ኢትዮጵያ ታላቅ እና የሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤት ብቻ ሳይሆን፤ ያልተቆራረጠ ሥርዓተ መንግሥት ባለቤት ስለመሆኗ አያሌ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል። የእነዚህ የታሪክና የሥርዓተ መንግሥት መሰናሰሎች ደግሞ፤ ኢትዮጵያን ገናን ስም፣ ደማቅ ገጽ፣ በዘመን ጅረት የማይደበዝዝ ገድል ባለቤት ሆና በዓለም እንድትገለጥ አድርገዋታል።
ምክንያቱም ኢትዮጵያ ታሪኳ ሲነሳ ቀድመው ከሚነሱ ጉዳዮቿ መካከል አንዱ፣ የነፃነት ሳይሆን የድል በዓል አክባሪነቷ ነው። ይሄ የድል በዓል ባለቤትነት ክብሯ ደግሞ አንድም ካልተቆራረጠ ሥርዓተ መንግሥት ያላት ከመሆኗ የሚመነጭ ነው። ሁለትም፣ በዚህ ያልተቆራረጠ ሥርዓተ መንግሥት ኑረት ውስጥ እየተገነቡ የመጡ ሀገራዊ ተቋሞቿ አማካኝነት የተገኘ ነው።
ከእነዚህ ዕድሜ ጠገብ የኢትዮጵያ ከፍታ ማሳያ ተቋማት መካከል ደግሞ አንዱና ዋነኛው ተደርጎ የሚጠቀሰው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር/ተቋም ነው። ይሄ ከአንድ ምዕተ ዓመት የተሻገረው ኢትዮጵያ የመከላከያ ተቋም ግንባታ እውነት፣ የራሳቸውን የመከላከያ ተቋም ፈጥረው ሉዓላዊነታቸውን ማስቀጠል ከቻሉ ቀዳሚ ሀገራት መካከል አንዷ የሚያደርጋትም ነው።
ዛሬ 116ኛ ዓመቱ የሚዘከርለት የኢትዮጵያ የመከላከያ ተቋም ምስረታ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ ሉዓላዊነትና ደህንነታቸው ተጠብቆ በክብር እንዲኖሩ ያስቻለ፤ ከሀገርም አልፎ ከፍ ያለ ዓለምአቀፍ ስምና ዝናን ያተረፈ የመከላከያ ሠራዊት እንዲፈጠር ዕድል የሰጠ ሆኗል።
ይሄ የመከላከያ ሠራዊት ደግሞ፣ ትናንት በአያት ቅድመ አያቶቹ ከፍ ያለ መስዋዕትነት ጸንታ የቆየችውን ኢትዮጵያ፤ ሉዓላዊነቱን አስከብሮና ነፃነቱን አጽንቶ የኖረውን ኢትዮጵያዊ፤ በነፃነቱ ልክ፣ በልዕልናው ከፍታ ላይ እንዲዘልቅ የማስቻል ኃላፊነትን የተሸከመ የሀገር ዓርማና ጋሻ የሆነ ኃይል ነው።
ይሄ ኃይል፣ በፈተና ውስጥ ተፈትኖ፤ እንደ ወርቅ በእሳት ነጥሮ እንዲወጣ ተደርጎ የተሠራ ነው። ይሄ ኃይል ኢትዮጵያን መስሎ የተሠራ፤ ኢትዮጵያን ሆኖ ኖሮ የሚያልፍ፤ ስለ ሀገሩና ሕዝቡ ሲል አንድያ ነፍሱን እስከመስጠት አለኝታነቱን በተግባር እየገለጠ ያለ የሀገር ዋልታ፤ የጠላ ት ራስ ምታት የሆነ ሠራዊት ነው።
ይሄ ኃይል፣ በየዘመኑ የሚፈራረቁ ሥርዓቶች እንደየራሳቸው አድርገው ሊሠሩን ቢጥሩም ተቋማዊ ቅርጹን ጠብቆ ሀገራዊ አለኝታነቱን እያረጋገጠ የዘለቀ የሕዝብ ልጅ ሕዝባዊ ኃይል ነው። ይሄ ኃይል የሀገሩን ሠላምና ዳር ድንበር አስጠብቆ፣ የዓለም ሠላም እንዲከበር ድንበር ሳያግደው፣ ውቂያኖስን አቋርጦ ለዓለም ሕዝብ ሁሉ የሠላም አቅም መሆን የቻለ ኃይል ነው።
ዛሬም ስለ ሀገሩ ከፍታ ሲል እየሞተ፣ አካሉን እያጎደለ፣ ደሙን እያፈሰሰና አጥንቱን እየከሰከሰ ለኢትዮጵያ አጥር፤ ለኢትዮጵያውያንም የሕልውናቸው ጋሻ የሆነ ኃይል ነው። ዛሬም፣ ሕዝባዊነቱን የሚያረጋገጥ ሕብረ ብሔራዊነቱን ተላብሶ፤ ጊዜው የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ ታጥቆ፤ የአሸናፊነቱን ልዕልና ተጎናጽፎ ከፍ ብሎ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ እንድትጓዝ አለኝታነቱን በዋጋ እያረጋገጠ ያለ ኃይል ነው።
ዛሬም፣ ስለ ኢትዮጵያ ውድቀት፣ ስለ ኢትዮጵያውያን ውርደት ከውስጥም ከውጭም ተባብረው የሚለፉ እኩያን፤ ቢችሉ እንዳይሞክሩ፣ አይ ብለው ከሞከሩም በአጭሩ እንዲቀሩ የሚያስችለውን ግርማ ሞገስ ተላብሶ በአደባባይም፤ በግንባርም የሚገለጥ የሀገር አቅም ነው።
ባለ ብዙ ገድሉ፣ ባለ ብዙ ገጹ፣ ባለ ብዙ የቤት ሥራው፣… የኢትዮጵያ መከላከያ ተቋምና ሠራዊት ታዲያ፤ ዛሬ 116ኛ የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል። ይሄን በዓሉን ሲያከብርም እንደ ትናንቱ ዛሬም የሀገር አለኝታነቱን እያረጋገጠ፤ የሕዝብ ወገንተኝነቱን እየገለጠ ነው። በፈተና ውስጥ ጽናቱን፤ በእሳት ውስጥ አብሪነቱን፤ በችግር የማይበገር አሸናፊነቱን እያረጋገጠ ነው።
ይሄ ደግሞ የትናንት የአባት አያቶቹ ውርስ፤ የዛሬ የባለታሪክ ባለቤትነቱ፤ የነገ አደራ አስረካቢነቱ ስሪት ማሳያው ነው። ትናንት አባቶቹ ያስረከቡትን ሀገር ጠብቆ ከፍ ወዳለ ልዕልናዋ የመሸጋገር ኃላፊነቱን እየተወጣ ስለመሆኑ ምስክር ነው።
የመከላከያ ሠራዊት በዓል ደግሞ በዚህ ረገድ የተለየ ገጽ አለው። በበዓሉ የትናንት ታሪኩ ይዘከራል፤ የዛሬ ጀብዱው ይነገራል፤ የነገ የጉዞ መስመሩ ይመላከታል።
በትናንት ታላቅ ስሙ ላይ የዛሬውን ጀብዱ ደርቦ፣ ስለ ነገ መዳረሻው ከፍ ያለ እሳቤ በአደባባይ ይናገራል። ከፍ ያለችው ኢትዮጵያን ከፍ ያደረገበት አቅሙ፤ በከፍታዋ ላይ የማቆየትና የማሸጋገር አቋሙ ይተነተንበታል። በዚህም ትውልድ ይማርበታል፤ ወገን ይኮራበታል፤ ጠላት ግን ይርድበታል።
ይሄ የመከላከያ ሠራዊት የምስረታ በዓል መከበሪያውም መገለጫውም እውነት ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደ ተቋምም፣ እንደ ሠራዊትም በዓሉን ሲያከብር የሚገለጥ፣ የሚነገር፣ የሚተረክ፣ የሚተላለፍ ታሪክም ግብርም ኖሮት ነው። ይሄ የትናንት እና የዛሬ ብቻ ሳይሆን፤ ለነገም የሚሸጋገር ነው።
ይሄ ደግሞ የሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን የሀገርና የሕዝብ ገድል ነው። የሺህ ዓመታት የሀገርና የሥርዓተ መንግሥት ምስረታ ታሪክ፤ የሺህ ዓመታት የሕዝብ ነፃነትና ሉዓላዊነት ታሪክ፤ የሺ ዓመታት የሀገር ክብርና አሸናፊነት ታሪክ፤… ደምቆ እንዲገለጥ ምክንያት የሆነ የአይበገሬዎቹ የሀገር አለኝታዎች በደም የተጻፈ፤ በሕይወት ዋጋ የታተመ ድርሳን ነው። ይህ እንዲሆን ላደረጋችሁ፤ በየዘመኑም ኢትዮጵያን ላጸናችሁ የኢትዮጵያ ወታደሮች ክብር ይግባችሁ። ለ116ኛው የምስረታ በዓላችሁም እንኳን አደረሳችሁ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም