በኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ክለቦችን ለማቋቋም መመርያ አዘጋጅቶ ለማጽደቅ እየሰራ ይገኛል፡፡ የፓራ ቴኳንዶ ስፖርትን መልሶ ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ተዘውታሪ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል ወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት አንዱ ቢሆንም፤ ክለቦች ግን በብዛት የሉም፡፡ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በወርልድ ቴኳንዶ ስልጠናቸውን ተከታትለው የሚመረቁ ወጣቶች ክለብ ባለማግኘት ሲቸገሩ ቆይተዋል። ምንም እንኳን ሰልጣኞች በተገቢ ሁኔታ ስልጠናቸውን በማጠናቀቅ ብሔራዊ ቡድንን እስከመወከል ቢደርሱም የተወሰኑት ግን ባክነው ይቀራሉ፡፡ ለሰልጣኞች ብክነትና በስፖርቱ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎች ላለመፍራቱ ዋነኛው ምክንያትም የክለቦች አለመኖር መሆኑ ፌዴሬሽኑ ያምናል፡፡ ነገር ግን ክለቦችን ለመመስረት በቅድሚያ መከናወን ያለባቸው ጉዳዮች ባለመሟላታቸው ሊሳካ አልቻለም፡፡ ክለብ ለመመስረት ፍላጎት ያላቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ቢኖሩም ፌዴሬሽኑ በሚያስቀምጠው መስፈርት መሰረት ክለብ እንዲያቋቁሙ ቢጠበቅም፤ በሚፈልገው ልክ እየተሰራ ባለመሆኑ ለየት ያለ መመርያ ማዘጋጀቱን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
በ2016 ዓ.ም የፓራ ቴኳንዶ ስፖርትን መልሶ ለመጀመር በፌዴሬሽኑ የታቀደ ሲሆን፤ በዓመቱ የአካል ጉዳተኞች የቴኳንዶ ውድድር የሚካሄድ በመሆኑ ከዚህ በፊት በስፖርቱ ውስጥ የነበሩትን እና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በማሰባሰብ ስልጠና የሚሰጣቸው መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ የአካል ጉዳተኞች የቴኳንዶ ውድድር ከዚህ በፊት ተጀምሮ ሲቋረጥ መልሶ ለመጀመር እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም 12 የሚደርሱ የፓራ ቴኳንዶ ስፖርተኞች ተመርጠው በቅርብ ጊዜ በአንድ ቦታ የሚሰባሰቡም ይሆናል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለፓራሊምፒክ ስፖርት የሚደረገው ድጋፍ ከፍተኛ በመሆኑ በውድድሮች ለመሳተፍ መታቀዱንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሩ ተቋም፣ ከክለቦች ምስረታ ጋር የተያያዘውን ጉዳይ ያብራራሉ፡፡ ‹‹ትልቁና እስከ ዛሬ መሰራት የነበረበት ክለብን የማቋቋም ጉዳይ ነው፡፡ ስልጠና ተመጋጋቢ በመሆኑ ታዳጊዎች አካዳሚ ገብተው ስልጠናቸውን አጠናቀው ከሚወጡት የተወሰኑት ብሔራዊ ቡድንን የሚቀላቀሉ ናቸው፡፡ ክለቦች ባለመኖራቸውም ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡትን ጨምሮ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይበተናሉ፡፡ ክለብ ቢኖር ግን እነዚህን አቅፎ የሚይዝ ይሆናል፡፡ ከአካዳሚ የሚመረቁ ስፖርተኞችም የክለብ ተጫዋች በመሆን ተጠቃሚ ይሆናሉም›› ብለዋል። ክለቦች ሲመሰረቱ የክለብ መስፈርትን በማሟላት ደመወዝ መክፈልን ጨምሮ በሁሉም ውድድሮች ስለሚሳተፉ የክለብነት ስያሜን ያገኛሉ፡፡ ለዚህም ለየት ያለና ስፖርተኛውንም ሆነ አሰልጣኙን የሚጠቅም እና ስፖርቱን የሚያሳድግ የቴኳንዶ መመሪያ በመዘጋጀት ሂደት ላይ እንደሆነም ተረጋግጧል፡፡
የክለቦች መመሪያ ተዘጋጅቶ የተጠናቀቀ ሲሆን በተያዘው ወር መጨረሻ በሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ከጸደቀ በኋላ ክልሎች በመመሪያው መሰረት ክለብ እንዲመሰርቱ እንደሚያደርግም ኃላፊው ተናግረዋል። በዚህም ውስጥ ለውስጥ ንግግሮች እንዳሉና ክለቦችን ለመመስረት እቅድ ያቀዱ ተቋማትም አሉ፡፡ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ ተቋማትና ባንኮችም ክለብ ለመመስረት እቅድ ካላቸው ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚም ጉዳዩን ከክልሎች ጋር በመሆን መሰረት ለማስያዝ የመጀመሪያ እቅድ አድርጎ ይዟል፡፡ እስከ አሁን መሰራት ኖሮበት ባለመሰራቱ በተያዘው ዓመት የፌዴሬሽኑ የመጀመሪያ ስራው ክለብ መመስረትም ይሆናል፡፡ እስካሁን መዘግየቱም የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት መመሪያና ደንብ ባለመኖሩ ምክንያት ነው፡፡ መመሪያው በዓለም አቀፍ ደንብና ልምድ መሰረት ተዘጋጅቶ የተጠናቀቀ በመሆኑ በቀጣይ ጠቅላላ ጉባኤ ጸድቆ ተግባራዊም ይሆናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የሚዲያ ሽፋን ለማግኘት ከዲኤስ ቲቪ ጋር ስምምነት እያደረገ ሲሆን፤ ለዚህም ፕሮፖዛል ተዘጋጅቷል።
ፌዴሬሽኑ ክለቦችን ከማቋቋም ባለፈ በ2015 ዓ.ም ታቅደው ያልተሰሩ ስራዎችን ከ2016 ዓ.ም እቅዶች ጋር አጣምሮ ማቀዱንም ጠቁሟል፡፡ የአቅም ግንባታ ስልጠናን ጨምሮ አብዛኞቹን እቅዶች ማሳካቱን አስታውቋል፡፡ የአሰልጣኝነት፣ የዳን ፕሮሞሽንና የዳኝነት ሰልጠናዎችንም በሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር መስጠትም ችሏል። በተጨማሪም አምስት የአፍሪካ ሀገራት የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ የዳኝነት ስልጠና በሀገር ውስጥ አዘጋጅቶ ሊሰጥ ችሏል፡፡ ኢትዮጵያም አዘጋጅ በመሆኗ ከአርባ በላይ ዳኞች ተሳትፈውበታል፤ ከ40 ዳኞች 33ቱ ምዘናውን በማለፍ ዓለም አቀፍ ዳኞች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2016