የቱሪዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅ የተዘጋጀችው የቁንጅና ውድድር አሸናፊ

ወጣት ማኅደር ፍቃዱ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው የአትሌቶች መፍለቂያ ተብላ ከምትጠራው አርሲ በቆጂ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸር አግኝታለች። ከልጅነቷ ጀምሮ ከምታየው ነገር በመነሳት በቁንጅና ውድድር ላይ የመሳተፍ ፍላጎት ነበራት። ‹‹ቪዝት ኦሮሚያ›› የተሰኘው የቁንጅና ውድድር ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ግን የመወዳደር ፍላጎቷ እየጨመረ በዘንድሮ ውድድር እንድትሳተፍ መነሳሳትን ፈጥሮላታል። ለውድድሩ የሰጠችው ትልቅ ትኩረት፣ ውስጣዊ ፍላጎትና በራስ መተማመን ለአሸናፊነት እንዳበቃት የምትናገረው ማኅደር ፍቃዱ የዘንድሮው ሚስ ቱሪዝም ኦሮሚያ አሸናፊ ናት።

ማኅደር፤ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የሞዴሊንግ ወይም የቁንጅና ውድድሮች ላይ ተሳትፋ ባታውቅም የመሳተፍ ውስጣዊ ፍላጎቱ ግን ነበራት። እስከ አሁን ሙሉ ጊዜያዋንና አቅሟን ለትምህርቷ አድርጋለች። ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ግን ውድድሩን የመቀላቀል ፍላጎቷ ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ባጠናቀቀች ማግስት ፊቷን ወደ ቁንጅና ውድድር አዙራለች።

‹‹በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የሚዘጋጀው ውድድር ከተጀመረ አንስቶ የመወዳደር ህልምና ጉጉት ነበረኝ›› የምትለው ማኅደር፤ ኢትዮጵያ እጅግ አስገራሚና የታወቁ የቱሪዝም መስዕቦች ያሏት ውብ ሀገር መሆኗን ጠቅሳ፣ ሀብቷን በአግባቡ መጠቀም እንዳልተቻለ ነው የገለጸችው። ለዚህም ሀገሪቷ ያላትን ዕምቅ የቱሪዝም ሀብት በማስተዋወቅና መጠቀም ላይ ብዙ የሚቀሩን የቤት ሥራዎች አሉ ትላለች። እዚህ ላይ ብዙ መሥራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘበችው፤ ‹‹እኔም ሙያዬን ተጠቅሜ ባለኝ አቅም የቱሪዝም መስህቦችን የማስተዋወቅ ፍላጎቱ ቀድሞውኑ በውስጤ ስለነበር ውድድሩን ለመሳተፍ እድሉን ሳገኝ ለመጠቀም ችያለሁ›› ትላለች።

‹‹በቁንጅና ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ስመዘገብ ጀምሮ አእምሮዬ ለሁሉም ነገር ዝግጁ ነበር። በራስ መተማመንን መጨመርና ስለውድድሩ በደንብ ማወቅ በራሱ ውድድሩን

 50 በመቶ የማሸነፍ ያህል በመሆኑ ይህን ለራሴ በደንብ ነገሬው ራሴን አሳምኜ ስለነበር ለማሸንፍ ዝግጁ ነበርኩ›› የምትለው ማኅደር፤ በውድድሩም የጠበቀችው እንደገጠማትና ያሰበችው ተሳክቶላት ማሸነፏን ተናግራለች።

ማኅደር እንደምትለው፤ ኮሚሽኑ ለውድድሩ የተለያዩ መስፈርቶች አዘጋጅቷል። የመጀመሪያው የቁመት፣ የክብደት እና ሦስት ቋንቋዎችን (አፍን አሮሞ፣ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች) መናገር መቻል እና መሰል መስፈርት ነበር። ከዚህ በኋላ ስለቱሪዝም በሦስቱ ቋንቋዎች የመገለጽ ፈተናም የውድድሩ አካል እንደነበር ታስታወሳለች። እንዲህ እንዲህ እያለ በመጨረሻ በመድረክ ላይ በሚደረገው ውድድር ላይ በኦሮሚያ ካሉት 21 ዞኖች የደረሳትን የአንዱን አካባቢ የቱሪዝም መዳረሻዎች ባህላዊ አለባበስና መሰል ሀብቶች በመግለጽ አስተዋውቃለች። ልዩ ተሰጥኦን ማሳየትም ሌላኛው የውድድሩ አካል መሆኑን ጠቅሳ፤ የመጨረሻው ፈተና በመድረኩ ላይ የሚቀርቡ ጥያቄዎች በመመልስ ስለነበር በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ አልፋ ማሸነፍ ችላለች።

ወደ ውድድሩ ከመግባቱ አስቀድሞ በክልሉ ስላሉ የቱሪዝም መስህቦች በደንብ ማወቅና መዘጋጀት ተጠባቂ ተግባር ነው የምትለው ማኅደር፤ ‹‹እኔ የደረሰኝ የጉጂ አካባቢ ባህላዊ አልባሳትን እና የቱሪዝም መስህቦችንና መዳረሻዎችን በሚገባ ተረድቶ ማስረዳትና ማስተዋወቅ ነበር ትላለች። ባህላዊ አልባሳቱን ለብሳ በማሳየት፤ ስለመዳረሻዎቹና ስለባህላዊ አልባሳቱ በሚገባ በመግለጽ ማስተዋወቅ ችላለች።

እሷ እንዳለችው፤ የሚስ ቱሪዝም ኦሮሚያን ውድድር ማሸነፌና የኦሮሚያ የቱሪዝም አምባሳደር በመሆኔ ብዙ ሥራዎች ይጠብቃታል። ከክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር በመሆኑን እንደ ብራንድ አምባሳደር የቱሪዝም ሀብቶች፣ መስህቦችና መዳረሻዎችን ማስተዋወቅ፣ ስለቱሪዝም ህብረተሰቡ በቂ መረጃ እንዲያገኝ፣ ቱሪስቶች ወደ ሀገራችን መጥተው እንዲጎበኙ ማድረግ ይኖርባታል። የተለያዩ ሃሳቦች ላይ የተለያዩ አዲዲስ ነገሮች በመፍጠር በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በማስተዋወቅ የክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ተቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲሆኑ መሥራትም ይኖርበታል።

እንዲህ ዓይነት የቁንጅና ውድድሮች መዘጋጀታቸው በተለይ ወጣቶች በራስ መተማመናቸው እንዲጨምር ያደርጋል የምትለው ማኅደር፤ በተለይም ባሉት የቱሪዝም ሀብቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባ ጠቁማለች። በሌሎች ዘርፎችም እንዲሁ ያሉ ብዙ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑን ገልጻለች። የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ያለን እውቀት ለማዳበርና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን ለመውሰድ ራሳቸውን ማሻሻልና ማሳደግ ላይ እንዲሰሩ የሚያበረታታ እንደሆነና የሚፈልጉትን አድርገው ማሳየት እንዲችሉ እድሉን እንደሚፈጥርም አመልክታለች።

‹‹ሰዎች ስለቁንጅና ወይም ስለውበት ያላቸው አመለካከትና አገላለጽ ይለያያል። ቁንጅና የአፍንጫ፣ የጸጉር እና የሌሎች መገለጫ ብቻ አይደለም፤ ሁላችንም የምንስማማበት አንድ ዓይነት መገለጫ የለውም›› የምትለው ማኅደር፤ ‹‹እንደኔ አመለካከት ቁንጅና ወይም ውበት በሚጠበቅብኝ ቦታ ላይ የሚጠበቀውን እውቀት ይዞ መገኘት ነው። ›› ብላለች። በየጊዜው እውቀትን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ አዳዲስ ነገሮችን መሞከር እና የራስን አቅም ማጎልበት ከዘመኑ ጋር አብሮ መጓዝ መቻል እና እነዚህ ነገሮች ማሳካት መቻል እኔ ቁንጅና ወይም ውበት ነው ብዬ አምናለሁ›› ብላለች።

በወጣቶች ዘንድ ብዙ ጊዜ ያልተለመደው በራስ መተማመን መቻል ነው የምትለው ማኅደር፤ ‹‹ስለራሳችን በሙሉ ራስ መተማመን መንፈስ ስላለን ስለምናውቀው ነገር በመናገር ራሳችንን መግለጽ ካልቻልን ማንም ሰው ስለኛ ጠንካሬና ጉብዝና ሊናገርልን አይችልም›› ነው የምትለው።

ማኅደር እንደምትለው፤ አሁን ላይ ዘመኑ ነገሮች በቀላሉ ፈልጎ ለማግኘት፣ ለመማር የተመቸ ስለሆነ እነዚህን አማራጮች በመጠቀም በትምህርትም ሆነ በሥራ ራስን ብቁ አድርጎ ከዓለም ጋር እኩል መራመድ መቻል ከወጣቱ የሚጠበቅ ትልቁ ጉዳይ ነው። ‹‹እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ፍላጎቱ ካለን፣ ማድረግ የምንፈልገውን በእቅድ የምናደርግና በቁርጠኝነት የምንፈጸም ከሆነ ካሰብነው እንዳንደርስ የሚያደርገን ነገር የለም›› ትላለች።

ማኅደር እንዳለችው፤ አሸናፊ ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት ድረስ የክልሉ የቱሪዝም አምባሳደር ሆና ታገለግላለች። በዚህ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በዘርፉ የራሷ ትልቅ ዐሻራ ማሳረፍ ትፈልጋለች። በቱሪዝም ዘርፉ ስኬቶች እንዲመዘገቡ መሻሻሎች እንዲመጡ፣ አዳዲስ ነገሮች እንዲፈጠሩ እና ካሉት የቱሪዝም ሀብቶች መጠቀም እንዲቻል የሚያደርጉ ሥራዎችን ጠንክራ ትሰራለች።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በርካታ ኢንቨስትመንቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲመጡ የሚያደርግ ዘርፍ ነው። ማኅደርም የተመረቀችበትን የአርትቴክቸር ሙያም ተጠቅማ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው አንድ ርምጃ ወደፊት እንዲጓዝ ለማድረግ አቅዳለች።

‹‹ለውጥ ከራሳችን የሚጀምር በመሆኑ ያሉንን ሀብቶች ማሳየት፣ እርስ በእርስ በመማማር እና በአካባቢያችን ያሉትን ሰዎች ማስተማር ስንችል ከፍ እያልን ዓለም አቀፍ ደረጃ መድረስ እንችላለን›› የምትለው ማኅደር፤ ሁላችንም ከአካባቢያችን ጀምረን ያለንን ማወቅና ማሳወቅ ላይ ትኩረት ሰጥተን መሥራት አለብን ስትል ታስገነዝባለች። ይህን በማድረግም ራሳችንንም ሀገራችንንም መጠቀም መቻል አለብን የሚል ጽኑ እምነት እንዳላትም ተናግራለች።

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You