ሠላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? በትምህርት፣ በጥናት፣ በንባብ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በጨዋታ እና ቤተሰብን በመርዳት እንዳሳለፋችሁ ጥርጥር የለውም። ልጆች ትምህርታችሁን በርትታችሁ እየተከታተላችሁ እንደሆነ ይታመናል። አያችሁ ልጆች ትምህርት የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን በመገንዘብ በርትታችሁ መማር ይኖርባችኋል። በትምህርታችሁ ውጤታማ ለመሆን ታዲያ በራሳችሁ ከምታደርጉት ጥረት ባሻገር በትምህርታቸው ጎበዝና ታታሪ የሆኑ ተማሪዎችን አርአያ መከተል ይኖርባችኋል። ከዚህ በመቀጠል ተሞክሯዋን የምናቀርብላችሁ ሁለት ጎበዝ ተማሪዎች ለእናነት በትምህርት መጎበዝ ይጠቅማልና እንካችሁ።
ታዳጊ ሔመን በቀለ የሚኖረው አሜሪካ ነው። የአስራ አራት ዓመቱ ኢትዮጵያዊ የ2023 የታዳጊ ሳይንቲስቶች ሽልማት አሸናፊ መሆን ችሏል። ታዳጊው ሽልማቱን ያገኘው በምን መሰላችሁ ልጆች? የቆዳ ካንሰርን የሚከላከል ሳሙና ፕሮጀክት በማቅረብና በእርሱ ደረጃ ካሉ ታዳጊ ሳይንቲስቶች ጋር ተወዳድሮ በማሸነፉ ነው። የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሔመን ውድድሩን በማሸነፉ በታላላቅ ሳይንቲስቶች ሥር ሆኖ ከፍተኛ ስልጠና የሚያገኝበት ዕድል እና ለቀጣይ ሳይንሳዊ ምርምሩ ሁለገብ ድጋፍ የሚያገኝበት ሁኔታ እንደሚፈጠርለት የተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የውድድሩ አሸናፊ በመሆኑ የ25 ሺ ዶላር ተሸላሚ ከመሆኑም ባሻገር ‹‹ከፍተኛ የአሜሪካ ታዳጊ ሳይንቲስት›› የሚል ማዕረግ ማግኘት ችሏል። ስለዚህም እንደ ሔመን የምርምር ውጤት ወይም ሃሳብ ያላችሁ ልጆች ለወላጆቻችሁ እና ለመምህራኖቻችሁ በመንገር ድጋፍ አግኝታችሁ የብዙዎችን ችግር መቅረፍ ትችላላችሁ። በዚሁ አጋጣሚ ዝንባሌያችሁንም አውቃችሁ በቀጣይ በመረጣችሁት የትምህርት መስክ ውጤታማ ለመሆንም ያግዛችኋል።
ሌላዋን ጎብዝ ተማሪ ደግሞ እናስተዋውቃችሁ። ተማሪ ሐናን ናጂ ትባላለች። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የክሩዝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ስትሆን የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት 649 በማስመዝገብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሚባል ውጤት አምጥታለች። ተማሪዋ ትምህርቷን በሚገባ ተከታትላ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ ወላጆቿ ኩራትና ደስታ እንዲሰማቸው አድርጋለች። እናም ልጆች ለራሳችሁ እንድትሆኑ ቤተሰባችሁም በሚገባ ደስተኛ እንዲሆኑላችሁ ትምህርታችሁን በሚገባ በርትታችሁ መከታተል ይኖርባችኋል።
ተማሪ ሐናን የ12ኛ ክፍል ፈተናን ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እቅድ አውጥታ በሚገባ ስታጠና የነበረች ሲሆን፤ ብዙ ጊዜዋን በንባብ፣ አስተማሪ ከማስተማሩ በፊት ቀድማ የክፍለ ጊዜውን ትምህርት ይዘት ለመረዳት ቀድማ የማንበብ ልምድ ስለነበራት አስተማሪዎች ሲያስተምሩ ትምህርቱን በደንብ እንድትረዳ አስችሏታል። ለሁሉም የትምህርት አይነቶች እኩል ትኩረት በመስጠት ለፈተናው አስፈላጊውን ዝግጅት ቀድማ ማጠናቀቋ ለውጤት እንድትበቃ ያስቻላት ሲሆን፤ ለሁሉም ነገር ትኩረት ተሰጥቶበት ከተሠራ የማይሳካ ነገር እንደሌለ የእርሷ ውጤት ምስክር ነው። ተማሪዎች ከሰው ከመጠበቅ ይልቅ ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው ለውጤት መስራት እንዳለባቸውም የእርሷ የትምህርት ውጤት ያስ ተምራል።
ልጆች! በርግጥ ቴክኖሎጂን ማወቅና ከግዜው ጋር አብሮ መሄድ የግድ ቢልም በተለይ ኢንተርኔትንና ከኢንተርኔት ጋር የተያያዙ ነገሮችን አስፈላጊ ሲሆን ብቻ መጠቀም እንዳለባችሁ በተደጋጋሚ መግለጻችንን ታስታውሳላችሁ አይደል? አዎ! ስለዚህ ሁሌም ቢሆን ይህን ምክር አትዘንጉ። ሐናንም ኢንተርኔትን ለትምህርቷ ግብዓት ለሚሆኑ መረጃዎች የምትጠቀም ሲሆን ዓላማና ግብ አስቀምጣ አጥንታ ባገኘችው ውጤት ደስተኛ ለመሆን በቅታለች። ለትምህርቷ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለሚያዘናጓት ሁኔታዎች ቦታ አልሰጠቻቸውም። በቀጣይም ‹‹ፋርማኮሎጂ›› የማጥናት ፍላጎት አላት።
የተማሪ ሐናን እናት ወይዘሮ ሽኩሪያ ሽፋ እና አባቷ አቶ ናጂ አሕመድ ልጃቸው ሳትሰለች በርትታ በማጥናት የልፋቷን ውጤት በማግኘቷ ከፍተኛ ኩራትና ደስታ ተሰምቷቸዋል። አላማዋን ለማሳካት እቅድ አውጥታ እያንዳንዱን ነገር ከመፈጸም ወደ ኋላ እንደማትል እና በቀጣይ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደምትደርስ እምነታቸው ከፍተኛ ነው።
ወላጆቿ እንዳሉት ተማሪዎች በትክክለኛው የሕይወት መስመር እንዲጓዙ የወላጆች ሚና ከፍተኛ ነው። ለዚህም አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይገባል። በተጨማሪም ተማሪ ሐናን ከክፍል ጓደኞቿ ጋር መረዳዳትን የምትወድ፤ የምታውቀውን ለሌሎች የምታካፍል የትምህርት ቤቱ አረዓያ ስትሆን፤ እናንተም ልጆች ከእርሷ በመማር ካጠናችሁ፣ ቀድማችሁ ካነበባችሁ፣ ትኩረታችሁን ለሚስቡ ነገሮች ዕድል ካልሰጣችሁ፣ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመረዳዳት እና የምታውቁትን በማካፈል በትብብር ከሠራችሁ ጥሩ ውጤት እንድታመጡ ያግዛችኋል።
ወላጆችም ልጆቻችሁ እንዲያጠኑ ክትትል በማድረግ እንዲሁም አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር እገዛ ማድረግ ይጠበቅባችኋል። ከዚህ በተጨማሪም ልጆቻችሁ ልዩ ተሰጥኦ ካላቸው ተሰጥኦቸውን የሚያወጡበት ሁኔታ በማመቻቸት ልጆቻችሁን ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማብቃት ይኖርባችኋል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2016