ሀገራት የኢንቨስትመንት ዘርፋቸውን በማሳደግ ጥቅል ሀገራዊ እድገታቸውን ዘላቂ ለማድረግ ከሚተገብሯቸው አሰራሮች መካከል አንዱ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን (Special Economic Zones) ማቋቋም ነው፡፡ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የሚፈጥሩትን የሥራ እድል፤ ለሀገር በቀል የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪው መስፋፋት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ፤ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርንና የባለሙያዎችንና የሠራተኞችን ክህሎት ለማሳደግ እና የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚኖራቸውን ወሳኝ ሚና እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ ያላቸውን አበርክቶ በአጠቃላይ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት መሻሻል የሚኖራቸውን ጉልህ ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገራት ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን ያቋቁማሉ፣ ያስፋፋሉ፡፡
ኢኮኖሚያዊ ትስስር ስር እንዲሰድ ለማድረግ እንዲሁም የግብርና ልማትን፣ የምግብ ዋስትናን፣ የኢንዱስትሪ ልማትንና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ወሳኝ የሆነውንና የሰዎች፣ የካፒታል፣ የእቃዎችና አገልግሎቶች ነፃ እንቅስቃሴ የሰፈነበት አህጉራዊ ገበያ ለማምጣት ያለመው ‹‹አጀንዳ 2063›› ስኬታማ እንዲሆን ነፃ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች ልማት አስፈላጊ እንደሆነ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መመስረቻ ሰነድ ላይም ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለንግድና ኢንቨስትመንት በቂ መሠረተ ልማት ለመዘርጋት እንዲሁም ቀረጥን በመቀነስ ወይም ደረጃ በደረጃ በማስወገድ እና ለንግድና ኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑትን ቀረጥ ያልሆኑ መሰናክሎችን ለማስወገድ በስምምነቱ አባል ሀገራት ዋስትና ያለው የእቃዎችና አገልግሎቶች ገበያ ለመፍጠርና ለማስፋፋትም ነፃ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በሰነዱ ላይ ተመላክቷል፡፡
ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እንዲሁም መሬትን ጨምሮ ሌሎች እምቅ ሀብቶች ያላት ኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን በማቋቋም ረገድ በመዘግየቷ ከእነዚህ ቀጣናዎች ልማት ማግኘት የሚገባትን ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም ማጣቷ ተደጋግሞ ሲገለፅ ቆይቷል። የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እግር ከወርች አስረው የያዙት አንዳንዶቹ መሰናክሎች ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች በሚያስገኟቸው ጥቅሞች የሚፈቱ ስለመሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን በማቋቋም የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ለማልማት የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ተመርቆ ሥራ የጀመረው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠናም (Dire Dawa Free Trade Zone) የዚሁ ጥረት አካል ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነባው ‹‹አዲስ ቱሞሮው›› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እና ግንባታው በኦሮሚያ ክልል የሚከናወነው ‹‹ገዳ›› ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑት የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች ግንባታ አካል ናቸው። ግንባታው በ35 ሄክታር ላይ የሚያርፈው ‹‹አዲስ ቱሞሮው›› ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በቻይናው ‹‹ፈርስት ሀይዌይ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ›› (China First Highway Engineering Corporation) ሽርክና የሚገነባ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናው የባህል፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርክ እንዲሁም የቢዝነስና የንግድ፣ የመኖሪያና የመዝናኛ ማዕከላትን ያካትታል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በብሔራዊ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ ፖሊሲ ሰነድ ላይ ውይይት በማድረግ፣ ፖሊሲው በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ ምክር ቤቱ ፖሊሲው በሥራ ላይ እንዲውል ውሳኔ ያሳለፈው ኢትዮጵያ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት የጎላ አስተዋፅኦ ባለውና ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተስፋፋና እየጎለበተ በመጣው ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንድትሆን አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ ፖሊሲው የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ሥርዓት ለማሻሻል፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበትን ለማሳደግ፣ የወጪ ንግድ አቅምን ለማጎልበት፣ ሰፊ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር እንዲሁም በሀገሪቱ ዋና ዋና የንግድ ኮሪደሮች የደረቅ ወደቦችን ለማስፋፋትና የሎጂስቲክ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ሥርዓቶችን እውን ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና በኢባዳን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማ እንደሚገልፁት፣ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለምርት አቅርቦት እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ የእነዚህ ቀጣናዎች ዋና ዋና ዓላማዎች የሥራ እድል ፈጠራን እና ምርትንና ምርታማነትን መጨመር፣ የወጪ ንግድን ማስፋትና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እንዲሁም ካፒታልና ቴክኖሎጂን መሳብ ናቸው። ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የራሳቸው የምርት ሥፍራ/ወሰን፣ የአስተዳደር ሥርዓት፣ የታክስ ሕግጋት እና የጉምሩክ ሥርዓት አላቸው፡፡ ቀጣናዎቹ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ በጥሬ እቃ አቅርቦት እንዲሁም በምርት አቅርቦትና ግብይት ተግባራት ላይ የሚሰማሩ አካላትን ቁጥር ይጨምራሉ፡፡ ይህም የልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ልማት ከኢንቨስትመንት እድገት ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዳለው ማሳያ ነው፡፡
እርሳቸው እንደሚያብራሩት፣ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የግል (Private) እና የመንግሥት (Public) ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታት የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲያድግ ያስችላሉ። ቀጣናዎቹ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (Foreign Direct Investment) በመሳብ የግል ባለሃብቶች በስፋት በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ያደርጋሉ፡፡ በሌላ በኩል ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ሰፊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን የሚፈልጉ በመሆናቸው መንግሥት በመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት (Infrastructural Investment) ላይ እንዲሰማራ በማድረግ የመንግሥት ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ እድል ይፈጥራሉ፡፡ በአጠቃላይ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ለባለሃብቶች ምቹ እድሎችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ተነሳሽነት ይኖራቸዋል፡፡
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በተለየ ሁኔታ የተመረጡ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለዘርፎቹ ልማት አቅም ባላቸው የተመረጡ አካባቢዎች የተለዩ አሰራሮችን በመከተል የሚቋቋሙ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ እነዚህ ቀጣናዎች የኢንቨስትመንት ካፒታልን መሳብን ታሳቢ በማድረግ የሚቋቋሙ ሲሆኑ፣ የራሳቸው የንግድ፣ የታክስና ሌሎች ሕግጋት ይኖሯቸዋል፡፡ የኢንቨስትመንት ካፒታልንና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ጉልህ ሚና አላቸው፡፡ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ የሥራ እድል እንዲፈጠር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር እውን እንዲሆን በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰት ትርጉም ባለው መልኩ እንዲጨምር ያስችላሉ። ቀጣናዎቹ ለኢንቨስትመንት እድገት ምቹ የሆኑ አሰራሮችን ተከትለው የሚሰሩ በመሆናቸው የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ ምቹ እድል የሚፈጥሩ የኢኮኖሚ ማሳለጫ ሥፍራዎች ናቸው፡፡
‹‹ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እንዲስቡ ተደርገው የሚዋቀሩና ወደ ሥራ የሚገቡ ናቸው፡፡ አጠቃላይ ዓላማቸው ኢንቨስትመንትን በመሳብ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብትን ማሳደግ ነው፡፡ የልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ዋና ዓላማ ኢንቨስትመንትን መሳብና ማሳደግ ነው። ኢንቨስተሮችን በተሻለ ሁኔታ ለመሳብ ታስበው የሚደራጁ ሥፍራዎች ናቸው›› ይላሉ፡፡ በልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ልማት ዘርፍ ቻይና ተጠቃሽ እንደሆነች ያስታወሱት ዶክተር ሞላ፣ ሌሎች የእስያና የደቡብ አሜሪካ ሀገራትም በዚህ ዘርፍ ትልቅ እመርታ እያሳዩ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ፡፡
በልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ውስጥ የሚተገበሩ ሕጋዊ አሰራሮች ቀለል ያሉና ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዶችን የሚቀንሱ በመሆናቸው ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሰማራት የሚያደርጉትን ጥረት በአንፃራዊነት ቀላል ያደርጉላቸዋል፡፡ በነፃ የንግድ ቀጣናው ውስጥ ገብተው የሚሠሩ ባለሀብቶች፣ አስመጪና ላኪዎችም ሆኑ ድርጅቶች የልዩ ልዩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
በልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ውስጥ ያሉ የንግድ (የግብርና የጉምሩክ) ሕግጋት ከሌሎቹ የንግድ አሰራሮችና ሕግጋት የተለዩ እንደሆኑ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፣ በቀጣናዎቹ የሚሰማሩ ባለሃብቶች የታክስ ቅነሳ እንዲሁም ቀላልና አመቺ የሆነ የጉምሩክ ሥርዓት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ፡፡
ዶክተር ሞላ በበኩላቸው ‹‹በልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች የሚሰማሩ ባለሃብቶች ከሚያገኟቸው ልዩ እድሎችን ጥቅሞች መካከል አንዱ የታክስ እፎይታና ቅናሽ ተጠቃሚነት ነው፡፡ በተጨማሪም የታሪፍ ቅነሳ እድል ያገኛሉ፡፡ የተሻሉ የመሠረተ ልማት አቅርቦቶች ተጠቃሚም ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ ቀጣናዎቹ ለኢንቨስተሮች ሳቢ የሆኑ ጥቅሞችን የያዙ በመሆናቸው የባለሃብቶችን ተሳትፎ ያበረታታሉ›› በማለት ይገልፃሉ፡፡
ኢትዮጵያ ምቹ የአየር ንብረት፣ ብዙ የሰው ኃይል፣ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት በመሆኗ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ልማትን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችና እድሎች እንዳሏት የሚናገሩት ዶክተር ሞላ፣ በመሠረተ ልማት፣ በሰው ኃይል አቅርቦት፣ በሕግ ዝግጅት፣ በአገልግሎት አሰጣጥና ለልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ውጤታማነት አስተዋፅኦ በሚያበረክቱ ሌሎች ግብዓቶች አቅርቦት ረገድ የላቀ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡
‹‹የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የሕግና ቢሮክራሲ፣ በሕግ… የተሻለ ካደጉ ሀገራት ስለሚመጡ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ ይገባል፡፡ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቱ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ሕግጋት ሲሻሻሉ ክፍተቶች እንዳይኖሩና ለሥራ ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ጥራት ያለው አሰራርን ለመዘርጋት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል›› በማለት የልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ልማት ውጤታማነት ትልቅ ጥረት እንደሚጠይቅ ያስገነዝባሉ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ በበኩላቸው፣ በልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ልማት ትግበራ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት የወሰደቻቸው ተሞክሮዎች በጥልቀት መታየት እንዳለባቸው ያሳስባሉ። ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ሲቋቋሙ የመሬት ወረራ እንዲሁም ያልተገባ የመሬት ዋጋ ንረት ሊከሰት ስለሚችል ጥብቅ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና ጠንካራ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ፡፡
ሰላምና ፀጥታን ማስፈን ሊዘነጋ እንደማይገባና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ሌሎች የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተቋማትና እና ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎቹ የሚቋቋሙባቸው አካባቢዎች የአስተዳደር አካላት ስለቀጣናዎቹ አጠቃላይ አሰራር በጋራ መሥራት እንደሚኖርባቸውም ይመክራሉ፡፡
ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ከሚሰጠው ከልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ሥርዓት ርቃ መቆየቷ ብዙ ጥቅሞችን አሳጥቷታል፡፡ የእነዚህ ጥቅሞችና እድሎች መታጣት ደግሞ በአጠቃላይ እድገቷ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባት አይካድም። ስለሆነም ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎችን ለማቋቋም የተጀመሩትን ጥረቶች በማጠናከር ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገቱ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያስመዘግብ ማድረግ ይገባል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም