‹‹መምህር ማንነቱ በሥነ ምግባርና እውቀቱ ትውልድ መገንባቱ!!›› እንዲህ ያለ መልእክት ያለው ጽሑፍ በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ የተለመዱ ናቸው፡፡የመማር ማስተማር ሥራቸውን የሚገልጹ በግድግዳዎች ላይ በመለጠፍ የተለያዩ መልእክቶችን ያስተላልፋሉ፡፡ እኛም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እድሜ ጠገብ ከሆኑ ትምህርት ቤቶች አንዱ በሆነው በየካ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኮከበ ጽባህ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በተገኘንበት ወቅት ነበር በቅኝታችን ይህን መልእክት ያየነው፡፡
በትምህርት ቤቱ የተገኘነው ለ35 ዓመታት በፊዚክስ መምህርነት ያገለገሉትን መምህር ፈልገን ነበር፡፡ የፈለግናቸው መምህር በሙሉ ስማቸው ሳይሆን በቁልምጫ ስማቸው እንደሚታወቁ ቀድመው ነግረውን ስለነበር እርሳቸው እንዳሉን በፍቅርና አክብሮት በሚጠሩበት ስማቸው መምህር ሚኪን ብለን በመጠየቅ ነበር፡፡ የሚለዩት በቁልምጫ ስማቸው ብቻ ሳይሆን በሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነትም ነው፡፡ የጠየቅናቸው ሰዎች ‹‹ሚኪ የፊዚክስ መምህር›› ነበር ያሉን፡፡ ሙሉ ስማቸው ሚካኤል ኤጃሞ ነው፡፡
መምህር ሚካኤል ኤጃሞ፣ ከፍተኛው የአገልግሎት ዘመናቸው በኮከበ ጽባህ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ይሁን እንጂ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ከወጡ ጀምሮ እስከ ጡረታ ዘመናቸው ያገለገሉት በመምህርነት ነው። በ2016 ዓ.ም ጥር ወር ጀምሮ ጡረታ እንደሚወጡ አጫውተውናል። እንደርሳቸው በመምህርነት ረጅም ዓመት ላገለገሉና በሥራቸውም ምስጉን ለሆኑ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ባዘጋጀው የእውቅና መርሃ ግብር ላይ አስተዳደሩ እውቅና ከሰጣቸው መካከል መምህር ሚካኤል አንዱ ናቸው፡፡
መምህር ሚካኤል፣ ስለ ትውልድና እድገታቸው እንደነገሩን ከሆነ በቀድሞ ከምባታና ሀዲያ ተብሎ በሚጠራው ዱራሜ ከተማ ጠዛ ገርባ አነስተኛ መንደር ውስጥ በ1956 ዓ.ም ነው፡፡ በትምህርት ቤትም በሥራም ያስመዘገቡት ዘመን በመሆኑ እንጂ አንድ ሁለት ዓመት ትርፍ ሊኖር ይችላል የሚል ጥርጣሬ አላቸው፡፡በትውልድ አካባቢያቸው የሚነገረው ቋንቋ ከንባቲኛ ነው፡፡ አካባቢው ላይ አማርኛም ስለሚነገር ማህበረሰቡ በሁለቱም ቋንቋ ይጠቀማል፡፡ የአካባቢው ስያሜም ከከንባታና ከኦሮምኛ ቃል የተወሰደ ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል፡፡
መምህር ሚካኤል ተውልደው ያደጉት በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ እርሳቸው ለትምህርት የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡ አባታቸውም ቢሆኑ የትምህርት ጥቅምን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው፡፡ ነገር ግን በእርሻ ሥራ እንዲያግዟቸው ስለሚፈልጉ ወደ ትምህርት እንዲሳቡ አያበረታቷቸውም፡፡ አካባቢው ላይ ዘመናዊ ትምህርት ቤት የለም፡፡ የነበረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የቄስ ትምህርት ተብሎ የሚሰጠው እና በካቶሊክ ሚሽነሪዎች የሚሰጥ ትምህርት ነው፡፡
የአባታቸውን ፈቃድ አግኝተው ለመማር ባለውለታቸው ታላቅ ወንድማቸው ነበሩ፡፡ወንድማቸው በካቶሊክ ሚሽን የመማር እድል አግኝተዋል፡፡ በወቅቱም ከቤተሰብ ርቀው ስለሚኖሩ ከእርሳቸው ጋር በደብዳቤ በመጻጻፍ ለመገናኘት የተማረ ሰው እንደሚያስፈልግ አባታቸውን ያሳምናሉ። በዚህ ምክንያት መምህር ሚካኤል ከአባታቸው ፍቃድ አግኝተው ካቶሊክ ሚሽን ውስጥ ለመማር እድሉን አግኝተው ፊደል ቆጠሩ፡፡ በወቅቱም የነበሩት መምህራን የፊደል ገበታውን ያስቆጠሯቸው በአማርኛና በከምባትኛ ቋንቋዎች ነበር፡፡
ትምህርት የመማር ፍላጎቱ ስለነበራቸው የትምህርት አቀባበላቸውም ጥሩ ነበር፡፡በወቅቱ ይማሩበት የነበረው ካቶሊክ ሚሽን ውስጥ የነበሩት የፈረሳይ ሀገር ዜጎች ስለነበሩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን የሚያካሂዱት በቋንቋቸው ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚም በልጅነት እድሜያቸው አንዳንድ የፈረሳይኛ ቃላት ለማወቅ ዕድሉን አግኝተዋል፡፡
የአንድ ዓመት የትምህርት ቆይታቸውም ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ነበር፡፡ ሁለተኛው ዓመት ላይ ለትምህርታቸው እንቅፋት የሚሆን ነገር ገጠማቸው፡፡ በወባ ተነድፈው ታመሙ፡፡ ከሕመማቸው እንዳገገሙ ደግሞ አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩዋቸው፡፡ በተለይም የአባታቸው መሞት ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ ከእርሳቸው በላይ አራት ልጆች ቢኖሩም በቤት ውስጥ ባለመኖራቸው እናታቸውን በኢኮኖሚ ማገዝና ታናናሾቻቸውን መርዳት ኃላፊነት በእርሳቸው ላይ ወደቀ፡፡
የሚፈልጉት ትምህርት እንዳይቋረጥ፣ ኑሮንም ለማሸነፍ መፍጨርጨር ነበረባቸው፡፡ በአካባቢያቸው በሚገኝ አንድ ሻይ ቤት ተቀጥረው ቤተሰባቸውን እያገዙ፣ ጎን ለጎንም ይማሩ ነበር፡፡ ተቀጥረው የሚሰሩበት ሻይ ቤት በወር የሚከፍላቸው ደመወዝ በሳንቲም ደረጃ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በሳንቲም ብዙ ነገር መገበያየት ስለሚቻል የደመወዝ ማነስ ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ የገንዘብ ጉዳይ የማያስጨንቅ የነበረው ኑሮን መሸፈን ከቻለ በቂ ስለነበር ነው፡፡ በተጨማሪም ዶሮ ያረቡ ነበር፡፡ ቤተሰቡን የሚያግዙት የቤተሰቡንም የእርሻ ሥራ በማከናወን ጭምር ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ሲወጡ የነበረው በታዳጊነት እድሜያቸው ነው፡፡
ያለፈውን አሁን ላይ ሲናገሩ ቀላል ይምሰል እንጂ በወቅቱ ለእርሳቸው ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ፊደል ከመቁጠር ወደ ንባብ ወይንም ‹A› ክፍል ለመዘዋወር ኑሮን ለማሸነፍ ያደርጉ የነበረው ጥረት ጫና ፈጥሮባቸው ነበር፡፡ ጠንክረው በመማራቸው ግን ስኬታማ መሆን ችለዋል፡፡ ወደሚቀጥለው ክፍል የተዘዋወሩት በየወሩ የሚሰጠውን የክፍል ፈተና በጥሩ ውጤት በማለፋቸው ነበር፡፡ ጠንክረው በመማር 6ኛ ክፍል ደረሱ፡፡ በብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናም 99 ነጥብ በማምጣት ወደ 7ኛ ክፍል ተዘዋወሩ፡፡
ትምህርት ቤታቸውንም ቀይረው ቃለ ሕይወት ሚሽን ገቡ፡፡ በዚያ ግን የነበራቸውን የትምህርት ቆይታ አልወደዱትም፡፡ በተለይም እንግሊዝኛ ቋንቋ ላይ እንደቀደመው የተማሩበት ካቶሊክ ሚሽን አልሆነላቸውም። ሆኖም እስከ 9ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል፡፡ እዚያም ቢሆን የነበሩት የደረጃ ተማሪ ነው፡፡ በመካከል ላይ የዘውዳዊው ንጉሥ ሥርዓት በወታደራዊ የደርግ ሥርዓት ተተክቶ የመንግሥት ለውጥ ተደረገ፡፡ የተተካው የደርግ መንግሥትም ይማሩበት በነበረው ቃለሕይወት ሚሽን ውስጥ የነበሩትን የውጭ ዜጎች በማስወጣቱ የተሻለ ትምህርት አላገኝም በሚል መንግሥት ትምህርት ቤት መግባት ምርጫቸው አደረጉ፡፡ በወቅቱም ዱራሜ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው ከ10ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሩ፡፡
ሁለተኛ ደረጃ የተማሩበት ትምህርት ቤት የትምህርት መሠረት ከያዙበት በትምህርት ሥርዓቱም ሆነ በትምህርት ቤት ባህሪያት ልዩነት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የፈጠረባቸው ክፍተት ይኖር እንደሆንም መምህር ሚካኤል ላቀረብንላቸው ጥያቄ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ በኋላ የተሻለ ሆነው የተገኙት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንደነበሩ ነግረውናል፡፡
በካቶሊክም ሆነ በቃለ ሕይወት ሚሽን ውስጥ የነበሩት የውጭ ዜጎች ከሀገር እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ጥንካሬው ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር። አንድ እውነት ደግሞ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ክፍተት ያለባቸው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ላይ ብቻ ነው እንጂ በሂሳብ፣ ሳይንስና ሌሎችም የትምህርት አይነቶች የተሻሉ እንደሆኑ አውግተውናል፡፡ ሥነ ጽሑፍን ጨምሮ በተለያየ ሙያ ጠንካራ ተማሪዎች ከመንግሥት ትምህርት ቤት ይወጣሉ፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጥሩ ተናጋሪ ለመሆን ግን ሚሽን ውስጥ መማር እንደሚጠቅም ነግረውናል፡፡
እርሳቸውም በነበራቸው የትምህርት ቆይታ የሚያዘነብሉት ወደ ሂሣብ ትምህርቱ ነበር፡፡ ሂሳብ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ሳይንስ የትምህርት አይነቶች ያስደስቷቸው ስለነበር በእነዚህ ላይ ትኩረት ያደርጉ ነበር፡፡ በ1972 የ12ኛ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወስደው አጠቃላይ ውጤታቸው ሁለት ነጥብ ስድስት (2.6)ነበር፡፡
በወቅቱም ሁለት ነጥብ ስምንት ውጤት ያገኘ ተማሪ መማር የሚፈልገውን የትምህርት ዓይነት የመምረጥ እንዲሁም የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል የማግኘት ምርጫ ነበረው፡፡ እርሳቸው ይሄን እድል ለማግኘት ያመለጣቸው ለጥቂት ነው፡፡ይህም በልጅነታቸው አባታቻውን በሕይወት በማጣታቸው በቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረው የኢኮኖሚ ጫና የፈጠረባቸው ተጽእኖ በመሆኑ እንጂ ለትምህርታቸው ትኩረት ሰጥተው ቢሆን ኖሮ ውጤቱን ያሳኩ እንደነበር አጫውተውናል፡፡ ውጤታቸው ግን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችል በመሆኑ እድሉን አግኝተዋል፡፡
በእርሳቸው ወቅት የትምህርት ሥርዓቱ በተለይም ከፈተና አሰጣጥ ጋር ልዩነት እንደሚኖር በመገመት ኩረጃንም አስመልክተው ምላሽ እንዲሰጡን ጠየቅናቸው በሰጡን ምላሽ፤ እርሳቸው የ12ኛ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተኛ ከመውሰዳቸው ከሁለት ዓመት በፊት ምርጫ እውነት ሐሰት በሚል ሳይሆን የነበረው በማብራሪያ ወይን (ፃፍ) የሚባለው የፈተና አሰጣጥ ነው፡፡ በእርሳቸው ጊዜ የዚህ የፈተና ዘዴ ቢለወጥም ፈተናው ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡
ኩረጃን የሚወስዱት የተማሪ ባህሪ አድርገው ነው፡፡ ሆኖም ግን በእርሳቸው የትምህርት ዘመን አንድ የሚያጠራጥር ጥያቄ ሲያጋጥም ሌላው እንዴት አድርጎ መለሰው ለማለት የማየት ሁኔታ ካልሆነ የሌላውን መልስ ለመጠቀም የሚሞክር እንዳልነበር ነው የተናገሩት። እርሳቸው እንዳሉት ፍርሃቱ አለ፡፡ በተጨማሪም በሌላው መልስ ተማምኖ ለመገልበጥ የሚሞክር የለም፡፡ ደግሞም የሚኮርጀውም፣የሚያስኮርጀውም ከትምህርት ገበታ ይባረራል የሚለው ስጋት ስላለ ሁሉም ይጠነቀቃል፡፡ እንኳን በብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በክፍል ትምህርትም መኮራረጅ የሚታየው እንደነውር ነው፡፡ በመሆኑም ኩረጃ ሙሉ ለሙሉ የቀረ ነው ማለት ባይቻልም እንደ ችግር የሚነሳ ግን አልነበረም፡፡
11ኛ ክፍል በነበሩበት ጊዜ ደግሞ ወታደራዊው መንግሥት መሃይምነትን ከሀገር ውስጥ ለማጥፋት ሁሉም ዜጋ እንዲማር ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚያደርግበት ወቅት ነበር፡፡ ጊዜው 1971ዓ.ም ነው። የዚህ የዘመቻ እንቅስቃሴ የሚባለው መሠረተ ትምህርት ነበር፡፡ ልጅ አዋቂ ሳይቀር እንዲማር ከፍተኛ ቅስቀሳ ይደረግ ነበር፡፡የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሄደው እንዲያስተምሩ በዘመቻ መልክ ይላኩ ነበር፡፡ መምህር ሚካኤልም አንዱ ዘማች ነበሩ፡፡ እንዲያስተምሩ የዘመቱ፡፡ ወቅቱ የክረምት ጊዜ ስለነበር ከትምህርት እረፍት በመሆናቸው ትምህርታቸው አልተስተጓጎለም።
እርሳቸውም መምህር መሆናቸው ትልቅ ደስታ ሰጥቷቸዋል፡፡ የአርሶ አደሩም አቀባበል በጣም ጥሩ ሆኖ ስላገኙት ዘመቻውን የተቀበሉት እንደመዝናናትም ጭምር ነው፡፡ በመሠረተ ትምህርት የመማር እድል ያገኙ አንዳንዶች በትምህርታቸው ፕሮፌሰር ደረጃ የደረሱ መኖራቸውንም ያስታውሳሉ፡፡
የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ እንደ ሀገርም ከሌላው ዓለም እውቅና ያስገኘና የዜጎችን እውቀት ከፍ ለማድረግ የጠቀመ እንደነበር የሚያስታውሱት መምህር ሚካኤል፤እርሳቸውም የዚህ አካል መሆናቸውን እድለኛ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ዘመቻው 12ኛ ክፍል ከደረሱ በኋላም በድጋሚ ስለደረሳቸው ከመሃይምነት ነፃ በማውጣቱ ተግባር ላይ የተሳተፉት በሁለት ዙር ነው፡፡
መምህር ሚካኤል በዚህ ሁኔታ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ የተማሩበትን አካባቢ ለቀው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ገቡ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ የገቡት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመመደባቸው ነበር፡፡ ሁሉ ነገር ለእርሳቸው አዲስ ነበር፡፡ ከፍ ያለ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ መግባታቸው፣ ለከተማውም አዲስ መሆናቸው ግርታን ፈጥሮባቸው ነበር፡፡
‹‹ሁለት ዩኒቨርሲቲ በይው፡፡ የሕይወት ተሞክሮና መደበኛው ትምህርት ከባድ ጊዜ ነበር›› ነው ያሉት። እርሳቸው እንዳሉት ከዩኒቨርሲቲው ብዙም አይወጡም። ወጣትነቱ ስላለ ከትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሚያወጣ ነገር እንዳያጋጥም ለመሸሽና ከተማውንም ስለማያውቁ በዚያው የመጥፋት ሁኔታ ይኖራል ከሚል ስጋት ነበር ጊዜያቸውን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የወሰኑት፡፡
በተማሪዎች መካከል የነበረውም ውድድር ከፍተኛ ስለነበር ጊዜ የሚሰጡት ለትምህርት ነበር፡፡ ውድድሩ
በተለይ እርሳቸውን ጨምሮ ከገጠሪቱ ክፍል የመጣው ተማሪ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ካሉ እንደ ሴንጆሴፍ፣ ናዝሬት የልጃገረዶች ትምህርት ቤትና ሌሎችም የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከተማሩ ተማሪዎች ጋር ስለነበር ጥረት ሲያደርጉ የነበረው ተሽሎ ለመገኘት ነበር፡፡ የኢኮኖሚ አቅም ያለው ቤተሰብ ስለሌላቸው የነበራቸው ምርጫ በትምህርት ጠንክሮ መገኘት ነው። ዩኒቨርሲቲ በነበሩ ጊዜም ወንድማቸው ካልሆኑ ሳንቲም የሚሰጣቸው ባለመኖሩ ወደ ከተማ ወጥተው የሚዝናኑበት አቅሙም አልነበራቸውም፡፡
እንዲህ ያለው ሁኔታ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት በነበረው የትምህርት ውጤታቸው ላይ ተጽእኖ አሳድሮ እንደነበርም መምህር ሚካኤል ያስታውሳሉ፡፡ለትምህርት ጫና ብለው ካነሷቸው በተጨማሪ ወጣትንትም ፈታኝ ስለሚሆን በአቻ ጓደኛ ግፊትም ይሁን እራሳቸውም በፍቅር ተሸንፈው በተቃራኒ ጾታ በኩል የገጠማቸው ፈተና ይኖር እንደሆንም አንስተንላቸው ‹ሀ› ብለው የፊደል ገበታ በቆጠሩበት ካቶሊክ ሚሽን ውስጥ ግብረገብ ትምህርትን በደንብ በመማራቸው የተቃራኒ ጾታ ጉዳይ ላይ ብዙም ትኩረት እንዳልነበራቸውና አጣብቂኝ ውስጥም እንዳልገቡ ለጠያቄያችን ምላሽ ሰጥተውናል። በዚያን ወቅት መቀራረቡ ቢኖር እንኳን ግንኙነቱ ከከንፈር መሳሳም ያለፈ እንዳልሆነም አውግተውናል፡፡
መምህር ሚካኤል እንዲህ ያሉ የትምህርት ቤትና የወጣትነት ትውስታዎችና ጥሩ የትዳር አጋር ለማግኘት አማራጮችን ለማግኘት አሁን ላይ ሆነው ሲያስቡት ያስፈልግ ነበር ይላሉ፡፡ በጾታ ግንኙነት በኩል ያለውን ሁኔታ በእርሳቸው ዘመን የነበረውን የበዛ ቁጥብነት፣ በአሁኑ ጊዜም ከኢትዮጵያ ባህል ያፈነገጠ መስሎ የታያቸውን አግባብ እንዳልሆነም ትዝብታቸውን ገልጸውልናል፡፡ እርሳቸው ዘመናቸውን ያሳለፉት በልጅነትም እንደልጅ፣ በወጣትነታቸውም እንደወጣት ሳይሆኑ ነው፡፡
ቀሪዎቹን ሁለት ዓመታት ግን አካባቢን በመልመድ፣ የተማሪዎችንም አቅም በመፈተሸ፣ የመምህርንንም የትምህርት አሰጣጥ በመልመድና የተለያዩ ጫናዎችንም በመቋቋም በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ማምጣት ብቻ ሳይሆን ያጠናቀቁት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ (ሰቃይ) ተማሪ በመሆን ነበር፡፡
በዩኒቨርሲቲ የትምህርት ቆይታቸው የትምህርት ምርጫቸው ፊዚካል ሳይንስ የሚባለው የትምህርት ዓይነት ስለነበር በዚህ ትምህርት አራት ዓመት ተምረው በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቁ፡፡ ጠንክረው በመማራቸው እንጂ አብረዋቸው ከገቡት ወደ 60 በመቶ የሚሆኑት ዝቅተኛ የፈተና ውጤት በማግኘታቸው ከዩኒቨርሲቲው የተሰናበቱት ገና በመጀመሪያው ዓመት ነበር፡፡ በፊዚክስ የትምህርት ክፍል ብቻ ወደ 120 ከሚሆነው ተማሪ ለምረቃ የበቃው ወደ 20 አ ካባቢ ተማሪዎች ነበሩ፡፡
በአራት ዓመት የዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቆይታቸው ከተማሪዎች ጋርም የነበራቸው መግባባትና መከባበርም አልዘነጉትም፡፡ እርሳቸው እንዳሉት የሚቀራረቡት የአንድ ቤተሰብ ያህል ነበር፡፡ በዚህም ጥሩ ትዝታ አላቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተማሪዎች በቅሬታ የሚነሳው የምግብ አቅርቦት ላይም በእርሳቸው ዘመን የምግብ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንደማይገባ አጫውተውናል፡፡ በዚያን ጊዜ የተመገቡትን ፓስታ ጣዕም አሁን ባሉበት ዘመን እንዳላገኙትም ነግረውናል።
መምህር ሚካኤል በትምህርት ከሁለተኛ ዲግሪ በላይ አልዘለቁም፡፡ ሶስተኛ ዲግሪ(ፒኤች) ደረጃ ለመድረስ ጥረት ቢያደርጉ በተለያየ ምክንያት ሳያሰኩ እድሜ ገደባቸው፡፡ ምንም እንኳን ትምህርት እድሜ አይገድበውም የሚል አባባል ቢኖርም ከጡረታ ዘመን በኋላ ለመማር የሚያነሳሳ ነገር መኖር ይኖርበታል፡፡ እርሳቸውም ለዚህ ይመስላል እድሜን እንደ ምክንያት ያነሱት፡፡
መምህር ሚካኤል በመጀመሪያ ዲግሪ ካጠናቀቁ በኋላ ከትምህርት ቤት እንደወጡ የሥራ ዕድሉን ያመቻቸላቸው መንግሥት ነበር፡፡ የሥራ ምርጫም አልነበራቸውም፡፡ በእርሳቸው የትምህርት ዘርፍ የተመረቁትን በሙሉ መንግሥት በመምህርነት እንዲቀጠሩ ነው ያደረገው፡፡ በወቅቱም ትምህርት ሚኒስቴር መምህራኑን በእጣ እንዲመደቡ በማድረጉ መምህር ሚካኤልም እጣ ሲያወጡ ትግራይ ክልል መቀሌ ነበር የወጣላቸው፡፡ መምህርነቱን ባይጠሉትም በሌሎች ተቋማት ውስጥ የመቀጠሩን እድል ቢያገኙ በኢኮኖሚ በተሻለ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር እሳቤው ነበራቸው፡፡ ተወልደው ካደጉበት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲመጡ ትምህርቱን ጨምሮ የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ለመልመድ ጫናዎችን ተቋቁመው በማለፋቸው የሥራ ቦታቸውም በለመዱበት አካባቢ ቢሆን ይመርጡ ነበር፡፡
መምህር ሚካኤል የመንግሥትን ምደባ ተቀብለው ወደ መቀሌ አቀኑ፡፡ በወቅቱ የተቀበላቸው መቀሌ ውስጥ የሚገኘው አጼ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱን ቀድሞ መረጃ ስለነበረው መምህር ሚካኤልን የጠበቋቸው በጉጉት ነበር፡፡ መምህር ሚካኤልን በጉጉት የጠበቋቸው ትምህርት ቤቱ በዲግሪ የትምህርት ደረጃ የፊዚክስ መምህር ስለተመደበለት ነበር፡፡
መምህር ሚካኤል ወደ መቀሌ በሄዱበት ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶ የነበረበት ጊዜ ነበር።፡ 1977 ዓ.ም በተለይ ደግሞ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተጎዳበት ጊዜ መሆኑ በተጨማሪ ደግሞ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ከወታደራዊው የደርግ መንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ አካባቢው መሄድ ስጋት ሆኖባቸው ነበር፡፡ ወስነው የሄዱት ሌላ አማራጭ ስለሌላቸው ነበር፡፡
ኑሮ በመቀሌ ‹ሀ› ብለው ሲጀምሩ በአንድ ሆቴል ቤት በቀን 45 ብር እየከፈሉ ምግብም እንዲሁ በሆቴል እየተመገቡ ነበር የተለማመዱት፡፡ ‹‹በጣም ጣፋጭ የሆነ የበግና የፍየል አሩስቶ አንድ ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም ነው ይሸጥ የነበረው›› ሲሉም ከፍተኛውን የምግብ ዋጋ ነበር የነገሩን፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ምንም እንኳን ኑሮ ርካሽ ነው ቢባልም ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ሲነጻጸር በአንዳንድ ነገሮች ላይ የሁለትና የሶስት ብር ልዩነት የዋጋ ጭማሪ አለው፡፡ ይህ ነው ኑሮ መቀሌ ላይ ውድ ነው ያስባለው፡፡
በሂደትም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መለማመድ ሲጀምሩ ኑሮአቸውንም ወደዱት፡፡ በቋንቋ በኩልም ችግር አልገጠማቸውም፡፡ እንደውም ትግርኛ ብቻ የሚነገር ቢሆን በቋንቋው በደንብ ለመግባባት ያስችላቸው እንደነበር ነው ያጫወቱን፡፡ ትግርኛ መናገር ባይችሉም ስለሚሰሙ አይታሙም፡፡ በዚህ ሁኔታ ነበር የተሰጣቸውን የመማር ማስተማር ሚናቸውን መወጣት የተያያዙት፡፡ በወቅቱ የወር ደመወዛቸው 500 ብር ሲሆን፣ መንግሥታዊ የሆኑ ወጪዎችና ለእናት ሀገር ጥሪ የሚያዋጡትን ጨምሮ ተቆራርጦ 380 ብር ነበር የተጣራ የሚደርሳቸው፡፡ከሚያገኙት ገቢ ለእናታቸውም ተቆራጭ ያደርጉ ነበር፡፡
ከፍ ያለ ነገር ለማድረግና ለመቆጠብም የሚተርፋቸው ነገር ባይኖርም ገንዘቡ በሳንቲም ደረጃ ዋጋ ስላለው ለኑሮአቸው በቂ እንደነበር ነው ያጫወቱን።አካባቢውን ከለመዱ በኋላና በትምህርት ቤቱም ያላቸውን ትርፍ ጊዜ አመቻችተው በግል ትምህርት ቤት በማስተማር የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ ጥረት ያደርጉ እንደነበርም ገልጸውልናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነበር በመቀሌ ለአምስት ዓመታት የቆዩት፡፡
አምስተኛው ዓመት ለእርሳቸው ከባድ ጊዜ ነው የነበረው፡፡ በወቅቱ ወታደራዊ የደርግ መንግሥትና ሕወሓት መካከል የነበረው ጦርነት ተፋፍሞ ችግሩ እየከፋ መጣ፡፡ በመጨረሻም የደርግ መንግሥት ተሸንፎ አለመረጋጋቱ ሲፈጠር መምህር ሚካኤል አካባቢውን ለቀው ለመውጣት ወሰኑ፡፡ ወቅቱ 1981ዓ.ም ነበር፡፡ በወቅቱም ብዙ ሰው ከየአካባቢው እየተፈናቀለ እግር ወደመራው ይሄድ ነበር፡፡እርሳቸውም ከአካባቢው ውጣ ያላቸው ሰው ባይኖርም ችግር ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ሆነው ከመቀሌ እስከ ኮረም በእግራቸው ተጉዘው ባገኙት መኪና ነበር ተሳፍረው አዲስ አበባ ከተማ የገቡት፡፡ በዚህ መልኩ ከመቀሌ ለመውጣት መወሰናቸውን አሁን ላይ ሆነው ሲያስቡት አጉል ድፍረት እንደነበር ነው የሚገልጹት፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከተማ ጉዞ በሚያደርጉበት ወቅት ወሎ ላይ ቀርተው በመምህርነታቸው እንዲቀጥሉ ሃሳብ ቀርቦላቸው እንደነበርና የእነርሱ ፍላጎት ግን አዲስ አበባ ከተማ መግባት ስለነበር እንዳልተቀበሉ ነው የነገሩን። አዲስ አበባ ከተማ እንደገቡም ትምህርት ሚኒስቴር በመሄድ የሚሞላ ፎርም ሞሉ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ለመመደብ ትንሽ ቢያንገራግርም ከየአካባቢው የተፈናቀለው ብዛት ስለነበረው ለመመደብ ተገደደ። እርሳቸውም በሞሉት ፎርም መሠረትም አሁን የሚያስተምሩበት ኮከበ ጽባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ተመደቡ፡፡ጊዜው 1982 ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 35 ዓመታት የፊዚክስ መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡ 2016 ጥር ወር ጀምሮ በጡረታ የአገልግሎት ዘመናቸው እንደሚያበቃም ገልጸውልናል።
መምህር ሚካኤል በዚህ የረጅም ጊዜ የአገልግሎት ዘመናቸው ከማስተማር ሥራቸው የተለዩት ለአንድ ዓመት ብቻ ነው፡፡ የዚህን አጋጣሚ እንዳጫወቱን፤ባለፈው የሕወሓት ሥርዓት ወቅት ደቡብ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ደህዴን) ወክለው የድርጅት አባል ሆነው በፖለቲካው ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ በሹመት በአንድ ቀበሌ ውስጥ በአስተዳደርነት እንዲሰሩ ተመደቡ፡፡ ሥራው ግን ምቾት አልሰጣቸውም። አልወደዱትም፡፡ ከመምህርነት ሙያቸውም የሚበልጥ ሆኖ አላገኙትም፡፡ ፖለቲከኛ መሆን እንደማይችሉም በሹመት በተሰጣቸው ሥራ አረጋገጡ፡፡ ፖለቲካንም እንዲጸየፉ ነው ያደረጋቸው። የእርሳቸው ግምትና ፖለቲካም አልተገናኘላቸውም፡፡
የልማት ቅስቀሳው ከፍተኛ በመሆኑ የነበሯቸውን የልማት ፈጠራና ክህሎት ተጠቅመው በልማት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ሲሉ ነበር ወደ ፖለቲካው የተጠጉት፡፡ ያገኙትን አጋጣሚ በልማቱ ለመጠቀምም ጥረት አድርገዋል፡፡ ለአብነትም በተለምዶ የጅብ ጥላ የሚባለውን መሽሩም እንዲሁም በሐር ትል ላይ እና በዶሮ እርባታ ሰፊ የልማት ሥራ እንዲሰራ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ሆኖም ግን እንዳሰቡት የልማት አርበኝነቱ አልተሳካላቸውም፡፡
የፖለቲካው አዝማሚያ ስላላማራቸው፤ ከፖለቲካው ውስጥ ለመውጣት ዘዴ ፈለጉ፡፡ ከፖለቲካው ለመውጣትም ከባድ ስለሆነ ዘዴ መፈለግ ግድ ነበር።በግላቸው ሥጋ ቤት ከፈቱ፡፡ ‹‹እንዴት አመራር ሆኖ ሥጋ ቤት ይከፍታል›› ተብለው በድርጅት ተገመገሙ፡፡ ውጤትም ‹ሲ› ተሰጣቸው፡፡ እርሳቸውም የሚፈልጉት ስለነበር በዘዴ ከድርጅት አባልነት ወጡ፡፡
ከድርጅት አባልነት እንደወጡም ወደ ሙያቸው ወደ ማስተማር ተመለሱ፡፡ ወደ ሥራቸውም የመለሳቸው አሁን የሚያስተምሩበት ኮከበ ጽባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ትምህርታቸውንም ለማሻሻል ሁለተኛ ዲግሪ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርት መከታተል ጀመሩ፡፡
መምህር ሚካኤል አዲስ ነገር መፍጠር፣ በኑሮ መለወጥና ማደግ ከፍተኛ ፍላጎት ስላላቸው ብዙ ነገሮችን ይሞክሩ ነበር፡፡ ኮምፒውተር ቤት ሁሉ ከፍተው ሰርተዋል፡፡ እነዚህ ጥረቶቻቸው ‹‹በርታ ግፋበት›› የሚያስብሉ አልነበሩም፡፡በተቃራኒው ለቅጣት ነበር የዳረጓቸው፡፡
መምህር ሚካኤል በረጅም ጊዜ የማስተማር ዘመናቸው፡፡ በትምህርታቸውና በሥራቸው አንቱ የተባሉ አፍርተዋል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ ውስጥ በሕክምና ሙያቸው በተለይም በኩላሊት ንቅለ ተከላ አንቱ የተባሉ ፕሮፌሰር ማህተመ የተባሉትን እንዲሁም ናሳ ውስጥ የገቡ ሳይንቲስቶች፣ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ላይ ከሚገኙት ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮምን የሚመሩት ፍሬህይወት ታምሩን ተማሪዎቻቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በሀገር ውስጥ በውጭ ኑሮአቸውን ያደረጉ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ በርካታ ተማሪዎችን በማፍራታቸውም ደስተኛ ናቸው፡፡ ‹‹የድካሜን ዋጋ እያየሁ ስለሆነ ደስተኛ ነኝ›› ነው ያሉት፡፡ባለውለታነታቸውንም በአንዳንድ ተማሪዎቻቸው ምሥጋና እንደተቸራቸውም ነግረውናል፡፡
መምህር ግን የልፋቱን ዋጋ እያገኘ አይደለም። በዚህ የአገልግሎት ዘመኔ ደመወዜ 13 ሺ 927 ብር ነው የደረሰው፡፡ አሁን ጡረታ ላይ ነኝ›› ሲሉም መምህር ሚካኤል ቁጭታቸውንም አካፍለውናል። እርሳቸው ቢያልፉትም ቀሪ መምህራን ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥት እንዲመለከታቸውም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ አሻራቸውን ለማኖር ትምህርት ቤቱ ዲጂታል ላይብራሪ (ቤተ መጻሕፍት) እንዲኖረው ጥረት አድርገዋል፡፡ ተማሪዎች ስለግብርና የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸውም በትምህርት ቤት ውስጥ ባለው ሰፊ ቦታ የአትክልት ልማት ሥራ እንዲከናወን በሰጡት ሃሳብም ወደ ትግበራ ተገብቶ ትምህርት ቤቱ ሞዴል መሆን ችሏል፡፡
የጀመሩበትንና የደረሱበትን የመምህርነት ዘመን በተለይም ከትምህርት አሰጣጥና ከተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ጋርም አነጻጽረው ሃሳብ እንዲሰጡንም ላቀረብንላቸው ጥያቄ መምህር ሚካኤል በምላሻቸው፤ ትምህርት ወድቋል እየተባለ በሚተቸው ደረጃ ትምህርት አልወደቀም፡፡ አሁንም ሳይንቲስትና የሌላም ባለሙያ ባለቤቶች ሊሆኑ የሚችሉ ተስፋ የሚጣልባቸው ተማሪዎች አሉ፡፡ ጥቂት ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ ብቻ መወሰን ሳይሆን በቁጥር የበዙ ባለሙያዎችን ማፍራት ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቱ በትምህርት ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም ሲሉም ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
መምህር ሚካኤል ስለቤተሰባቸውም እንዳጫ ወቱኝ የሁለት ልጆች አባት ናቸው፡፡አሁን ላይ ከልጆቻቸው እናት ጋር ሳይሆን፣ ከሁለተኛ የትዳር አጋራቸው ጋር ነው የሚኖሩት፡፡ ከጡረታ በኋላ ቀሪውን እድሜያቸውንም በግል ትምህርት ቤት ውስጥ በማስተማር በሙያቸው ለመቀጠል ነው ያሰቡት፡፡
መምህር ሚካኤል በነበረን ጨዋታ ወደኋላ መለስ እያሉ ስለኑሮአቸው ሲያስቡ በተሻለ ኢኮኖሚ ላይ አለመገኘታቸው፣ በትምህርታቸውም በፒኤች ደረጃ መማር አለመቻላቸው የሚቆጫቸው ቢሆንም ሀገር ሰላም ሆኖ እርሳቸውም በጤና ቀሪውን እድሜያቸውን መኖር ነው የተመኙት፡፡ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ፣ መምህራንም የተሻለ ዜጋ ለሀገር የማስረከብ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ መንግሥትም ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም