‹‹ሴትን ልጅ ማስተማር ህብረተሰቡን ማስተማር ነው›› የሚለው አባባል ሴቶች በማህበረሰብ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸው መሆኑን የሚገልጽ ነው:: ሴቶች ጥራት ያለው የትምህርት ዕድል ካገኙና ጤናቸው እንዲሁም ደህንነታቸውና መብታቸው ከተጠበቀ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ይታመናል:: ይሁንና በርካታ ሴቶች በብዙ ዕድል ማጣትና ኋላቀር በሆኑ አስተሳሰቦች ምክንያት አቅማቸውን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል:: ከዚህም በላይ ሴቶች በብዙ ችግርና ፈተናዎች ውስጥ ሲያልፉ መመልከት የተለመደ ነው::
ሴቶች ከሚገጥሟቸው በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች መውጣት እንዲችሉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚያደርጉት ጥረት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም:: በተለይም የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ሴት ልጆች ከሚገጥሟቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መላቀቅ እንዲችሉ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል:: በመሆኑም ዕድሉን ያገኙና ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው በርካታ ሴቶች እንቅፋቶቻቸውን መሻገር ችለዋል:: ከራሳቸው አልፈውም ለሌሎች መነቃቃትን ፈጥረዋል::
የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና አቅማቸውን አሟጠው መጠቀም የሚችሉበትን ዕድል ከማመቻቸት አንጻር ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል ሴት ልጆችን የተመለከቱ የተለያዩ መድረኮች ይጠቀሳሉ:: ለዚህም ዓለም አቀፍ የሴት ልጆች ክብረ በዓል አንዱ ነው:: እኤአ በየዓመቱ ጥቅምት 11 ቀን በሚከበረው (International day of girls) ዓለም አቀፍ የሴቶች ልጆች ቀን ክብረ በዓል በርካታ ጉዳዮች የሚነሱበትና ሴት ልጆች የሚገጥሟቸውን መሰናክሎች ለመቅረፍ ጥረት የሚደረግበትን መንገድ አንድ ማሳያ ነው:: ይህን ክብረ በዓልም ከሰሞኑ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር አክብሯል::
በሴት ልጆች መብት ዙሪያ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ፤ (International day of girls) ዓለም አቀፍ የሴቶች ልጆች ቀን ክብረ በዓል የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ ሴት ልጆች፣ የወጣት ተወካዮችና ወጣት አምባሳደሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በጋራ በተከበረበት ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መቅድም ጉልላት ናቸው:: ወይዘሮ መቅድም እንዳሉት ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በሴት ልጆች ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ተቋም ነው::
በተለይም የተለያዩ ግጭቶችና በአየር ንብረት ለውጥ የመጀመሪያዎቹ ተጎጂ የሚሆኑት ሴቶችና ሕጻናት እንደመሆናቸው ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ችግር የሚገጥማቸውን ሴት ልጆች በመታደግ የገጥማቸውን ችግር በመፍታት ወደ ትምህርት እንዲመለሱና በትምህርታቸው፣ በጤናቸውና በሥነ ልቦና የሚገጥማቸውን ችግር ለማቃለል ከመንግሥትና አጋዥ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ይሠራል::
በሴቶች መብትና ሴቶችን ማብቃት ላይ ትኩረት በማድረግ ዓላማውን ከሚደግፉ የመንግሥት አካላት ማለትም ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባባር በርካታ ሥራዎችን የሚሠራ ተቋም መሆኑን አስረድተዋል:: ተቋሙ በርካታ ፕሮግራሞችን ቀርጾ የሴቶችን ጉዳይ በአጀንዳነት ይዞ የሚሠራ ስለመሆኑ የጠቀሱት ወይዘሮ መቅድም፤ በተለይም የሴቶች ልጆች መብት የተከበረ እንዲሆንና የሚገጥማቸው ማንኛውም የመብት ጥሰት እንዲወገድላቸው ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል:: የተለያዩ ግጭቶች፣ ጦርነቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ደግሞ ዕለት ዕለት የሚታዩት የሴት ልጆች የመብት ጥሰት የበለጠ የሚጎላ በመሆኑ በዚህ ወቅት ሴት ልጆች ለከፋ አደጋ ይጋለጣሉ ነው ያሉት::
እሳቸው እንደሚሉት ሴቶች በተለይም በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የሚደርስባቸው ችግርና መከራ ለቁጥር የበዛ መሆኑን ተቋሙ በተግባር ማረጋገጥ ችሏል:: በዚህም የመደፈር፣ ወላጆቻቸውን የማጣትና ሌሎች ችግሮችን መመልከት የቻለው ተቋሙ ሴት ልጆች የሚደርስባቸውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችለውን የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ እንደሆነም ተመላክተዋል::
ድርጅቱ ሴት ልጆች መብታቸው ተጠብቆ የመማር፣ ጤናቸውን የመጠበቅና ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸው የተሟሉ እንዲሆኑ በተለይም በትምህርት፣ በውሃ ፕሮጀክቶች፣ በሕጻናት ጥበቃና በሌሎችም ተያያዥ ዘርፎች ይሠራል:: በእነዚህና መሰል ፕሮግራሞቹ ሴት ልጆችን፣ ቤተሰቦቻቸውንና አለፍ ሲልም ማህበረሰቡን የሚያግዝ ሥራ እንደሆነ የጠቀሱት ወይዘሮ መቅድም፤ ከዚህ በተጨማሪም የተሻሉና የሚረዱ ፖሊሲዎች እንዲቀረጹ የሚያመላክቱበት የተለያዩ መንገዶች እንዳሏቸው ተናግረዋል::
በሀገሪቱ በሰሜኑ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት በርካታ ጉዳቶች በሴቶች ላይ ስለመድረሱ አስታውሰው በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ድጋፍና እገዛ ማድረጋቸውን የጠቀሱት ወይዘሮ መቅድም፤ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድርጅት እንደመሆኑ ለጉዳዩ እጅግ ቅርብ ሆኖ ሲከታተልና የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ በጦርነት ምክንያት የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው በመጠለያ ካምፕ የተጠለሉትን ልጆች በማግኘት የደረሰባቸውን ጉዳት፣ ችግር፣ ህመምና ስቃያቸውን ተመልክተዋል:: ተቋሙ እንደ አንድ ሰብዓዊ ድርጅት ተፈናቃዮች በተጠለሉበት መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ልጆች ከንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ጀምሮ የተለያዩ ርዳታዎችን ሲያደርግ ቆይቷል:: ከትምህርት ጋር ተያይዞም እንዲሁ በርካታ ሥራዎችን የሠራ ሲሆን፤ ተቋሙ በተለይም ትግራይ፣ አማራና አፋር ላይ ባሉት ፕሮጀክቶች ያዘኑና የተከፉ ሕጻናት ወደ ደስታና ሳቃቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራን አበክሮ ሲሰራ መቆየቱን አመላክተዋል::
በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ችግሮች በዓመት አንድ ቀን በሚከበር ክብረ በዓል ብቻ የሚታይና የሚፈታ አይደለም:: የሚሉት ወይዘሮ መቅድም፤ ነገር ግን ቀኑ ሲከበር ያሉትን ችግሮች ማየትና ወደፊት መሠራት ስለሚገባቸው የቤት ሥራዎች መረዳት ያስችላል:: ከዚህም ባለፈ የቀኑ መከበር መፋጠን ስለሚገባቸው ጉዳዮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ ነው የጠቀሱት፡፤
የሴት ልጆችን ችግር ለማገዝና ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ በርካታ መሰናክሎች የሚገጥሙ እንደሆነ ያነሱት፤ ወይዘሮ መቅድም፤ ከፋይናንስ አቅም ጀምሮ የሚገጥሙ የተለያዩ ችግሮችን በመቋቋም እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል:: እንደሳቸው ገለጻ፤ በሴት ልጆች ላይ የሚደርሱ ፈተናዎችን ከባድ የሚያደርጉ ጦርነቶች፣ ግጭቶችና መፈናቀሎች ባሉበት አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ሰብዓዊ ርዳታና እገዛ ማድረግ መቻል በራሱ ፈተና ነው:: በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሠራተኞችን ደህንነት ጠብቆ ሥራቸውን መሥራት እንዲችሉ ማድረግና ምቹ ሁኔታዎች በሌሉበት ቦታዎች ላይ ጭምር በመገኘት ችግር የገጠማቸውን ሴት ልጆች ለማገዝና ለመደገፍ የሚደረገው ጥረት ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ስለመሆናቸው ነው ያስረዱት::
የሴት ልጆች በዓልን ማክበር የሴቶችን ኃይል፣ አቅምና መብት እንዲከበር ከማድረግ ባለፈ ሴት ልጆች ድምጻቸው እንዲሰማና በሴት ልጆች ትምህርትና መብት ላይ የሚሰሩ አካላት ጭምር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያስችል ትልቅ በዓል እንደሆነም የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መቅድም ተናግረዋል::
በዕለቱ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር አማካሪ ወይዘሮ ዘቢደር ቦጋለ በበኩላቸው፤ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የሴት ልጆች ቀን (International day of girls) ማክበሩን ጠቅሰዋል:: የክብረ በዓሉ ዋና ዓላማም የታዳጊ ሴቶችን መብት በማስጠበቅ ያላቸውን ዕምቅ አቅም ለመጠቀም፣ ለማብቃትና የበለጠ ዕድሎችን በመፍጠር በአድሏዊ ልዩነቶች ምክንያት የሚደርስባቸውን የተለያዩ ችግሮች መፍታትና የህበረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሆነ አመላክተዋል::
ከዚህም ባሻገር ዓለም አቀፍ የሴት ልጆች ቀን ክብረ በዓል ታዳጊ ሴት ልጆችን የሚያበረታታና ድምጻቸውን የሚያጎላ ታላቅ ሁነት መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ዘቢደር፤ ታዳጊ ሴቶች ጾታን መሠረት ካደረገና የወደፊት ህልማቸውን፣ ተስፋቸውንና ህልውናቸውን ከሚያጨልሙ ጥቃቶችና ጎጂ ተግባራት ከተጠበቁ፣ መብታቸው ከተከበረላቸው ያላቸውን ዕምቅ አቅም አውጥተው መጠቀም እንደሚችሉ ነው የገለጹት:: እሳቸው እንደሚሉት ሴቶች ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው እንዲሁም ጥረታቸውን መደገፍ ከተቻለና ካበረታታናቸው በራስ የመተማማንና ጠንካራ ሥነ ልቦና በማዳበር በግል ሕይወታቸው ስኬታማ መሆን ይችላሉ:: ከዚህም ባለፈ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በሀገር ደረጃ የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ::
ይሁንና በሀገሪቱ በተለይም በተዛባ በሥርዓተ ጾታ ግንኙነት፣ በማህበረሰቡ ዘንድ በዘልማድ በሰፊው እየተተገበሩ ባሉ ጎጂ ድርጊቶች፣ ጥቃቶች፣ እንዲሁም በአስፈጻሚ አካላት መካከል የቅንጅታዊ አሰራር መጓደል፣ የአፈጻጸም አቅም ውስንነት በመኖርና የተጠያቂነት አሰራርም በሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱ የተነሳ ታዳጊ ሴቶች አሁንም ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች ይዳረጋሉ:: ያሉት ወይዘሮ ዘቢደር፤ በዚህ የተነሳም ለአዕምሯዊ፣ ለአካላዊ፣ ለሥነ ልቦናዊና ለሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጡ እንደሆነ አመላክተዋል::
በሌላ በኩል ግጭቶችና ተፈጥሯዊ የሆኑ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕጻናትና ታዳጊ ሴቶች ከመኖሪያ ቤታቸው የሚፈናቀሉበት፣ የትምህርት ዕድል፣ የጤና፣ የመሠረተ ልማት መጓደል የሚያጋጥሙ ችግሮች እንደሆኑ ጠቅሰዋል:: ከዚህ ባለፈ ልጃገረዶችና ሴቶች ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባቸውና በምላሹም ውስብስብ ለሆኑ የማህበረሰብና የሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንዲሁም የጤና ዕክሎች የሚጋለጡበት አጋጣሚ የሰፋ እንደሆነ ያነሱት ወይዘሮ ዘቢደር፤
ይህም የታዳጊ ሴት ልጆችን መብታቸውንና ደህንነታቸውን በማስጠበቅ ሁሉንም ዓይነት አድሏዊና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ጥቃቶችን ለማስወገድ የተዘጋጀው የ10 ዓመት ዕቅድ ከዘላቂ የልማት ግብ ጋራ በማያያዝ ተግባራዊ ለማድረግና ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል ነው ያሉት:: ስለሆነም ግጭትና መፈናቀል በታዳጊ ሴቶች ሕይወት ላይ በተለያየ መልኩ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ፈርጀ ብዙ በመሆኑና ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ ለኃይል ጥቃቶችና የመብት ጥሰቶች በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሚያደርጋቸው በመሆኑ ሁሉም ሰው ለሴት ልጆች የተለየ ጥበቃና ከለላ በማድረግ ሊታገልላቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል::
በተለይም ወላጆችና ትምህርት ቤቶች በልጆች አስተዳደግና በስብዕና ቀረጻ ላይ የሚኖራቸው ሚና ጉልህ መሆኑን አንስተው፤ ዛሬ የታዳጊ ሴቶች ትውልድን ማዕከል የሚያደርጉና ተስፋቸውን የሚያደናቅፉ ማንኛውንም ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቆሙ ማድረግና ማብቃት የሚጠበቅባቸው እንደሆነ ገልጸዋል:: በተያያዘም ሌሎች ማህበራዊ ወጎችን ከምቹ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር እንዲሁም ከሕግና ፖሊሲዎች ጋራ የተያያዙ ውጤታማ ስልቶችን ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ታዳጊ ሴቶች የወደፊት የሥራ ዕድሎቻቸውን በማስፋት፣ ሙሉ ተሳትፎ ኖሯቸው የኢኮኖሚ አቅማቸውም እንዲያድግ ለማድረግ ተገቢውን ክህሎትና ስልጠና የታጠቁ እንዲሆኑ አበክሮ መሥራትን የሚጠይቅ እንደሆነ አብራርተዋል::
ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከክልል መዋቅሮችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ልዩ ልዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ዘቢደር፤ በተለይም በታዳጊ ሴቶች መብት፣ በልጃገረዶች ትምህርት ፋይዳ፣ በሥርዓተ ጾታ እኩልነትና ታዳጊ ሴቶች በሚገጥሟቸው ችግሮችና መፍትሔዎች ዙሪያ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባሻገር በተቋማት አካቶ ትግበራ ስኬታማነት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል::
ታዳጊ ሴቶች የተጎናጸፏቸው መብቶች እንዲከበሩ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ አቅማቸው እንዲያዳብርና ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ብሩህ የወደፊት ሁኔታ በውል መረዳት እንዲችሉ መሥራት ተገቢ ነው የሚሉት ወይዘሮ ዘቢደር፤ መብትና ደህንነታቸውን ማስከበር፣ ማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ዙሪያ የሚሠራው ሥራ አስቸኳይ ተግባር ብቻ ሳይሆን ለሀገር ዕድገት ብልጽግና ብልህ ምርጫ እንደሆነ አጽንኦት በመስጠት ነው የገለጹት::
ዓለም አቀፍ የሴት ልጆች ቀን (International day of girls) በዓለም ለ11ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ‹‹ታዳጊ ሴቶችን እናብቃ መብትና ደህንንታቸውን እናስጠብቅ›› በሚል ሀገራዊ መሪ ሃሳብ ለ10ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2016