
ኢሬቻ የአብሮነትና የምስጋና በዓል ሆኖ በኦሮሞ ህዝቦች ዘንድ በየዓመቱ ሲከበር የኖረ በዓል ነው። በዓሉ የክረምቱ ወቅት ተጠናቆ ምድር በአረንጓዴ ስታጌጥ የኦሮሞ ሕዝብ እርጥብ ሳር ይዞ ወደ ወንዝ በመውረድ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ታላቅ የምስጋና በዓል ነው።
በዓሉ በብዙዎች ዘንድ በጨለማ የሚገለጸው ክረምት በሰላም ተጠናቆና የወንዞች ሙላት ቀንሶ ሰዎች በሰላም ከጨለማ ወደ ብርሃን በመሸጋገራቸው ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ መሆኑንም ብዙዎች ይናገራሉ።
ኢሬቻ አባገዳዎች፣ ወጣቶች፣ አባቶች፣ ሴቶችና ህጻናት ያለ ልዩነት በጋራ በአደባባይ የሚያከብሩት በዓል ነው። በዓሉ ከመላው ኢትዮጵያ ከሚመጡ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በጋራ የሚከበር በመሆኑ የሕዝቦች ትስስርን በማጠናከር የራሱ የሆነ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው እሙን ነው።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኦሮሞ ፎክሎርና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ደረጄ ፉፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ኢሬቻ ቱባ ባህሉ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚያሳትፍ በመሆኑ ለአብሮነት መጠናከር ጉልህ ሚና አለው።
የኢሬቻ በዓል አከባበር መሠረታዊ ዓላማው ህዝብን ለማቀራረብና የተቋረጡ ግንኙነቶችን ለማደስ ነው የሚሉት ዶክተር ደረጄ፤ በዓሉ ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚዳብሩበትና ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚወገዱበት እንደሆነ ጠቁመዋል።
የኢሬቻ በዓል ሕጉንና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ከተከበረ ለአብሮነት ያለው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶክተር ደረጄ ስለበዓሉ ምንነት በመገንዘብ በዓሉን የወንድማማችነት ዓርማ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል። ዶክተር ደረጄ አክለውም የኢሬቻ በዓል የህዝቦች አንድነት የሚጠናከርበት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር መቀራረብ የሚችልበት እንደሆነም ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል እሴት ቡድን መሪው አቶ ኦላና ተሾመ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት የኢሬቻ በዓል ከፈጣሪ ጋር ግንኙነት መፍጠርና የሰው ልጅና ተፈጥሮ የሚገናኙበት ነው። በዓሉ የሚከበረው በጋራ መሆኑን ጠቁመው በዓሉን የኦሮሞ ሕዝቦች በጋራ እንዲሁም ከአጎራባች ክልል ሕዝቦች ጋር በአንድነት የሚከበር መሆኑን አመላክተዋል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በሆራ ሀርሰዴ በነበረው የኢሬቻ በዓል አከባበር ከሀላባ፣ ከሲዳማ፣ ከወላይታ፣ ከስልጤና ከጉራጌ በዓሉን ለማክበር ሲመጡ እንደነበር መመልከታቸውን አስታውሰው አሁን ላይ ይሄ በበለጠ አድጎ የተለያዩ ብሔር በሔረሰቦችና ክልሎች በዓሉን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በጋራ ለማክበር እንደሚመጡና ይህም አብሮነትን በማጠናከር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
በዘንድሮ ዓመት ከጎረቤት ሀገራት ከኬንያ፣ ከታንዛንያ፣ ከኡጋንዳና ጅቡቲ ጭምር ኢሬቻን በጋራ ለማክበር እንግዶች እየመጡ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ኦላና ይህ የሕዝብ ለሕዝብ አብሮነትና መተሳሰብን ለማጠናከር የሚደረግ ክንውን ነው ብለዋል።
በዓሉን በጋራ ማክበር ከተጀመረ ረጅም ጊዜ ማስቆጠሩን የሚናገሩት አቶ ኦላና ከኦሮሞ ሕዝቦች አልፎ የኩሽ ሕዝቦች በጋራ አባያ ወንዝ ዳርቻ ሲያከብሩ እንደነበር ታሪካዊ ቁሳቁሶች እንደሚያመላክቱ አስረድተዋል።
በኦሮሞ የጥናትና ምርምር ማዕከል የታሪክ ቡድን መሪና የታሪክ ባለሙያው አቶ ግርማ ነመራ በበኩላቸው እንደሚገልጹት ኢሬቻ የእርቀ ሰላም ማውረጃና በአራቱም አቅጣጫ የሚኖር የኦሮሞ ህዝብ የሚገናኝበት በመሆኑ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለው ሚና ታላቅ ነው።
በኢሬቻ የሚከወነው ቱባ ባህል አብዛኛው ብሔረሰብ የሚጋራው መሆኑን ጠቁመው በበዓሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ሥርዓቱን የሚታደሙ በመሆኑ በዓሉ ለሀገር አንድነት የማይተካ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል። እንደ አቶ ግርማ ገለጻ በዓሉ በአንድነትና በአብሮነት ስሜት ማክበር ከማህበራዊ ጠቀሜታው ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትና ለኢኮኖሚያዊ እድገት የማይተካ ሚና አለው።
በኦሮሞ ባህልና ቱሪዝም የኦሮሞ ባህል ማዕከል የባህልና ታሪክ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ኃይሌ እንደሚሉት ደግሞ እንደ ኢሬቻ ዓይነቱን መልካም እሴት በመጠቀም የተጎዳው እንዲካስ፣ የበደለውም እንዲክስ ማድረግ፣ የተከፋውንም ማስታረቅ ይቻላል። አንዱ ለሌላው የሚያስብ፣ የሚጠነቀቅ፣ የሚሳሳ እንዲሆን በማድረግ የተሳሳተውን ነገር ለመመለስም ይቻላል።
ኢሬቻ የእርቅ፣ ምልጃ እና የሠላም ቀን መሆኑን የሚገልጹት አቶ አለማየሁ እርቅ መውረድ ያለበት ከፈጣሪ ጋር ብቻ ሳይሆን በቅድሚያ እርስ በእርስ መተራረም እና ወደሠላም ስምምነት መምጣት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢሬቻ ማሕበራዊ መስተጋብርን እና የሕዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ረገድ የራሱ የሆነ ትልቅ ድርሻ አለው። ሕዝቦች የቋንቋና የእምነት ድንበር ሳይለያቸው ኢሬቻን ባሕሉንና እሴቱን እንደጠበቀ ለዘመናት ሲያከብሩ ቆይተዋል። ይህንን የሀገር እና የሕዝብ ሀብት የሆነውን ታላቅ በዓል እሴቱን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ሥራ መቀጠል አለበት።
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2016