በመጪው ሕዳር አዲስ አበባ ከሚካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እውቅ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ጎን ለጎን በበይነ መረብ የታገዘ ሩጫ በእንግሊዝ ለንደን እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ ዓለም አቀፍ ይዘት ባለው በዚህ የሩጫ ውድድር ላይ የውጭ ሀገራት ዜጎች በብዛት ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑንም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡
ሳምንታት ብቻ የቀሩት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘንድሮ ለ22ኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች እንዲሁም በርካታ አትሌቶች የሚካፈሉበት ይህ ሩጫ በዋናነት በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዘንድሮ ግን ከኢትዮጵያ ባለፈ ኑሯቸውን በአውሮፓ ያደረጉ ዜጎች በኢንተርኔት ታግዘው ርቀት ሳይገድባቸው (የቨርቹዋል) ሩጫ እንዲካፈሉ የሚደረግ መሆኑን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ኑሯቸውን በእንግሊዝ ያደረጉ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት በዋና ከተማዋ ለንደን በኢንተርኔት የታገዘ ‹‹Virtual Run›› ያካሂዳሉ። በዚህ ሩጫ ላይም 200 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ይሳተፋሉ ተብሎ በሚጠበቅ ሲሆን፤ ውድድሩ በአዲስ አበባ በሚደረግበት ተመሳሳይ ቀን ህዳር 09/2016ዓ.ም የሚከወንም ይሆናል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሰል ውድድር ሲያካሂድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፤ ከዚህ ቀደም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመላው ዓለም መሰራጨቱን ተከትሎ የጋራ ሩጫ ውድድሩ በመሰረዙ በኢንተርኔት አማራጭ በመላው ዓለም ማካሄድ ተችሎ ነበር፡፡
በመላው ዓለም እጅግ ተወዳጅ ከሆኑ የጎዳና ላይ ውድድሮች መካከል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ውድድሩ አዝናኝ ከመሆኑ ባለፈ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከሌሎች ሀገራት የተገኙ በርካታ አትሌቶች ተካፋይ የሚሆኑበትም ነው፡፡ በዓለም የማራቶንና የጎዳና ሩጫዎች ማህበር (AIMS) ዕውቅና ያለው እንደመሆኑም የ 10 ኪሎ ሜትር ሩጫው ዓለም አቀፍ ይዘትን የተላበሰ ነው፡፡ በመሆኑም የውጭ ሀገራት ዜጎች በብዛት ተሳታፊ እንደሚሆኑበት ታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ አምባሳደሮች እና የኤምባሲ ሠራተኞች የተሳትፎ ክብረወሰን ለመስበርም እየተሠራ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከ20 በላይ የተለያዩ የውጭ ኤምባሲዎች ምዝገባ ተከናውኗል ተጨማሪ ተሳታፊዎችም የሚጠበቁ መሆኑንም ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአዲስ አበባ ከሚገኙ ኤምባሲዎች ፍላጎት ጎን ለጎንም ከመቶ በላይ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ይገኛሉ፡፡ ሩጫው ከኢትዮጵያ ውጪም ፍላጎት እያሳደረ በመሆኑ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ለሚገኙ በርካታ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች የተሳትፎ ጥሪ ካደረገ በኋላ ብዙ ተሳታፊዎች በመመዝገብ ላይ ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘም የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ ህሊና ንጉሴ በሩጫው ላይ ያለው ዓለም አቀፍ ፍላጎት በአዲስ አበባ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው ዝግጅት እና በዓለም ላይ ካሉ ልዩ ልዩ ሀገራት የመጡት ሯጮች ተሳትፎ የተገኘ መሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹በእውነቱ ልክ እንደሌሎች የጎዳና ላይ ሩጫዎች ልዩ የሆነ የጎዳና ውድድር ነው። በተጨማሪም ጠንካራ የአትሌቶች ውድድር አለው፡፡ ነገር ግን ይህን ሩጫ ልዩ የሚያደርገው የካርኒቫል ድባብ እና በተሳታፊዎች የሚደረገው የሚያነቃቃ መንፈስ ነው›› ሲሉም አብራርተዋል።
የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ‹‹ክትባት ለሁሉም ህጻናት›› በሚል መሪ ሃሳብ ከ44 ሺ በላይ ተሳታፊዎች ይታደሙበታል። የሩጫው አካል ለመሆንም የጎረቤት ሀገር ኬንያ እና ኡጋንዳ አትሌቶችን ጨምሮ የደቡብ አፍሪካ፣ ህንድ፣ ብራዚል፣ ስዊዘርላንድ፣ አውስትሪያ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ሯጮች ተሳትፎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከሯጮች ባለፈ የውጪ ሀገራት መገናኛ ብዙሃንም ሁነቱን በዘገባቸው ሽፋን ለመስጠት አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ ይሆናል፡፡ ከእነዚህም መካከል ባለፉት 30 ዓመታት በዩሮስፖርት ኮሜንታትርነት ሲሠራ የቆየው እንግሊዛዊው ቲም ሃቺንስ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንግሊዛዊው የቀድሞ የመካከለኛና ረጅም ርቀት አትሌት ቲም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉባቸውና ድል ያደረጉባቸው ውድድሮች ሽፋን በመስጠትም ይታወቃል፡፡ ይኸውም የስፖርት ቱሪዝምን ከማስፋፋት አንጻር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም