የማህፀን እጢና ቀዶ ህክምና

በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ የሚገኘው የሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል ግንቦት አራት ቀን 2015 ዓ.ም አንድ እንግዳ ክስተት አስተናግዷል:: በጊዜው የሆስፒታሉ ሀኪሞች እንደተለመደው የእለት ከእለት ተግባራቸውን እያከናወኑ ነበር:: በእነርሱ ላይ እምነታቸውን ጥለው ህክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ ለመጡ ታካሚዎች ለህመማቸው መፍትሄ ለመስጠት ላይ ታች ይሯሯጣሉ:: የሆስፒታሉ የማህፀንና ፅንስ እስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ግላንዴ ግሎ በእለቱ ለአንዲት እናት ቀዶ ህክምና ለማድረግ የህክምና ቡድናቸውን አስከትለው ወደ ቀዶ ህክምና ክፍል ገቡ::

አንድ ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ በፈጀው የቀዶ ህክምና በሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል ከአንዲት እናት 30 ኪሎ ግራም የሚመዝን የማህፀን እጢ (ovarian tumor) በቀዶ ጥገና ህክምና መወገዱ ተሰማ:: ነገሩ በሆስፒታሉ ቅጥር ጊቢ ከዚህ በፊት ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ በመሆኑ በርካቶችን ያስገረመ ክስተት ነበር:: ዜናው ከሆስፒታሉ አልፎ በመላው ሀገሪቱ በመሰራጨቱ ብዙዎችን አስደንቋል:: ምን እንኳን በተለያዩ ጊዜያት በእንዲህ አይነት የቀዶ ህክምና እናቶች እጢ ወጣላቸው የሚሉ ዜናዎች ተሰምተው የነበረ ቢሆንም ይህን ያህል ክብደት ያለው እጢ በቀዶ ህክምና ሲወገድ ግን የመጀመሪያ ሳይሆን እንዳልቀረ መረጃዎች ጠቁመዋል::

በወቅቱ ቀዶ ህክምናው የተደረገላት እናት ከወለደች በኋላ የሆዷ መጠን ባለመቀነሱና ትንፋሽ እያጠራት በመቸገሯ የነገሩን ምንነት ለማወቅ ወደ ሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል በመሄድ የአልትራሳውንድ ምርመራ አድርጋ የማህፀን እጢ መሆኑ ታውቆ በቀዶ ህክምና እጢው እንደተወገደላት ሆስፒታሉ አስታውቋል::

የሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተርና የፅንስና ማህፀን ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ግላንዴ ግሎም እንደሚናገሩት፣ የማህፀን እጢ (እንቁልጥ) የካነሰርነት ባሕሪ የሌለው የማህፀን ውስጥ እባጭ ሲሆን በአብዛኛው የሚከሰተው በወጣትነት የእድሜ ክልል ነው:: ይህ የማህፀን እጢ በፍጥነት ወይም በዝግታ የሚያድግ ሊሆን ይችላል:: ከተከሰተ በኋላም በራሱ የሚጠፋበት እድል ይኖራል:: እጢው በሴቶች ላይ እጅግ የተለመደ በመሆኑ ምክንያት ከአራት ሴቶች ውስጥ ሶስቱ በህይወት ዘመናቸው የማህፀን እጢ እንደሚያጋጥማቸው ጥናቶች ያመላክታሉ::

የማህፀን እጢ በአብዛኛው ምንም አይነት ምልክት የማያሳይ ቢሆንም በአንዳንድ ሰዎች ላይ ከሚከሰቱ ምልክቶች መካከል፤ ከፍተኛ የሆነ የወር አበባ መዛባት፣ ከሰባት ቀን በላይ የሚቆይ የወር አበባ መፍሰስ፣ ማህፀን አካባቢ የሚከሰት ግፊት ወይም ህመም፣ የሆድ ድርቀት፣ የጀርባና የእግር ህመም ስሜት እና አልፎ አልፎ ከፍተኛ የሆነ ወይም አጣዳፊ ህመም ይገኙበታል::

የማህፀን እጢ በዋናነት የወር አበባ በሚያዩ ሴቶች ላይ ይከሰታል:: በተጨማሪ ሁሉም የማህፀን እጢ (ovarian tumer) ካንሰር ባይሆኑም የካንሰር መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ:: በሳውላ ጀነራል ሆስፒታል በተደረገ የቀዶ ህክምና ከእናቲቱ የተወገደው የእጢ አይነትም የወር አበባ በሚያዩና መውለድ በሚችሉ ሴቶች ላይ የሚከሰት የእጢ አይነት ነው::

እንደ ዶክተር ግላንዴ ማብራሪያ የማህፀን እጢ ብዙ ጊዜ በመውለድ እድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሴቶች የሚከሰት ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን ህፃናት እንዲሁም የወር አበባ ማየት ያቆሙ ሴቶች ላይ ጭምር ሊከሰት ይችላል:: ነገር ግን እስካሁን ድረስ ከ15 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ዕጢ አሁን እንጂ ከዚህ በፊት አልታየም::

እጢው ከሰው ሰው ይለያይ እንጂ ሁሉም ሴቶች ላይ ሊከሰት የሚችል ነው:: የወር አበባ መጥቶ እንቁላል ወደ ሰውነት ከተለቀቀ በኋላ ወደ /ovarian cyst/ የመቀየር እድል ይኖረዋል:: ይህም በሶስት ወር ውስጥ የሚጠፋ ከሆነ በተፈጥሮ የማይጎዳው የ/ ovarian cyst/ አይነት ይሆናል:: ነገር ግን አንዳንድ ሰው ላይ መጠኑ ጨምሮ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ ምርመራ ተደርጎ የህክምና ክትትል ሊደረግበት ይገባል::

ዶክተር ግላንዴ እንደሚሉት የእጢው መጠን መጨመር በጤና ላይ የሚያደርሰው የራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል:: የትንፋሽ ማጠር፤ የተፈጥሮ ሳምባ የሚያንቀሳቅሰውን ጡንቻ (ዲያፍራም) ተጭኖ በመያዝ ትንፋሽ መከልከል፤ ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት መሰማት ፣ ሆድ መንፋትና የምግብ ፍላጎት መቀነስ እጢው የሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው::

በሆስፒታል ከእናቲቱ በቀዶ ህክምና የወጣው እጢ ክብደት ብዙ ጊዜ የተለመደ አይደለም:: ክብደቱ ከፍተኛ የሆነ እጢ ያለባቸው ሴቶች በወሊድ ወቀት ፈንድቶ በውስጡ የያዘውን ነገር በሆድ ውስጥ በመልቀቅ ለሞት ሊዳርጋቸው የሚችልበት እድል አለ:: ከዚህ ባሻገር በጊዜ ሂደት ያን ያህል ባይሆንም እጢው ወደ ካንሰርነት የመቀየር እድል ይኖረዋል:: ከዚህ አንፃር ያልተቋረጠ የጤና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል::

ነፍሰ ጡር እናቶች በእርግዝና ወቅት ቢያንስ ፅንስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሶስት ወር የመጀመሪያ ዙር ክትትል እንዲሁም በእርግዝና ወቅት ቢያንስ እስከ ስምንት ዙር በባለሙያ ክትትል እንዲያደርጉና ሁለት ጊዜ በአልትራሳውንድ መታየት ይኖርባቸዋል:: እናቶች የወር አበባ ማየት ካቆሙ ወይም በእርግዝና ወቅት ሆድ መንፋት፤ የሰውነት ክብደት መቀነስ፤ የምግብ ፍላጎት መቀነስና መሰል ችግሮች ካጋጠማቸው በፍጥነት በባለሙያ መታየት ይገባቸዋል::

ሰላሳ ኪሎ ግራም እጢ የተወገደላት እናት በወቅቱ እኛ ጋር ስትመጣ ከነበረችበት የጤና ሁኔታ አንፃር አሁን ሙሉ በሙሉ ጤናማ መሆኗን ዶክተር ግላንዴ ይገልፃሉ:: እናቲቱ ወደ ሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል የመጣችው ከወለደች በኋላ ሆዷ ሳይቀንስ በመቅረቱ እና የትንፋሽ እጥረት ችግር አጋጥሟት ስለነበር መሆኑንም ይናገራሉ:: በመጀመሪያ የአልትራሳውንድ ምርመራ ከተደረገላት በኋላ ለቀዶ ህክምናው ሁለት ቀን ቀጠሮ ተሰጥቷት አስፈላጊው ዝግጅት ከተደረገ በኋላ የቀዶ ህክምና እንደተደረገላት ያስረዳሉ:: የቀዶ ህክምናው ከተደረገላትና እጢው ከወጣ በኋላ በመሉ ጤንነት ላይ እንደምትገኝም ነው ዶክተር ግላንዴ የሚገልፁት::

ከዚህ ቀደም በሆስፒታሉ እንደዚህ አይነት ቀዶ ህክምና ተደርጎ እንደማያውቅ የሚናገሩት ዶክተር ግላንዴ፤ የማህፀንና ፅንስ እስፔሻሊስት ሀኪም ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ወደ ሌላ ቦታ በመላክ ቀዶ ህክምናው ይደረጋል እንጂ አገልግሎቱ በሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል ይሰጥ እንዳልነበረ ይጠቁማሉ:: ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን የቀዶ ህክምና አገልግሎቱ መስጠት እንደተጀመረ ይጠቅሳሉ:: እንዲያም ሆኖ ግን እስከዛሬ በተደረጉ ቀዶ ህክምናዎች ይህን ያህል መጠን ያለው እጢ በቀዶ ህክምና ወጥቶ እንደማያውቅ ይገልፃሉ::

ዶክተር ግላንዴ እንደሚያስረዱት በትኢትዮ ጵያም ቢሆን ከዚህ ቀደም ይህን ያህል መጠን ያለው እጢ በቀዶ ህክምና ወጥቶ አያውቅም:: ይሁንና ከዚህ በፊት በህክምናው ዘርፍ ሌሎች የተለያየ መጠን ያላቸው እጢዎች በቀዶ ህክምና ማስወገድ እንደተቻለ ሪፖርቶች አሳይተዋል:: ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በመጠን ከ10 እስከ 15 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ እጢዎች በብዛት በቀዶ ህክምና እንደሚወገዱም መረጃዎች ያሳያሉ:: 30 ኪሎ ግራም የሚመዝን እጢ ግን ከዚህ ቀደም አጋጦሞ አያውቅም:: በተመሳሳይ በዓለም አቀፍ ደረጃም በየጊዜው የተለያዩ በህክምናው ዘርፍ የተከሰቱ አዳዲስ ነገሮች ይፋ ይደረጋሉ:: በዚሁ መሠረት ይፋ በተደረጉ ሪፖርቶች እስካሁን በቀዶ ህክምና የተወገደው ትልቁ የማህፀን እጢ መጠን 59 ኪሎ ግራም ነው::

በዚህ የማህፀን እጢ ሴቶች እንዳይጋለጡ በተለይ መውለድ የሚችሉት ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ በየጊዜው የህክምና ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል:: እጢው መኖሩን የሚያረጋግጡ የተለያዩ ምርመራዎችን ማድረግም እጅግ ጠቃሚ ነው:: የወር አበባ ማየት ያቆሙ ሴቶች ለካንሰር የሚያጋልጡ የእጢ አይነቶች በመኖራቸው የሆድ መነፋትና በመጠን መጨመር ምልክቶች ሲከሰቱ በአፋጣኝ ሀኪም ጋር መቅረብና ማማከር ይኖርባቸዋል::

ከዚህ ባለፈ እንዲህ አይነቱን በሀገር ውስጥ የሚካሄድ ቀዶ ህክምናን ከማበረታታት አንፃር መንግሥትም ሆነ ህዝቡ በጋራ በመሆን መሥራት ይኖርበታል:: በቀዶ ህክምና ዘርፍ ያለው ቴክኖሎጂና እውቀት በሀገር ደረጃ ደካማ ነው ተብሎ ስለሚገመት እንደዚህ አይነት ውስብስብ የጤና እክሎች ሲከሰቱ ወደ ውጭ ሀገራት ወይም ወደ አዲስ አበባ ተልከው እንዲሠሩ ይደረጋል:: አሁን ግን ባለው ልምድ እውቀትና የመመርመሪያ ማሽኖች በመታገዝ የቀዶ ህክምናውን በክልሎች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎች መስጠት ይቻላል::

በመሆኑም የወለዱ ሴቶች እንዲህ አይነቱ የጤና ችግር ሲጋጥማቸው ምንም ሳይደናገጡ በአቅራቢያቸው ወዳለ የህክምና ማዕከል በመሄድ መታከም ይችላሉ:: ከዋና ከተሞች ወጣ ብለው የሚገኙ የህክምና ተቋማት አመርቂ የሆነ የህምክና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ግን ተጨማሪ የመመርመሪያ መሣሪያዎችን ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ በመንግሥት በኩል ሊመቻች ይገባል::

ምንም አይነት ምልክት የማያሳየው የማህፀን እጢ ከ75 እስከ 80 በመቶ በሚሆኑና ከ20 አስከ 40 ባለው የወሊድ እድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ላይ እንደሚከሰት ዓለም አቀፍ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ከመቶ ሴቶች መካከል ከ10 እስከ 15 የሚሆኑት የማህፀን እጢ እንደሚገኝባቸውም በዚሁ ረገድ የተሰሩ ጥናቶች ያመላክታሉ:: ምልክት የማይታይባቸው 100 ሴቶች አልትራሳውንድ ቢነሱ 70 ከመቶ የሚጠጉት የማህፀን እጢ ይኖርባቸዋል ተብሎ እንደሚታሰብም ነው እነዚሁ ጥናቶች የሚያሳዩት::

ከዚህ እንፃር ማንኛውንም አይነት የህመም ስሜት ሲያጋጥም በፍጥነት ወደህክምና ተቋም ሄዶ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል:: ከሁሉ በላይ ደግሞ የህመም ስሜት ከመሰማቱ በፊት ወደጤና ተቋም በየጊዜው በመሄድ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በህክምና ባለሙያዎች ይመከራል::

በለጥሻቸው ልዑልሰገድ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You