ሀደ ሲንቄዎች -የሰላም እናቶች

ሕዝብ እንደ ሕዝብ የሚያምነውና የሚያከብረው ባህሌ ወጌ ብሎ በውስጡ ተጠልሎ ለሐግና ደንቡ ተገዢ ሆኖ የሚኖርለት ነገር ይኖረዋል፡፡ በተለይም ይህ ተገዢ የሚሆንለት ባህል እምነት አልያም ሌላ ነገር ራሱን ለማስተዳደር ልጆቹን በሥነ ምግባር ኮትኩቶ ለማሳደግ አልፎ ተርፎም የእርስ በእርስ ማህበራዊ መስተጋብሩ ያላአንዳች ችግር ይሳለጥ ዘንድ የሚጠቀምበት ስለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ ላያስፈልግ ይችላል፡፡

ይህ ብዙኃኑ የሚተዳደሩበት ባህልና ወግ በሚጣስበትም ጊዜ ደግሞ አጥፊውን የሚቀጣ ሌላውን ደግሞ የሚያስተምር ቅጣትም የሚተላለፍበት የራሱ ሥርዓት ያለውም ስለመሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ግንኙነት ውስጥ ወንዶችም ሴቶችም የሚሳተፉበት ነው፡፡ በተለይም ሴቶች ካላቸው ማህበራዊ ግንኙነት ስፋት ከእናትነታቸውና አርቆ አስተዋይ ከመሆናቸው ጋር በተገናኘ ውሳኔ አሰጣጡ ላይም የራሳቸውን ጉልህ ድርሻ ማኖራቸው የማይታይበት ሀቅ ነው።

ሴቶች በማህበራዊ ፍትሁ እንዲሁም ሕዝብ ባህሌ ወጌ ብሎ በተቀበለው ትውፊተያዊ ሂደት ላይ የነቃ ተሳትፎን እንዲያደርጉ ከሚፈቅደው አካሄድ አንዱ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ በሥራ ላይ የሚውለው የአባገዳ ሥርዓት ነው። ይህ ሥርዓት በተቻለ መጠን ዴሞክራሲያዊ አካሄዶችን የሚከተል ሲሆን በዳይና ተበዳይ ፍርድ ሳይዛባ በትክክል ዳኛ ፊት ቆመው የሚዳኙበት ማህበረሰብ የሚተዳደርበትና የሚያኖረውን ሕግ የሚያገኝበት ከምንም በላይ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚታይበትና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ጎልቶ የሚንጸባረቅበት ሂደት ነው። በዚህ ውስጥ ደግሞ የሰላም እናት የሆኑ ሀደ ሲንቄዎች ያላቸው ሚና በቀላሉ የሚታይም አይደለም።

የኦሮሞ ሕዝብ ባህሌ ብሎ የሚያምንበትና የሚተዳደርበት መንገድ ነው የሲንቄ ባህላዊ ሥርዓት፤ የሲንቄ እናቶች የሚይዙትና በቁመታቸው ልክ የሚዘጋጀው ቀጥ ያለና ሀሮሬሳ ከሚባል ዛፍ የሚዘጋጀው ዘንግም የሚሰጠው ላገቡ ሴቶች ሲሆን ሚናቸውም በማህበረሰቡ መካከል ሰላምን ማውረድ ነው። ይህንን ብትር የያዘችና ሀደ ሲንቄ የሆነች እናትም በአካባቢዋ የትኛውንም ዓይነት የሰላም መደፍረስ ለማብረድ ትልቅ ኃይል ያላት ናት። እሷ ብትሯን ይዛ ቆማ የማይሰማ የለም።

ለምሳሌ ባልና ሚስት ሲጣሉ ጸቡን የሰማች ሀደ ሲንቄ ብትሯን ይዛ እልልታዋን እያቀለጠች ትወጣለች፤ የእሷን እልልታ የሰሙ ሌሎች በአካባቢው ላይ ያሉ ሀደ ሲንቄዎችም ተመሳሳይ እልልታን እያሰሙ ይወጡና ይሰባሰባሉ፤ በነገራችን ላይ እልልታው ዝም ተብሎ መጠራሪያ ብቻ አይደለም ይልቁንም በእኛ ኃላፊነት እጆቻችን ላይ ያለውን ብትርና የተሰጠንን ኃላፊነት ተጠቅመን ልባችንን አንድ በማድረግ የተፈጠረውን ችግር እናስወግድ ፤ ሰላምን እናስፍን የሚልም ጥሪም ጭምር ነው።

ሀደ ሲንቄዎች ሴቶች ጸቡ ወደተፈጠረበት ቤት ገብተው በትራቸው ከወረወሩ እሱን ተሻግሮ ጸብ የሚቀጥልም ሆነ መልስ የሚሰጥ አካል የለም። እንደ ዋዛ የሚወረውሯት በትርም የሚንቀለቀለውን የነገር እሳት በማብረድ ከፍ ወዳለ ምናልባትም አሰቃቂ ሁኔታን ሊፈጥር የሚችል ጸብን በማብረድ ውሃ የማድረግ ኃይል አላት።

ነገር ግን ይህችን ታምረኛ ብትር ተሻግሮ ጸብ አነሳላሁ፤ አልያም እማታለሁ ያለ ሰው ይህንን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የብዙዎች መተዳደሪያ የሆነውን ባህል ጥሷልና ከዛ በኋላ ጸቡ ከሚሆነው ከሚስቱ አልያም ከባላንጣው ጋር ሳይሆን ከማህበረሰቡ ጋር ነው። በመሆኑም እናቶችን የሚያከብር ብሎም ከማህበረሰቡ ጋር አብሮ መኖር የሚፈልግ አካል የፈለገ ነገር ቢፈጠር ብትሯን አይሻገርም። ፍትህ ሊያገኝ ነውና ከሚንቀለቀለው ቁጣውም ታገስ ይላል።

እንግዲህ በገዳ ሥርዓት ውስጥ ካሉ በተለይም ሰላምን ለማስፈን ከሚያግዙ ሥርዓቶች መካከል ሀደ ሲንቄ ተጠቃሽ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ሀደ ሲንቄ ሆና የምትመረጥ ሴትም ያገባች፤ የወለደች የቤተሰብ ኃላፊነቷን በአግባቡ የምትወጣ በማህበረሰቡ ውስጥ ጥሩ ስም ያላት ሴት ልትሆንም ይገባል።

በነገራችን ላይ ይህ ሁኔታ ሴቶች ለሰላም ያላቸውን ወይም የሚኖራቸውን ትልቅ ሚና የሚያጎላ ነው። ሴቶች ለችግር መላ በማፈላለግ ፈጥኖ መፍትሔ በማምጣት ያላቸው ሚናም ላቅ ያለ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰላም ወዳድ ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው ሰላምን በመፍጠር በኩል ላቅ ያለ አስተዋጽኦን የሚያበረክቱ ናቸው።ይህ ጥበባቸው ደግሞ የሀደ ሲንቄነት ሚና ሲጨመርበት ያች ሁሉን የምታበርድ ብትር በእጃቸው ሲይዙ ጎልቶ ይወጣል።

ሀደ ሲንቄዎች በአካባቢያቸው የገጠማቸው ችግሮች በሰላም ከቋጩ በኋላ ለሽምግልና የሚቀመጡት አባገዳዎች ናቸው። እዚህ ላይ ግን በዳይም ተበዳይም ንግግር የሚጀምሩት ሀደ ሲንቄዎችን አስፈቅደው ሀደ ሲንቄዎቹም መናገር ይችላሉ ብለው ሲፈቅዱ ብቻ ነው። ሀደ ሲንቄዎችም በተጠየቁት መሠረት አዎ ይናገሩ ሲሉ ፍቃዳቸውን በመስጠት እርጥብ ሳርን በጥሰው ይረጫሉ።

በጠቅላላው ግን ሀደ ሲንቄ በወጣችበት በወረደችበት ሁሉ ሰላም አለ ፤ ፍቅርም እንደሸማ ሁሉም የሚለብሰው ይሆናል። በማንኛውም ወቅትና ቦታ ላይ ሀደ ሲንቄ ተገኝታ የተናገረችው ወይም በትሯን ከፍ አድርጋ የለመነችው ነገር ሁሉ ቦታውን መያዙ አይቀሬ ነው። አባ ገዳ ያለ ሀደ ሲንቄ ትርጉም የለውም። በመሆኑም ሀደ ሲንቄ በሄደችበት ሁሉ ሰላምን የምታውጅ ትልቋ ኢትዮጵያ ናት።

ሀደ ሲንቄ ግጭት ማስወገድ ሰላምን ማስፈን ብቻ አይደለም ሚናዋ ይልቁንም የእናቶችና የሴቶችንም መብት በማስከበሩ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ያላት ናት። ሴቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲጠናከር እንዲሁም ውሳኔ ሰጪነት ሚናቸው እንዲጎላና እድሉ ተመቻችቶላቸው በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረጉ ረገድ ሀደ ሲንቄዎች የሚወጡት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ሀደ ሲንቄዎች በተለይም በትዳሯ ተጽዕኖ እየደረሰባት አልፎ ተርፎም ባለቤቷ እየደበደባት ያስቸጋራትን ሴት የሚያሸማግሉበት የራሳቸው የሆነ ጥበብ አላቸው፤ ይህም ጥበባቸው ሲንቄ ዱላቸውን በመያዝና ሰውየውን በማነጋጋር ችግሩን እንዲናገር በማድረግ ለችግሩ መፍትሔ በመስጠት በኩል የሚሰሩት ሥራ ያለ ሲሆን በተለይም ተበዳይ የሆነችው ሴት ከቤት ወጥታ ከሆነ በሬ አርዶ እሷንና ጎረቤቶቿን እንዲሁም ለእርቀ ሰላሙ የመጡትን ሀደ ሲንቄዎች አበልቶ ሲሸኝ እርቀ ሰላሙ የሚወርድበት ሁኔታም አለ።

የሰላም እሴት ማለት የባህሪ የአመለካከት የአኗኗር ወዘተ የእሴቶች ስብስብና ዘይቤ ነው፡፡ ይህንን እሴት ደግሞ ከሚያመጡ መካከል ከላይ ምግባራቸውን የገለጽንላቸው ሀደ ሲንቄዎች ተጠቃሾቹ ናቸው።

የሰላም እሴት ከጦርነት ከአመፅ ከሽብር ወዘተ ተግባሮች የራቀ ማንኛውንም ሁከትና ብጥብጥ የሚጸየፍ የተፈጠሩ ግጭቶችን ሁሉ በውይይትና በመግባባት የመፋታት ባህል መሻጋገር ማለት እንደሆነም ነው የአባገዳዎቹ አጋሮች ሀደ ሲንቄዎች የሚመክሩት፡፡

ዜጎች አለመግባባትን በሰላማዊ ውይይትና ድርድር እንዲሁም ከማንኛውም ሁከት ነፃ በሆነ መልኩ መፍታት የሚችሉበትን ጥበብም በማስተማር፣ አሉታዊ የሆኑ ደንብና ሥርዓቶች እንዲቀረፉ ሰላም መገንባት እንዲሰፍንም ይሰራሉ፡፡ እስከ አሁንም ብዙ ሰርተዋል ወደፊትም በተመሳሳይ ይሰራሉ።

ሕብረተሰቡ በዘልማድ ከሚደነግገው የወንዶች የበላይነት ወደ ሕገ-መንግሥታዊ የፆታ እኩልነት የአመለካከት አድማሱን በማስፋት ግንዛቤውን ሲይዝ የሰላም ባህል ተሸጋጋሪ መሆኑን ያሳያል፡፡

በሕብረተሰቡ (በዜጎች) ዘንድ የሚታዩ መከፋፈሎች ተቀርፈው አንድነት እና መተሳሰብ በዜጎችና በግለሰቦች ዘንድ እንዲፈጠርም የበኩላቸውን ይወጣሉ፡፡

በማንኛውም ወቅትና ጊዜ ዲሞክራሲያዊ ትግልና ተሳትፎ በነፃነት የመግለጽ ሥርዓት በሰፊው ሲለመድ እና በሕብረተሰቡ ሲተገበሩና ተቀባይነታቸው የሚጎለብተውም የእነዚህን እናቶች የሰላም አካሄድ እንደ ተሞክሮ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይም ማስፋት ሲቻል ነው፡፡ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ግልጽ ግንኙነት ሲኖርና ዜጎች እንደ መርህ ወይም መመሪያ ሲጠቀሙበት ማየት የሚጀመረውም ይህንን መልካምና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣን የኦሮሞ ማህበረሰብን የሀደ ሲንቄዎች የሰላም አምባሳደርነት ማስፋት ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ሁሉም ሰው ሰብዓዊ መብትን ማክበር የተለመደ ተግባር ሆኖ እንዲታየው ሀደ ሲንቄዎች ይሰራሉ፣ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ የዜጎችን ደንብና ሥርዓት መሠረት ባደረገ መልኩ ስልጣንን በአግባቡ እንዲጠቀምም በአባገዳ ውስጥ ሆነው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግሩን ሲመሩትም ተስተውለዋል፡፡

በዜጎች ደንብና ሥርዓት ለውጥ ውስጥ እድገት ከገንዘብ እና ከሃብት አቅም ይልቅ ለማህበረሰቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖማያዊና ፖለቲካዊ እድገትና ለውጥ በማተኮር ፍትሃዊና ዘላቂነቱ የተረጋገጠ አካባቢያዊ መስተጋብር ሲኖር የሰላም እሴት ያሳያል፡፡ በሌላ መልኩ የሰላም አደናቃፊዎች ደግሞ የግል አረዳድ የተዛባ ግላዊ ቅድመ ትንቢያ አድሎአዊ አሰራር እና ማግለል የአባገዳ ቀኝ እጆች የኦሮሞ ሕዝብ እናቶች በጠቅላላው ሀገር የሆኑትን የሰላም እናቶች (ሀደ ሲንቄዎች) ማክበር ለኦሮሞ ሕዝብ ብቻ የተተወ ሳይሆን እንደ ሀገር ተሞክሮዎችን ወስደን በብዙ መልኩ ልንጠቀምበት የሚገባ ነው። ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ሰላም ያስፈልገናል ይህ ማለት ደግሞ የሀደ ሲንቄዎችን ሚና እንፈልጋለን ማለት ነው። እንደ እናት ያጠፋን ልጆቻቸውን መክረው አንተም ተው አንተ ብለው መንገድ ሊያሳዩንም ኃላፊነቱ አለባቸው። እኛም እነሱን አለመስማት ኢትዮጵያን አለመስማት መሆኑን በመገንዘብ ያሉትን ሁሉ ሰምተን የሰላም አምጪዎች ልንሆን ይገባል።

በሌላ በኩልም ዛሬም ድረስ በርካታ ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው በዘመዶቻቸው እንዲሁም የእኔ በሚሏቸው ሰዎችና በማያውቋቸውም በርካታ ጾታዊ ጥቃትን የሚያስተናግዱበት ጊዜ ነው። ሀደ ሲንቄዎች ለዚህም መላ አላቸውና መላቸው ከማህበረሰብ አልፎ ወደ ሀገር ከፍ ቢል ብዬም መመኘቴ አልቀረም። አዎ ከፍ ቢልም እናተርፍ ይሆናል እንጂ የምንጎዳው ነገር የለም።

 እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን መስከረም 29/2016

Recommended For You