ለዲጂታል ሥርዓቱ የበለጠ መስፋፋትና ውጤታማነት

ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችላት የዲጂታል 2025 ስትራቴጂን ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች፡፡ በእዚህም ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መተግበር ከተጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆነውም፣ ለውጦች እየተመዘገቡ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ዲጂታል የነዳጅ ግብይት እንዲሁም ሌሎች በርካታ የዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች በሀገሪቱ ተግባራዊ መሆን መጀመራቸው አበረታች የሚባል ለውጦች ለማስመዝገብ ምክንያት ሆነዋል፡፡ እንደ ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ያሉት መሠረተ ልማቶች እየተስፋፉ የመጡበት ሁኔታ “ዲጂታል ኢትዮጵያን” እውን የማድረጉ ሂደት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

ሌላው የዲጂታል የክፍያ ሥርዓቱ እንዲከናወንባቸው በተግባራ ላይ ከዋሉት የክፍያ መንገዶች አንዱ ቴሌ ብር ነው፡፡ በቴሌ ብር አማካኝነት በ2015 ዓ.ም ብቻ የተፈጸመን የገንዘብ ዝውውር ብንመለከት 679 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በዚህ ሥርዓት ውስጥ መዘዋወሩን እንመለከታለን፡፡ በተመሳሳይ በዘመናዊ የገንዘብ ልውውጥ ሥርዓቱ ኤ.ቲ.ኤም፣ ሞባይል ባንኪንግ፣ ፖስት ማሽኖችን፣ ሲቢኢ ብርና ሌሎች በርካታ የዲጂታል ክፍያ አማራጮች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ባንኩ በ2015 ዓ.ም ብቻ ሦስት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ብር በዘመናዊ ግብይት የገንዘብ ልውውጥ አድርጓል፡፡ ይህም የባንኩን አጠቃላይ ሀብት ሦስት እጥፍ ሊሆን ትንሽ የቀረው ገንዘብ እንደሆነ መረጃው ያመለክታል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በቅርቡ በሀገሪቱ በዓመት አራት ትሪሊየን ብር በዲጂታል የክፍያ አማራጮች እየተዘዋወረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ የዲጂታል ክፍያ አማራጭ በሀገሪቱ መስፋፋቱ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር እንዲቀነስ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በቅርቡ መስከረም 21 በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እንደተመለከተው፣ የጥሬ ገንዘብ ዝውውሩ ባለፉት ሁለት ወራት በከፍተኛ መጠን ቀንሷል፡፡

መንግሥት ከፍተኛ የገንዘብ ልውውጥ የሚደረግባቸው ግብይቶች በዲጂታል እንዲከናወኑ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከ170 በላይ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ውስጥ መግባታቸውንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት፡፡

የዲጂታላይዜሽን አሠራሩ ተግባራዊ በመደረጉ ፈጣን፣ ግልጽና ቀልጣፋ አሠራር እንዲኖር ከማድረጉ ባሻገር ዘመናዊ የገንዘብ ዝውውር እንዲኖር በማድረግ በጥሬ የሚደረገው የገንዘብ ዝውውር እንዲቀንስ እያደረገው መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አቶ አቤኔዘር ወንደሰን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ እና የኢትስዊች የፕሮግራም ማኔጀመንት ቢሮ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አሠራር ተግባራዊ ማድረጓ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች አሉት። ትግበራው መጀመሩ ተወዳዳሪነትን በመፍጠር ኢኮኖሚውን ያሳድጓል፡፡ ኢኖቬሽን (አዳዲስ ፈጠራ) ከማበረታታት፣ ምርታማነት ከመጨመር እና አዳዲስ የቢዝነስ ሞዴሎች (የሥራ እድሎችን) እንዲፈጠሩ ከማድረግ አኳያም ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል፡፡ የውጭ ኢንቪስትመንት በቀላሉ ለመሳብ ያግዛል ሲሉ ያብራራሉ፡፡

የተሻሻሉ አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት እንዲቻልም እድል ይሰጣል፡፡ የተደራሽነት ችግር ያለባቸው ቦታዎች ላይ በቀላሉ ለመገኘት ያስችላል። በትምህርት፣ በጤና እና በመሰል ዘርፎች ተደራሽ መሆን ያልቻሉ አካባቢዎች ላይም እንዲሁ ውጤታማ ያደርጋል፡፡ ተገልጋዩ ሕብረተሰብ ባለበት ቦታ ሆኖ በሞባይል ባንኪንግ ተጠቅሞ በቀላሉ ፍላጎቱን ማሟላት ያስችላል። ከዚህ በፊት አገልግሎቱን ሲያገኙ ያልነበሩ አካባቢዎችን በቀላሉ ሞባይል ዋሌቶችን እንዲጠቀሙ እድል ይከፍታል፡፡ ይህ ደግሞ የፋይናንስ አገልግሎት አካታችነትን በማሳደግ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የባንክ ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

‹‹የማህበረሰቡን ንቃተ ህሊና ይጨምራል፡፡ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል በማድረግ፤ ግልጽነት እንዲኖር፣ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና የመንግሥት ወጪዎች እንዲቀንሱ ያስችላል›› የሚሉት አቶ አቤኔዘር፤ እንዲሁም ለግብርና ዘርፍ ቢሆንም የሚሰጠው ጠቀሜታ ትልቅ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ግብርና ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በማምጣት የተለያዩ ሞባይል መተግበሪያዎች በመጠቀም የተለያዩ ለግብርና የሚጠቀሙ መረጃዎች ለአርሶ አደሩ በወቅቱ በማድረስ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲወሰዱ መፍትሔ የሚሰጥ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ አርሶ አደሩ ዲጂታል መተግበሪያዎችን (ኢኮሜርስን) ተጠቅሞ ምርቱን ለሽያጭ እንዲያቀርብ እድል እንደሚከፍት ጠቅሰው፤ ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲኖር በማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በስፋት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እየተቀላቀለች ብዙ ሥራዎችም እየተሰሩ መሆኑን የሚገልፁት አቶ አቤኔዘር፤ ከተሰሩ በርካታ ሥራዎች መካከል አንዱን የዲጂታል የነዳጅ ክፍያ ሥርዓት መሆኑን ይናገራሉ። ይህ ርምጃ በነዳጅ ላይ ግልጸኝነት የሰፈነበት ውጤታማ የሆነ አሠራር እንዲፈጠር ማድረጉን በምሳሌነት ማንሳት እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ የተዘረጋው የአሠራር ሥርዓት በጣም ፈጣን የሆነ ውጤታማ ሥራ የተሰራበትና አበረታች ለውጦች የተመዘገቡበት እንደሆነም አንስተዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ የተለመደው የወረቀት አሠራር ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል ክፍያ ስለሚቀይር ማንዋል ሂደቱ የሚወስደውን ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ነው፡፡ ከተለያዩ ስህተቶችም የጸዳ፣ በጣም ፈጣን የሆነ የክፍያ ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችል ነው፡፡ ወጪዎች ይቀንሳል፤ የአስተዳደር ጫናዎችንም ይቀንሳል፡፡ በመንግሥት በኩል ትልልቅ ወጪዎች ሲያስወጡ የነበረ ብዙ ኦፕሬሽናል ወጪዎችን ይቀንሳል፡፡ የፋይናንሻል አስተዳደር ላይ የራሱ ጥቅም እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ከክፍያ ሥርዓቶች ጋር በቀላሉ ማስተሳሳር ስለሚቻል ነጻ የሆነ የክፍያ ሥርዓትን መገንባት ያስችላል፡፡ ለምሳሌ ጨረታዎች ሲወጡ የጨረታው ሂደት ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲታየ ስለሚያደርግ ተጠያቂነት በማስፈን ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

“ዲጂታል አሠራሩ ተግባራዊ ሲደረጉ የተለያዩ ችግሮች ሊጋጥሙ ይችላሉ” የሚሉት አቶ አቤኔዘር፤ የዓለም ተሞክሮች እንደሚያሳዩት በዚህ ረገድ የሚጠበቁ ችግሮች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ ዲጂታል ሲስተም ማላመድ ጥቅም እንዳለው ሁሉ እራሱን የቻለ ስጋቶችና ተግዳሮች ይዞ እንደሚመጣ ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያ የሳይበር ደህንነት ስጋት እንደሆነ አንስተው ይህ ስጋት የሚኖርና የሚጠበቅ መሆኑን ይገልፃሉ። የሳይበር ደህንነት ስጋት ዲጂታል አሠራሩን ተጠቅሞ የዳታ መሰረቅ፣ ዳታው መታየት በማይገባ ሰው መታየትና አስፈላጊ (ጠቃሚ) የሆኑ መረጃዎች መውጣት እና የመሳሳሉት ዓይነት ችግሮች ሊገጥሙ እንደሚችሉ ያመላክታሉ፡፡

እነዚህን የሳይበር ደህንነት ስጋቶች የተለያየ መንገዶችን ተጠቅሞ መከላከል እንደሚቻል የሚያነሱት አቶ አቤኔዘር፤ ሲስተሙን ሁልጊዜም ወቅታዊ በማድረግ፣ ለዚህ ተብለው የተዘጋጁ ፕላትፎርሞችን በመጠቀም ስጋቱን መቀነስና ማስወገድ አማራጭ መሆኑን ይናገራሉ። ሌላው ትልቁ ነገር ተገልጋዩን ግንዛቤ የመጨመር ሥራ በስፋት መሥራት ነው፡፡ አሁን ላይ እየጋጠመ ያለው ችግር በግንዛቤ እጥረት የሚከሰት ነው፡፡ በስህተት የመለያ ቁጥር( ፒን ኮድ) አሳልፎ ለሌላ ሰው መስጠት፣ በጥንቃቄ ካለመያዝ የሚከሰቱ ስርቆቶች በብዛት የሚስተዋሉት ናቸው፡፡ እነዚህን ስጋቶች ለማስወገድ የተጠቃሚውን ግንዛቤ ማስፋትን ይጠይቃል፡፡

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉም የሚናገሩት አቶ አቤኔዘር፤ በተለይ ቴክኒካል ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን ያነሳሉ። በዚህ ምክንያት አገልግሎቱን ለሰዓታትም ይሁን ለተወሰነ ደቂቃ ሊያቋርጡ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ እነዚህን በመፍታት ተኪ የሆኑ ሲስተሞችን ማዘጋጀት እና እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ መፍታት የሚያስችል እቅድ አዘጋጅቶ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፤ በቀጣይ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ለማድረግ የመጀመሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በስፋት በዘመቻ መልኩ መስጠት አለበት፡፡ ከመንግሥት መሥሪያ ቤት ጀምሮ እስከ ተገልጋዩ ድረስ ላሉ አካላት የዲጂታል አሠራር ጥቅምና ስጋት የሆኑ ነገሮች ላይ የተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫዎች የመስጠት ያስፈልጋል፡፡

“በእኛ ሀገር ብዙ ጊዜ በዲጂታል ዙሪያ ወርክ ሾፖችን መስጠት አልተለመደም” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የሚሰጡ ካሉም በጣም ውስን ናቸው ይላሉ፡፡ ጎረቤት ኬንያን እንኳን በሳምንት አምስት ቀን ስለ ዲጂታል ውይይትና ምክክር እንደሚደረግና ወርክሾፖች እንደሚካሄዱ ይገልፃሉ፡፡ ወርክሾፖች በማዘጋጀት በሁሉም ተቋማት ላይ ስለዲጂታል ግንዛቤ እንዲፈጠር በማድረግ ሕብረተሰቡ ግንዛቤው ሊኖረው እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡ የዘርፉ ተዋናዮች እንደ ባንኮች፣ ጥቃቅንና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት፣ ብድርና ቁጠባ ተቋማት፣ ቴክኖሎጂ የሚያቀርቡና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እና መሰል ተቋማት የሚያደርጉት ተሳትፎ መጨመር አለበት የሚሉት አቶ አቤኔዘር፤ የፋይናንስና ተቋማት በትብብርና በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪ የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ ሳፍሪኮም መምጣቱ መሠረተ ልማት የተደራሽነት እያደገ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣ መሠረተ ልማቱን በይበልጥ ማደራጀት በገጠሪቱ የሀገራችን አካባቢዎች አገልግሎት ተጠቃሚ ያልሆኑት ቦታዎች ላይ የዲጂታል አገልግሎትን የተደራሽነትን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። ይህ በራሱ ለመሠረተ ልማት እድገት ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

በዲጂታል አሠራር የሀገራትን ተሞክሮ ስንመለከት ኢትዮጵያ ገና ጀማሪ ከመሆኗ አንጻር እያስመዘገበች ያለችው ለውጥ አበረታች ነው የሚሉት አቶ አቤኔዘር፤ ኬንያ በጥሬ ገንዘብ ከሚካሄድ ግብይት ወጥታ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ዲጂታል ገብታለች ሲሉ በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ በእ.ኤ.አ 2021 የወጣ መረጃ ዋቢ አድርገው እንዳብራሩትም፤ በኬንያ ያለው ከ79 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የባንክ ተጠቃሚ ነው፡፡ በአንጻሩ በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው የባንክ ተጠቃሚ 45 በመቶ ያህል ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጻር ኬንያ በደንብ እንደምትበልጥ ያሳያል፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለምሳሌ ዛምቢያ 49 በመቶ፣ ታንዛንያ 52 በመቶ፣ ጋና 68 በመቶ፣ ኡጋንዳ 66 በመቶ ያህል እድገት ነበራቸው፡፡

ኢትዮጵያ በዘርፉ ከፍተኛ አቅም እንዳላት ጠቅሰው፣ ከዚህ በላይ ማደግ እንደምትችል መረጃዎች ያሳያሉ ሲሉ አቶ አቤኔዘር ይገልጻሉ፡፡ የሕዝብ ብዛቷ ከሌሎቹ እጥፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዲጂታል ላይ ሥራዎች በስፋት ቢሰሩና አሁን የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ቢቀጥል ሁሉም ሀገሮች ከደረሱበት የእድገት ደረጃ በላይ ማስመዝገብ እንደምትችል ይጠቁማሉ፡፡

አቶ አቤኔዘር እንዳብራሩት፤ ሌሎች ሀገራት አካታች የፋይናንስ አገልግሎትን በመኖሩ ምክንያት እድገታቸው ፈጣን ነው ፡፡ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ካለው ተጠቃሚ አንጻር ስንመለከት በኢትዮጵያ 36 በመቶ ሲሆን፤ በኬንያ 85 በመቶ ተጠቃሚ ነው ያለው፡፡ ይህም ከአካታች ፋይንናስ ተጠቃሚዎች መካከል 85 በመቶው ዲጂታል መንገዶችን የሚጠቀሙ መሆናቸው ያመለክታል፡፡ ጋናም እንዲሁ 85 በመቶ ተጠቃሚ ያላት ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ተጠቃሚ ብዛት የዚህን ሁለት እጥፍ ማድረግ ይችላል፡፡ በተመሳሳይም የሞባይል ገንዘብ ዝውውር (ልክ እንደቴሌ ብር አይነቶችን) ተጠቃሚዎች ቁጥር የኬንያን አምስት እጥፍ፣ የጋናን ሰባት እጥፍ መድረስ እንደሚችል አቶ አቤኔዘር ያብራራሉ፡፡

በተለያየ መልኩ የሌሎች ሀገራት ከኛ ብዙ ርቀት ተጉዟል የሚሉት አቶ አቤኔዘር፤ ‹‹ጠንካራ የሆነ የፋይናንስ ሥርዓት ካላቸው ከነዚህ ሀገሮች ብዙ ተሞክሮዎችን ቀስሞ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፤ በዚህም ኢኮኖሚያችንን መደገፍ ይቻላል›› ብለዋል፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ሀብታሙ ዳምጤ በበኩላቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ ለሀገራችን የጥሬ ብር ሕትመት የሚወጣው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረቱም በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ተግባራዊ በመደረጉ የክፍያ ሥርዓቶች ሁሉ ዲጂታል እንዲሆኑ በመደረጉ ምክንያት የተፈጠሩትን እንደ ቴሌ ብር ዓይነቶቹን መተግበሪያዎች ስንመለከት የዲጂታል ዘርፉ ከተሰራበት ተጠቃሚው ምን ያህል ፈላጎት መጠቀም እንደሚችል የታየበት ነው፡፡ በዘርፉ እንደ ሀገር ገና ጀማሪ እንደመሆናችን ብዙ ሥራ መሥራት ቢጠብቅብንም፤ አሁን ላይ በዲጂታል የክፍያ ሥርዓቶች እየታየ ያለው ለውጥና እየተመዘገበ ያለው ውጤት አበረታች ነው፡፡ በተለይ የክፍያ ሥርዓቶቹ አብረው የብድር አገልግሎቶች ሳይቀር ይዘው መቅረባቸው ጥሩ ጅምርና አበረታች ነው፡፡

የአቶ አቤኔዘር ሃሳብንም በማጠናከር ለዲጂታል ክፍያ አሠራሩ የበለጠ ውጤታማነት ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ብዙ ሥራዎች መሥራት እንደሚያስፈልግ አቶ ሀብታሙም ይጠቁማሉ፡፡ ሕብረተሰቡ ወደ ሲስተሙ ገብቶ መጠቀም ሲጀምር ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ እየተታለለና ችግር እየገጠመው መሆኑን እሳቸውም በመጠቆም፣ የሚስጥር ቁጥሩ ለሌላ የማጋራት፣ የመታለል፣ ሊንኮች ተጨነው ሲገቡ የሚያጋጥም ችግሮች እና መሰል ችግሮች እየተፈጸሙ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህን መሰል ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ጠንከር ያለ የሕግ ማዕቀፍ ሊኖር እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡ ዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ መሆኑን ችግሩን ሊያቀለው እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ በሀገራችን ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት መተግበር ከጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ ትልቅ ለውጥ የታየበት ነው፡፡ በቀጣይ የግሉ ዘርፍ የራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ ዲጂታል ሥርዓቱ ተስፋፍቶ ሁሉም በአንድ ተዋህዶ በቅንጅት መሥራት ቢቻል ደግሞ የበለጠ ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡

ዲጂታል ሥርዓቱ በሀገራችን በቅርቡ ቢጀመርም በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነትና በቀላሉ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ ይህ ማለት ደግሞ ፍላጎቱ እንዳለ እንደሚያሳይ ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም በቀላሉ ገበያውን መቆጣጠር እንደሚቻል ጠቅሰው፤ ከተሰራበት ትልቅ ውጤት ማምጣት እንዲሚቻል ማሳያ ነውና ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን ለግሰዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን መስከረም 29/2016

Recommended For You