አዲስ አበባ፦ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አገልግሎት ሳይሰጡ የነዳጅ ድጎማ ያለ አግባብ የተጠቀሙ ሁለት ሺህ 102 አሽከርካሪዎች ገንዘቡን እንዲመልሱ መደረጉን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የብሔራዊ የታለመለት ነዳጅ ድጎማ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሰልማን መሀመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴሩ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ሳይሰጡ የተጠቀሙትን የነዳጅ ድጎማ ተመላሽ የሚያደርጉበት አሠራር አለው። በዚህ መነሻ መሠረት በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አገልግሎት ሳይሰጡ የነዳጅ ድጎማውን ያለአግባብ የተጠቀሙ ሁለት ሺህ 102 አሽከርካሪዎች ከአራት ሚሊዮን 416 ሺህ 143 ብር እንዲመልሱ ተደርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በኩል እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገ ቁጥጥር ከአንድ ሺህ 318 ተሽከርካሪዎች ሁለት ሚሊዮን 767 ሺህ በላይ ብር ተመላሽ እንዲያደርጉ ተደርጓል ያሉት አቶ ሰልማን፤ ተሽከርካሪዎቹ ተመላሽ ያደረጉት አገልግሎት ሳይሰጡ የተጠቀሙትን የነዳጅ ድጎማ ገንዘብ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በነበረው ሂደትም ተሽከርካሪዎች ከሐምሌ 2014 እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አገልግሎት ሳይሰጡ የተጠቀሙት የነዳጅ ድጎማ ብር 7 ሚሊዮን 183 ሺህ 381 እንደመለሱም ተናግረዋል።
በሩብ ዓመቱ ከድጎማ እንዲታገዱ የተደረጉ ተሽከርካሪዎች ከአምሥት ሺህ በላይ መድረሳቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በተመሳሳይ ከሐምሌ 2014 እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ከነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚነት የታገዱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 35 ሺህ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሰልማን ገለፃ፤ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ከተጀመረ አንስቶ እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ከ23 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ ለተሽከርካሪዎች ድጎማ ተደርጓል። በ2016 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ለተሽከርካሪዎች ድጎማ ተደርጓል።
በድጎማ ሥርዓቱ የሚካተቱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 240 ሺህ 890 ተሽከርካሪዎች ወደ ዲጂታል ሥርዓቱ ገብተዋል ያሉት አቶ ሰልማን፤ በሩብ ዓመቱ ዘጠኝ ሺህ 872 ተሽከርካሪዎች ለድጎማ ተመዝግበዋል ብለዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2016