የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ሀገር በቀል ከሆነው ሁሉ ስፖርት ቤቲንግ ከተባለ የውርርድ ተቋም ጋር በጋራ ለመሥራት የ11 ሚሊየን ብር የአጋርነት ስምምነት ተፈራርሟል። በሁለቱ አካላት መካከል የተፈረመው ውል ለሁለት ዓመት እንደሚቆይም ታውቋል። ሁሉ ስፖርት ቤቲንግ ለፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበሩ በገንዘብ ከቫት ውጪ 6 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በጥሬ እቃ በገንዘብ ሲሰላ 6 ሚሊዮን ብር የሚሰጥ መሆኑ ትናንት ፊርማው ሥነ ሥርዓት ላይ ተነግሯል።
የውርርድ ተቋሙ በአንፃሩ አርማው ያረፈበትን የመጫወቻ ኳሶችን ከቀጣይ ጨዋታዎች ጀምሮ በማቅረብ እንዲሁም የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር አባላት፣ የውድድር እና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴዎች፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች እና ሌሎችም የውርርድ ተቋሙ አርማ ያረፋበትን ልብሶች አድርገው ሜዳ ላይ እንዲታዩ ይፈልጋል።
አክስዮን ማህበሩ ከዚህ ቀደም የፕሪሚየር ሊጉን የስያሜ መብት ከገዛው ‹‹ቤት ኪንግ›› ጋር ያለ ስምምነት መለያየቱ የሚታወስ ነው። ቤት ኪንግ የሀገሪቱን የፋይናንስ ሕግ ጠብቆ መሥራት ባለመቻሉ በራሱ ጊዜ እንደወጣም ተብራርቷል። ከሁሉ ስፖርት ጋር የተደረገውን ስምምነትም የሊጉን አክሲዮን ማህበር በመወከል ሥራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሰይፈ እና የሁሉ ስፖርት ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይትባረክ ካሳሁን ተፈራርመዋል። ሁለቱ አካላት ስምምነቱን ከፈጸሙ በኋላም የመጫወቻ ኳስ ርክክብ አድርገዋል።
ስምምነቱ ከስድስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግም ይሆናል። ስምምነቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፣ አክስዮን ማህበሩ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሀብት ማመንጨት እንደሚችል ማሳየት የቻሉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ‹‹ቤት ኪንግም ከኢትዮጵያ የወጣው በምሬት ሳይሆን ሥራ መሥራት አቅቶት እና የሀገሪቱን ሕግና ሥርዓት ጠብቆ መሥራት ባለመቻሉ ነው›› ሲሉም አስረድተዋል። አዲሱ ስምምነትም በተቀመጠው የአሰራር መመሪያና ደንብ መሠረት የሚቀጥልና ከዛ ውጭ ከሆነ ግን እንደሚያስጠይቅ ጠቁመዋል።
ማህበሩ ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ የውድድር ኳስ የሚያቀርበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሆኑን የጠቀሱት አቶ ክፍሌ፤ አሁን ግን ኳስ ስለተወደደና ሀገር ውስጥ ለማስገባትም አስቸጋሪ በመሆኑ ሁሉ ስፖርት መፍትሔ ይዞ እንደመጣ ገልጸዋል። የሚቀርበው ኳስም በፊፋ የጥራት ደረጃን ያሟላና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ጥራቱን እንደሚያረጋግጥ ተጠቁሟል። ክለቦችን ከስምምነቱ ጋር ለማጣጣም ውይይት መደረጉንም አክለዋል።
የሁሉ ስፖርት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይትባረክ ካሳሁን፣ ፕሪሚየር ሊጉ ብዙ ድጋፎችን የሚፈልግ በመሆኑ ከቁሳቁስ አቅርቦት ጋር የተያያዘውን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ስምምነት እንደተደረገ ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በዲኤስ ቲቪ ቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ሲያገኝ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘንድሮ መቋረጡ ይታወቃል። ከ6ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ጨዋታዎች ጀምሮ ግን የቀጥታ ሥርጭት ሽፋኑ እንደሚመለስ በስምምነቱ ወቅት ተጠቁሟል።
ስለተቋረጠው የሊጉ የቀጥታ ሥርጭት ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የአክሲዮን ማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ፣ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከመጀመሩ አስቀድመው ውድድሩን ከሱፐር ስፖርት ሰዎች ጋር ያለፉትን ዓመታት የሥርጭት ሂደት መገምገማቸውን አንስታውሰዋል። ዘንድሮም 180 ጨዋታዎችን በቀጥታ ለማስተላለፍ የታሰበ ቢሆንም አልተሳካም።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ የዘንድሮ የቀጥታ ሥርጭት ላይ እክል ያገጠመውም ከዚህ ቀደም ባለፉት ሦስት ዓመታት የሊጉን ጨዋታዎች የፕሮዳክሽን ሥራ ለመሥራት ከሱፐር ስፖርት ጋር ስምምነት የነበረው “ላይቭ አይ” የተባለ መቀመጫውን በኬንያ ያደረገ ተቋም በድንገት መቅረቱን ተከትሎ ነው። በዚህም የነበረውን ክፍተት ለመሙላት የመጀመሪያውን የጨዋታ ሳምንት ከአንድ የሀገር በቀል የሚዲያ ተቋም በተገኙ መሳሪያዎች ጨዋታውን ለማስተላለፍ ጥረት ቢደረግም ሥርጭቱ ከጥራት ጋር ተያይዞ በቀረበበት ጥያቄ እንዳይቀጥል ተደርጓል። ይህን ተቋም በዘላቂነት ለመተካትም ከሌሎች የሀገር በቀል ተቋማት ጋር ንግግሮች ቢደረጉም የጠየቁት ዋጋ እጅግ የተጋነነ መሆኑን ተከትሎ ሱፐር ስፖርት ሌሎች አማራጮችን ሲያጤን ቆይቷል።
በዚህም ሱፐር ስፖርት የሊጉን ስርጭት ለማስቀጠል መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ካደረገ የፕሮዳክሽን ተቋም ጋር ስምምነት የፈፀመ ሲሆን በቀጣይም ከስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታዎች አንስቶ የሊጉን የቀጥታ ሥርጭት ዳግም እንደሚጀምር ማረጋገጫ መስጠቱን አቶ ክፍሌ ተናግረዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም