አዲስ አበባ፡- በተያዘው በጀት ዓመት ከኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት፣ ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭና አገልግሎት 30 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ሁለት ሺህ ከ993 በላይ ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ይደረጋል፡፡ በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከውጭ ሀገራት ኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት፣ ከሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ሽያጭና ከተለያዩ አገልግሎቶች 30 ቢሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ እየተሠራ ነው፡፡
በበጀት ዓመቱ ለሦስት የአፍሪካ ሀገራት ማለትም ለሱዳን፤ ለኬንያ እና ለጅቡቲ ሁለት ሺህ 993 ነጥብ አራት ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት በማድረግ 182 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሠራ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ይህም አሁን ባለው የዶላር ምንዛሬ 10 ቢሊዮን ብር ይሆናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዘንድሮው በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች፣ ከባቡር መስመር የኃይል ሽያጭና ከተለያዩ አገልግሎቶች 20 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2015 በጀት ዓመት ተቋሙ 22 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ገቢ ከኤክስፖርት፣ ከሀገር ውስጥ ሽያጭና ከአገልግሎት ማግኘቱን ለማንፀሪያነት አንስተዋል። ከተገኘው ገቢም አምሥት ነጥብ አምሥት ቢሊዮን ብር የሚሆነውን የሚሸፍነው የውጭ ኤክስፖርቱ ነው ሲሉ አስታውሰዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት ለሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ አንድ ሺህ 701 ጊጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ተደርጎ እንደነበር ያነሱት አቶ ሞገስ፤ በዘንድሮው በጀት ዓመት የሚላከው ኃይል መጠኑ ወደ ሁለት ሺህ 993 ጊጋ ዋት ከፍ ይደረጋል ብለዋል።
በዚህም ካለፈው ዓመት ጋር በንፅፅር ሲታይ የኤክስፖርት ገቢውን በእጥፍ የማሳደግ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይልን ለውጭ ሀገራት ኤክስፖርት በማድረግ የሀገሪቷን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግ አዳዲስ ስምምነቶች እየተደረጉ ነው ያሉት አቶ ሞገስ፤ ስምምነቶች በተያዘላቸው ቀነ ገደብ የሚጠናቀቁ ከሆነ በዘንድሮው በጀት ዓመት ወደ ታንዛኒያ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል።
ታደሰ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም