የማዘውተርያ ስፍራ እጦት- የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት ፈተና

ከፍልሚያ ስፖርቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ፤ እአአ በ1966 ከደቡብ ኮርያ ተነስቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፌዴሬሽን ተመሥርቶ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ይገኛል:: ስፖርቱ ወደ ሁሉም የዓለም ክፍሎች የተስፋፋ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ተዘውታሪ ከሆኑ ስፖርቶች ተጠቃሽ ነው:: የቤት ውስጥ ስፖርት እንደመሆኑ የተወዳዳሪዎችን ምቾትና ደህንነት የሚያረጋግጥ የማዘውተርያ ስፍራን ይሻል:: ኢትዮጵያ ግን ይህን ሁኔታ የሚያሟላ የማዘውተሪያ ስፍራ ትልቁ ችግር ሆኖ ይገኛል:: ስፖር ካለው የተሳታፊ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የመወዳደርያ ቦታ ባለማግኘቱም ከባድ ችግሮች እያጋጠሙት ነው:: ፌዴሬሽኑ ደረጃውን የጠበቀና ተመልካች የሚይዝ የማወዳደርያ ስፍራ በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ የሀገር ውስጥ ውድድሮችን ለማካሄድ ከመቸገር ባለፈ በርካታ ዕድሎችን እያጣ መሆኑንም አስታውቋል:: ይህም ችግር እንዲቀረፍ ስፖርት ወዳዱ ህዝብና መንግሥት ርብርብ ማድረግ እንደሚኖርበት ተጠቁሟል::

የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ስፖርት በአዲስ አበባ ደረጃ የውድድር መስፈርቶች ተፈጥሮለት እየተስፋፋ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የታዳጊ፣ የክልሎች፣ የክለብና ብሄራዊ ቻምፒዮናዎች እየተካሄዱበት ይገኛል:: በዚህም ስፖርቱ በአዳራጅ ኮሚቴ በመቋቋም ከዛም ወደ አሶሴሽን አሁን ደግሞ በፌዴሬሽን ደረጃ እተመራ ይገኛል:: እዚህ ደረጃ እስኪደርስም የራሱን ሕጎች አርቅቆ እስከ መምራትና ውድድር ማካሄድን ጨምሮ ስፖርቱ እንዲስፋፋ መደላድልን ሊፈጥሩ የሚችሉ ተግባራት ተከናውነዋል:: ይሁን እንጂ ስፖርቱ የተጓዘውን ርቀትና በደረሰበት ደረጃ ልክ መጓዝ ያልቻለው የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ችግር ነው:: ይህም ፌዴሬሽኑ የሚፈልገውን እንዳይከውን እና የሚፈልገው ደረጃ እንዳይደርስ እንቅፋት መፍጠሩ ተጠቁማል::

ይህ ችግር ቢኖርም አሁን ባለበት የፌዴሬሽን ቁመናም የተለያዩ ውድድሮችን በማካሄድ ብዙ ስፖርተኞችን በማፍራት ላይ ነው:: ፌዴሬሽኑ በ2015 ዓ.ም እንደ ከተማና ክልል በርከት ያሉ እና ሰፊ ስፖርተኞችን ያሳተፉ ውድድሮችን መከወን ችሏል:: በአዲስ አበባ ደረጃ ሁለት ቻምፒዮና አንድ የመላው ኢትዮጵያ ውድድር ተካሂዷል:: በሁሉም የእድሜ ደረጃ የተፈጠሩ የውድድር እድሎች ከበቂም በላይ እንደሆነ ፌዴሬሽኑ ጠቁማል:: የስፖርቱ ባህሪ መቆራረጥን የማይፈቅድ በመሆኑ ዓለም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተጠቃበት ወቅትም ጭምር ውድድሮችን በበይነ ማረብ ማካሄድ ችሏል:: ይህም ቀላል እንዳልነበረና የበጀት ችግርን በመቋቋም እንደሆነም ተገልጿል:: በዚህ ሁሉ ጉዞ ከበጀት እጥረት በበለጠ የማዘውተርያ ስፍራ በበቂ ደረጃና ጥራት አለመኖር ስፖርቱን ፈትኗል::

ውድድሮች በተለያዩ ደረጃዎች የሚካሄዱና በርካታ ተመልካቾች የሚታደሙባቸው ቢሆንም በቂና ተመጣጣኝ የማዘውተርያ ስፍራ አለመኖር ትልቁ ችግር ነው:: የማዘውተርያ ስፍራ እጦት በኢትዮጵያ ለሚዘወተሩ በርካታ ስፖርቶች ችግር ሆኖ የቆየ ቢሆንም የቤት ውስጥ ስፖርቶችንም በሚፈለገው ደረጃ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓል:: የኢንተርናሽንል ቴኳንዶ ስፖርትም የገጠመውም ከዚህ የተለየ አይደለም:: ካለው በርካታ የውድድርና የተሳትፎ መጠን ጋር የሚመጣጠን እና ውድድሩን ለመከታተል የሚመጣን ተመልካች የሚይዝ ማዘውተርያ አለመኖሩ ችግር እንደሆነም ፌዴሬሽኑ ገልጿል:: ይህም የሆነው ስፖርቱ አሳታፊ፣ ህዝብን ማዕከል ያደረገና ዕድሜን የማይገድብ በመሆኑ ነው::

የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽኑን ፕሬዚዳንት ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ጌታቸው ሽፈራው፣ የቴኳንዶ ስፖርት ከሌሎች ስፖርቶች ጋር ሲነጻጸር የውድድር አማራጩ ሰፊና አሳታፊ ቢሆንም የማዘውተርያ ወይም የመወዳደርያ ስፍራ እጦት እንደ ፌዴሬሽን ብዙ የሆነ ጥቅሞችን እያሳጣው እንደሆነ ይናገራሉ:: እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፣ ደረጃውን የጠበቀ የማወዳደርያ ስፍራ ቢኖር በኢትዮጵያ የዓለም ቻምፒዮናን የማዘጋጀት አቅም ይፈጥራል:: ችግሩ ስፖርቱን ብቻም ሳይሆን የውጭ ምንዛሪን በማምጣት ሀገርን መጥቀምም ይቻላል:: የሀገር ውስጥ ውድድሮች በወወክማ እና ራስ ኃይሉ ጂምናዚየም ቢካሄዱም በቂ አይደለም:: ስለዚህ ሀገርን የሚመጥን የማዘውተርያ ስፍራ መገንባት አስፈላጊ ነው:: የስፖርተኛ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በቂ ማዘውተርያ ስፍራ አለመኖሩ ስፖርቱ ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ ከባድ ነው::

ለዚህ ችግር መፍትሄ ይሆን ዘንድ የማርሻል አርት ጥምረት ተመስርቶ ፕሮፖዛል ለመንግሥት አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ ይገኛል:: በዚህም መንግሥት ትኩረት በመስጠቱ የመወዳደርያ ስፍራው የሚገነባ ከሆነ ፌዴሬሽኑ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማምጣት እንደሚቀለው ጠቅሷል::

እንደ ፕሬዚዳንቱ አስተያየት፣ ስፖርቱ እራሱን ችሎ ገቢ በመፍጠር ሊተዳደር ይገባል:: ለዚህም የማዘውተርያ ስፍራ ዋንኛው መሠረት በመሆኑ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል:: ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት የሚመደብለት በጀት አነስተኛ ቢሆንም ራሱ በሚያመነጫቸው ገቢዎች በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛል:: ይህ ጥረት እንዲቀጥልም የማዘውተርያ ስፍራ ጥያቄ በተቻለ ፍጥነት ምላሽ ሊያገኝ ይገባል::

 ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You