በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት 50 የሰንበት ገበያዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው

ሆሳዕና፡- የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት 50 የሰንበት ገበያዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ክልሉ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የሚረዱ 50 የሰንበት ገበያዎች በተለያዩ ከተሞች ተቋቁመው ለአገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

በተያዘው በጀት ዓመት ከ70 በላይ የሰንበት ገበያዎች ለማቋቋም ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዳንኤል፤ 50ዎቹ አገልግሎት እየሰጡ በመሆኑ 20 የሰንበት ገበያዎች በቀጣይ ተቋቁመው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋሉ ብለዋል።

የሰንበት ገበያዎች የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ክልሉ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ የሰንበት ገበያዎቹ በሚፈለግባቸው ልክ ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ቁጥጥር ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የሰንበት ገበያዎቹን የማጠናከርና ቀሪዎቹን ወደ ሥራ ለማስገባት ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው የወረዳ መዋቅር ድረስ እየተሠራ መሆኑን አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል።

በአምራቹና በሸማቹ መካከል ላይ የሚያጋጥሙ ሕገ-ወጥ ደላሎች ለማስቀረት የሰንበት ገበያው አማራጭ መፍትሔ መሆኑን ተናግረው፤ ሸማቾች በአቅራቢያዎቻቸው በሚገኙ የሰንበት ገበያዎች በመሄድ በርካታ ግብይቶችን እየፈጸሙ መሆኑን አስረድተዋል።

የቢሮ ኃላፊው እንደገለጹት፤ በክልሉ ገበያውን ለማረጋጋት ከሰንበት ገበያ በተጨማሪ አምራቹንና ሸማቹ በቀጥታ የማገናኘት እንዲሁም በአቅራቢያ የማይገኙ ምርቶች በሸማች ማኅበራት አማካይነት የማቅረብ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል።

መሠረታዊ ፍጆታዎች በተለይ የስኳርና የዘይት ምርቶች የአቅርቦት ችግር እንዳይከሰት ከሚመለከተው የፌዴራል መሥሪያ ቤት ጋር በመነጋገር እንዲገባ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ለሸማች ማኅበራት ብድር ለማመቻቸት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ብድር በማቅረብ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ አስታውቀዋል።

በተለይ ለሸማች ማኅበራት የሚፈቀደው ብድር የአቅርቦት ችግር ከመቅረፍ ብሎም ገበያውን ከማረጋጋት ጎን ለጎን ለሥራ ዕድል ፈጠራ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው አቶ ዳንኤል አመላክተዋል።

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ በገበያው ላይ የተለያዩ አሻጥር የሚሠሩና በሕገ-ወጥ መንገድ የሚዛን ቅሸባዎች የሚፈጽሙ አካላት ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል። በቀጣይም የንግድ ቤቶችን እስከማሸግና የንግድ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ ርምጃ ይወሰዳል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

 አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You