ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚጠበቁበት የቺካጎ ማራቶን ነገ ይካሄዳል

በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የቺካጎ ማራቶን ነገ ለ45ኛ ጊዜ ይካሄዳል። 45ሺ ተሳታፊዎች በሚካፈሉበት በዚህ ውድድር የአትሌቲክሱ ዓለም ከዋክብትም ለአሸናፊነት የሚፋለሙ ይሆናል። አምና በዚህ ውድድር በሁለቱም ጾታ አሸናፊ የነበሩት የኬንያ አትሌቶች በድጋሚ በቦታው መሮጣቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል።

በወንዶች በኩል አምና የቺካጎ ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊ አትሌት ቤንሰን ኪፕሩቶ እና ሁለተኛ ሆኖ ውድድሩን የፈጸመው ኢትዮጵያዊው ሰይፉ ቱራ በድጋሚ የቦታውን ክብር ለመቀዳጀት የሚፋለሙ ይሆናል። ኬንያዊው አትሌት ለሁለተኛ ጊዜ በዚህ ማራቶን ተሳትፎ የበላይነቱን መቆጣጠር ይፈልጋል። በአንጻሩ እአአ በ2021 የቺካጎ ማራቶን አሸናፊ የነበረው ሰይፉ ለሶስተኛ ጊዜ በመድረኩ በሚኖረው ተከታታይ ተሳትፎ አሸናፊ ለመሆን ተዘጋጅቷል። አትሌቱ ያለፈው ዓመት ለአሸናፊነት ብርቱ ጥረት ያደረገ ቢሆንም በ25 ሰከንዶች ብቻ ብልጫ ተወስዶበት ነበር የአሸናፊነት ዕድሉን የተነጠቀው። በመሆኑም ይህንኑ ለማስመለስና በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን የሚያደርገው ጠንካራ ፉክክር በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ከወዲሁ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጓል።

እአአ ከ2017 አንስቶ ከመካከለኛ ርቀት ውድድር ወደ ጎዳና ላይ ፉክክሮች የተሸጋገረው አትሌት ሰይፉ በሴኡል ማራቶን የመጀመሪያ ተሳትፎው ሁለተኛ ደረጃን ይዞ

 በማጠናቀቅ ነበር በርቀቱ ውጤታማነቱን ያረጋገጠው። አትሌቱ በቀጣይም በዱባይ፣ ሚላኖ እና ሻንጋይ ማራቶኖች በመሳተፍ ልምድ ማካበት ችሏል። በርቀቱ 2:04:29 የሆነ ሰዓት ያለውም ሲሆን፤ ይህም በኦሪጎኑ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሀገሩን እንዲወክል አስችሎት ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው። ከወር በኋላ ቺካጎ ማራቶንን በመሮጥም ፈታኝ ፉክክር በማድረግ ሁለተኛ ሆኖ ነበር ውድድሩን የፈፀመው። በነገው ውድድርም ኬንያዊያንን አትሌት በመርታትም የቦታውን ክብር በድጋሚ ለመቀዳጀት ይፋለማል።

ከሰይፉ ቱራ በሁለት ሰከንዶች የተሻለ የርቀቱ ሰዓት ያለው ኢትዮጵያዊው አትሌት ዳዊት ወልዴም በውድድሩ ከጠንካራ ተፎካካሪዎች መካከል አንዱ ነው። እአአ የ2019ኙ የቫሌንሲያ ማራቶን አሸናፊ እንዲሁም በ2022 በለንደን ማራቶንን አራተኛ በመሆን ያጠናቀቀው አትሌት ክንዴ አጣናው በዚህ ውድድር ይካፈላል። በቶኪዮ ማራቶን ለጥቂት አሸናፊ መሆን ያልቻለው አትሌት ሁሰዲን ሞሃመድ እንዲሁም የዚህ ዓመት የዴጉ ማራቶን አሸናፊው ሚልኬሳ መንገሻም በኢትዮጵያ በውድድሩ ተፎካካሪ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር የ2022 ቺካጎ ማራቶን አሸናፊዋ ኬንያዊት አትሌት ሩት ቺፕጌቲች የምትካፈል ቢሆንም በርካታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተሳትፎ መረጋገጡ ለአትሌቷ አሸናፊነት ስጋት ሆኖባታል። 2:17:36 የሆነ ፈጣን ሰዓት ያላት ወጣቷ ኢትዮጵያዊት አትሌት ታዱ ተሾመ ኬንያዊቷን ተከትላ የተቀመጠች ሲሆን፤ ጠንካራ የአሸናፊነት ፍልሚያ እንደምታደርግ ይጠበቃል። ይሁንና ለአሸናፊነት ከሚደረገው ጥረት ባለፈ በመም ውድድሮች ከፍተኛ ፉክክር የነበራቸው ሁለት አትሌቶች በጎዳና ውድድር በድጋሚ መገናኘታቸው ፉክክሩን እንዲጠበቅ አድርጎታል። ይህም በመካከለኛ ርቀት ክብረወሰኖችን እንዲሁም ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ የምትታወቀው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ እና አሁንም ድረስ በመም መካከለኛና ረጅም ርቀቶች ተጽእኖ ፈጣሪ አትሌት በሆነችው ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሃሰን መካከል የሚደረግ ነው።

ከ2020 ወዲህ በጎዳና ላይ ሩጫዎች እየተካፈለች የምትገኘው ገንዘቤ የመጀመሪያ ተሳትፎዋ በሆነው የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን አሸናፊ ነበረች። ባለፈው ዓመት ደግሞ በአምስተርዳም ማራቶን ሮጣ የሀገሯን ልጅ አልማዝ አያናን ተከትላ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃ ነበር። በዚያ ውድድር ያስመዘገበችው 2:18:05 የሆነው ሰዓቷም በቺካጎ ማራቶን ተሳታፊ ከሆኑ ምርጥ አትሌቶች አራተኛው ፈጣን ሰዓት ነው። ይኸውም አትሌቷ በተካነችበት ፈጣን አሯሯጧ ታግዛ ድሉን እጇ ታስገባለች የሚል ግምት ከወዲሁ እንድታገኝ አድርጓታል።

በአንጻሩ በ1ሺ500ሜትር የገንዘቤ ተፎካካሪ የነበረችውና በቅርቡ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሶስት ርቀቶች ተካፋይ የነበረችው ሲፋን ሃሰን ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ በቺካጎ ትሮጣለች። ይኸው የሁለቱ አትሌቶች ብርቱ ፉክክርም በማራቶንም ይደገም ይሆናል የሚለው የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። ሲፈን ከወራት በፊት በተካሄደው የለንደን ማራቶን በመሮጥ በርቀቱ ያላትን ተስፋ አሳይታለች። አትሌቷ የገባችበት 2:18:33 የሆነ ሰዓትም በቺካጎ ተካፋይ ከሚሆኑት አትሌቶች ሰባተኛው ፈጣን ነው።

በማራቶን ሰፊ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ሱቱሜ ከበደ፣ ትዕግስት ግርማ እና አባበል የሻነህ ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አትሌቶች አይደሉም።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016

Recommended For You