የኑሮ ሸክም አቅላዮቹ ሴቶች

በዚህ በምንገኝበት ዘመን የሰዎች የዕለት ተዕለት የአኗኗር ዘይቤ እየተለወጠ ነው። በተለይ የጊዜ ጉዳይ የብዙዎች ጥያቄ እየሆነ የመምጣቱ ጉዳይ፤ማልዶ ከቤት መውጣትና ምሽት ላይ ወደ ቤት መመለሱ የማጀቱን ሥራ ለማከናወን፣ማህበራዊ ጉዳይንም ለመወጣት፣ለራስም ሆነ ለቤተሰብ ጊዜ መስጠት እያስቻለ አይደለም። ኑሮ ሩጫ እየሆነ ነው። በአሰልቺነትም እየተገለጸ ነው። ሰዎች ከሥራ በኋላ ቤታቸው ሲገቡ ልጆቻቸውን የመመልከት፣ ምን እንደተማሩ የመጠየቅ፣ የቤት ስራቸውን ማገዝ ፣በእረፈት ቀንም ቢሆን ልጆችን ወደ መዝናኛ እየወሰዱ ማጫወት እየፈለጉ አልቻሉም። እድር፣ እቁብ፣ ለቅሶና ሌሎች ማህበራዊ ግዴታዎች መወጣትም እያዳገተ ነው።

በተለይ እድር ማህበራዊ አገልግሎት፣ሰው ሲሞት አባላት ተረኛ ሆነው ቁርስ፣ምሣ እና በእራት ሰአት በማስተናገድ ኃላፊነት መወጣት የተለመደ ነው። አሁን ላይ እንኳን ይህን አላፊነት ለመወጣት ቀብር መቅበርና ለቀስተኛውን ማጫወት እያዳገተ ነው። በተለይ በሥራ ላይ ላሉት ችግር እየሆነ ነው። ቤት የሚውለውም ሰው ቢሆን ለራሱ ጉዳይ ወጥቶ ትራንስፖርት አጥቶ በመጉላላት ቶሎ ወደቤቱ የሚመለስበት ጊዜ ረጅም በመሆኑ ችግር መሆኑ አልቀረም። እድር ደግሞ የአባላቱን ሁሉ ተሳትፎ ይጠይቃል።

በሰራተኛው በኩል ችግር እየሆነ ያለው አብዛኛው ሰው የሚሰራበትና የመኖሪያ አካባቢ የተራራቀ መሆኑ ነው። በሥራው ላይ በሰአቱ ለመገኘት ከቤቱ ማልዶ መውጣት ይኖርበታል። ማታ ወደ ቤቱ ሲመለስ ደግሞ በተለያየ ምክንያት መሽቶ ነው የሚገባው። ከፊሉ የሰርቪስ አገልግሎት አግኝቶ ትራንስፖርት የመጠበቁ ጉዳይ ቢቃለልለትም በመንገድ መዘጋጋት ምክንያት ይመሽበታል። ትራንስፖርት ጠብቆ የሚገባው ደግሞ የበለጠ ይቸገራል። በዚህ የተጣበበ ሁኔታ ልጆችን መከታተልና ሌሎች ተግባራት ማከናወን አይቻልም። ያለው ጊዜ ምግብ ከመመገብ አይተርፍም።

እነዚህ ነገሮች በተለይም ከተማ በሚኖረው ላይ ጎልተው የሚታዩ ቢሆንም ሴቶች ላይ ሲሆን ግን ጫናው ከፍ ብሎ ይታያል። ሴቶች የውጭውን ሥራ ከውነው ከመምጣት ባሻገር በቤታቸው ደግሞ እናትም ሚስትም ናቸውና ብዙ ኃላፊነቶችን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ምንም እንኳን ኃላፊነትን የሚጋሩ አባወራዎች እንዳሉ ቢታወቅም የሴቶች ኃላፊነት ድርብ ድርብርብ መሆኑ ይታወቃል። ምንም እንኳን ጊዜውን በማብቃቃት የቤታቸውንም ሌላውንም ማህበራዊ ጉዳይ እየከወኑ ቢሆኑም ድካሙ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ከዚህ አንጻር ከጊዜ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ሴቶችን እያስጨነቀ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

የአኗኗር ዘይቤን መቀየር ግድ እየሆነ ነው። እንደቀደመው ጊዜ እንደ በርበሬ፣ሽሮ የመሳሰሉ ለምግብ የሚውሉትን በቤት ውስጥ ከማዘጋጀት የተዘጋጁ ምግቦችን ገዝቶ መጠቀም ይገባል። በዚህም ኑሮን በማቃለልና እራሳቸውንም በገቢ እያገዙ የሚገኙትን በማህበር ተደራጅተው እየሰሩ ያሉትን እንደ እነ ዝናሽ ሀይለማርያምና ጓደኞቿን መጥቀስ ይቻላል። ብዙ ሴቶችን ከድካምና ሃሳብ ብሎም ከተጋነነ የገንዘብ ወጪ በማዳን እያገዙ ናቸው።

እኛም ስለአገልግሎታቸው አነጋግረናቸዋል። ወይዘሮ ዝናሽ ሀይለማርያም ተወልዳ ያደገችው ደብረብርሃን አካባቢ ነው። ሆኖም ግን ብዙውን የእድሜ ዘመኗን አዲስ አበባ ከተማ ነው የኖረችው። ዝናሽ በትዳር ነው የምትኖረው።

ከባለቤቷ ጋር እየተሳሰቡ ነው የሚኖሩት። በትዳር ዘመናቸውም በልጆች መባረክንም አገኙ። ዝናሽ ከባለቤቷ ጋር አንተ ትብስ እኔ እየተባባሉ ችግርንም ደስታንም አብረው እየገፉ አራት ልጆችን ወልደው እያሳደጉ ባሉበት ወቅት ግን ያላሰቡት ነገር ገጠማቸው ። አብሮ ለመኖር የማያስችላቸው ደረጃ ላይ ደረሱና ተለያዩ። ዝናሽ ከባሏ በገቢ ዝቅ ያለች በመሆኗ ልጆቿን ብትፈልጋቸውም ብትወዳቸውም ማሳዳግ አትችለምና ለአባታቸው ሰጥታ ከቤት ወጣች።

ዝናሽ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በኑሮ ጉስቁልና ውስጥ ወደቀች ምንም እንኳን ልጆቿን የሚያሳድገው አባታቸው ቢሆንም እሷም መኖር አለባትና የቤት ኪራይ የምትከፍለው ለቀለብ የምታውለው ገንዘብ በእጅጉ አጠራት፤ ቁጭ ብዬ አልሞትም በማለትም በየሰው ቤት እየሄደች ልብስ ማጠብ ፣እንጀራ መጋገርና ሌሎች ስራዎችን በመስራት ገቢ ማግኘት ብትጀምርም ስራው ከገቢው ይልቅ ድካሙ አመዝኖባት መቋቋም ስላቃታት ተወችው።

ይህም ቢሆን ግን ቤት ኪራዩም ሆነ ቀለብ ጊዜ የማይሰጥ ነውና ዝናሽ ራሷን ለማስተዳደር ሌሎች አማራጮችን ማየት ፈለገች ለጊዜው ይሆናል ብላ ያገኘችውም ወፍጮ ቤት ላይ ቁጭ ብላ ጊዜ ለሌላቸው ሴቶች በርበሬ ሽሮ ስንዴ እንዲሁም የገንፎና የአጥሚት እህል ለቅማ ቀንጥሳ አዘጋጅታ አስፈጭታ ለሸማቹ በኪሎ በማቅረብ ገቢ ለማግኘት ነበር ያቀደችው። እቅዷንም ይዛ ወደ ወፍጮ ቤት ሄደች። ወፍጮ ቤቱም ፈቀደላት።

ሥራ ፈጣሪዋ ዝናሽ አሁን ላይ በተለይም በጊዜ ማጠር ማዘጋጀት ለማይችሉ ሰዎች ማቅረቡን ተያያዘችው። ደንበኞችዋም በስፋት የመንግሥት ሰራተኞች ናቸው። የአነርሱን የኑሮ ጫና በማቅለል ፤እሷም መተዳደሪያ ገቢ ልታገኝበት ችላለች።

“…በስራዬ ደስተኛ ነኝ ፤ደስተኛ የሆንኩት ደግሞ የማገኘው ገቢ በቂ ሆኖ ሳይሆን የብዙዎችን ችግር ተጋርቼ በርበሬውን በሚፈልጉት መንገድ አዘጋጅቼ ስሰጣቸው በጣም ስለሚደሰቱ ነው። በጠቅላላው ኑሯቸውን ስላቀለልኩላቸው ነው” ትላለች።

ዝናሽ በተለይም በርበሬን በኪሎ ከስድስት እስከ ሰባት ብር እየተቀበለች ትቀነጥሳለች፣ ትለቅማለች ቅመሙንም በተመሳሳይ አዘጋጅታ ታስፈጭና ባለቤቶቹ መጥተው እንዲወስዱ ታደርጋለች። በዚህ የሚደሰቱ ሰዎችም አንዳንድ ጊዜ ከዋጋው በላይ ጉርሻ ይሰጧታል።

‹‹በፊት ሰው ቤት እየተንከራተትኩ ከምሰራ ሥራ በመጠኑም ቢሆን ይህ ሥራ ይሻላል የቀን ገቢ ይገኝበታል፤ አሁን ላይ ልጆቼም መጥተው ይጠይቁኛል፤ እኔም ሲመቸኝና ስችል የእናትነቴን አንዳንድ ነገሮች አደርግላቸዋለሁ። በጠቅላላው ግን ስራው መጥፎ አይደለም ለብዙዎችም እረፍት የሰጠ ነው›› ትላለች።

በተመሳሳይ እዛው ወፍጮ ቤት ላይ የዝናሽ አይነት ሥራን ስትሰራ ያገኘናት ወይዘሮ ዙሪያሽ ይታየው ትባላለች። እሷም እንደምትለው ሰው ቤት እየዞሩ መስራት ጉልበት ይጨርሳል ፤በዛ ላይ ለብዙ አይነት ጾታዊ ጥቃቶች አጋላጭ ነው። ይህ ሥራ ግን ልክ እንደ ቢሮ በጠዋት እንገባለን ደንበኞቻችን መጥተው በርበሬ እንድናዘጋጅላቸው ገዝተው ሰጥተውን ይሄዳሉ። አንዳንዶቹም አዘጋጅተን እስከምንሰጣቸው ድረስ ቁጭ ሊሉ ይችላሉ ከዛም የሚገባንን ከፍለውን ተመሰጋግነን እንለያያለን። እናም ጥሩ ነው ትላለች።

አሁን አሁን በየወፍጮ ቤቱ ልክ አንደ እኛ ኑሮን ቀለል የሚያደርጉ በሰሩት (በሚሰሩት ) ስራም ለራሳቸው ገቢን የሚያገኙ ሴቶች እየተበራከቱ መጥተዋል የምትለው ወይዘሮ ዙሪያሽ እሷ ይህንን ስራ ሰርታ ትዳሯን ቤቷን እየደጎመች ልጆቿንም በጥሩ ሁኔታ እያሳደገች ስለመሆኑም ትናገራለች።

ወይዘሮ ዙሪያሽ የቤት እመቤትና የሶስት ልጆች ናት ስትሆን፤ባለቤቷም የቀን ሥራ እየሰራ ቤቱን የሚያስተዳድር ነው ። ነገር ግን እሱ የሚያመጣውን ገንዝብ ብቻ ጠብቆ መኖሩ ኑሮን አክብዶባት እንደነበር ገልጻ ዛሬ ላይ ግን እሷም በአቅሟ ወጥታ እየሰራች ገቢ እያገኘች በመሆኑ ቤቷ ሙሉ እንደሆነላት በመግለጽ በተለይም ጊዜ አጥተው የሚቸገሩ እህቶቿን በዚህ መልኩ ማገዟ ትልቅ ደስታን እንደሚፈጥርባት ትናገራለች።

ወይዘሮ ዙሪያሽ ቤት ቁጭ ብለው የባሎቻቸውን እጅ በማየት ለሚቸገሩ ሴቶች የምለው አለኝ ትላለች፤” ….ትዳር የሁለት ሰዎች የጋራ ጉዳይ ነው። አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ የሚሆንበት ሁኔታ ትክክል አይደለም፤ በተለይም የአንዱ ገቢ በቂ ባልሆነበት ሁኔታ ተቀምጦ መቸገር አስፈለጊ አይደለም ፤በመሆኑም ማንኛዋም ሴት በተለይም የጤና ችግር እስከሌለባት ድረስ ወጥታ እንደ እኛ የምትችለውን ስራ ፈጥራ መስራትና ገቢ ማግኘት በዛም ቤቷን መደጎምና ልጆቿ ሳይቸገሩ እንዲማሩ ማድረግ ትችላለች። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመንግት ሥራ ተወጥረው ለቤታቸው የሚሆን ጊዜ አጥተው የሚሰቃዩ እህቶቻችንን ሰርተን ብንደግፋቸው ደስታው የጋራ ነው” በማለት ሃሳቧን ትገልጻለች።

በዛው ወፍጮ ቤት በርበሬ እንዲዘጋጅላት ሰጥታ እስኪጠናቀቅ ቆማ ስትጠብቅ ያገኘኋት ወይዘሮ መቅደስ ተክለሃይማኖት የመንግሥት ሰራተኛ ስትሆን የሥራ ቦታዋ በጣም ሩቅ እንደሆነ፣ከሰኞ እስከ ቅዳሜ እንደምትሰራና ጠዋት ወጥታ ምሽት ወደቤቷ እንደምትመለስ ነው ያጫወተችን። ያላትን አንድ የእረፍት ቀንም ለተለያዩ ማህበራዊ ጉዳይ እንደምትጠቀም ነው የገለጸችው። በዚህ ምክንያት እንደ ሽሮና በርበሬ በቤቷ ውስጥ ማዘጋጀት ባለመቻሏ በወፍጮ ቤት ውስጥ እያዘጋጁ ከሚሸጡ ለመጠቀም ምርጫዋ ማድረጓን ነግራናለች።

ወይዘሮ መቅደስ ትዳር ከመሰረተች ሶስት ያህል ዓመታት እንደሆናትና የአንዲት ሴት ልጅ እናት መሆኗን ገልጻ፤ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያት በርበሬ፣ ሽሮ ጤፍና ሌሎች የሚፈጫጩ ነገሮችን በእናቷ ቤት እየተዘጋጀላት ስትጠቀም መቆየቷን ነግራናለች። አሁን ግን እናቷ ከዚህ አለም በሞት ስለተለዩ ሁለተኛ አማራጭ ባደረገችው እየተጠቀመች እንደሆነ ነው የገለጸችው።

ወይዘሮ መቅደስ እናቷን በሞት እንዳጣች ግራ ገብቷት ነበር። በተለይ በርበሬ ከባዕድ ነገር ጋር ይቀላቀላል፤ግዥ ጥሩ አይደለም የሚለውን አስተያት ትሰማ ስለነበር በጣም ተጨንቃ ነበር። በዋጋም ተመጣጣኝ አለመሆንም እንዲሁ አስቸግሯት እንደነበርና አሁን ላይ ግን በወፍጮቤት ውስጥ አዘጋጅተው የሚሸቱ ሴቶች ማግኘቷ ችግሯን እንዳቃለላት ታስረዳለች።

እንደእሷ ለማዘጋጀት ጊዜና ረዳት ለሌላቸው ሴቶች ትልቅ አቅም የሚሆኑ ስለመሆናቸውም መስክራለች። ሊበረታቱና በስራውም ሊገፉበት እንደሚገባም አመልክታለች።

ሌላዋ ወይዘሮ እሙዬ በላቸው ትሰኛለች። ወጣት ባለትዳር ስትሆን ካገባችም አስር ያህል አመታትን አስቆጥራለች። በርበሬ ሲበላ እንጂ ሲዘጋጅ አሰልቺና አድካሚ ጊዜ የሚወስድ ነው ትላለች። እሷም ምንም እንኳን የቤት እመቤት ብትሆንም ስራው ከባድ ስለሆነ ግን ሁሌም በርበሬ ስትፈልግ የምታሰራው እነሱን ስለመሆኑ ታብራራለች።

‹‹በርበሬን ቤት በሰራተኛ ማዘጋጀት ራሱን የቻለ አድካሚና ወጪም ያለው ነገር ነው፤ እዚህ ከሆነ ግን ወዲያው ይገዛል ይቀነጠሳል ይለቀማል ቅመሙም ጎን ለጎን ይዘጋጃል ይፈጫል። በጣም ጊዜና ገንዘብን ቆጣቢ ነው። ወፍጮ ቤቶቹም እንደ ድሮው በርበሬው ይደለዝ ይድረቅ ምናምን ብለው ሰፊ ጊዜ ከመውሰድ ተላቀው ዛላውን መፍጨት መጀመራቸው ከሴቶቹ አገልግሎት ባልተናነስ እነሱም እያገዙን ነው ሊመሰገኑም ይገባቸዋል›› ትላለች።

ኑሮ በዘዴ ማለት ይህ ነው። ሴቶች በዚህ መልኩ በተለይም ጊዜ የሌላቸውን መሰሎቻቸውን ለማገዝ ስራ ሲፈጥሩ ወፍጮ ቤቶች ደግሞ ከዘመኑ ጋር የሚራመዱ የአገልግሎት መስጫዎችን ሲያዘጋጁ ጥሩ መናበብ ስለሚኖር ሁሉም ነገር ያለድካም ይጠናቀቃል። እነ ወይዘሮ ዝናሽና ጓደኞቿም ለሥራ ፈጣሪነታቸው ሊመሰገኑና ሊበረታቱ ይገባል።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2016

Recommended For You