በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠያቂነትን ለማስፈን ከ630 በላይ መዝገቦች ተከፍተዋል

አዲስ አበባ:- በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተጠያቂነትን ለማስፈን ከ20 በላይ ትልልቅ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንደተመሰረተባቸውና ከ630 በላይ መዝገቦች በፍርድ ቤት ክርክር ላይ እንደሚገኙ ብሄራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2015 ዓ.ም በጉዳዩ የተጠረጠሩ ከ20 በላይ ትልልቅ ተጠርጣሪዎች ክስ ተመስርቶባቸው በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ይገኛሉ። ከ630 መዝገቦች በላይ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ አንስቶ እስከ ደቡብ አፍሪካ በተዘረጋ የሰው ንግድ ሰንሰለት ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ከ20 በላይ ትልልቅ ተጠርጣሪዎች ክስ ተመስርቶባቸው ክርክር ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

የሕግ ማስከበር ሥራው እየተሻሻለ ቢገኝም ተግባሩ ሊጠናከር ይገባዋል ያሉት ኃላፊው፤ አሁንም ዋናዎቹን ደላሎች ከመያዝ፣ ግንኙነታቸውን ከመበጣጠስ፣ በመልማዩችና በመዳረሻ ሀገራት ባሉ ተቀባዩች ያለውን ትስስር በማፍረስ በኩል ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ አመልክተዋል።

ሀገር ውስጥ በሁሉም አካላት ጠንካራ ትብብር ማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር እና ተጎጂዎች በፖሊስ ጣቢያ መጥተው ከሚተገበረው የወንጀል ምርመራ አሠራር መውጣት መፍትሄ መሆኑንም ነው የተናገሩት። ይህንን ለመተግበር ጠንካራ እና ቅንጅታዊ አሠራር መዘርጋት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከወንጀል ተሳታፊዎቹ የበለጠ የተደራጀ አቅም እና ቅንጅት መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል።

ድርጊቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ክልሎች አባል የሆኑበት ብሄራዊ ምክር ቤት መቋቋሙን፤ በፌዴራል ደረጃ በፍትህ ሚኒስቴር የሚመራ ብሄራዊ የትብብር ጥምረት የፍልሰት አስተዳደር መዘርጋቱንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አብርሃም ገለፃ፤ አሁንም ዜጎች በበረሃ ለማቋረጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለስቃይ እና ለሞት ይዳረጋሉ። ከግንዛቤ ፈጠራው ጎን ለጎን፤ ደላሎችን፣ መልማዮችን፣ አዘዋዋሪዎችን ለሕግ በማቅረብ መደበኛውን ፍልሰት የሚያበረታቱ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል። ወንጀሉን በደህንነት መረጃ ጥናት ላይ በመመስረት የወንጀለኞቹን መረብ ሊበጣጥስ የሚችል ሥራ መሠራት አለበት።

የዜጎች በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር እንቅስቃሴ የሀገር ገጽታ የሚያበላሽ፣ አንገት የሚያስደፋ ከፍተኛ ችግር ያለበት በመሆኑ ብዙ ሥራ መሠራት አለበትም ሲሉ አክለዋል።

500 ሺህ ሰዎችን በሕጋዊ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር ለመላክ በመንግሥት የተቀመጠው እቅድ በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በከፍተኛ መጠን በመቀነስ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣልም ብለዋል።

ዘላለም ግዛው

 አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You