶ ስንታየሁ አበጀ ልመናውን በእንባ ጭምር ወደ አምላኩ ያቀረበው።

አቶ ስንታየሁ ጤናው ሲመለስለት ነገ የገባሁትን ቃል አከብራለሁ፤ ዛሬ ራሴን ልለውጥ አላለም። ልክ ገና ከሕመሙ እንዳገገመ ነው ቃሉን በተግባር ለመለወጥ ሥራውን አሀዱ ያለው። ትናንት እርሱ የነበረበትን ሕይወት ሌሎች እንዳይኖሩት ለማድረግ ከሚኖርበት አካባቢ ነበርም ሥራውን የጀመረው። የሚኖርበት አካባቢ አዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሽሮ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ሲሆን፤ ሰዎችን ከወደቁበት አንስቶ አጥቦና አልብሶ በተቻለው ሁሉ መመገብ ነበር። ሰዎችን የሚሰበስብበት ቦታ ግን አልነበረውም። እናም አረጋዊያንን ቢያነሳቸውም የሚያስቀምጥበት ቦታ የት መሆን እንዳለበት ያውጠነጥን ጀመር።

በመጨረሻም አንድ ሃሳብ ላይ ውሳኔውን አሳረፈ። በአቅራቢያው የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አለችና የመቃብር ባለቤቶችን ቤት በማስፈቀድ አረጋውያኑን፣ ሕሙማኑን፣ አካል ጉዳተኛውን ለማሰባሰብ አሰበ። አስቦም ብቻ አልቀረም ፤ ፈቃዱን አገኘና ወደ ተግባሩ ገባ።

የአቶ ስንታየሁ ጥንካሬና ቃል አክባሪነት የሚታየው ማህበሩን ሲጀምረው የነበረው ሁኔታ ነው። ለሦስት ወር የአልጋ ቁራኛ ከመሆኑ በፊት ያጠራቀማትን ስምንት ሺህ ብር ይዞ ሥራውን ለመጀመር ነበር ሃሳቡ። ሆኖም ያጠራቀመው ብር ጥቅም ላይ የሚውል አልሆነለትም። ምክያቱም ታማሚ ስለነበር የብር ማስቀመጫው ፍራሹ ሥር ስለነበር በሥርዓት ባለመቀመጡ የተነሳ ከጥቅም ውጭ ሆኗል፤ ሻግቶም አገልግሎት የሚሰጥ አልነበረም። ከዚህ ውስጥ ደህና ሆና የተገኘችው ሁለት ብር ብቻ ናት። ሁለት ብር ምንም ማድረግ አይችልም።

ለትናንቱ እድሜ ለማኝ ለዛሬው ቃል ተርጓሚ ሰው ግን ሁለት ብር ዋጋ ነበራት። የውኃ መቅጃ ጀሪካን ተገዝቶባት ለብዙ አቅመ ደካሞች ንጽህና መጠበቂያ ውኃን ማመላለሻ ሆናለች። ብዙዎችን ከውሃ ጥምና ከርሃብ መታደግ እንዲቻልባት እድል ሰጥታለች። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ዓመታት ቢገፉም ዘለቄታዊነቱ ግን በብዙ መልኩ እንዲፈተን ሆኗል። አንደኛው የማኅበሩ ሕጋዊ ዕውቅና ጉዳይ ሲሆን፤ ይህንን ከብዙ ድካምና ልፋት በኋላ በ1990 ዓ.ም. አሳክቶታል።

‹‹ከሕመሜ ከተፈወስኩኝ ጧሪ ቀባሪ ያጡትን አረጋውያን፣ ሕሙማንና አካል ጉዳተኞችን በቀሪው የሕይወት ዘመኔ አገለግላለሁ›› የሚለው ቃሉም እስከዛሬዋ ዕለት በመፈጸም ላይ የሚገኘው ስንታየሁ፤ ሁሌም ተስፈኛ ነው። ትናንት ማህበሩን ሲመሰረት እንኳን ብዙ ካፒታል ሳይኖረው ማህበረሰቡን አጋሮቹ እንደሚሆኑ አምኖ ዛሬን አይቷል። ነገም ቢሆን በዚህ መልኩ እንደሚቀጥል ያስባል። ምክንያቱም እርሱ 15 ዓመት ቢጠይቅም 25 ዓመታትን ተችሮት የማህበሩን የኢዮቤልዮ ዓመት እንዲያከብር አድርጎታል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙ ነገሮችን መለወጥ ችሏል።

ለአብነት ትናንት በሁለት ብር በገዛት ጀሪካን ውኃ በአካባቢው ካለ ወንዝ በማመላለስ የአረጋዊያኑን ገላ፣ ልብሳቸውን ያጥብ ነበር። የሚውሉበትን የሚያድሩበትን ቤት ያጸዳልም፤ ከሕዝብ የተሰበሰበውን ምግብ በማቅረብና በመመገብ ቃሉን በተግባር ይተረጉምም ነበር። ዛሬ ደግሞ ነገሮች ተቀይሮ ጀሪካኑ ከቧንቧ እንጂ ርቀት ሄዶ ከወንዝ አይቀዳበትም። ሕዝቡም ቢሆን በተሰራለት ንጹህና ባለፎቅ ቤት ብቅ እያለ ይመግበዋል፤ አይዞህ እያለም ያለብሰዋል። በተጨማሪም እንክብካቤ የሚያደርጉ ሠራተኞችና የጤና ባለሙያዎች ሞልተዋል።

አረጋውያን ከኅብረተሰቡም ሆነ ከሚመለከተው አካል ተገቢው ትኩረት እየተሰጣቸውም ነው። ለዚህ ደግሞ የማኅበራቸው መመስረት ዋነኛ መሠረት ነው። በአሁኑ ጊዜ ማዕከል አስገንብቶ ከ200 በላይ የሚሆኑ አረጋውያንን እየተንከባከበ ይገኛል። በተጨማሪም ከማዕከሉ ውጭ ሆነው በተመላላሽ አገልግሎት የሚያገኙም እንዳሉ ጠቁሟል። በተጨማሪም የወደቁትን አንሱ የነዳያን ማኅበር አረጋውያንን የሚንከባከቡ ነርሶችንም የአጭር ጊዜ ልዩ ሥልጠና በመስጠት የሕክምና ዕርዳታን እየሰጡ ነውም።

ይህ ሁሉ ለውጥ ደግሞ የተነሳው ከሰሞኑ በተከበረው የአረጋውያን ቀን ላይ ሲሆን፤ ማህበሩም ጎን ለጎን በተለያዩ መርሐ ግብሮች 25ኛ ዓመቱን አክብሯል። እናም አቶ ስንታየው በክብረ በዓሉ ላይ እንዳለው፤ ማህበሩ ዘርፈ ብዙ ሥራ በአረጋውያኑ በኩል ይሠራል። አንደኛውና ዋነኛው አረጋውያኑን መንከባከብ ሲሆን፤ ሌላኛው ተግባሩ ደግሞ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ለማዘጋጃ ቤት በማሳወቅ ሰዎቹ በክብር እንዲቀበሩ ማድረግ ነው። በተጨማሪም እንደየእምነታቸው ተለይተው እንዲቀበሩም ያመቻቻል።

አቶ ስንታየሁ ሥራውን ጀምሮ በብዙ ፈተና ውስጥ እያለ ሁለት ወጣቶችን ተዋውቋል። ንጉሤ ሀብታሙና ካሳሁን ከበደ የሚባሉ ወጣቶች ናቸው። ሥራው ተመልክተው እርሱን ለማገዝ የታተሩ ሲሆኑ፤ ተሳትፏቸው ደግሞ ራሳቸውን ብቻ የያዘ አልነበረም። ቤተሰቦቻቸውን ጭምር አሳትፈውና አስተባብረው ከማኅበሩ ምሥረታ ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው። ዛሬም ቢሆን ከስንታየሁ ጎን ቆመው የቻሉትን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ። አቶ ሰንታየሁ ስለእነርሱ ሲያወሳ ‹‹አምላክ ለሰዎች በሰዎች ላይ አድሮ ይደርሳልና የእኔን ቃል እንድተገበር እነርሱን ጨመረልኝ›› ይላል።

አቶ ስንታየሁ ዘወትር ከአፉ የማይለየው አንድ አባባል አለው። ይህም ‹‹ልጅ አይሙት ይታመም›› የሚለው ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ ልዩ ልዩ ነው። አንደኛው በልጅ ሕመም ውስጥ መሥራትና ለሌሎች መኖርን ማየት ይቻላል። በሕመም ውስጥ የሌሎችን ችግር መጋራትና ለመፍትሔ መነሳትን ያመጣል። እናም እርሱ ልጅ ነበረ፤ በሕመሙ ውስጥ ዓመታትን ተሻግሮ ሌሎችን አየ፤ ለማስታወስም ቻለ። እናም ሌሎችም ይህንን ያደርጋሉ ብሎ ያምናል።

ማህበሩ 25ኛ ዓመቱን ሲያከብር ብዙዎችን ያሰባሰበ ሲሆን፤ በወቅቱ የተገኙ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች መካከል የአርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ አንዱ ናቸው። በፎቶ አውደ ርዕዩ መክፈቻ ወቅት እንደተናገሩትም፤ ‹‹አረጋዊያን ሀገርን በደማቸው ያሻገሩ፤ ትውልድን በምርቃት የገነቡ ችግር መፍቻ ቁልፎች ናቸው። ነገ ምን እንደሚሆን ቀድመው የሚተነብዩና የሚያዩ ፤ ለሌሎች ጭምር የሚያመላክቱ ነብያቶችም ናቸው። በዚህ ውስጥ ግን የሚመለከታቸው ያጡና ምርቃታቸውን ሳይሆን ርግማናቸውን እየሰጡ ያለፉ ሆነዋል። እናም አሁን ተረጋሚ እንዳንሆን ሳይወድቁ ልናነሳቸውና ልንንከባከባቸው ይገባል። የዚህን ጊዜ ከምርቃታቸው በረከትን፤ ከተሞክሯቸው ነጋችንን እናገኛለን።›› ብለዋል።

ሌላው በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙትና ንግግር ያደረጉት ደግሞ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ የሚኒስትሯ አማካሪ አቶ ሰለሞን አስፋው ሲሆኑ፤ ማህበሩ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በቁጥር 1195 ህጋዊ የምዝገባ ፍቃድ አግኝቶ እየሰራ የሚገኝ መሆኑን ለታዳሚው አስረድተዋል። ቀጥለውም እንዳሉት፤ በርከት ያሉ መደበኛ አባላቶችና በጎ ፍቃደኛ አባላቶች ያሉት ሲሆን፤ ሃይማኖት፣ ዘርና ፆታ ሳይለይ የሦስተኛ ወገን ድጋፍ ለሚያስፈልገው ሰው ለሆነው ፍጡር ሁሉ አገልግሎት የሚሰጥ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፤ የማህበሩ የሀብት ምንጭ በዋነኛነት ዓላማው አድርጎ የተነሳው እኛው በእኛው በሚል መርህ ከኢትዮጵያዊ ግለሰቦች፤ በኢትዮጵያ ህጋዊ ሰውነት አግኝተው ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች፤ ተገልጋዮችን በየጊዜው ከሚጎበኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች በዓይነትና በገንዘብ ከሚያገኘው ድጋፍ በየወሩ ከመደበኛ አባላት ከሚሰበሰብ መዋጮ ነው። የሰው ኃይልን በተመለከተ በባለሙያ በጎ ፍቃደኞች የሚደረግ የሙያ እገዛን ያካተተ ነውም።

አቶ ሰለሞን፤ ማህበሩ በአሁኑ ሰዓት ከ200 በላይ ለሚሆኑ አረጋውያኖች ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ በምግብ፣ በአልባሳት፣ በመጠለያ፣ በሕክምና እንዲሁም ክብርና ፍቅር በመስጠት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አንስተው፤ ከወረዳው ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት፣ ከወረዳው አረጋውያን ማህበር እንዲሁም ከአካባቢው እድሮች በሚያገኘው መረጃ መሠረት ደጋፊ ወገን የሌላቸውን አረጋውያን በመለየት በማዕከሉ ቅጥር ግቢ መጥተው በየዕለቱ የምግብ አገልግሎትና በመካከለኛ ክሊኒኩ የነጻ ሕክምና በመስጠት ቁጥራቸው ከ100 ለማያንሱ ችግረኛ አረጋውያን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ። በተጨማሪም በዓልን አስመልክቶ የምግብ፣ የንጽህና እቃና አልባሳት ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የሚያብራሩት።

ማህበሩ በቀጣይ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ትልቅ ርዕይ መሰነቁንና በ2040 በአረጋውያን ሁለንተናዊ ድጋፍ፣ እንክብካቤና ሕክምና በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ሆኖ መገኘት ነው በሚል ጉዞውን ለመጀመር በመንደርደር ላይ መሆኑን የጠቆሙት አማካሪው፤ በዚህም መሠረት በሀገራችን የመጀመሪያ የሚሆነውን የአረጋውያን ሕክምና ማዕከል ለመገንባትና አገልግሎት ለመስጠት የዲዛይንና የእስታንዳርድ ጥናት እያስጠና እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ለአረጋውያኖች ከሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ ማዕከሉ በጥናትና ምርምር እንዲሁም ለሕክምና ባለሙያዎች ስልጠና የሚሰጥበት የልህቀት ማዕከል እንደሚሆን አብራርተዋል።

ማህበሩ አሁን ባለበት ሁኔታ ለዚህ ሕክምና የሚሆን የባለሙያ ፍላጎት ለማሟላት የአረጋውያን ነርሶችን የማስልጠን ሂደት መጀመሩንና የማኅበሩ ፖሊሲና ስትራቴጂ የሀገር ውስጥ ሀብትና እውቀትን በማስተባበር ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ አስተሳሰብ ይዟል ይላሉ። ‹‹በህብረተሰብ የሚደገፍ ወገን ለወገኑ መደጋገፍ ይችላል›› በሚል መርህ የወገን ተደራሽነቱን በተግባር ያሳየ እና ለሌሎች መሰል ድርጅቶች አርአያ የሚሆን እንደሆነም ያነሳሉ። በተጨማሪም በአረጋውያን ዙሪያ ከሚሰሩ መሰል ድርጅቶች ጋር ትስስር ፈጥሮ እየሰራ መሆኑ የአረጋውያኖችን ድምጽ በጋራ በማሰማት፤ የልምድ : ለውውጥ በማድረግና በአጠቃላይ እርስ በእርስ በመረዳዳት ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ እንዲሄድ አድርጎታልም ባይ ናቸው። እናም ዛሬም ሆነ በቀጣይ ይህንንና መሰል ድርጊቶቹን በመደገፍ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከጎኑ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

አዎ እንደ እነዚህ ዓይነት ተግባራት በመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ውጭ ባሉ ሌሎች ድርጅቶችም ሊደገፉ ይገባል። ምክንያቱም ጉዳዩ ሰውን ማገዝ ነው፤ ሰውን ከአለበት ችግር መታደግና ለነገ የሚሆን መልካም ስንቅ ማስቀመጥ። አቶ ስንታየሁ መልካሙን ነገር ተመኝቶ 15 ዓመት ጠይቆ 25 የበረከት እድሜ እንደተሰጠው ሁሉ በዚህ መልካም ሃሳብ ውስጥ ሁሉ የተሳተፈ ሰው የበረከት እድሜን ያፍሳል። ስለዚህም ተግባሩ መልካምነትን መቃረሚያ ነውና ሁሉም ይጠቀምበት እያልን ለዛሬ የያዝነው በዚህ አበቃን። ሰላም!!

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2016

Recommended For You