በማዕድን፣ በውሃ፣ በመሬት ሀብቶች ባለፀጋነቱ የሚታወቀው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ በግብርና፣ በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፎች ለሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት እምቅ አቅም ያለው አካባቢ ነው። የክልሉ ሕዝብ ዋና የኢኮኖሚ መሠረት ግብርና ሲሆን፣ ከሕዝቡ ከ92 በመቶ በላይ የሚሆነው የተሠማራውም በዚሁ ዘርፍ ላይ ነው። የክልሉ ጠረፋማ ወረዳዎች ከግብርናው በተጓዳኝ በባሕላዊ መንገድ የወርቅ ቁፋሮ ሥራ ያከናውናሉ።
የግብርናው ዘርፍ በዓመታዊ ሰብሎች፣ በቅባት እህሎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡናና በቅመማ ቅመም፣ በእንስሳት እርባታና ዓሣ ልማት እንዲሁም በንብ ማነብ ዘርፎች ከፍተኛ አቅም አለው። በማምረቻው ዘርፍ ደግሞ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር እንዲሁም በወረቀትና የወረቀት ውጤቶች ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ክልሉ ምቹ ነው።
ክልሉ በወርቅ ሀብታቸው ከሚታወቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ ሲሆን፣ ከወርቅ በተጨማሪ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚን በብርቱ የሚደግፉ እና ለሀገር ውስጥ ምርት የሚውሉ የሌሎች ማዕድናት መገኛም ነው። የግራናይት፣ ቶርማላይን፣ ግራናይት፣ መዳብ፣ ብረት፣ እምነበረድ፣ ጥቁር ድንጋይ፣ ኖራ፣ ጅብሰም፣ ጠጠርና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ክምችት አለው። ክልሉ የግዙፉ የዓባይ ግድብ መገኛ መሆኑ፣ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲሆን ተጨማሪ አቅም ይፈጥርለታል።
ክልሉ ከሚታወቅባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል አንዱ የእርሻ ኢንቨስትመንት ነው። ለእርሻ ተግባር ምቹ የሆነው ሰፊው የክልሉ መሬት፣ ለዘርፉ ልማት አስቻይ ሁኔታዎችን የሚፈጥር የሀገር ሀብት ነው። በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ለምርት አቅርቦት፣ ለሥራ እድል ፈጠራና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ሚና አላቸው። ለሀገር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ያላቸው አበርክቶም ቀላል አይደለም። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመሬት እና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ ስለክልሉ የእርሻ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የእርሻ ኢንቨስትመንት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በግብርና፣ በተለይም በእርሻ፣ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እምቅ አቅም ካላቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ ነው። ክልሉ ለእርሻ ምቹ የሆነ ሰፊ መሬት ባለቤት ነው። ለእርሻ ምቹ የሆነውን የክልሉን መሬት መጠን በጥናት የመለየቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም፣ ክልሉ ለእርሻ ኢንቨስትመንት ሊውል የሚችል ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጥ መሬት አለው።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ 633 ባለሃብቶች በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ይገኛሉ። 75 ባለሃብቶች በእጣን ምርት ላይ ተሰማርተዋል። ባለሃብቶቹ ከክልሉ መንግሥት ጋር ውል ፈፅመው በ448ሺ 289 ሄክታር መሬት ላይ የእርሻ ኢንቨስትመንት ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።
የክልሉ መንግሥትም ከዚህ ቀደም የነበሩ ኢንቨስተሮችን በማጠናከር አዲስ ለሚመጡ የእርሻ ኢንቨስተሮች መሬት ለመስጠት ዝግጅት አድርጓል። በዚህም በ2016 በጀት ዓመት 46ሺ ሄክታር መሬት ተለይቶ በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ለማስተላለፍ ዝግጅት ተደርጓል፤ የባለሃብቶቹ አቅምና ዝግጅት ተገምግሞ በአቅማቸው መሠረት የመሬት ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ይደረጋል። ለግብርናው ዘርፍ እድገትና ለመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑና ክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ አቅም ስላለው ለእርሻ ኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ይሰጣል።
በክልሉ የሚገኙ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች በሰፋፊ መሬቶች ላይ የሚከናወኑ በመሆናቸው ከኢንቨስትመንቶቹ የተሻለ ውጤት ለማግኘት ሥራውን ከአምራች ዘርፉ ጋር በማስተሳሰር እሴት (Value) በመጨመር ማምረት ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ በክልሉ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እስካሁን የተከናወኑ ሥራዎች በቂ እንዳልሆኑ የሚናገሩት አቶ ቢኒያም፣ ጉዳዩ ከክልሉ የእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ‹‹የእርሻ ኢንቨስትመንትን ከኢንዱስትሪው ጋር ማስተሳሰር ከዘርፉ የሚገኘው ውጤት የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል። እሴት የተጨመረበት ምርት የተሻለ ዋጋ ያወጣል፤ የምርቱን ተፈላጊነትም ይጨምራል። የእርሻ ሥራዎቹ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች በእርሻ ምርቶች ላይ እሴት የሚጨምሩ ኢንዱስትሪዎችን ማደራጀት ያስፈልጋል። ለአብነት ያህል ጥጥ በሚመረትባቸው አካባቢዎች የጥጥ መዳመጫዎች እንዲደራጁ እየተደረገ ነው። ሆኖም እስካሁን የተሠሩ ሥራዎች በቂ ስላልሆኑ ትኩረት ይፈልጋል›› ይላሉ።
የዘርፉ ዋና ዋና የትኩረት መስኮች
በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ አቅም ያለው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ለጥራጥሬና ለቅባት እህሎች እንዲሁም ለጥጥ ምርት ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። ክልሉ በአገር አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተተገበረ በሚገኘው የስንዴ ልማት መርሐ ግብር የራሱን አስተዋፅዖ ለማበርከትና ሀገራዊ ንቅናቄው ስኬታማ እንዲሆን ለማድረግ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም በቆላ ስንዴ ልማት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ይደረጋል። ባለሀብቶቹ የመስኖ ልማት መከናወን በሚችልባቸው አካባቢዎች እንዲሰማሩና ልዩ ትኩረት እንዲያገኙም እያደረገ ነው።
የኅብረተሰብ ተጠቃሚነት
የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ካሏቸው ፋይዳዎች መካከል አንዱ ፕሮጀክቶቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ለባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሲሰጥ ባለሀብቶች በተለያዩ መንገዶች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በማሰብ ነው። ማኅበረሰቡም ከኢንቨስትመንት ሥራዎች በሥራ እድል ፈጠራ፣ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ እድል ተጠቃሚ እንዲሆን ይጠበቃል። በዚህ ረገድ በክልሉ የሚከ ናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለክልሉ ኅብረተሰብ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እያስገኙ እንደሆነ አቶ ቢንያም ይገልፃሉ።
የእርሻ ኢንቨስትመንቶች በሚከናወኑባቸው አካባቢ ያለው የክልሉ ኅብረተሰቡ በሥራ እድል ፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ተጠቃሚ እየሆነ ነው። የሥራ እድል ፈጠራው ለኅብረተሰቡ የገቢ ምንጭ በመሆን ኑሮውን እንዲያሻሽል አስችሎታል። የቴክኖሎጂ ሽግግሩ ደግሞ የአካባቢው ኅብረተሰብ የእርሻ ሥራዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ ሆነው የተሻሉ ውጤቶችን እንዲያስገኙ አግዘዋል። ከሥራ እድል ፈጠራና ከቴክኖሎጂ ሽግግር ባሻገር በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ የተሠማሩ ባለሃብቶች በማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ ላይ በመሳተፍ ኅብረተሰቡ የጤና፣ የትምህርትና የንጹሕ መጠጥ ውሃ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገዋል።
‹‹ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ላይ ሲሰማሩ ለክልሉ መንግሥት ግብር ይከፍላሉ። ከባለሃብቶች የተሰበሰበው ግብር ደግሞ የክልሉን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ይከናወኑበታል›› በማለት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ለኅብረተሰቡ ካላቸው ቀጥተኛ ፋይዳ በተጨማሪ በተዘዋዋሪ ስለሚያስገኙት ጥቅምም ያስረዳሉ።
የመሠረተ ልማት አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ
በኢንቨስትመንት ዘርፍ ስኬት ላይ ጉልህ ሚና ካላቸው ግብዓቶች መካከል የመሠረተ ልማት አቅርቦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ተጠቃሾች ናቸው። የእርሻ ኢንቨስትመንት ተግባራት በቅድመ ምርት፣ በምርት ወቅትና በድህረ ምርት ጊዜያት ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልጉ በመሆናቸው የመሠረተ ልማት አቅርቦት ጥራት እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ግብዓት ነው።
‹‹በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ዋናው የመሠረተ ልማት ግብዓት መንገድ ነው›› የሚሉት አቶ ቢኒያም፣ በክልሉ ለእርሻ ኢንቨስትመንት የተለዩት ቦታዎች ለባለሃብቶች ተደራሽ መሆን የሚችሉ እንደሆኑና በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር መሬቶቹን ተደራሽና ምቹ የማድረግ ተግባራት እንደሚከናወኑ ይገልፃሉ።
አቶ ቢኒያም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ለባለሃብቶች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ ሲያብራሩ ‹‹ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሠማሩ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። የመሬት አስተዳደር ሥራ ከሙስና የፀዳና በዲጂታል አሠራር የታገዘ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው። ባለሃብቶች ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች አሟልተው ከተገኙ ያለምንም ውጣ ውረድ፣ በፍጥነት እንዲስተናገዱ እየተደረገ ነው። የክልሉ መንግሥት ተቋማትን የበለጠ ውጤታማ በሚያደርጋቸው መንገድ ያከናወነው የሪፎርም ሥራ በእርሻ ኢንቨስትመንት የሚከናወኑ ተግባራት ቀልጣፋ እንዲሆኑ እገዛ አድርጓል።
የኢንቨስትመንት ተግዳሮቶች
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፍ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በርካታ ፈተናዎችን እንደደረሱበት ይታወቃል። ከእነዚህ ችግሮች መካከል የፀጥታ መደፍረስ፣ መሬት ወስዶ ወደ ሥራ አለመግባት እና መሬቶችን ከኢንቨስትመንት ይልቅ ለሌሎች ተግባራት ማዋል ይጠቀሳሉ። እነዚህ ችግሮች ክልሉም ሆነ ባለሃብቶች ባቀዱት ልክ ወደ ሥራ እንዳይገቡ እና ሥራቸውን እንዲያቋርጡ ጫና በማሳደር ዘርፉ በምርት አቅርቦት፣ በሥራ እድል ፈጠራም ሆነ በቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያስገኛቸው ጥቅሞች እንዲቀንሱ አድርገዋል።
መሬትና ብድር ወስደው በተገቢው ሁኔታ ወደ ሥራ በማይገቡ ባለሃብቶች ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች ባለሃብቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማስቻላቸውን አቶ ቢኒያም ይገልፃሉ። በዚህ ረገድ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከማግኘታቸው በፊት ለሥራው ብቁ መሆናቸውን የመገምገም እና ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላም አፈፃፀማቸውን የመከታተል ሥራ በትኩረት ይከናወናል። የክልሉን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመመለስ ረገድ የተገኘው ውጤትም ባለሃብቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ አድርጓል። ‹‹በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥረው በነበሩ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሃብቶች ነበሩ። በአሁኑ ወቅት የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ የተሻለ በመሆኑ ባለሃብቶች ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችል እድል ፈጥሯል። አሁን የፀጥታ ችግር ለኢንቨስትመንት መሰናክል የሚሆንበት ደረጃ ላይ አይደለም›› በማለት ያስረዳሉ።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም