በ90ናዎቹ፤ ሬዲዮኖች ብዙ አድማጮች በነበሯቸው ጊዜ፤ ኤፍ ኤም ሬዲዮኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በተደመጡበት ወቅት ነበር ማርታ ደጀኔ ከአራት ኪሎ የምትል አንዲት ለስለሳ ድምፅ ያላት ወጣት በሬዲዮ ሞገዶች አልፋ አድማጭ ጆሮ ውስጥ መግባት የጀመረችው። ማርታ ለጥያቄና መልስ ውድድሮች ለመመለሰ ማንም አይቀድማትም ነበር። በወቅቱ በርካቶች ልብ ውስጥ ስሟ የታተመው ማርታ ደጀኔ ማናት? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን ጠይቀን በቅንነት ለተሰጡን መልሶች አመስግነን በዚህ መልኩ ይዘንላችሁ ቀርበናል መልካም ቆይታ።
ማርታ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ልዩ ስሙ «አራት ኪሎ» ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጡረታ ሚኒስቴር ጀርባ በሚገኝ ሰፈር ነበር። የማርታ እናትና አባት የጤና ባለሙያዎች ነበሩ። የማርታ እናት በወቅቱ የሚሰጠውን የፖሊዮ ክትባት አንዴ ካስከተቧት በኋላ ክትባት ቢበዛ ምንም አይጠቅምም አንዱ ይበቃታል ብለው ይተውታል። ያኔ እንደ ቀላል ችላ ያሉት የፖሊዮ ክትባትን አለመከተብ መዘዝ ማርታ ገና የሁለት ዓመት ሕፃን እያለች ፤ ገና ድክ ድክ ማለት እንደ ጀመረች ነበር ለአካል ጉዳት የዳረጋት።
ቤተሰቦቿ «ትድናለች» በሚል ተስፋ ብዙ ሙከራ ቢያደርጉላትም ሊሳካ አልቻለም። ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ ከመንፈሳዊ እስከ የባዕድ አምልኮ ሁሉንም ሞክረውላታል። ለአካል ጉዳተኝነት በወቅቱ ይሰጥ የነበረው አመለካከት የተዛባ በመሆኑና የማርታ ቤተሰቦች እንድትድን ካላቸው ጉጉት የተነሳ በየዕለቱ አዳዲስ ነገርን በመሞከር ላይ ስለነበሩ ማርታ ቶሎ ወደ ትምህርት ቤት አልገባችም ነበር።
ጊዜ ጊዜን እየወለደ ቢመጣም ማርታ በጤናዋ ላይ ምንም ለውጥ ባለማምጣቷ፣ እሷ ቤት ተቀምጣ ከሷ በኋላ የተወለዱት ልጆች ሳይቀሩ ትምህርት ቤት መሄዳቸው ለምን እኔስ እንድትል አድርጓት እንደነበረ ትናገራለች።
ማርታ ከፊደል ጋር የተዋወቀችበትን አጋጣሚ በዚህ መልኩ ነግራናለች «ታላቅ ወንድሜ ትምህርት ቤት ይሄዳል፤ የእሱ መሄድ ሳያንስ ታናናሾቼም ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ጀመሩ። ያኔ እኔስ በማለት መብቴን ስጠይቅ አባቴ የሰፈሩን ሰው አስተባብሮ አነስ ያለች ቤት ከሰሩ በኋላ አንድ ቄስ የቄስ ትምህርት እንዲያስተምሩ አመጣቸው። ያኔ እኔና ሌሎች ልጆች ትምህርት ጀመርን። በወቅቱ ያስተምሩን የነበሩት አባት እስኪደንቃቸው ድረስ በአንድ ሳምንት ውስጥ ፊደልን፤ አቦጊዳን ጨርሼ መልዕክተ ዮሐንስ ደረስኩ» ትላለች።
ከዚያ አባ በምን ምክንያት ከትምህርት ቤቱ እንደቀሩ ባላታስታውስም ሌላ መምህር ከሳምንት በኋላ መጥቶ ማስተማር ጀመረ። በወቅቱ የአካል ድጋፍ ባለመኖሩና ማርታ መራመድ ስለማትችል ወደ ትምህርት ቤት የሚያመላልሷት አባቷ አቅፈዋት እንደነበር ታስታውሳለች። የተቀየረው መምህር አስተምሮ ሲጨርስ ልጆቹ እየሮጡ ወደየቤታቸው ሲሄዱ ተነስታ እንድትሄድ ቢነግራትም በእግሯ መሄድ የማይሆንላት ልጅ መልስ ሳትሰጠው ዝም ትላለች።
አባትዬውም ልጃቸውን አቅፈው ለመውሰድ በሚመጡበት ጊዜ መምህሩ የሕፃንዋን ማርታ ቁንጮ በመያዝ እንድትነሳ ሲነግራት ሕፃን ማርታ ማልቀስ ጀመረች። ያን ጊዜ የልጃቸውን ለቅሶ የሰሙት አባት ከመምህሩ ጋር ተጣልተው ልጃቸውን ወደ ቤት ይዘው ገቡ። ያች አንድ ሳምንት ከፊደል ጋር በደንብ ያግባባቻት ማርታ ከዚያ በኋላ ቤት ውስጥ ሆና የእህት የወንድሞቿን መጽሐፍ በማንበብ ሯሷን አስተማረች።
ከልጅነቷ ጀምሮ ብሩህ አእምሮ ስለነበራት የእህትና ወንድሞቿን መጻሕፍት በማንበብ ከወንድሞቿ ሁሉ ልቃ መገኘቷን የተመለከቱት ቤተሰቦቿ መጻሕፍት እየገዙ ያቀርቡላት ጀመር። ሌላው ቀርቶ ዕቃ ሲገዛ የተጠቀለለበት ጋዜጣን እንኳን «ቆይ እሷ ትየው!» ይባልና ይቀመጥ እንደነበር ታስታውሳለች።
ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ እሷም የመማር መብቷን ደጋግማ የመጠየቅ፣ ቤተሰቦቿም ድና እንደ እኩዮቿ ውላ ትገባለች የሚለው ውጤት አልባ ድካማቸው ተስፋ ስላስቆረጣቸው ማርታ ትምህርት ቤት እንድትገባ ውሳኔ ላይ የደረሱት፡፡ ከዚያም ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ እንድትጠቀም ሆኖ በአፄ ናኦድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከትምህርት ጋር ተዋወቀች፣ 2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተከታተለች። አካል ጉዳተኛ በመሆኗ እንደ ዕድሜ እኩዮቿ ተሯሩጣ ተጫውታ ባታድግም ከመጻሕፍት ጋር ጥብቅ ቁርኝት የነበራት መሆኑን ትናገራለች።
በማንበብ ፍቅር ታንጻ ያደገችው ማርታ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ለገዳዲ እና ፋና ላይ የሚተላለፉ ዜናና ፕሮግራሞችን በትኩረት ከመከታተል ባሻገርም በጠቅላላ እውቀት ጠንካራ ተሳታፊም ነበረች፡፡ «ማርታ ደጀኔ ከአራት ኪሎ» የሚለው ስም በብዙ የሬዲዮ አድማጮች ዘንድ ጎልቶ ታወቀ። «ማን ትሆን?» የሚለውን የአድማጮችን ጥያቄ ምላሽ ያገኝ ዘንድም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከታሜሶል ኮሚኒኬሽን ጋር በትብብር በሚያቀርበው የሐሙስ ማታ የጥያቄና መልስ ውድድር ላይ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ተወዳድራ በማሸነፍ ማንነቷን ለማስተዋወቅ ተጠቅማበታለች። ሁለተኛው ውድድር ላይ ስትሳተፍ ግን ማርታ ዓላማ ነበራት።
12ኛ ክፍል አጠናቅቃ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስገባትን ውጤት በመጠባበቅ ላይ እያለች ለወራት ያለሥራ መቀመጥ አልፈለገችም። እናም የግል ጋዜጣ ጀምራ ለመሥራት ፍላጎት አደረባት፤ ግን ገንዘብም ሆነ ሥራውን ለመሥራት የሚያስችሏት ቁሳቁሶች አልነበራትም። ፈቃድ ለማግኘት ደግሞ በባንክ አካውንቷ ብር 10,000 የተሟላ ቢሮ ኮምፒዩተርን ጨምሮ ማሟላት ግዴታዋ ነበር። ገንዘቡን ከማይክሮ ፋይናንስ በብድር ስታገኝ፣ በጠቅላላ እውቀት ተሳትፎ ደግሞ ኮምፒዩተሩን አሸንፋ የጋዜጣ ማሳተም ህልሟን እውን አደረገች። ያሰበችውን ለማሳካት ምንም ነገር እንቅፋት እንዳይሆንባት የምትጥረው ማርታ፣ የጋዜጣዋን ስም «እውን» አለችውና በሥነ-ጽሑፍ የምታውቃቸው ጓደኞቿን በማሰባሰብ በተከራየቻት አንዲት ጠባብ ቢሮ ውስጥ ሥራቸውን ጀመሩ። ነገር ግን የተበደረችውም ገንዘብ ሲያልቅ ‹‹እውን›› ጋዜጣ በዚያው ቆመች።
የማርታ የጋዜጠኝነት ፍቅር ግን አልቀነሰም፤ ጥረቷንም አላቋረጠችም። የከፍተኛ ተቋም መግቢያ ውጤትም ይፋ ሆነና ማርታ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን አካል ጉዳት ከምትፈልግበት ያላገዳት የጥንካሬ ተምሳሌት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ ዲፓርትመንትን ተቀላቀለች።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያለች በዛሚ 90.7 ኤፍ.ኤም ላይ ተወዳድራ በመግባት ለ4 ዓመታት በጋዜጠኝነት አገልግላለች። ከዩኒቨርሲቲው በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋንም ተቀብላለች።
ከዚያም «እውን የማስታወቂያ ሕትመትና ፕሮሞሽን ሥራ ድርጅት»ን በ2000 ዓ.ም በማቋቋም ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር በአካል ጉዳተኝነት ላይ ትኩረት ያደረገ «ማዕዶት» የተሰኘ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለ5 ዓመታት ያህል ስታቀርብ ቆይታለች። ከመደበኛ ፕሮግራሟ ባሻገር ሃይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላትን የቴሌቪዥን የአየር ሰዓት በመውሰድ ማስታወቂያ የሚያስነግሩና ስፖንሰሮችን በማሳተፍ አዝናኝ ፕሮግራሞችን በመሥራት ትታወቃለች።
ማርታ ከዚህ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጎን ለጎንም «ተምሳሌት» እና «ጠብታ» የተሰኙ መጽሔቶችንም በማሳተም ለአንባብያን በነፃ በማድረስ ላይ ነች። ተምሳሌት መጽሔት በማስታወቂያ ድርጅቷ አማካይነት የሚታተም ሲሆን፤ አካል ጉዳተኝነታቸውን በምክንያትነት ሳያስቀምጡ ችሎታቸውን አውጥተው ከራሳቸው አልፈው ለሌላውም መትረፍ የቻሉ በሀገር ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተቸራቸውን ምሳሌ የሆኑ ግለሰቦች የሕይወት ተሞክሮ የሚስተናገድበት ነው።
ጠብታ መጽሔት Ewin Charitable Association ሥር የሚታተምና የማኅበሩ ልሳን ሲሆን፤ በየዓመቱ ኅዳር ወር ላይ ተከብሮ የሚውለውን ዓለም አቀፉን የአካል ጉዳተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ የሚታተም ዓመታዊ መጽሔት ነው።
እሷ ካለፈችበት የአካል ጉዳተኝነት ውጣ ውረድ ብሎም የሴትነት የሕይወት ጫና እንዲሁም በሙያዋ ከገጠሟት በመነሳት «እውን የበጎ አድራጎት ማኅበርን» በማቋቋም አካል ጉዳተኞች በእጅጉ የሚቸገሩበትን ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ (ዊልቸር) ሀገር ውስጥ በመገጣጠም ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን በማዳን ረገድ አስተዋጽኦ የሚኖረውን የበጎ አድራጎት ሥራ በመሥራት ላይ ትገኛለች።
አካል ጉዳተኝነት በራሱ የሚፈጥረው ጫና እንዳለ ሆኖ በተለይ ሴት አካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖ ቀላል የማይባል መሆኑን ማርታ ተናግራለች። ለዚህም በጤናና ሥነ-ተዋልዶ ዙሪያ ያልተዳሰሱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የድርሻዋን ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። በተለያዩ ጊዜዎች የሚሠሩ መሠረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አለማድረጋቸውን እንደ ችግር ታነሳለች። (መንገድ፣ ት/ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ የተለያዩ ሕንፃዎች ወዘተ.) አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው ባለመገንባታቸው እንደሌላው ውሎ ለመግባት አስቸጋሪ መሆኑን ትናገራለች።
ለአካል ጉዳተኞች ትዳር መመሥረት፣ ልጆችን መውለድና ቤተሰብ ማፍራት ከባድ ስለሆነ እንዲህ ዓይነት ሃሳብ ካላት ቢቀርባት መልካም እንደሆነ ብዙ አስተያየቶች ተሰጥቷት የነበረ ቢሆንም ያንን ተሻግራዋለች። ከትዳር አጋሯ ጋር የተገናኙበትን አጋጣሚ ማርታ በእንዲህ መልኩ ትገልፀዋለች።
«አንድ ቀን አባቴ በጠና ታሞ ፖሊሰ ሆስፒታል ተኝቶ ነበር። ያን ቀን ከአራት ኪሎ ወደ ሜክሲኮ የሚሄድ ታክሲ ይዤ እየሄድኩ ነበር። በአጋጣሚ ታክሲው ውስጥ እኔና የአሁኑ ባለቤቴ ብቻ ነበርን። ታክሲው ውስጥ አካል ጉዳተኛ ስለሆነኩ ይሁን ሌላ… በጣም ተንከባከበኝ እያወራን ስንሄድ አባቴ መታመሙን ነገሬው ስልኬን ተቀብሎኝ ወረደ። በነጋታው ሲደውል አባቴ አርፎ ነበርና የለቅሶ ድምፅ ሰምቶ አድራሻውን ጠይቆ መጥቶ አፅናናኝ። በዚያው ተለማምደን ጎጆ ከመቀለስም አልፈን የአራት ልጆች ወላጆች ለመሆን በቅተናል» ትላለች።
ማርታ በትዳር ሕይወት ውስጥ ያለውን ኃላፊነት በአብዛኛው ሴቶች ላይ እንደመውደቁ ከአካል ጉዳት ጋር እንዴት እንደተሻገረችው ስታስረዳ «የልጆች፣ የትዳር የቤት ውስጥ ኃላፊነት በአብዛኛው የሴቶች መሆኑ እንዳለ ሆኖ በእኔ አቅም ነው ወይ? ይሄንን ያደረኩት እስክል ድረስ ቤት ውስጥ አጋዥ ሳልቀጥር ባለን አቅም እየተጋገዝን በመኖራችን ፈጣሪን አመስግናለሁ። በባለቤቴ እርዳታ ከቤተሰቦቼ አንድ አካባቢ መኖሬ ሳይከብደኝ እንድኖር የረዳኝ ይመስለኛል» ብላለች።
መልካም የትዳር አጋርነቷን፣ በፈጣሪ የተቸራትን የእናትነት ጸጋዋን ከላይ ከሚታየው የአካል ጉዳት ሁኔታዋ ጋር እያስተያዩ በጎ ያልሆነ አስተያየት የሰጧትም ነበሩ። ሌላው ቀርቶ ጋዜጣ በምታሳትምበት ወቅትም ይሁን የቴሌቪዥን ፕሮግራሟን ስታዘጋጅ «የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ እኔንም ይመለከተኛል!!» ባይ ተቆርቋሪ አለመኖሩና የሚደግፋት ማጣቷ አሳዝኗትም ያውቃል። ነገር ግን ሁሌም የምትሞክር፣ የማትሰለችና ትእግስትን የሕይወት መመሪያዋ አድርጋ የምታምን በመሆኗ ሁሉንም ታግላ አሸንፋለች።
ማርታ እንደምትለው ሕይወት ውስጥ ምንም ዓይነት ፈተና ቢኖር ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ሕይወት ሁልጊዜም ሁለት አመራጭን የምትሰጥ በመሆኗ ይሆናል ወይም አይሆንም የሚለውን አማራጭ ሃሳብ ይዞ እስከ መጨረሻው መታገል ሰው ያለ ምንም ተስፋ መቁረጥ እንዲጓዝ የሚያስችለው መሆኑን ታስረዳለች።
«ሴቶች ስለወለዱ ብቻ በድካም ከመቀመጥ የመውለድ ፀጋነቱን ተቀብለው የልጆች ኃላፊነትንም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን ጎን ለጎን ማስኬድ እንደሚችሉ በማመን መጠንከር ይገባቸዋል» ትላለች።
ሌላው አካል ጉዳተኝነት እንቅስቃሴን ከማገዱ በስተቀር ሌላ ሰፊ አመራጭን የሚያድል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ትላለች።«ለምሳሌ እኔ በልጅነቴ እንደ ሙሉ አካል እንዳላቸው ልጆች ብጫወት ኖሮ መጻሕፍትን የማንበብ ዕድል አይኖረኝም ነበር። መጻሕፍትን በማንበቤ ዛሬ ለምኖርበት ጥንካሬና በራስ መተማመን አይኖረኝም ነበር» ትላለች። ከማርታ ጋር በርካታ ቁም ነገሮችን ተጨዋውተን ለሰው የሚጋባ ጥንካሬዋን ተጋርተን ተመልሰናል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም