-‹‹ከጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ የመጀመሪያ ዙር ህትመት ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል››ትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፡- የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደት የተጀመረ ቢሆንም የመማሪያ መጻሕፍት እንዳልደረሳቸው የአዲስ አበባ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና ርዕሰ መምህራን ገለጹ። ከጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ የመጀመሪያ ዙር የመጻሕፍት የህትመት ውጤቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ተማሪ በለጡ በሪሁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገረችው፤ ትምህርታቸውን መምህራን በሚሰጧቸው ማስታወሻ እና በቴሌግራም በሚለቀቅ ሶፍትኮፒ እየተማሩ እንደሆነ ገልጻ ምንም አይነት መማሪያ መጻሕፍት እንዳልደረሰ ተናግራለች።
ይህም በመማሪያ ክፍል ውስጥ መምህራን ከሚሰጡት ማስታወሻ ውጪ የተብራራ ጽሁፍ ለማግኘት ብሎም ለሚቀጥለው ትምህርት እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የሚያደርግ ባለመሆኑ በትምህርታቸው ላይ ተጽእኖ የሚፈጥር መሆኑን ተናግራለች። በዚህም የሚመለከተው አካል ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥም ጠይቃለች።
ሌላው ተማሪ ሰለሞን ዮናታን በአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ባለፉት ጊዜያት በክፍል ውስጥ ትምህርቱን ከመጻሕፍት በመከታተል እና የሚሰጠውን የክፍል ሥራ ከመጻሕፍት ይሠራ የነበረ መሆኑን አስታውሶ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እስከ አሁን መምህሩ በክፍል ውስጥ በሚሰጠው ማስታወሻ ብቻ ለመማር የተገደደ መሆኑን ገልጿል።
የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ናትናኤል ሞርኬ፤ ትምህርቱን በቴሌግራም እንዲከታተሉ የተደረገ ሲሆን ስልክ የሌላቸው ብዙ ተማሪዎች በመኖራቸው የትምህርት ሂደቱን እያስተጓጎለ ነው ብሏል።
የመጻሕፍት አቅርቦት ካለመኖሩ በተጨማሪም አዲስ ሥርዓተ ትምህርት መሆኑ የመማር ሂደቱን ከባድ አድርጎታል። መጻሕፍት ከተዘጋጁ በኋላ ነበር የሥርዓተ ትምህርቱ መቀየር ያለበት ሲልም ሃሳቡን ገልጿል።
የጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር የሆኑት አቶ ገዙ በለጠ እንደገለጹት፤ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ሙሉ በሙሉ በዚህ ዓመት ይተገበራል የተባለ ቢሆንም እስካሁን የማስተማሪያና መማሪያ መጻሕፍት ማግኘት አልተቻለም። የመጻሕፍት አቅርቦቱ ቀደም ብሎ በማቅረብ ከትምህርቱ ጋር አብሮ ቢሄድ የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሻለ ይሆን ነበር። ይህንን ችግር ለመፍታት ለመምህራን እና ተማሪዎች ሶፍት ኮፒ በቴሌግራም እና በኮምፒዩተሮች ላይ በማቅረብ በጊዜያዊነት ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከሶፍት ኮፒ በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ የተወሰኑ ገጾችን በማባዛት ለመምህራን እንዲጠቀሙ መደረጉን ገልጸው፤ ለተማሪዎችም በቤተጻሕፍት ውስጥ በማስቀመጥ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
አቶ እንዳልካቸው ደጀኔ የአዲስ ከተማ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሲሆኑ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ እስካሁን ምንም የደረሰ መጻሕፍት አለመኖሩን ገልጸው፤ ለጊዜው በሶፍት ኮፒ ለመምህራና ለተማሪ ተሰጥቷል ብለዋል።
ለትምህርት ሥርዓት መጻሕፍት ወሳኝ ነው ያሉት አቶ እንዳልካቸው፤ ይህንን ለመፍታት በቤተመጻሕፍት እና አይሲቲ ማዕከላት ውስጥ በሶፍት ኮፒ የማስቀመጥ ብሎም ለተማሪዎች በቴሌግራም የማቅረብ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት ለቀረበው የሁለተኛ ደረጃ የመማሪያ የመጻሕፍት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የሁለተኛ ደረጃ መጻሕፍት ህትመት ብሎም ስርጭት ትምህርት ሚኒስቴር እንጂ ቢሮው የማይመለከተው መሆኑን ተናግረዋል። ነገር ግን ቢሮው አሁን ላይ በከተማዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመጻሕፍት ፍላጎት ዝርዝር ለትምህርት ሚኒስቴር ያስገባ መሆኑን አስታውቀዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አመለወርቅ እዝቅኤል በበኩላቸው ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሁለተኛ ደረጃ ማስተማሪያ መጻሕፍትን አዲስ ሥርዓተ ትምህርት በመንደፍ ዘንድሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ያደርጋል።
ለዚህም የመጻሕፍቱን በውጭ ሀገራት የሚያሳትም ሲሆን መጻሕፍቱን በተለያዩ ዙሮች ወደ ሀገር የሚያስገባ ይሆናል። የመጀመሪያው ዙር መጻሕፍ እትምም ከጥቅምት ወር አጋማሽ ጀምሮ ሀገር ውስጥ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል። እስከዛ ድረስም ትምህርት ቤቶች ትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅቶ ባሰራጨው ሶፍት ኮፒ በማስተማር ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ዳግማዊት አበበና ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም