ልጆች ሀገራችሁን እወቁ!

ሰላም ልጆችዬ እንዴት ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ያው እንደ ሁልጊዜው በትምህርት እና በጥናት እንዳሳለፋችሁት ምንም ጥርጥር የለኝም:: ልጆችዬ ስለ ሀገራችሁ ምን ያህል ታውቃላችሁ? መቼም ሀገራችን ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ ጥበብ፣ ታሪክ፣ ባሕል፣ ቅርስ እና ሌሎች መስህቦች እንዳሏት ታውቃላችሁ ወይም ለማወቅ ጥረት ታደርጋላችሁ:: በዚህ በኩልም የቤተሰቦቻችሁ (የአሳዳጊዎቻችሁ) ሚና ከፍተኛ እንደሆነም እተማመናለሁ::

ልጆች ስለ ሀገራቸው ታሪክ፣ ባሕል እና መሰል ነገሮች እውቀት እንዲሁም ግንዛቤ እንዲኖራቸው የቤተሰብ፣ የመምህራን፣ የመንግሥት፣ የእናንተም ድርሻ እና ጥረት ከፍተኛ መሆን ይኖርበታል:: ከነዚህ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎቻቸው ታሪካቸውን፣ ሀገራቸውን እና አካባቢያቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ ወደ ተለያዩ የጉብኝት ስፍራዎች በመውሰድ ሀገራቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ያደርጋሉ:: ልጆችዬ እናንተስ እንዲህ አይነቱ ዕድል ገጥሟችሁ ያውቃል? ‹‹ዕድሉን ገጥሞን ጎብኝተናል›› የሚል ምላሽ እንደምትሰጡኝ ተስፋ አደርጋለሁ:: ከዚህ ቀደምስ ‹ሀገርህን እወቅ› የሚል ክብብ በማቋቋም የተለያዩ ጉብኝቶች ይደረጉ እንደነበር ምን ያህሎቻችሁ ታውቁ ይሆን? ልጆችዬ ካላወቃችሁ ወላጆቻችሁን በመጠየቅ መረዳት ትችላላችሁ ::

ልጆች መገናኛ ብዙኃን እናንተ ስለ ሀገራችሁ እንድታውቁ ለማድረግ በቴሌቪዥን፣ በራዲዮ፣ በመጽሐፍ እና በጋዜጣ መልክ መረጃዎችን በመስጠት ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ:: እኛም በዛሬው ጽሑፋችን የጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ በኩል ተመራጭ ከሆኑት መካከል ጥቂቱን መርጠን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል::

እንጦጦ ፓርክ

ከባሕር ጠለል በላይ በ3200 ሜትር ላይ የሚገኘው የእንጦጦ ተራራ አዲስ አበባ ከተማ ከተቆረቆረችበት ሥፍራ ነው:: ይህ ታሪካዊ ቦታ አዲስ አበባን ከላይ ወደ ታች ለማየት ምቹ ሲሆን፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተቀየሰው ‹ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት› አማካኝነት አይነተኛ የቱሪስት ማዕከል ሆኖ እንዲለማ ተደርጓል:: ቦታውም የእግር ጉዞ ለማድረግ እና ለጎብኚዎች አመቺ እንዲሁም አዝናኝ እንዲሆን ተደርጎ ተሠርቷል:: ለልጆችና ለአዋቂዎች የብስክሌት፣ የፈረስና ሌሎችም የተለያዩ መዝናኛዎችንም ይዟል::

አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ

አዋሽ ፓርክ ከአዲስ አበባ 215 ኪሎ ሜትር በምሥራቁ የአገራችን ክፍል ይገኛል:: ፓርኩ የተቋቋመው 1958 ዓ.ም ነው:: በውስጡም አጥቢ እንስሳት፣ ከአራት መቶ በላይ የተለያዩ አዕዋፋት፣ ተሳቢ እንስሳት እና ከአራት መቶ በላይ የዕፅዋት ዓይነቶችን ይዟል:: የፓርኩ መለያ ዓርማ የሆነው ሳላ የተባለው የዱር እንስሳ በብዛት የሚኖርበት በመሆኑ ጎብኚዎች ወደ ፓርኩ ያቀናሉ:: በተጨማሪም የአዋሽ ፏፏቴ፣ የተፈጥሮ ፍልውሃ፣ ረዣዥም ሳሮች፣ ከ20 የሚበልጡ የተፈጥሮ መስህቦችን ያየዘ ፓርክ ነው:: የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌና በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ ውስጥ ይገኛል:: ፓርኩ አምስት መቶ ዘጠና ስኩየር ኪሎ ሜትር ቦታንም ያካልላል::

የወንጪ ሐይቅ

ይህ ሐይቅ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ እጅግ ማራኪ እና ውብ ሐይቅ ነው:: ሐይቁ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ሲሆን፤ በውስጡም ሐይቆችን፣ ፍልውሃዎች እና ሸለቆዎችን አቅፎ የያዘ ነው:: በሐይቁ ደሴት የሚገኘው ጥንታዊ ቤተክርስቲያንም ለአካባቢው ተጨማሪ መስህብ ሆኗል::

የታላቁ ቤተ መንግሥት አንድነት ፓርክ

የአንድነት ፓርክ በታላቁ ቤተ መንግሥት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መስህቦችን እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ መገለጫ የሆኑ ሀብቶችን የያዘ ነው:: በውስጡም በጣም ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩ በርካታ ታሪካዊ ሕንፃዎች፣ ከቤተ መንግሥቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቅርሶች፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች ባሕል እና እሴት የሚያንፀባርቁ እልፍኞች ተገንብተው የፓርኩ የመዳረሻ አካል እንዲሆን ተደርጓል:: በተጨማሪም ብርቅዬ የዱር እንስሳትን የያዘ የተፈጥሯዊ የእንስሳት መኖሪያ ገጽታ ያለው መካነ እንስሳት (የእንስሳት ቦታ)፤ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ አገር በቀል እጽዋትን የያዘ የእጽዋት ማዕከል እንዲሁም ውብ የአረንጓዴ ሥፍራ የያዘ በመሆኑ ለሀገራችን የቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል::

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከባሕር ጠለል 3600 ሜትር በላይ ይገኛል:: በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኘው ይህ ፓርክ፤ በብርቅዬ የዱር አራዊት መስህብ የታደለ ነው:: በሰሜን ተራሮች ከሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት መካከል ዋልያ አይቤክስ እና ጭላዳ ዝንጀሮ ተጠቃሽ ናቸው::

ልጆችዬ መቼም ስለ እነዚህ ስፍራዎች ስታውቁ ‹‹ሄደን በጎበኘነው›› ብላችሁ እንደተመኛችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም:: ልጆች ለዛሬው ይህንን ያህል ካልናችሁ ሌሎቹን ደግሞ በሌላ ጊዜ እናስተዋውቃችኋለን:: ለአሁኑ ግን ቤተሰቦቻችሁ የሚችሉ ከሆነም ሙዚየሞችን፣ ፓርኮችን እና የተለያዩ ስፍራዎችን በመጎብኘት የኢትዮጵያን ጥንታዊ ቅርሶችን ከማየት በሻገር ስለ ሀገራችሁ ያላችሁን ግንዛቤ ከፍ እንድታደርጉ ያስችላችኋል::

 እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2016

Recommended For You