በክልሉ የአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ተኪ ምርቶችን ለማምረት ታቅዷል

አዲስ አበባ፡- በ2016 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን ለማምረት መታቀዱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአማራ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ በዘርፉ በርካታ ውጤቶችን ማስገኘት እንደቻለ ተገልጿል፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አዳዲስ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን መሳብ፣ የተኪ ምርቶችን ምርት ማሳደግ፣ ነባር ኢንዱስትሪዎች ላይ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት የሚሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

በንቅናቄው በ2015 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በተኪ ምርት በማዘጋጀት የውጭ ምንዛሬን ማዳን የተቻለ ሲሆን፤ በ2016 በጀት ዓመት በተኪ ምርቶች አማካኝነት ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማዳን መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡

ከጨርቃጨርቅ፣ ከማኑፋክቸሪንግና ከተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚገኙ ተኪ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ገቢ ለማግኘት እንደሚሠራ ጠቁመዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ከአምስት ሺህ በላይ ለሆኑ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ቢታቀድም በክልሉ ባጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት በሩብ ዓመቱ የኢንቨስትመንት ፍሰት መዳከሙን አንስተዋል።

የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ከማህበረሰቡና ከፀጥታ አካሉ ጋር በመረባረብ በመፍታት በሩብ ዓመቱ የባከነውን ጊዜ ለማካካስና የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡ የክልሉ መንግስት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በሙሉ አቅም ለማገዝ፣ ችግር ያለባቸው መመሪያዎችንና አሠራሮችን ለማሻሻልና በቅንጅት ለመሥራት የሚያግዝ ውሳኔ አሳልፏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ማህበረሰቡ ድረስ ለማውረድ ትኩረት ተደርጓል ያሉት አቶ ተፈሪ፤ ሁሉም ማህበረሰብ የድርሻውን እንዲወጣ የተለያዩ አደረጃጀቶችን የመፍጠርና በጀት የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በዘርፉ ከሚስተዋሉት ማነቆዎች መካከል የመሬት ዝግጅት አንዱ ነው ያሉት አቶ ተፈሪ፤ መሬት በክላስተር ከተዘጋጀ በኋላ ባለሀብቱ ለአርሶአደሩ ተገቢውን ካሳ ከፍሎ እንዲያለማ የሚያግዝ መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደትግበራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሌላኛው የዘርፉ ማነቆ መሆኑን ጠቁመው፤ በርካታ የኢንዱስትሪ መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙት ለነዋሪዎች ተብሎ ከተዘረጋ መስመር በመሆኑ ችግር መፈጠሩን ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታት ከሰብስቴሽን ወደ ኢንዱስትሪ መንደሮች እራሱን በቻለ መስመር ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት ከአምስት ሺህ 700 በላይ አዳዲስ ባለሀብቶች ወደክልሉ መጥተው የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረው፤ 578 ባለሀብቶች 780 ሄክታር መሬት ተቀብለው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡ 28 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ 255 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደሥራ ከማስገባት በተጨማሪም በተለያዩ ማክንያቶች ሥራ ያቆሙና የማምረት አቅማቸው ዝቅተኛ የነበሩ 149 ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅም ወደሥራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።

 ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2016

Recommended For You