ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ረገድ ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅና ማስፋፋትን ይጠይቃል። ይህም የመንግሥትንና የግሉን ዘርፍ ቅንጅትና ትብብር የሚጠይቅ ሲሆን የግሉ ዘርፍ ቴክኖሎጂ በመፍጠር፣ በማስፋፋት ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነና የመሪነት ድርሻ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የኅብረተሰቡን ኑሮ በማቅለል የዜጎችን ምርታማነት የሚያሳድግ፣ የሀገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች በማስፋፋት ረገድ በየዘርፉ የተጀመሩ አበረታች ሥራዎች ለመኖራቸው በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። በቅርቡ የቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ኢንቨስትመንት አውደ ርዕይ ላይ የቀረቡትን የቱሪዝሙን ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችሉ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። «ጉዞ ቴክኖሎጂስ» የተሰኘው ድርጅት የቱሪዝም ዘርፉን ሊያዘምኑ የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሠሩት የቴክኖሎጂ ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
አቶ ዳንኤል ጌታቸው «ጉዞ ቴክኖሎጂስ» መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው። «ጉዞ ቴክኖሎጂስ» የተሰኘው ድርጅት በኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ላይ የሚሠራ ሲሆን፤ አዳዲስ ከሚባሉት የቴክኖሎጂ ዘርፎች ቨርችዋል ሪያሊት (የምናባዊ እውነታ) እና በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ለአራት አመት ያህል ሲሠራ መቆየቱን ይናገራል።
ድርጅቱ በዋናነት የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ትኩረት አድርጎ ዘርፉን ለማስተዋወቅ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠራ እንደነበር የሚናገረው አቶ ዳንኤል፤ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ልዩ ልዩ ቦታዎችና የማይዳሰሱ የቱሪዝም መስህቦች (እንደ መስቀል፣ እሬቻ እና የመሳሰሉትን) ሰዎች ካሉበት ቦታ ሆነው እንዲጎበኙ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ብዙ ሥራዎች ሲሠራ እንደነበር ይገልጻል። በአራት ዓመታት ቆይታ በቱሪዝም ዘርፍ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ቨርችዋል ሪያሊት የዲጂታሉን ዓለም በቀጥታ ከገሃዱ ዓለም ጋር በማያያዝ የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ይናገራል። ቨርችዋል ሪያሊቲ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ስለኢትዮጵያ ቀድመው አውቀውና ተረድተው ይበልጥ እንዲጎበኙ ጉጉትና ፍላጎት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ እንደሆነ ይናገራል።
ሁለተኛው በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ወደ ሌላ ሀገራት ጉዞ የሚያደርጉ መንገደኞች በኢትዮጵያ በሚቆዩበት ውስን ሰዓት ስለሀገሪቱ የቱሪዝም መስህቦች የሚጎበኙ ቦታዎች ምንም ዓይነት የማወቅ ዕድሉን የማያገኙ መሆኑን ነው አቶ ዳንኤል የጠቆመው። እነዚህም ጋር ተደራሽ ለመሆን የቱሪዝም መስህቦችን (ቅርሶቹን) ከያሉበት ወደ አየር መንገድ አምጥቶ ማስጎብኘት ባይቻልም ቨርችዋል ሪያሊቲ በመጠቀም ተደራሽነትን ማስፋት እንደሚቻል ይገልጻል።
ሦስተኛው ለአካል ጎዳተኞች፣ በተለያዩ ምክንያቶች ቦታው ድረስ መሄድ ለማይችሉ ሰዎች እና በጸጥታ ችግር ምክንያት ለመጎብኘት የማይቻሉ የቱሪዝም መስህቦችን ሳይቀር ቨርችዋል ሪያሊቲ ተደራሽ በማድረግ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪዎችን ማስገኘት የሚቻል መሆኑን ነው አቶ ዳንኤል የሚናገረው።
በምናባዊ እውነታ (ቨርችዋል ሪያሊቲ) በመጠቀም በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ጨምሮ ከ20 በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በእያንዳንዱን ሙዚየም ቨርችዋል ሪያሊቲ የሠሩ ሲሆን፤ ሌሎች ፕሮጀክቶችንም እንዲሁ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን መሥራታቸውን አመላክቷል።
«ታሪኩ ሆነ ቴክኖሎጂው ቀደም ሲልም ጀምሮ ያለ ሲሆን አሁን ላይ እኛ ዘዴውን እየፈጠርን ነው ያለነው» የሚለው አቶ ዳንኤል፤ እስካሁን በድረገጽ፣ በቪዲዮ እና በመሰል ቴክኖሎጂ ዘዴዎች ተጠቅመው ሲሠሩ እንደነበርና አሁን ደግሞ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ በቨርችዋል ሪያሊቲ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም አንድን ነገር ለሰዎች ቅርብ አድርጎ በማሳየት ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራ ነው።
በተመሳሳይ ድርጅቱ በትምህርት ዘርፍ ላይ እየሠራ መሆኑን የሚናገረው አቶ ዳንኤል፤ በምናባዊ እውነታ (ቨርችዋል ሪያሊቲ) በመጠቀም ለመማሪያ አቅርቦት ደረጃ ብዙ ወጪ የሚጠይቁትን በአነስተኛ ወጪ በመሥራት ተማሪዎች በቀላሉ እንዲማሩና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ የሚያስችል ሥራን እየሠሩ መሆኑን ይናገራል። አሁን ላይ ከተወሰኑ ተቋማት ጋር በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት ማስተማሪያ ዘዴዎች እየሠሩ መሆኑን አመላክቷል።
አቶ ዳንኤል እንደሚለው፤ «ጉዞ ቴክኖሎጂስ» የቴክኖሎጂ ተቋም እንደመሆኑ መጠን አንድ የቴክኖሎጂ መሣሪያ በተለያዩ መስኮች እያስገባ መፍትሔ የሚሰጡ ፕሮጀክቶችንና ሃሳቦችን የሚያስተዋውቅ ድርጅት ነው። በቱሪዝም ዘርፍ አሁን ላይ የሚጎበኙ ታሪኮች፣ የድሮ ቅርሶች እና መሰል የቱሪዝም መስህቦችን በቨርችዋል ሪያሊቲ መግለጽ ይቻላል። በተለይ አሁን ላይ ልናገኛቸው የማንችላቸውን እንደ ዓድዋ ጦርነት ያሉ ሁነቶችን ለመጎብኘት ብንፈልግ ቦታው ላይ ብንሄድ የምናገኘው ተራራ ብቻ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከመጽሐፍና ከፊልም የምናገኛቸው ነገሮች ይኖራሉ። ይሁንና የዓድዋን ጦርነት በቨርቹዋል ሪያሊቱ ማሳየት ተችሏል።
ይህ በምናባዊ እውነታ /ቨርችዋል ሪያሊቲ/ ቴክኖሎጂ) «እስቶሪ ቤዝድ ዓድዋ» የሚል ፕሮጀክት ተሠርቶ ሰዎች (ጎብኚዎች) ካሉበት ቦታ ሆነው በቨርችዋል ሪያሊቲ አማካኝነት የዓድዋን ሁነት እንዲያዩ እና ልክ የዚያን ዘመን አካል ሆነው እንዲጎበኙ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነም አመላክቷል።
አንድን የቱሪዝም መስህብ ስናስተዋውቅ ለማስተዋወቅ የምንጠቀምበት መንገድ በቨርችዋል ሪያሊቲ መሆኑ ትልቅ ጠቀሜታ ከፍ ያለ እንዲሆን ያደርገዋል የሚለው አቶ ዳንኤል፤ ሰዎች የዚያ ታሪክ አካል ሆነው እንዲጎበኙ ያስችላቸዋል። የጎብኚዎች ቁጥርም እንዲጨምር ያደርጋል ይላል።
‹‹ሌላው ደግሞ በጣም ያለፉ ታሪኮችን በአካል ብንሄድ ልናገኛቸው የማንችለው ለአብነት የፋሲል ቤተመንግሥት ብንወስድ ቤተመንግሥቱ ቦታው ላይ ልናገኘው እንችላለን፤ ነገር ግን በዚያ ዘመን የነበረው ድባብና እንዲሁም ሲጠቀሙባቸው የነበረውን ቁሳቁሶች ማየት አንችልም። ይህንን ለማየት ስንፈልግ የምናገኘው አብዛኛውን በፊልም የተሠራውን ነው። ነገር ግን ሰዎች እንዲጎበኙት በሚያስችል መልኩ በምናባዊ እውነታ ተጠቅሞ ቢሠራ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ እንዲያዩ ያስችላል። የዚያን ዘመን አሁናዊ ሁኔታ እንድናይና እንድናሸት የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ የሀገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻዎች ይበልጥ ለማስተዋወቅ ዕድል ይሰጣል›› ይላል።
ለአብነት ሩዋንዳ መሄድ ባይቻል እንኳን በቨርችዋል የመገናኛ መንገዶችን በመጠቀም ልናወራ እንችላለን። እንዲሁም ቅርሶችን በአካል ሄዶ መጎብኘት ባይቻልም በቨርችዋል ሪያሊቲ መጎብኘት ይቻላል። ይበልጥ ተመራጭ የሚሆነው ደግሞ በቨርችዋል ያዩትን በአካል ሄደው ለማየት እንዲጓጉ በማድረግ ፍቅሩ እንዲያድር የሚያደርግ መሆኑ እንደሆነ ይናገራል።
በተመሳሳይም በአየር መንገድ ላይ ይህንን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የቱሪዝም መስህቦችን እዚያ ባሉበት እንዲያዩቸውና እንዲያውቋቸው በማድረግ ማስተዋወቅ እንደሚቻል ይናገራል። አሁን ላይ በአየር መንገድ የሚታየው የቡና ሥነሥርዓት (ሴሪሞኒ) እና የተለያዩ ባሕላዊ አልባሳት የሚቀመጥበት መሆኑን ጠቅሶ፤ በቨርችዋል ሪያሊቲ ከዚህ ላቅ ባለ ደረጃ የሀገራችን የቱሪዝም መስህቦች በማስተዋወቅ ጎብኚዎች በቀላሉ እንዲያዩ በማስቻል ቱሪዝሙ ብቻ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት የሚቻል እንደሆነ ነው አቶ ዳንኤል ያመላከተው።
እስካሁን ይዘቶችን በማዘጋጀት ረጅም ጊዜ እንደወሰዱ የሚጠቁመው አቶ ዳንኤል፤ ከፌዴራልና ክልል መስሪያ ቤቶች እና የቱሪዝምና የባሕል ተቋማት ጋር አብሮ በመሆን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መሥራታቸውን ይናገራል። በቀጣይ ይህንን በማሳደግ በቨርችዋል ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የሀገሪቱን የቱሪዝም መስህቦች ለዓለም የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠሩ ይገልጻል።
‹‹በኮቪድ ጊዜ ሁሉ ነገር ዝግ በሆነበት ሰዓት በቨርችዋል ሪያሊቲ ተጠቅሞ ቱሪዝሙ ዘርፍ እንቅስቃሴ እንዳይቆም ማድረግ ይቻል ነበር፤ እኛ ዘግይተናል። ›› የሚለው ዳንኤል፤ ይህ ሀገር በቀል ድርጅት በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት መፍትሔዎች በማሰብ የሚሠራ እንደሆነ ይገልጻል። ድርጅቱ የመፍትሔ ሃሳቦችን በመፍጠር ከሌሎች ሀገራት በተሻለ መልኩ የእኛ ሀገር የቱሪዝም መዳረሻዎች ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ለማስተዋወቅ እንደሚተጋ አመላክቷል።
አቶ ዳንኤል ‹‹ጉዞ ቴክኖሎጂስ›› የነበሩ የቱሪዝም መስህቦች ቨርችዋል አድርጎ ለእይታ የማቅረቡ ሥራ እንዳለ ሆኖ አሁን ላይ የሌሉትን መስህቦች ደግሞ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ከተለያዩ የታሪክ መዛግብት እንዲሁ በታሪኩ ዙሪያ ጥናት ካደረጉ ታሪኩን የሚያወቁ ተመራማሪዎችን በመጋበዝ ባለሙያዎች በማምጣት የሚሠራ እንደሆነ ይናገራል። ለምሳሌ ዓድዋ፤ ቦታውን ሊገልጹ የሚችሉ ቀድሞ የተሳሉ ስዕሎች እና የመጻሕፍት ላይ ፎቶዎች ወስዶ በመጠቀም በተቻለ መጠን አካባቢውን ሊገልጹ የሚችሉ ነገሮችን በመውሰድ ታሪኩን እንደ አዲስ እንደገና በመፍጠር በቨርችዋል ቴክኖሎጂ እንደሚሠራ ይገልጻል። በተመሳሳይ የዓድዋ ተራሮችን ለመሥራት ቴክኖሎጂው በፈቀደልን ልክ እንደገና ዳታዎችን በመውሰድ የሚሠራ ይሆናል። ‹‹ተራሮችን በአካል ልናገኛቸው እንችላለን ማግኘት የማይቻለው የወቅቱ ድባብ ነው›› የሚለው አቶ ዳንኤል፤ ነገር ግን የተለያዩ ፈጠራዎችን በመጠቀም ያንን እሳቤ ማምጣትና በመፍጠር ከታሪኩ ጋር ተናብቦ ታሪኩን ሊገልጽ እንደሚችል ተረጋግጦ ልክ እንደ ፊልም የሚሠራ ነው» ይላል።
‹‹ይህንንም የታሪኩ ባለቤቶችና ታሪኩን የሚያወቁትን ሰዎች በማሳተፍ ቴክኖሎጂን አንድ ላይ በማምጣት ወደ ሚታየው ምናባዊ ፈጠራ እናመጣለን›› የሚለው አቶ ዳንኤል፤ ሙዚየሞችንም ሆነ ቅርሶችን ሲሠሩ ፎቶ ስካን የሚባል ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚሠራ እንደሆነ ይናገራል። ‹‹ለአብነት የሰው ዘር መገኛ የሆነችውን ‹‹ሉሲን›› በሙዚየም ስንመለከት በእጃችን መንካት ሆነ መዳሰስ አንችልም። ነገር ግን በደንብ ለማየትና ለመዳሰስ በሚያስችል መልኩ በፎቶ ስካን ወደ 3ዲ ቴክኖሎጂ በመቀየር በቀላሉ እንድትያዝና እንድትጨበጥ አድርጎ እንድትጎበኝ ማድረግ ይቻላል›› ይላል።
በተለይ የወደሙ ቅርሶች ሙሉ አካል ለመፈጠር በቦታው መገኘትና መሥራት የሚያስፈልጋቸው ቅርሶች ስለሚኖሩ በቦታው ድረስ በመሄድ የተለያዩ ዘዴዎች ተጠቅሞ በመሥራትና እንዲገጣጠሙ በማድረግ ሙሉ የቅርሱን የቀድሞ ይዞታ እናገኛለን የሚለው አቶ ዳንኤል፤ ታሪክን ላለማፍረስ የታሪክ ባለሙያዎች ይዞ መሥራት የግድ እንደሆነም ነው የሚናገረው።
ይህንን ዓይነት ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ፕሮጀክቶች መሥራት ብዙ ውጪን እንደሚጠይቁ የጠቆመው አቶ ዳንኤል፤ ‹‹ይህንን የእኛን ሃሳብ አምነውበት የተወሰነ ፈንድ የሚደርጉ የውጭ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አሉ፤ ድርጅቱን ከተለያዩ ሥራዎች የሚያገኘውን ገንዘብ ለእንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ላይ ያውላል›› ይላል። የሚሠሩትን ሥራ ሃሳቡን ሊወዱት፤ ሊያደንቁት የሚችሉ ብዙ ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሶ፤ ነገር ግን የወጪው ጉዳይ ሲነሳ በብዙ ተቋማት ከባድ ስለሚሆንባቸው አብሮ ለመሥራት ወደ ኋላ እንደሚሉም ተናግሯል። እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክት አብዛኛው ጊዜ ለትርፍ ታስበው ሳይሆን ለሀገር ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አንጻር ታይተው የሚሠሩ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ሥራው ብዙ ወጪን የሚያስወጣ፤ ለሥራው የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎች ከውጭ ማምጣት የሚጠይቅ ሲሆን እነዚህ ቁሳቁሶችም እንደ ቅንጦት ዕቃዎች ስለሚታዩ ያለው የታክስ ወጪም ሥራውን ለመሥራት የሚያበረታታ እንዳልሆነ ይገልጻል። እስካሁ ባለው ሥራ ሁሉንም ነገር በራሳቸው እየተጋፈጡ እየሠሩ መሆኑን ገልጾ፤ በጊዜ ሂደት ለውጦች ይኖራሉ ለሚል ተስፋ እንዳለውም አጫውቶናል።
አቶ ዳንኤል፤ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ ቱሪዝምን የሚያስተዋውቁ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሆነ ይናገራል። በሌላ መልኩ በጨዋታ (ጌም) መልኩ እንዴት የሀገራችንን ቅርጾች ማስተዋወቅ ይቻላል የሚለውን ሃሳብ በጨዋታ መልኩ ይዘው እንደቀረቡ ይናገራል። ‹‹ይህም አእምሮአችን እየተዝናና የቱሪዝም መስህቦችን የሚጎበኝበት ሁኔታ እንዲኖር የሚያደርግ ነው›› ይላል።
አውደ ርዕዩ የሀገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚያስተዋወቅ ሥራ ተቀራራቦ መሥራት የሚያስችል እንደሆነ በመግለጽ፤ ‹‹እኛ በግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂው ላይ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግን በመንግሥት ዘርፍ ቱሪዝም ላይ ይሠራል። ስለዚህ ሁለታችንም ቱሪዝም ላይ የምንሠራ በመሆኑ ተቀራራበው መሥራት ይጠበቅበናል›› ይላል።
እንደዚህ ዓይነት አውደ ርዕዮች መዘጋጀታቸው ያሉንን ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎች ለኅብረተሰቡ በማሳየት እንደሀገር ያለንን የቴክኖሎጂ አቅም ማሳየት የሚያስችል ነው የሚለው አቶ ዳንኤል፤ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ተጨማሪ ፕሮጀክቶች ለመሥራት የሃሳብ ልውውጦች እንዳሉ ጠቅሶ፤ በቀጣይ በጋራ የሚሠሩ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራም ተናግሯል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም