የሠለጠነ ዜጋ ወቃሽ ሳይሆን ነቃሽ ነው

ብዙዎቻችን ወቃሾች ነን እንጂ ችግሩን ለመቅረፍ ራሳችን ጥረት አናደርግም። ለምሳሌ፤ ሕግ ባለመከበሩ መንግሥትን እና ሕግ የጣሱ አካላትን እንወቅሳለን። ‹‹መቼ ይሆን እዚች ሀገር ላይ ሕግ የሚከበረው?›› እንላለን፤ ዳሩ ግን የመፍትሔው አካል ለመሆን አንሠራም። በብልሹ አሠራሮች እናማርራለን፤ ዳሩ ግን ያንን ብልሹ አሠራር ለማስቀረት ጥረት አናደርግም፤ ይባስ ብሎ ተባባሪ የምንሆንበት አጋጣሚም አለ።

ይህን ያስታወሰኝ ከሰሞኑ የአንድ ምሁር ገጠመኝ በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ አንብቤ ነው። ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ ይባላሉ። በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ እየተጋበዙ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ። በማኅበራዊ ገጻቸውም በፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን ይጽፋሉ። ባለፈው ሳምንት የጻፉትን ገጠመኝ ግን ለብዙዎቻችን ልምድ መሆን ስላለበት ወዲህ አመጣሁት። ገጠመኛቸውን ቃል በቃል ልውሰደውና የሚከተለው ነው።

‹‹…ከሥር ያስቀመጥኩት ፎቶ (በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ተቀምጧል) የሚያመለክተው ከአለርት ሆስፒታል ወደ አየር ጤና አደባባይ ለመድረስ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩ የትራፊክ ምልክት ተብሎ በመንገዱ አካፋይ የተተከለ ነው፤ መኪናውን አቁሞና ወርዶ ብቻ ነው ምንነቱን ማወቅ የሚቻለው።

እንግዲህ ትናንት ወደ 10:30 አካባቢ ይህ ምልክት በምልክትነት ተቆጥሮ ሦስት የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎችና አንድ የሴት ትራፊክ ፖሊስ ወደ መጡበት አቅጣጫ U-Turn የሚመለሱትን መኪናዎች አስቁመው እንደ ጉድ እየቀጡ ነበር። ባለመኪኖቹም ያለአንዳች ማንገራገር በቴሌ ብር ቅጣቱን እየከፈሉ ይሄዳሉ። እኔም የመቀጣት (ቅጣት ከተባለ) ዕጣው ደርሶኝ ከሦስት የትራፊክ መንገድ ሠራተኞች አንዱ ሙግቴን ተከትሎ የቅጣት ወረቀቱን ፃፋብኝ። ከመንገድ ትራንስፖርት ሠራተኛው ጋር በነበረኝ ቆይታ የታዘብኳቸው አራት ነጥቦች፤

አንደኛ፤ ዋናው ምልክቱ ወደ ሌላ አቅጣጫ በዞረ እና ፈፅሞ በማይታይ ምልክት ለምን ትቀጣላችሁ? ስለው፣ ምልክቱ እንደማይታይ አምኖ እኔን ግን… እሱን ሂድና ትራፊክ ጽሕፈት ቤት አመልክት… በማለት ጋጠወጥ ምላሽ ሰጠኝ። እሱን ከእኔ ይልቅ አንተ ነህ መጠቆም ያለብህ በምልበት ደቂቃ እሱ የቅጣት ማዘዣውን በመፃፍ ‹‹ቢዚ›› ነበር።

ሁለተኛ፤ እኔን ቀድሞ የታጠፈ ሌላ መኪና ነበር፤ እኔን ያስቆመኝ እሱን ትቶ ነው። እንደዚህ ሚዛናዊ ባልሆነ መልኩ እየመረጣችሁ መቅጣቱንስ ሕጉ ይፈቅድላችኋል ወይ? በማለት ስጠይቀው ‹‹አምልጦ ነው የሄደው፤ ታርጋውን ይዘናል›› አለኝ። ሚዛናዊነታችሁን ማረጋገጥ ስላለብኝ የያዛችሁትን ታርጋ አሳዩኝ ስለው፤ ‹‹እንዲያውም አያገባህም›› የሚል ምላሽ ሰጠኝ። ታርጋውን ይዘናል ያለው ውሸቱን ነበር።

ሦስተኛ፤ በቅጣት ወረቀቱ ላይ ከሥር ቅጣቱን የፃፈው ሠራተኛ ስም እንዲፃፍ የሚጠይቅ ቦታ አለ። ቦታው ላይ የመንገድ ትራንስፖርት ሠራተኛው የራሱን ስም ብቻ ነበር የፃፈው። እኔም የአባትህንም ስም ጨምረህ ፃፍልኝ ብዬ ስጠይቀው ‹‹የእኔ ስም ብቻውን በቂ ስለሆነ የአባቴን ስም አልፅፍም›› ብሎ በቁጣ ተናገረኝ።

ጉዳዩን ለማመልከት ወደ ኮልፌ ቀራኒዮ የመንገድ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ስሄድ 11፡00 ሰዓት ሞልቶ ነበርና ቢሮው ዝግ ነበር። ዛሬ ሄጄ የመንገድ ትራንስፖርት ሠራተኞቹን ጋጠወጥነትና የማን አለብኝነት ባሕርያቸው ምንጩ ምን እንደሆነ የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች ለመጠየቅ ወስኜአለሁ።…››

ኢንጂነር ጌታሁን ፎክረው አልቀሩም። ጉዳዩን ሄደው በማመልከታቸውና ቅሬታቸውን በግልጽ በመናገራቸው የዞረው እና የማይታይ የነበረው የትራፊክ ምልክት ተስተካክሏል። የኮልፌ ቀራኒዮ ትራፊክ ማኔጅመንት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በትህትና ቅሬታቸውን እንዳደመጡና ጥፋቱን የሠራው ሠራተኛም ይቅርታ እንደጠየቃቸው ተናግረዋል።

እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ መባል አለበት። ኢንጂነር ጌታሁን ምሁር ናቸው። እንደምናየው እንደምንሰማው ደግሞ በሀገራችን ምሁራን ብዙም ታዋቂ አይደሉም። ሃሳባቸው እንጂ ፊታቸው እንደ አርቲስት በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ አይደለም። ከኢንጂነር ጌታሁን ገጠመኝ ሥር ከተሰጡ አስተያየቶች ውስጥ አንተ ታዋቂ ስለሆንክ ነው ያስተናግዱህ የሚል ይዘት ያላቸው ነበሩ። እርሳቸውም ለእነዚህ አስተያየቶች በሰጡት መልስ ‹‹… ከይቅርታ ጋር እኔን እናንተ በምትሉት መልኩ ያወቀኝ የለም፤ የሚያውቁኝ መስሎኝ ዓይኔን ቁልጭ ቁልጭ ባደርግም ከዕውቅና ጋር በተገናኘ ከቁብ የቆጠረኝ አልነበረም (የፌስቡክ የሳቅ ምልክት)…››

ይህን የኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞን ገጠመኝ ያመጣሁት ከኃላፊነታቸው ሁላችንም እንድንማር ነው። ብዙዎቻችን እናማርራለን እንጂ በዜጋዊ ኃላፊነት ችግሩን ለመቅረፍ አንሠራም። አንድ የስንፍና መሸፈኛ ዘዴ አለን። ይሄውም ‹‹እኔ ተናግሬ ለውጥ ላላመጣ…›› የሚል ነው። ሁሉም ሰው እንደዚህ ካለ ለውጥ አይመጣም። አብዛኛው ሰው ‹‹እኔ ተናግሬ ለውጥ ላላመጣ…›› የሚለው ተናግሮ ሳይሞክረው ነው። እርግጥ ነው ቀልጣፋ እና ፈጣን ምላሽ ይገኛል ማለቴ አይደለም፤ ዳሩ ግን በኃላፊነትና በጨዋነት ያስተዋልነውን ብልሹ አሠራር ለሚመለከተው አካል ብናሳውቅ ችግሩ ይቀንሳል። ምናልባት በድንፋታ እና በቁጣ ከተናገርን ግን ችግሩ ይባባሳል እንጂ አይቀረፍም።

ከዚህ በፊት አንድ ጓደኛዬ ከፖሊስ ጋር ተጣልቶ የነበረውን ገጠመኝ አስነብቤያችሁ ነበር። ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሊያመለክት ሲሄድ ‹‹ኧረ ተጨማሪ በጥፊ እንዳይሉህ›› እየተባለ ተቀልዶበት ነበር። ፖሊስ ጣቢያ በትህትና አስተናግደው ከተጣላው ፖሊስ ጋር ይቅርታ አባብለዋቸው ነበር ጉዳዩ ያለቀው።

አንዳንድ ጊዜ በስሚ ስሚ ብቻ ‹‹አያስተናግዱንም›› በሚል እንሳነፋለን። ችግር የፈጠረውን አካል ወይም ሕግና ደንብ የተላለፈውን አካል ከመጠየቅ ይልቅ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያለውን የመንግሥት አካል መሳደብ ይቀለናል። ተከታትለን መጠየቅ ባህል እስካላደረግን ድረስ ሕግና ደንብ የሚጥሱ ሠራተኞች ይኖራሉ። የመጠየቅ ልማድ ከሌለን ማንም አይጠይቀኝም የሚል የልብ ልብ ነው የሚሰማቸው። እንዲህ እንደነ ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ ዓይነት ጠያቂ የሰለጠነ ዜጋ ቢኖር ግን ሕዝብ ሊያገለግሉ ኃላፊነት የወሰዱ ሠራተኞች በሰው አይቀልዱም ነበር። አብዛኞቹ ከሕግና ደንብ ውጪ ሰዎችን ያለአግባብ የሚቀጡት ተጠያቂነት እንደማያጋጥማቸው እርግጠኛ ስለሚሆኑ ነው።

እንደ ዜጋ ሕግና ደንቦችን ማስተካከል የሁላችንም ግዴታ ነው። አንድን ኃላፊ የሚጠይቀው ሌላ የበላይ አካል ብቻ ነው ብለን ዝም ካልን ችግሩ አይቀረፍም፤ ምክንያቱም ያ ኃላፊ ከበላይ ኃላፊዎቹ ይልቅ ለባለጉዳዮች ይቀርባል። የሚያጠፋውን ጥፋት የሚያውቀው ባለጉዳይ እንጂ የበላይ አለቃው አይደለም፤ የበላይ አለቃው ሲመጣማ ትሁት፣ ታታሪና ተቆርቋሪ ነው የሚሆነው።

ብልሹ አሠራሮቻችን ተቀርፈው፣ ሕግና ደንብ ተከብሮ፣ የሠለጠነ አሠራር እንዲኖር ወቃሽ ብቻ ሳይሆን ነቃሽም እንሁን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You